View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ፍቅር

“እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን ዐውቀናል፡፡ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል›› (1 ዮሐ 3፡16)
በዓለማችን ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ታላላቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ የታወቁ ፈላስፎች ስለ ፍቅር ብዙ ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የእውነተኛውን ፍቅር ምንነቱን የገለጹት፤ በተግባርም ያዋሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

እውነኛ ፍቅር ብዙ ስለ ተጻፈበት ወይም ተደጋግሞ ስለተነገረ ከሰው ልቦና አይገባም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ከእግዚአብሔር የሚገኝ የተለየ ጸጋና የክርስትና ሃይማኖትም መሠረት ነው፡፡  ‹‹ወዳጆች ሆይ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ፣ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ እርስ በርሳችን እንዋደድ›› (1ኛዮሐ 4፡7፤ ሮሜ5፡5)፡፡ 

የሰው ልጆች በሃይማኖት ጸንተው፣ በአገልግሎትም ተጠምደው ቢኖሩ ከዚያም አልፈው ንብረታቸውን ለነዳያን እየሰጡ፣ እየመጸወቱ መላ ሕይወታቸውን ቢያሳልፉ፣ ቢጾሙ፣ ቢጸልዩ፣ ቢሰግዱ፣ የሕግጋት መሣሪያ የሆነውን ፍቅርን ካልያዙ ከንቱ ነው (1ኛቆሮ 13፡ 2-3)፡፡ ፍቅር ከሌለ ሰላም የለም፡፡ ፍቅር የሌለው ሰው ተስፋ ቢስ ነው፡፡ ራሱን ይጠላል፡፡ ቅናትና ምቀኝነትን ተመልቶ የሌሎችንም ሰላም ይነሣል፡፡ ኃጢአትን ያለ ይሉኝታና ያለ ገደብ ይፈጽማል፡፡ ሸንጋይና በመጨረሻም ሃይማኖት የለሽ ይሆናል (መዝ. 14)፡፡ በአንጻሩ ፍቅር ካለ የጎደለው ይመላል፤ የጠመመው ይቃናል፤ መራራው ይጣፍጣል፤ ጥቂቱም ይበዛል፡፡ ‹‹ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና›› (1ጴጥ 4፡7፤ ማቴ 14፡19-20፤ ምሳ17፡1)፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ አደራውንና ትእዛዙን በሚሰጥበት ጊዜ ‹‹እኔ እንደወደድኋችሁ እናንተም ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት›› (ዮሐ 15፤12) በማለት ፍቅርን ምሳሌ ሆኖ አስተምሯል፡፡ ለዚህ ነው ፍቅርን ሐዋርያት የትምህርታቸው መጀመሪያና ማሣረጊያ ያደረጉት፡፡ ሊቃውንትም በመጻሕፍታቸው ሰፊ ዓምድ የሰጡት፤ መዘምራንም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የዘመሩት፡፡
 
ማንን ነው የምናፈቅረው?
ክርስቲያን እውነተኛ ፍቅር ሊኖረው ይገባል፡፡ የሚያመልከው የፍቅርን አምላክ ነውና፡፡ ይኸውም እውነተኛ ፍቅር ሁለት ዘርፎች አሉት፡፡ ‹‹ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ሀሳብህ ውደድ፡፡ ታላቂቱን ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት፡፡ ኦሪትና ነቢያት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸኑ›› (ማቴ 22፤ 37-40)፡፡
 
1ኛ. ፍቅረ እግዚአብሔር
‹‹ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፡፡ ታላቂቱን ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት›› (ማቴ 22፤37)፡፡ የሰው ልጅ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፣ ባለውለታነቱን ዐውቆ፣ ይወደው፣ ያመልከው፣ ያመሰግነው፣ ክብሩንም ዘወትር ይናገር ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ በመውደድም ይገለጣል፡፡
 
ሀ. ትእዛዛቱን በመጠበቅ
‹‹…ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለቸው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡›› ዮሐ 14፤21
‹‹የሚወደኝ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ከተለኝ፡፡›› ብሎ በፍቅር የጠራን አምላክ ‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› ብሎ ሕጉን በፍቅር አስቀመተልን፡፡ ማር 8፤36 ዮሐ 14፤15 ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፈስሶ በሞቱ ፍቅርን አስተማረን፡፡ ይህንን ፍጹም ፍቅሩን አስበን ስለምንወደው እንታዘዝለታለን፡፡ ስለዚህ ለክርስቲያኖች የተሠጠን የሐዲስ ኪዳን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው›› ያለው (ሮሜ 13፤10)፡፡ በመሆኑም ፍቅረ እግዚአብሔር ፈቃዱን በመፈጸማችን፣ ትእዛዛቱን በመጠበቃችንና ለእርሱም ከእውነት በመገዛታችን ይገለጻል፡፡ ‹‹ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና›› (1ዮሐ 5፤3)፡፡
 
ለ. ቅዱሳኑን በመውደድ
‹‹…እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን›› (1ዮሐ 5፤2)፡፡
ፍቅረ ቅዱሳን ለምእመናን ሁሉ የተሰጠ ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን እግዚአብሔር ለወደዳቸውና ላከበራቸው ቅዱሳን የተለየ ፍቅር አለን (ሮሜ 8፤30)፡፡ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለው ለጽድቅ የተሰደዱትን ነብያት፣ ቃሉን በዓለም ሁሉ ዞረው ያስተማሩትን ሐዋርያት፣ በስሙ መከራ የተቀበሉትንና ደማቸውን ያፈሰሱትን ሰማዕታት፣ በሕይወት ዘመናቸው በተጋድሎ የኖሩትን ጻድቃን፣ አገልጋዮቹ መላእክትን መውደድ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ ስለዚህም ኦርቶዶክሳውያን ቅዱሳንን እናከብራቸዋለን፤ ዘወትርም ስማቸውን እየጠራን በአማላጅነታቸው እንማጸናለን፡፡ ይህም እውነተኛ ፍቅር ምድራውያንን ከሰማያውያን ጋር ያገናዝበናል፡፡ በኋላም አንድ ያደርገናል፡፡ ይህ ፍቅር ነው ጌታችን በቤተልሔም ሲወለድ ሰዎችንና ሰማያውያን መላእክትን አንድ ዓይነት ዝማሬ ያዘመራቸው፤ አንድ ዓይነት ምሥጋና እንዲያቀርቡ ያደረጋቸው (ሉቃ 2፤3)፡፡
 
ሐ. የአገር ፍቅር
አገራችን ኢትዮጵያ የምንወዳት ወንዝ ተራሮችዋ ልምላሜዋ የተለየ በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሕገ ኦሪትን ቀድማ የተቀበለች፣ በሕገ ወንጌልም የጸናች፣ ታቦተ ጽዮንን እና ግማደ መስቀሉን የያዘች፣ ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ ለእመቤታችንም በአሥራትነት የተሰጠች የቃል ኪዳን ሀገር ስለሆነች ነው፡፡ በመሆኑም የአገር ፍቅር ከፍቅረ እግዚአብሔርና ከቅዱሳን ፍቅር ጋር ይገናኛል፡፡ አባቶቻችን ይህ ፍቅር ኖሯቸው ነው ነጻነቷንና አንድነቷን አስከብረው ያቆዩልን፡፡ በሰላምና በነፃነት የሚኖሩበት አገር ከሌለ እግዚአብሔርን በነፃነት ማምለክ ለእርሱም መገዛት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን አገሩን ሊያፈቅር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ስለ አገር ፍቅር የምታስተምረው፤ ስለ አገር ሰላምም የምትጸልየው፡፡
 
ኢትዮጵያውያን ይህ ፍቅር በልቦናቸው ስላለ በየትኛውም ዓለም ቢጓዙ ወገናቸውን የሚወዱ በራሳቸው ስም የሚጠሩ፣ በራሳቸው ትውፊትና ሃይማኖት የሚመሩ ናቸው፡፡ ዛሬ መናፍቃን የሚሯሯጡት በእውነት ወንጌልን ሊሰብኩን ሳይሆን ለዚህች የቅዱሳን ሀገር ለሆነች አገራችን ያለንን ፍቅር ለማጥፋት እና ግድ የለሾች እንድንሆን ለማድረግ ነው፡፡ ወንጌልን መስበክ እውነተኛ ዓላማቸው ቢሆንማ ኖሮ በአገራቸው ወንጀልን፣ ዝሙትን፣ የዕፅ ሱሰኝነትን መቆጣጠር ተስኗቸው፣ ስንቱስ ወገናቸው ወንጌል ጠምቶት አልነበር?!
 
2ኛ. ፍቅረ ቢጽ
‹‹ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፡፡ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትዕዛዝ ከእርሱ አለችን›› (1ኛ ዮሐ. 4፡20-21)፡፡
 
ፍቅረ ቢጽ (ባልንጀራን መውደድ) ማለት በሥላሴ አርአያ የተፈጠረውን የሰውን ልጅ ሁሉ በሰውነቱ መውደድ መለት ነው፡፡ ክርስቲያን የሰውን ክፉ ምግባሩን ይጠላል እንጂ ሰውየውን ስለ ሰውነቱ አይጠላም፡፡በመሆኑም ክርስቲያን አብሮት ካለው ባልንጀራው ወይም ወንድሙ ጀምሮ ለነፍስ እስከሚፈልገው ጠላቱ ድረስ ሊወደው ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን በሃይማት ከማይመስለንና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ከሆነው ጋር እንተባበር፣ አንድ እንሁን ማት አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ፍቅር ሳይሆን ሞኝነት ነው፡፡ ይህንንም ‹‹በክርስቶስ ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት፡፡ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፣ ሰላምም አትበሉት፣ ሰላም የሚለው በክፉ ሥራው ይካፈላልና›› በማለት ሐወርያው በሚገባ ገልጾልናል (2ኛ ዮሐ ቁጥር 10)፡፡ ይህንን ባለመረዳት ነው ብዙዎች በሃይማት ከማይመስሏቸው ጋር አጉል ወዳጅነት ፈጥረው በመጨረሻ የካዱት፤ ከፍቅር እግዚአብሔርም የተለዩት፡፡ በመሆኑም በፍቅረ ቢጽ ጠላትን እስከ መውደድ መድረስ ማለት ሃይማኖትን የሚያስክድ፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የሚለይ ይሁን ማለት አይደለም፡፡ ፍቅረ ቢጽ የሚገለጠው በሃይማኖት ነውና፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቻለሁ›› (ሮሜ 8፡38-39) ያለው፡፡ ስለዚህ በሃይማት ከማይመስሉን ከቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ጋር (በጋብቻ፣ በዝምድና፣ በወዳጅነት፣ በጓደኝነት) መወዳጀትና የጥፋትቸው ተባባሪ መሆን ፍቅረ ቢጽ ሊሆን አይችልም፡፡ ‹‹ከመያምኑ ጋር በማይመች አካሔድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከአመጻ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና?›› (2ኛ ቆሮ. 16፡14)፡፡
 
ይሁን እንጂ ለእንደዚህ ዓይነቱም ሰውም ሆነ በጊዜያዊ ግጭት የተጣሉት ሰው ቢኖር ከጥፋቱ ሳይተባበሩ ቢቸገር በመርዳት፣ በቀል ሳይዙ በጸሎት በማሰብ ፍቅርን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፣ ቢየማ አጠጣው›› (ሮሜ. 12፡20)፡፡ ይህንንም ዮሴፍ በጠላትነት ለሸጡት ወንድሞቹ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስም በድንጋይ ለወገሩት ወገኖቹ  ይቅርታ በማድረግ ፈጽመውታል (ዘፍ. 45፡ 5-7፤ የሐዋ. 7፡60)፡፡ እነ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራም ጠላትን በጸሎት ማሰብን በግብር አውለውታል፡፡
 
ዛሬ ብዙዎች ስለ ፍቅረ ቢጽ ሲናገሩ እንጂ በተግባር ሲያውሉት አይታዩም፡፡ ከቤተሰባቸው ጀምሮ ሰላም የላቸውም፡፡ አንዳቸው ሌላውን በክፋት ዓይን ያያሉ፡፡ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስምምነት የላቸውም፡፡ በሥራ ቦታ እርስ በርሳቸው ይቀናናሉ፡፡ ይጨቃጨቃሉ፡፡ነገር ግን ስለ ፍቅር ይሰብካሉ፡፡ፍቅር አላቸው የሚባሉትም ፍቅራቸው የታይታና ውጭአዊ ነው፡፡ አንዳንዶችም ወረተኞች ናቸው፡፡ ፍቅራቸው ጊዜያዊና የአንድ ሰሞን ብቻ ያውም በጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ፍቅር በቃላት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ ራስን ለሌላው አሳልፎ እስከ መስጠት የሚያደርስና በተግባር የሚገለጥ እንጂ! ‹‹በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ›› (1ኛዮሐ. 3፡18) እንዲል፡፡
 
ፍቅረ ቢጽ በተግባር እንዴት ይገለጻል?
 
ሀ. በመርዳት
ፍቅረ ቢጽ የተራበን በማብላት፣ የተጠማን በማጠጣት፣ የታረዘን በማልበስ፣ ያዘነንነ በማጽናናት፣ የታመመን በማከምና በማሳከም ይገለጻል፡፡ ይህ በፍኖተ ኢያሪኮ በዱላ ተቀጥቅጦ የወደቀውን መንገደኛ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ይህ ሰው ቀና አድርጎ ውኃ የሚያጠጣው፣ ቅስሉን የሚያክምለት እውነተኛ ወዳጅ ይሻ ነበር፡፡ ብዙዎች ከንፈራቸውን መጠውለታል፡፡ ፈሪሳውያንም እያዩ አልፈውታል፡፡ ሣምራዊው ግን ደረሰለት፡፡ ተቀጥቅጦ የወደቀውንና የተጣለውን መንገደኛ አስነስቶ ቁስሉን አከመለት፡፡ የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርጎ ፍቅሩን ገለፀለት፡፡ እውነተኛ ወዳጁም ሆነ (ሉቃ. 10፡29-37)፡፡ እውነተኛ ፍቅር እንደዚህ በተግባር የሚገለጥ እንጂ በመመቸት፣ በማግኘትና በማጣት ተወስኖ በቃላት የሚቀር አይደለም፡፡
 
እንዲሁም ክርስቲያን ቤተ ሰቡን ሊረዳ፣ ላሳደጉት ወላጆቹ መልካም ነገር ሊያደርግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ሳይፈጽም ለተቸገሩት ሲመጸውት ቢውል ፍቅሩን ገልጧል ማለት አይቻልም፡፡ ‹‹ነገር ግን ለእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለ ቤሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ፣ ከማያምንም ይልቅ የሚከፋ ነው›› (1ኛጢሞ.5፡8)፡፡
 
ለ. በኀዳጌ በቀልነት (ይቅር በማለት)
 
ክርስቲያን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሰው ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ቂም ሊይዝና ሊበቀል ግን አይገባም፡፡ ‹‹በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፣ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና›› (ማቴ 5፡44-45)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለጠላት መልካም እንደሚገባ ከገለጸ በኋላ ‹‹ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ›› (ሮሜ 12፡20) በማለት ኀዳጌ በቀል መሆን እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ፍቅረ ቢጽ በቀል ሳይዙ ለጠላት መልካም በማድረግና በጸሎት በማሰብ ሊገለጽ ይገባል፡፡
 
ሐ. በማስተማር
እውነተኛ ፍቅር ገንዘብን በማውጣት እንዲሁም በጉልበትና በዕውቀትም ይገለጣል፡፡ ፍቅር ያላቸው ገንዘባቸውን በመስጠት የተቀሩትም በጉልበታቸው ረዱ መምህራንም ደግሞ ዕውቀታቸውን በማካፈል ይገልጡታል፡፡ አውነተኛው የጽድቅ መንገድ የጠፋው ኃጢአተኛ ቃለ እግዚአብሔርን ሰምቶ በንስሐ እንዲመለስ ማይምነትና ድንቁርና እንዲጠፋ ማስተማር ፍቅረ ቢጽ ነው፡፡
 
ከዚህም ሌላ ‹‹ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፣ በደልን አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመጻ ደስ አይለውም፡፡ ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል›› (1ኛ ቆሮ. 13፡4-7)፡፡
 
በአጠቃላይ እውነተኛ ፍቅር የሃይማኖት ዋልታ፣ የምግባራት ራስ ነው፡፡ ያለ ፍቅር ሃይማኖተኛ መሆን ለእግዚአብሔርም መገዛት አይቻልምና፡፡ ፍቅር የተለያዩትን የሚያዋሕድ፣ የተራራቁትን የሚያቀራርብ፣ የጥልን ግድግዳ አፍርሦ ሰላምን የሚያንጽ የሕይወት መሠረት ነው፡፡ ሌላው ይቅርና ሊቁ ‹‹ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ ፍቅር ኃያል ወልድን ከመንበሩ ሳበው፣ እስከ ሞትም አደረሰው›› ብሎ እንደተናገረው አምላካችንን ከሰማያዊው ዙፋን ያወረደው፣ እስከ ሞትም ያደረሰው ፍቅር ነው፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያም ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለሙን ወድዶታልና›› (ዮሐ 3፡16)፡፡
 
እንግዲህ አምላካችንን እስከ ሞት ያደረሰውን ፍቅሩንና ለእኛ ያደረገልንን ወለታውን እያሰብን፣ ለሕጉ በፍቅር ተገዝተን እርስ በርሳች እየተዋደድን፣ ለሰማያዊ መንግሥት እንድንበቃ የእርሱ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ፣ የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

Written By: host
Date Posted: 2/20/2008
Number of Views: 10869

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement