View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

27ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መከረ

(አዲስ አበባ)፡- ቤተ ክርስቲያን በ 2000 ዓ.ም ባከናወነቻቸው ተግባራትና ስለ አጋጠሟት ችግሮች የመከረው 27ኛው የመንበረ ­ትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ከጥቅምት 7-11 ቀን 2001 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተካሔደ፡፡

ጉባዔው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ­ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ርዕሰ መንበርነት በደማቅ ሥነ ሥርዓት በጸሎት ተከፍቷል፡፡


ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለዐቢይ ጉባዔው አባላት ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺሕ ዓመተ ምሕረት ያከናወነቻቸውን ተግባራትና ያጋጠማትን ችግሮች የሚዘረዝር ዘገባ ያቀረቡ ሲሆን፤ የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና ብፁዓን አባቶች ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገረ የተከናወኑ የሥራ እንቅስቃሴዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን የሚመለከቱ ሪፖርቶች አቅርበዋል፡፡


የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ቤተ ክርስቲያን በ2000 ዓ.ም ያጋጠሟትን ችግሮች እንደዘረዘረው የሥራ ማስኬጃ ማጠር፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማጣት፣ የገቢና የወጪ ሒሳብ በምርመራ አለማጣራት በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 15 ንዑስ ቀጥር 3 ከተራ ቁጥር 1-6 በተደነገገው መሠረት የምንኩስና አሠጣጥ ጉዳይ መልክ አለመያዝ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው፡፡


በተጨማሪም የአብነት መምህራን በቂ መተዳደሪያ በጀት ማጣት፣ ቦታቸውን እየለቀቁ መፍለሳቸው፣ በገዳማት መተዳደሪያ መቁኑን እጥረትና የመናንያን ከገዳም መፍለስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በ2000 ዓ.ም ያጋጠማት ችግር መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም ደግሞ የተያዘ አጠቃላይ ዕቅድ በተመለከተ ክሊኒክ፣ ሆስፒታል መገንባት ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲተረጎሙ ማድረግ፣ በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረው ስምሪት እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሰበካ ጉባዔን በማጠናከር የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ያልተቆጠበ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ ለማካሔድ ታቅዷል፡፡


ከውስጥ አሠራር ውጪ ያጋጠሙትን ችግሮች በተመለከተ የእስልምና እምነት ተከታዮች «በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አልነጃሺ /ነጋሺ/ የሚባል ንጉሥ በአክሱም ነበረ» በማለት ታሪክ ማዛባታቸው፣ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም›› የሚል ስብከትና መጥፎ ቅስቀሳ ማድረጋቸው፣ የቤተ ክርስቲያንን የልማት ሥራ ማደናቀፋቸው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት የሚያወሳ ሲሆን የመናፍቃን እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱም ተካቷል፡፡


የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ከብፁዕ ወቅዱስ ­ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ጀምረው የሚገኙ መምሪያዎች ያከናወኗቸውን ዋና ዋና ተግባራት የዘረዘረ ሲሆን የብፁዕ ወቅዱስ ­ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ቅዱስነታቸው በ2000 ዓ.ም ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ያከናወኑትን ተግባራት ጠቁሟል፡፡


የቤተክርስቲያን የውጪ ግንኙነቱን ለማጠናከር ለመንፈሳውያን ተቋማት ደቀ መዛሙርትና አገልጋዮች የውጪ ትምህርት እንዲያገኙ የስኮላር ሺፕ ጥያቄ ለአኃት አብያተ ክርስቲያናቱ የውጭ ግንኙነት መምሪያ አቅርቧል፤ የሊቃውንት ጉባዔ የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ ተጠቃልሎ እንዲታተም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የኤፌዴሪ መንግሥት የትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና እምነቶች አስመልክቶ አንድ መጽሐፍ ለማዘጋጀት በማቀዱ በቤተ ክርስቲያናችን አጠር ያለ ጽሑፍ እንዲላክለት ስለጠየቀ የሊቃውንት ጉባዔው የቤተ ክርስቲያናችንን እምነትና ሥርዓት ያካተተ 12 ገጽ የያዘ ጽሑፍ አዘጋጅቶ አስረክቧል፡፡ በተጨማሪም በ2001 ዓ.ም ሃይማኖታውያን የሕዝብ በዓላት የሚውሉበት ቀናትን ለተወካዮች ምክር ቤት ልኳል፡፡


የካህናት አስተዳደር መምሪያ በበጀት ዓመቱ ከየአህጉረ ስብከቱ የመጡ 53 ጉዳዮች አስፈላጊው መልስ መስጠቱን በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈውን የዲቁናና የቅስና መዓርግ አሠጣጥን በተመለከተ ለየአህጉረ ስብከቱ መመሪያ እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ደግሞ ስለ አብነት ትምህርት ቤቶች ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ መመሪያ እንዲሰጥ እየጠበቀ እንደሚገኝና በመላው አህጉረ ስብከት የሚገኙ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች በቅጽ ተሞልተው እንዲላኩ ማድረጉ ተገልጿል፡፡


የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በ25 አህጉረ ስብከት ሐዋርያዊ ተልዕኮ ማከናወኑን፣ በማዕከል ደረጃ በተቋቋመው የስብከት ማስፋፊያና ማጠናከሪያ በወር ሁለት ጊዜና በየአሥራ አምስት ቀኑ የሚጠናከርበት መንገድ ማመቻቸቱ ተገልጿል፡፡ የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ በቀጣይ ጊዜያት የተቀላጠፈ ሥራ ለመሥራት በሥራ ላይ የሚገኘውን ቃለ ዓዋዲ እንዲሻሻል በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ምሁራንና የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ማቋቋሙ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡


በአስተዳደርና አቅም ግንባታ መምሪያ በኩል የተለያዩ ጥናቶችን አጥንቶ ለበላይ አካል መቅረቡ በቀጣይም ሁለገብ ጥናት ለማካሔድ ዝግጅቱን አጠናቆ የመረጃ አሰባሰብ ተግባር ጀምሯል፡፡ በጡረታና ሪኮርድ ክፍል ሠራተኞች የጡረታ ፎርም እንዲሞሉ አድርጓል፡፡ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ በበጀት ዓመቱ ሂሣብ የሚንቀሳቀስባቸውን 14 መመሪያዎችና ድርጅቶች የሒሳብ ምርምራ ያደረገ ሲሆን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ላይ በ1998 ዓ.ም ባደረገው የሒሳብ መርመራ ጉድለት ማግኘቱን አውስቷል፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ የወጪ ብልጫ ማሳየቱን ተገልጾ የቀረበው ሪፖርት ውሳኔ ባለማግኘቱ በ 2000 ዓ.ም ገንዘብ ያዥ የተደመጠው ሪፖርት ውሳኔ ሳያገኝ ሒሳብ አላስመረምርም ማለታቸው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም የእሥራምዕት በዓሉን ለማክበር ተቋቁሞ በነበረው ኮሚቴ ሲያንቀሳቀስ የነበረውን ሒሳብና ንብረት እንዲመረምር ታዞ እስከ አሁን መመርመርም ሆነ ንብረት መቁጠር አልተቻለም፡፡ ሲል በዘገባው ገልጿል፡፡


በበጀት ዓመቱ የማኅበረ ቅዱሳንን የሥራ ክንውን በተመለከተ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ማኅበሩ የሕዝብ ጉባዔ ማካሔዱን፣ በዝዋይና በጅማ ተተኪ መምህራን ማሠልጠኑን የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳማትን መርዳት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የግቢ ጉባዔ ለማጠናከር ቅኝት ማድረጉን የግንባታ ዲዛይኖችን ለሃያ አብያተ ክርስቲያናት መሥራቱን አውስተዋል፡፡ በተለያዩ አህጉረ ስብከት በብር 215,725.49 /ሁለት መቶ አሥራ አምስት ሺሕ ሰባት መቶ ሃያ አምስት ብር ከአርባ ዘጠኝ ሣንቲም/ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተተግብረው ርክክብ መደረጉንና በብር 1,022,065.44 /አንድ ሚሊዮን ሃያ ሁለት ሺሕ ስልሳ አምስት ብር ከአርባ አራት ሣንቲም/ የተቋቋሙ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡


በጉባዔው ማጠቃለያ ላይም ብፁዕ አቡነ ጳዉሎስ ባስተላለፉት መልእከት አባቶቻችን በደም ያቆዩልንን አደራ በአንድነት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል ብለዋል፡፡


በጉባዔው ላይ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግሮች በተሳታፊዎች ተነሥተው ለውይይት የቀረበ ሲሆን በተለይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሐሰተኛ መምህራን መናፍቃን በቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የፈጠሩት ጫና በዋናነት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡


ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ የሚገጥማትን ችግር ለመቅረፍና ምእመናን ከውስጥና ከውጪ የሚቃጣባቸውን የአጽራረ እምነት ትንኮሳ ነቅተው እንዲጠብቁ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ­ትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ጥናት የቀረበ ሲሆን፤ ስለ ምእመናን ቆጠራ በስትራቴጂክ ዕቅድና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በባለሙያዎች የጥናት ወረቀት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡


Written By: host
Date Posted: 11/14/2008
Number of Views: 5547

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement