View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ)

እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ዕለተ ቅዳሜ ናት፡፡

ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፤ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ስላረፈባት ሰንበት ዐባይ (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች (ዘፍ. 1፡3)፡፡ ይህችን ታላቋን ሰንበትም እንዲያከብሯት ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን ታዘው ነበር፡፡
 
ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የድኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፍጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደተደረገባት ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አሩ አምላክ በሐዲስ መቃብር አርፎባታል (ማቴ. 27፡61)፡፡
 
በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ በምሥጢር ከሰንበት ዐባይ ጋር ትገናኛለች፡፡ ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ) የተሰኘችውም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ መምህራቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ነገረ ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡     
 
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በሐዘን፣ በጾምና በጸሎት ዕለቷን እንዳከበሯት ክርስቲኖችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል፣ አሊያም ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም የጌታን ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
  
ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲን ይሰበሰባሉ፡፡ የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ›› - በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፣ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት ምእመናንም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡
 
የዚህ የቄጠማው ታሪክ መነሻው የኖኅ ዘመን ታሪክ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች በማየ አይህ ከጠፉ በኋላ የውኃውን መጉደል እንድትመለከት የተላከች ርግብ የምሥራች ምልክት የሆነ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ ተመልሳለች፡፡ በዚህም የውኃው መጉደል፣ የቅጣቱ ዘመን ማለፍ ተረጋግጧል (ዘፍ. 9፡1-29)፡፡  
 
ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነው ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት መተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፣ በጣታቸው ቀለበት ያደርጉታል፡፡
 
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲዖል (የሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
 
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፣ አሜን፡፡ 

Written By: host
Date Posted: 4/26/2008
Number of Views: 8312

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement