‹‹የተቀደሱ ተራሮች›› የተባሉ የእመቤታችን ወላጆችና ቅድመ አያቶች ሲሆኑ እኒህም እነ ኖኅ፣ እና አብርሃም ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ናቸውና፡፡
ኢያቄምና ሐናም ከተቀደሱት ተራሮች መካከል ሲሆኑ የእመቤታችን አባትና እናትም ናቸው፡፡ ሁለቱም በተቀደሰ ጋብቻ ፀንተው ቢኖሩም መካን በመሆናቸው ያዝኑ ነበር፡፡ ይሁንና በስተርጅና እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ብፅዓት ገቡ፡፡ ብፅዓቱም ‹ወንድ ብንወልድ ‹‹ወጥቶ ወርዶ፣ አርሶ፣ ቆፍሮ፣ ነግዶ፣ አትርፎ ይርዳን አንልም፣ ለቤተ እግዚአብሔር ጠባቂ አገልጋይ ይሁን እንጂ፤ ሴትም ብንወልድ እንጨት ሰብራ፣ እንጀራ ጋግራ፣ ውሃ ቀድታ፣ ወፍጮ ፈጭታ፣ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ውኃ ቀድታ መሶበ ወርቅ ሰፍታ ትኑር እንጂ›› የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔርም የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትንም የማይነሳ ቸር አምላክ ነውና ብፅዓታቸውን ፈጸመላቸው፡፡ በተቀደሰ ጋብቻ ንጽሕት ቅደስት ልጅ አገኙ፡፡ ይህንንም የልደቷን ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደስታ ታከብረዋለች፡፡
ስለ እመቤታችን ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ?
1. ወላዲተ አምላክ ናት
‹‹በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፣ ወደ ምንጣፌ አልጋ አልወጣም፣ ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፣ ለእግዚአብሔር ሥፍራ፣ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ›› (መዝ.131፡35)፡፡ ዳዊት ይህንን ሲናገር ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የሚለውን ረስቶ አይደለም፡፡ ልበ አምላክ ነውና (ኢሳ.66፡1)፡፡ ነገር ግን የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ የእግዚአብሔር ሥፍራ የተባለች እመቤታችን ናት፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሯልና፡፡ ስለዚህም ነው ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹የእግዚአብሔር ከተማ የእሥራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል›› ያለው (ኢሳ.6፡11)፡፡ ‹‹ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፣ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ›› (መዝ.131፡14)፤ ‹‹በውስጧም ሰው ተወለደ›› (መዝ.86፣5)፡፡
ማኅፀኗን ዓለም ያደረገው እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡ ‹‹ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል›› (ኢሳ.9፣6)፡፡ የተወለደው ሕፃን ኃያል አምላክ ስለሆነ እናቱም ወላዲተ አምላክ ትባላለች፡፡ ‹‹. . .ስለዚህም ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚብሔር ልጅ ይባላል›› (ሉቃ.1፣35)፡፡ ‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?›› (ሉቃ.1፣43)፡፡ ኪሩቤል መንበሩን ለመሸከም የሚርዱለትን እርሷ ፀንሳዋለች፣ አዝላዋለች፣ ጡቱንም አጥብታዋለችና ‹‹ከኪሩቤልም የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ›› አላት አባ ኤፍሬም፡፡
2. የዘላለም ድንግል ናት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሀልዮም በገቢርም /በሀሳቧም በሥራዋም/ ድንግል ናት፡፡ ‹‹ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደመቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር፣ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፣ ሰውም አይገባበትም፡፡ የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል›› (ሕዝ.44፣1)፡፡ ምሥራቅ የተባለች እመቤታችን ናት፡፡ በርም የተባለ ድንግልናዋ ነው፡፡ በተዘጋው በር /በድንግልና/ የገባው የእሥራእል አምላክ እግዚአብሔር የተባለ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹እህቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ፣ የታተመ ፈሳሽ ናት›› (መኃ.4፣12)፡፡ የተቆለፈ ገነት አላት፤ በተከፈተ ገነት ቅዱሳን ጻድቃን ገብተው እንደሚኖሩበት በተቆለፈ ገነት ግን /ድንግልና/ መግባት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለማጠየቅ፡፡ የተዘጋም ምንጭ አላት፤ ምንም ብትዘጋም /በድንግልና/ የሕይወት ውኃ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳዋለችና፡፡
3. ስግደት ይገባታል
የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፡፡ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ (ኢሳ.6፣14)፡፡ ‹‹ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኗ ውስጥ ዘለለ›› (ሉቃ.1፣41)፡፡ የእመቤታችን አክስት በማኅፀኗ የነበረው ፅንስ ለእመቤታችን የጸጋ፣ በማኅጸኗ ለነበረው ለጌታችን ደግሞ የአምልኮት ስግደት ሰግዷል፡፡ ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፡፡ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፣ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፣ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ (ኢሳ.49፣23)፡፡
4. አማላጃችን ናት
‹‹የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ›› (መዝ.44፣12)፡፡
‹ይማለላሉ› ማለቱ ድንግል ሆይ በፊቱ ሞገስ አግኝተሻልና ከአምላካችን ከአምላክሽ ምሕረትን /ይቅርታን/ ለምኝልን እያሉ ይማፀናሉ ለማለት ነው፡፡
‹‹በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ /ሞገስ/ አግኝተሻልና አትፍሪ›› (ሉቃ.1፣3)፡፡
እግዚአብሔር ለእመቤታችን ከሰጣት ጸጋዎች መካከል አንዱ በፊቱ ቆማ ማማለድ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህንንም ቃል የተናገረው ከእግዚአብሔር የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡
‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም› ዮሐ.2፣3፡፡
ከዚህ ጥቅስ ወረድ ብሎ ያለውን አባባል መነሻ በማድረግ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ›› ብሏታልና አታማልድም አይባልም፡፡ ጌታ ይህን የተናገረው አታማልድም ለማለት ቢሆን ኖሮ የለመነችውን ባላደረገላት ነበር፡፡ ቋንቋውም የእናትና የልጅ በመሆኑ ተግባብተውበታል፡፡ እንዲህ ማለቱም አንቺ ለምነሽኝ እንዳላደርግልሽ የሚያግደኝ ምን ጠብ አለኝ ለማለት ነው፡፡ አነጋገሩም ከእሥራኤል ወገን ተወልዷልና የእነርሱን ዘይቤ የተከተለ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ቃል የተናገረው ርኩስ መንፈስ /ጋኔን/ ቢሆንም ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለቱ መሳደቡ አይደለም፡፡ እንዲህ ብሎ ሰይጣን እግዚአብሔርን አይሳደብምና፡፡ ትርጉሙም ወዳዘዝኸኝ እሄዳለሁ ብቻ አታሰቃየኝ ማለቱ ነው (ማር.5፣7)፡፡
ያቺ ሴት ነቢዩን ኤልያስን ‹‹የእግዚብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› ብላዋለች (1ኛ.ነገ.17፣10)፡፡ እንዲህ ማለቷ መሳደቧ አልነበረም፡፡ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ ለማለት እንጂ፡፡ ልጇን እንዲያድንላት እየፈለገች አትሳደብምና (1ኛ.ነገ.17፣18)፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ አባባሎች የምንረዳው የእሥራኤላውን አዎንታዊ ንግግር መሆኑን ነው፡፡ ጌታችንም ለእመቤታችን ከዚህ የተለየ አልተናገረም፡፡
5. የእመቤታችን ክብሯ
መትሕተ ፈጣሪ፣ መልእልተ ፍጡራን /ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ/ ናት፡፡ ‹‹ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል›› (ኢሳ.60፣12)፣ እንዲሁም ‹‹በምድር ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ›› (መዝ.44፣16) ከሚሉት ጥቅሶች የምንረዳው እመቤታችንን የማያከብር፣ አማላጅነቷን የማያምን፣ የማይሰግድላትም ከእግዚአብሔር መንግሥት ዕድል ፈንታ ያጣል ማለትን ነው፡፡
6. ስለ ነቃፊዎቿ
‹‹ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ›› (ኢሳ.49፣25) እንደተባለ እመቤታችንን የማያከብሩ፣ አማላጅነቷንም የማያምኑ ሁሉ የሚጣሉት ከእርሷ ጋር አይደለም፡፡ ይልቁንም ከኃያላን ኃያል ከእግዚአብሔርም ጋር እንጂ፡፡
7. ምስጋና ይገባታል
መልአኩም ወደእርሷ ገብቶ ‹‹ደስ ይበልሽ ጸጋ የተሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣ አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አላት›› ሉቃ.1፣28፡ ‹‹በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፣ በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች፣ ‹አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው››› (ሉቃ.1፣42)፡፡ እመቤታችንን ማመስገን የሚችለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ብቻ ነው፡፡ ‹‹እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል›› (ሉቃ.1፣49) እንዲል፡፡
8. እናታችን ናት
‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል›› (መዝ.86፣5) እንደተባለው የሕያዋን ሁሉ እናት ተብላ የተጠራችው ሔዋን በአጠፋችው ጥፋት የሰው ዘር እናታችን ብሎ ለመጥራት የሚደሰትባትን እናት በማግኘቱ እናትነቱን ያመነባት ሁሉ ይናገረዋል፡፡ የእርሷ እናትነት ጽድቅን ለተራቡት ምግብ፣ ለተጠሙትም መጠጥ የሚሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘች በመሆኗ ከሴቶች ሁሉ የተለየ እናትነት ነው፡፡
እናት ለልጇ ወጥታ ወርዳ የሚበላውን እንድትሰጠው እመቤታችንም የአዳም ተስፋው እስኪሞላለት ድረስ ከመስቀሉ እግር አልተለየችም፡፡ እኛም እናትነቷን እስከመጨረሻው ሕቅታ ልንጸና ይገባል፡፡
በእናታችን በሔዋን የተነሳ እናቶች ምክንያተ ድኅነት ሆኑ፡፡ የቀደመችው ሔዋን ሞትን ቆርጣ ሰጠችን፣ ዳግማዊቱ ሔዋን እመቤታችን ግን ሕይወትን ወልዳ ሰጠችን፣ በሔዋን የተነሣ ከገነት ተባረርን፣ በድንግል ማርያም የተነሣ ግን ወደ ገነት ተመለስን፣ በሔዋን ስሕተት የሰው ልጅ በመበደሉ መላእክት ገነትን ዘግተው አስወጡን፣ እመቤታችን ጌታችንን ብትወልድ ግን ወደ እኛ መጥተው አብረውን ዘመሩ፡፡
ስለዚህም ነው እመቤታችንን ከጌታ የማዳን ሥራ ነጥለን አናያትም የምንለው፡፡ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ አብራው ነበረችና፡፡
እመቤታችን የጸጋ እናታችን ናት፡፡ ሰዎች ጸጋን ወጥተው ወርደው፣ ነግደው አትርፈው የሚያመጡት ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገን ዐውቆ በነጻ የሚሰጠን በረከት ነው፡፡ የሥላሴ ልጅነት ጸጋ ነው፡፡ እኛ አላመጣነውምና፡፡ ነገር ግን ተሰጠን፡፡ መንግሥተ ሰማያት ጸጋ ናት እኛ አልከፈትናትም ከፍቶ ሰጠን እንጂ፡፡ ሰው ሆኖ መፈጠር ጸጋ ነው ታግለን አላገኘነውም፣ ተሰጠን እንጂ፡፡ ሥጋና ደሙ ጸጋ ነው እኛ አልተጋደልንበትም፡፡ ራሱ እንደሚያስፈልገን ዐውቆ ያለ እርሱም ሕይወት ስለሌለን ሰጠን እንጂ፡፡ እመቤታችንም እንዲሁ የተሰጠችን የጸጋ እናታችን ናት፡፡ ‹እነኋት እናትህ› ብሎ በዮሐንስ አማካይነት ሰጥቶናልና (ዮሐ.19፣26)፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ስሟን የምትጠራው፣ በዓላቷን የምትዘክረው፣ እርሷንም የምታከብረው ይህን በመረዳት ነው፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለን፣ አሜን፡፡