View in English alphabet 
 | Thursday, October 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ለአዳም የሚያስፈልገው ማነው? ነቢይ? መልአክ? ሌላ ፍጡር? አምላክ?

አዳም አባታችን ጸጋው ተገፏል፤ /ራቁትን ሆኗል፤ ኃይሉን አጥቷል፤ እንግዳ ሆኗል ባሕይርው ጐስቁሏል ሰላሙን አጥቷል፤ ነጻነቱን አጥቷል፤ ሕያውነትን አጥቷል፤ እግዚአብሔርን መምሰል አጥቷል፤ ባለዕዳ ሆኗል፤ ገነትን አጥቷል/ታዲያ አዳምን ከዚህ ሁለ ዕዳ አውጥቶ ሞትን አሸንፎ በሐዲስ ተፈጥሮ ሊፈጥረው የሚችል፤ ወደ ወጣበት ርስት የሚመልሰው ባለጸጋ የሚያደርገው ማነው?

ነቢይ ነውን? 

ነቢያት ወደ ሕዝቡ ይላኩ የነበሩት ለሁለት ምክንያቶች ነበር፡፡ የመጀመያው ለትምህርት ለተግሳጽ ነው፡፡ ሙሴና ሳሙኤል ሕዝቡን ይመሩ ይገስጹ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ከሚመጣው ቁጣ ይተርፍ ዘንድ መጻእያቱን እየነገሩ ይገስጻሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ ዳንኤልና ኤርምያስ ኢሳይያስና ሕዝቅኤል በሕዝበ እሥራኤል ላይ ከሚደርሰው ጉዳይ አንሥቶ በዓለም ላይ እስከሚፈጸመው ድረስ በትንቢት መጽሐፋቸው እንደገለጡት፡፡

ነቢያት በየዘመናቱ ከደረሰውና ከሚደርሰው መከራ በምክራቸውና በትምህርታቸው በጸሎታቸውና በምልጃቸው ሕዝቡን በመዓት ከቁጣ ከሞት አድነዋል፡፡ መዝ. 1ዐ5፤23፡

ይህ ሁሉ የነቢያት ተጋድሎ አዳምን ከሲኦል ወደ ገነት ሊመልሰው፤ ከጥንተ አብሶ አላቅቆ ነፃነት ሊሰጠው፤ ዕዳ ሞትን ሊከፍልለት አልቻለም፡፡

እነርሱ ከአዳም ዕዳ ነፃ ስላልነበሩ ባለዕዳ ባለዕዳን ሊያድነው አልቻለም፡፡ መዝ.63፤5፡፡ በመሆኑም ለአዳም ከነቢያት የሚበልጥ አስፈለገው፡፡

መልአክ ነውን?

መላእክት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚላላኩ /ሉቃ. 1፤18-19/ የሰዎችን ጸሎት የሚያሳርጉ/ራዕ. 8፤1-5/፤ ስለ ሰዎች ኃጢአት የሚያማልዱ/ዘካ. 1፤12-17/ ሰዎችን ከክፋት መከራ የሚያድኑ/ዘፍ. 48፤16/፤ ከታናሽነት እስከ ዐዋቂነት የሚመግቡ/ዘፍ. 48፤15/፤ በሰዎች ንስሐ መግባት የሚደሰቱ/ለቃ. 15፤7/ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ተልእኩዋቸወ የሰውን ልጅ በገነት ሳለ ከገነት ከተባረረም በኋላ ሲራዱት፤ ሲማልዱለት፤ መንገዱን ሲመሩት ኑረዋል፡፡

ይህ ሁሉ ቢሆንም መላእክት አዳምን ከሲኦል ሊያወጡት፤ ገነትን ሊከፍቱለት፤ ሞትን ሊደመስሱለት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱምዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣላየእግዚአብሔር ከሆነ ጋር ሁሉ ተጣልቷል፡፡ የእግዚአብሔር መላእክት ወደ አዳም ይመጡ ነበርእንጂ አዳም ወደነርሱ መሄድ አልቻለም፡፡

  1. በአዳም የሞት ፍርድ የፈረደው እግዚአብሔር በመሆኑ እግዚአብሔር የፈረደውን ፍርድ መላእክት ማንሣት አልቻሉም፡፡
  2. ከገነት አዳምን ያስወጣ በመልአኩ ሰይፍ ገነትን ያስጠበቀ፤ እግዚአብሔር በመሆኑ እግዚአብሔር ያስወጣውን አዳም መላእክት ሊመልሱት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ለአዳም ከመላእክት የበለጠ ያሻው ነበር፡፡

መሥዋዕተ ኦሪት ነውን?

ከዘመነ አበው እስከ ዘመነ ካህናት በተራሮችና በቤተ መቅደስ መሥዋዕተ አበውና መሥዋዕተ ኦሪት ቀርበዋል፡፡ የበግና የላም የፍየል መሥዋዕት ግን አዳምን ሊያድነው አልቻለም፡፡

የሚሠዋው መሥዋዕት የፍጡር በመሆኑ ፍጡርን ፍጡር ማዳን አይችልምና ሊያድነው አይችልም፡፡ ፍጡርን ሊያድነው ቢችል ኖሮ ፍጡርን ፍጡር ሊፈጥረው በቻለም ነበር፡፡ ከየት እንዳመጣው፤ ምን እንደሰጠው ከሚያውቅ በቀር አዳምን ወዴት እንደሚወስደው ምንስ እንደሚመልስለት ሊያውቅ የሚችል አንዳች የለምና፡፡ በመሆኑም የፍጡር መሥዋዕት ፍጡርን ሊያድነው አልቻለም፡፡/ዕብ. 1ዐ፤1-5/

የሚሠዋው መሥዋዕት ሞት የሚያሸንፈው በመሆኑ ሞትን ድል አድርጐ አዳምን ከሞት ባርነት ሊያወጣው አልቻለም፡፡ በጉም ሆነ ፍየሉ ሟች ሙቶ በስብሶ የሚቀር የሞትን መውጊያ፤ የመቃብርን መዝጊያ ማሸነፍ የማይችል በመሆኑ ባለዕዳውን አዳም ትንሣኤን ሰጥቶ ከሞት ሊያወጣው አልቻለም፡፡

በመሆኑም ከበግና ከላም ከፍየል የበለጠ መሥዋዕት ያስፈልገው ነበር፡፡

እግዚአብሔር ነውን?

አዳምን ከምድር አፈር ያበጀው የሕይወት እስትንፋስንም የሰጠው እግዚአበሔር ነው፡፡ «አዳም ሆይ መሬት ነህና ወደ መሬትም ትመለሳለህ» ብሎ የፈረደበትም እግዚአበሔር ነው፡፡ ሕያው አዳምን ሞት እንዲያሸንፈው ፍርድ የሰጠበትም እግዚአበሔር ነው፡፡ ስለዚህም ከመሬት ያበጀውን ወደ መሬትም የመለሰውን መልሶ ከመሬት ለማንሣት ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሕይወት ለሰጠው ሰው ሞት የፈረደበት መልሶም ከሞት ቀንበር አላቅቆ ሕይወት መስጠት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

የቀደመው ሰው አዳም በእግዚአብሔር ተፈጥሮ በእግዚአብሔር የከበረ ነበር፡፡ የዳነው አዳም ግን «በፍጡር የተፈጠረ» በፍጡር «የዳነ» በፍጡር «የከበረ» ቢሆን ኖሮ አዳም ወደ ጥንተ ክብሩ ተመለሰ፤ ፍጹም ድኀነትን አገኘ ማለት ባልተቻለ ነበር፡፡ ምክንያቱም የቀደመው አዳም በግዚአበሔር ተፈጥሮ በእግዚአብሔር ከብሮ የሚኖር በመሆኑ ከኋለኛው አዳም ይበልጣል ያሰኛልና ነው፡፡

እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥር ማንንም አላማከረም፤ ሲፈርድበትም የማንንም ሀሳብ አልጠየቀም፡፡ በመሆኑም እንዴት እንደፈጠረውም እንዴት እንደፈረደበትም ምሥጢሩን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሊያድነው ወደ ጥንት ክብሩ ሊመልሰው ዕውቀቱም ጥበቡም ሥልጣኑም ያለወ እርሱ ብቻ ነው፡፡

ለአዳም ቀዳሚቷን ሕግ የሰጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ አዳም ሕጉን በጣሰ ጊዜ የቀጣው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሁለተኛዋን ሕግ የመስጠት ሥልጣን ያለውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም አዳምን ሊያድነው ከወደቀበት ሊያነሣው ወደ ጥንት ርስቱ ሊመልሰው «ኦ አዳም አይቴ ሀሎከ» እያለ የመጣው መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ፍጡር አይደለም፤ መልአክ አይደለም ነቢይ አይደለም /ነቢይነት የባሕርይ ገንዘቡ ነው ለነቢያትም ሀብተ ትንቢትን የሰጠው እርሱ ነው/ 

 


Written By: host
Date Posted: 2/1/2008
Number of Views: 7517

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement