View in English alphabet 
 | Saturday, April 20, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ኒቆዲሞስ

 የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሰንበትና ሳምንቱ ኒቆዲሞስ ይባላል። ኒቆዲሞስ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሰንበት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ «ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ መልአኮሙ ለአይሁድ ዞሖረ ኃቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ ለኢየሱስ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ፡- ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል የአይሁድ አለቃ የሆነ ከፈሪሳውያን ወገን አንድ ሰው ነበረ፡፡ እሱ አስቀድሞ ሌሊት ሄዶ ኢየሱስን በመቃብር አንቀላፋህ በትንሣኤህ አንሣኝ» ያለው ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ሰገደ መንፈቀ ሌሊት ለዘቀደሳ ለሰንበት፡- ሰንበትን ለአከበራት ጌታ ኒቆዲሞስ ኢየሱስን ረቢ አብ መምህር ሆነህ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው፡፡» እያለ ኒቆዲሞስ ሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ እየሔደ ይሰግድ እንደነበረና ምሥጢረ ጥምቀትን ከእሱ እንደተማረ እየጠቃቀሰ እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት ለዚሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከጌታ ለመማሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡ የዚህ በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በዮሐንስ ወንጌል ምዕ 3 ቁጥ 1 እስከ 21 ተጽፏል፡፡

በዚህ ክፍለ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ምሥጢረ ጥምቀትን ብቻ ሳይሆን ርደቱን፣ ስቅለቱን፣ አዳኝነቱን አስተምሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ ከአርማትያሱ ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ጌታን የገነዘው ታላቅ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሰንበት ከዚህ ጀምሮ የኒቆዲሞስ መታሰቢያ እስከ 3 ቀን ይከበራል ማለት ማክሰኞ ድረስ የኒቆዲሞስ ቀኖች ናቸው፡፡

ሮሜ 71-19

«ወንድሞች ሆይ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን) ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች፡፡ ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም፡፡

እንዲሁ ወንድሞቼ ሆይ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ እናንተ ለሌላው ከሙታን ለተነሣው ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ፡፡ በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤ አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን ከሕግ ተፈትተናል ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን) ሕግ ኃጢአት ነውን) አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና፡፡ ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና፡፡ እኔም ዱሮ ያለሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል፡፡ ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት፡፡

እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን) አይደለም ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር፡፡ ሕግ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ፡፡ የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው፡፡ እንጂ፡፡ በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም የማልወደውን ክፉውን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም፡፡»

1 ዮሐ 418

«ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም፡፡ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን፡፡ ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል) እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን፡፡»

 

የሐዋ.ሥራ 534-42

 

«ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፡፡ እንዲህም አላቸው የእሥራኤል ሰዎች ሆይ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ፡፡

 

ሰሙትም ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፤ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፡፡ እነርሱም ስለስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር፡፡ »

 

መዝ 163

 

ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመጻ በላዕሌየ
ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው

 

ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፡፡
ፈተንኸኝ ምንም አላገኘህብኝም፡፡
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፡፡

 

ዮሐ 31-12

 

«ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው፡፡ ኒቆዲሞስም፡- ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል) ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንደ ይችላልን) አለው፡፡ ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ እይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል ድምፁንም ትሰማለህ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡ ኒቆዲሞስም መልሶ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል) አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ የእሥራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን) እውነት እውነት እልሃለሁ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክራችንንም አትቀበሉትም፡፡ ስለምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ ስለሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ

 

 

ቅዳሴ - ዘእግዝእትነ /ጐሥዓ/


Written By: host
Date Posted: 4/12/2008
Number of Views: 6187

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement