View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ዐቢይ ጾም

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና ትውፊት መሠረት ይህ የያዝነው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡

ይህ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት፣ 56 ቀኖች አሉት፡፡ ከነዚህ ቀኖች ውስጥ ሰባት ቅዳሜ፣ ስምንት እሑድ ይገኛሉ፡፡ ዐሥራ አምስት ቀናት ማለት ነው፡፡ ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማጾሙ የጾሙ ወራት 40 ቀን ብቻ ነው፡፡ ይህም በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ በ384 ዓ.ም ገደማ ከእስፓን ወደ ኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ረጅም ጉዞ ያደረገችው ኤጌሪያ የተባለች ሴት ‹‹የተሳላሚ ጉዞ›› (Peregrination ed loca Sancta) በሚለው መጽሐፏ የጥንት ክርስቲያኖች በዚህ አቆጣጠር ሲጠቀሙ ማየቷን ጽፋለች፡፡ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ኤጲፋንዮስም በዚህ አቆጣጠር ይቆጥር ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ሳምንት ለይተው ይቆጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሕርቃል (ኢራቅሊዮስ) የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበትም ምክንያት የሚከተለው ነው፡፡
 
በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው፣ የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ተደስተው ለስሙ መታሰቢያ ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡለት እየተባለ ይነገራል፡፡ ግሪኮች ግን ጾመ ሕርቃል የሚባለውን ነገር አያውቁም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሳምንት ከዕንቁላልና ከአይብ ከዓሣ በቀር ሥጋ አይበላም ክልክል ነው ይላሉ፡፡ ጾም መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ዕንቁላል፣ አይብና ዓሣ መብላታቸውም በተድላ ደስታ የሰነበተ ሰውነት ወዲያው በጾም ሲደርቅ በሽታ እንዳያመጣባቸው ለጥንቃቄ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሳምንቱንም ስም ‹‹የአይብ ሳምንት ወይም ነጭ ጾም›› ይሉታል፡፡ የመጨረሻው ሳምንት ሕማማት ነው፡፡ ሐዋርያት የጌታችንን መከራ ሞት እያሰቡ የጦሙት ነው ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ከዐቢይ ጾም ጋር እንደ መርገፍና እንደ እጀታ ስለተያያዘ ከዐቢይ ጾም ይቆጠራል፡፡ ይህ ታላቅ የሆነው የጾማችን ወራት በተለያየ ስያሜ  ይጠራል፡፡
 
1. ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡
ሌሎች አጽዋማት ከቅዱሳን አበው የወረስናቸው የኑሮአቸው ፍሬዎች (ዕብ.13$7) ሲሆኑ ይኼኛው ግን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ (ታላቅ) ይባላል፡፡ የጌታ ጾም ስለሆነ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሡበት፣ ድል የሚነሡበት ጾም ስለሆነም ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡
 
2. ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡
ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት፣ የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ ዐዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ ይህንንም የጌታ ጾም የጌታ ወይም የጌታ ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታልና ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡
 
3. የካሣ ጾም ይባላል፡፡
አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት$ ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነበር፡፡ በሆዳምነቱ የወደቀውን የሰው ልጅ በፈቃዱ በጾመው ጾም ካሠው$ እንዲሁም አዳም ከገነት ሲባረር ረሃበ ጸጋ (መንፈሳዊ ረሃብ) ደርሶበት ነበርና ረሃቡን በረሃብ ካሠለት፡፡ የኛን ረሃብ እርሱ ተራበ፡፡
 
4. የድል ጾም ይባላል፡፡
ጌታችን ተጠምቆ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ ከሰው ተለይቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በመጾም አዳምና ሔዋንን በመብል የረታቸውን ዲያብሎስን እርሱ ድል አደረገላቸው፡፡ ዲያብሎስን ድል ያደርግ ዘንድ ከዚህ ዓለም ርቆ ወደ ገዳም መሄዱ አዳም ከዚህ ዓለም ርቃ በምትገኘው ገነት ድል ሆኖ ነበርና እርሱም ዲያቢሎስን በገዳም$ በዚህ ዓለም ርቆ ድል አደረገልን ለእኛም ፈቃደ ሥጋችንን የምናሸንፍበተ ኃይል ሰጠን፡፡ ይህ ጾም ጠላት ዲያቢሎስ የተሸፈነበት ነው፡፡
 
5. የመሸጋገሪያ ጾም ይባላል፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝቡን ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኣሪት ሲያሸጋግር አርባ መዓልትና ሌሊት በደብረ ሲና እንደ ጾመው ሁሉ ጌታችንም እኛን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሲያሸጋግረን አርባ መዓልትና ሌሊት ጾመ፡፡ ስለዚህም የመሸጋገሪያ ጾም እንለዋለን፡፡
 
6. ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡
ሁሉን ነገር በቅጽበትና ያለ ድካም ማድረግ የሚችለው አምላክ እኛን ልጆቹን ያስተምረን ዘንድ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ መልካም መምህር ተማሪዎቹ


ይገባቸው ዘንድ ዝቅ ብሎ በነርሱ ቋንቋ እየተናገረ በሚችሉት እየመሰለ እንዲያስረዳ ጌታችንም እኛን ወደርሱ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እርሱ ወደ እኛ መጣ፡፡ ረሃባችንን ተራበ$ ድካማችንን ደከመ$ ፈተናችንን ተፈተነ ለእኛም አርአያ ሆኖ ትሕትናን$ ትዕግሥትንና ፈተናን በጾም ማሸነፍን አስተማረን፡፡
 
7. የቀድሶተ ገዳም ጾም ይባላል፡፡
እነ መጥምቁ ዮሐንስ እነ ነቢዩ ኤልያስ የኖሩትን የብሕትውና ኑሮ ጌታ ባርኮ ሰጠን፡፡ ከከተማ ወጥቶ ከሰው ርቆ በበረሃ ከአራዊት ጋር እየኖረ በዲያብሎስ ተፈትኖ ድል አደረገ፡፡ ዛሬም ልጆቹ በየገዳማቱ ድምፀ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ተግሠው ዓለምን ንቀው$ ከሰው ርቀው በጾም በጸሎት ከአጋንንት ጋር ይታገላሉ$ ድልም ያደርጋሉ፡፡
 
8. የመዘጋጃ ጾም ይባላል፡፡
ለእሥራኤላውያን ስለ በዓለ ፋሲካ አከባበር ሲነገራቸው የፋሲካውን በግ ሥጋ ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበሉት ታዘው ነበር (ዘጸ.12$18)፡፡ ይኽም መራራ ቅጠል በግብፅ ይኖሩት የነበረውን የመከራ ኑሮ የሚያሳስባችውና ደግም ወደ ግብፅ (ምድረ ፋይድ) እንዳይመለሱ ከኃጢአተ ይርቁ ዘንድ የሚያስተምራቸው ነበር፡፡ የፋሲካው በግ ደግሞ እግዚአብሔር በፍቅሩ የሰጣቸውን ነፃነት ያሳስባቸዋል፡፡
 
ዛሬም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ትንሣኤው በፊት የጾም ወራት ያስቀደምነው ለዚህ ነው፡፡ ከመብል ስንከለከል ለአዳምና ሔዋን የተሰጠውን ሕግ እናስባለን$ ረሃብ ሲሰማን በሰው ልጅ ላይ ደርሶ የነበረው የጸጋ ረሃብ$ የመንፈስ ረሃብ ይታወሰናል$ ስንደክም ስንጐሰቁል በአዳምና ሔዋን የደረሰው የመንፈስ ጉስቁልና$ የበደልን የዕዳ ቀንበር ተሸክመው የደረሰባቸው ድካም ይታሰበናል፡፡ እኛም በነርሱ የደረሰችው ሞት በእኛ እንዳትደርስ ዳግም ወደ ኃጢአት እንዳንመለስ ይመክረናል ያሳስበናል፡፡
 
በጾሙም መጨረሻ የሐዲስ ኪዳንን በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን፡፡ ያን ጊዜም ሞትን ካሸነፈው አምላክ ጋር አንድ እንሆናለን (ዮሐ.6$55-58)፡፡ ሞታችን በሞቱ እንዳለፈ እናስባለን (1ቆሮ.11$26)፡፡ በመሆኑም ይህ ወቅት በዓለ ትንሣኤ- የሐዲስ ኪዳን ፋሲካን ለማክበር$ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ራሳችንን የምናዘጋጅበት የምንፈትንበት ነው (1ቆሮ.11$27)፡፡
 
9. የሥራ መጀመሪያ ጾም ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ሥራውን ከመጀመሩ$ የመንግሥተ ሰማያትን አንቀጽ ከማስተማሩ በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ መዓልትና ሌሊት ጾመ፡፡ ይህም ለእኛ የማንኛውም ነገር መጀመሪያው ጾም መሆኑን ሲያሰተምረን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያት ጾምን የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት፡፡
 
እንዲሁም ይህ የጾም ወቅት፡-
የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ተኩላዎች እንድንጠነቀቅ ያስተምረናል፡፡ ጠላት ዳያብሎስ ጌታችንን ሲፈትን ከመጽሐፍ ቅዱሰ እየጠቀሰ ነበር (መዝ 2ዐ$11)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም የጠራ፣ ጥቅስ የጠቀሰ ሁሉ መንፈሳዊ ሰው$ እውነተኛ ክርስቲያን ሊባል አይችልም፡፡ መጥቀስማ ዲያብሎስም ይጠቅሳል ሕይወቱን አይኖረውም እንጂ፡፡
 
እንዲሁም በዚህ የጾም ሰሞን ጠላታችን ዲያብሎስ ያዘጋጀልንን ወጥመድ አስበን ለገድል የምንዘጋጅበትም ነው፡፡ ጌታን ወደ መቅደስ ጫፍ አውጥቶ ወደ ታች ተወርወር እንዳለው ሁሉ እኛንም በትዕቢትና በከንቱ ውዳሴ ወደ ላይ አውጥቶ በኃጢአትና በውርደት በኃፍረትና ከመንፈስ በማራቆት ሊወረውረን ይሻል፡፡
 
ስለዚህ ትሕትናን በምታለብስ ጾም ድል እንንሣው፡፡
እንግዲህ ዐቢይ ጾም ማለት$
·        ጌታ ስለኛ ባየው መከራ የምናዝንበት፣
·        በሰጠን ኃይል ከሰይጣንና ከፈቃደ ሥጋ የምንዋጋበት፣
·        በበደልነው ተገብቶ የካሠልንን እያሰብን ዳግም ወደ ኃጢአት ላንመለስ ቃል የምንገባበት$
·        አርአያ ሆኖ ከሠራልን ሥርዓት፣ ከኖረልን ሕይወት የምንማርበት፣
·        ራሳችንን ለፋሲካው በግ ለሥጋ ወደሙ የምናዘጋጅበት ሰሞን ነው፡፡
በመሆኑም በሰላም፣ በፍቅር፣ በትሕትና ጾመን ለበዓለ ትንሣኤው በሰላም እንድንደርስ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቀን አሜን፡፡

Written By: host
Date Posted: 3/2/2008
Number of Views: 13727

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement