View in English alphabet 
 | Wednesday, October 27, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ጾም፣ የጽድቅ በር

የጾም ወቅት መንፈሳዊ ተጋድሎዎች የሚበዙበት፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እምነታችን የሚጠነክርበት፣ ከዲያብሎስ ጋራ የምንዋጋበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ቅርበትና ቤተሰባዊነት የምናሻሽልበት፣ ምሥጢራችንን ለአምላካችን የምንናገርበት፣ ድሆችን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህም የሚጾም ሁሉ በሥጋ ፈቃዱ ላይ ድል ይቀዳጃል፣ የለመነውን ያገኛል፣ ሰማያዊ የሆነውን ምሥጢር ለማየት ከዓላማዊ ነገሮች ተለይቶ ይነጠቃል፣ በዓለም እየኖረ ከዓለሙ ይለያል፡፡ ዮሐ.15÷19፡፡

ሀ. ጾም ለምን?
ብዙ ሰዎች ለምን እንደሚጾሙ ስለማያውቁ ከእህል ከውሃ ተከልክለው ለተወሰኑ ሰዓታት መቆየት፤ ከሥጋ፣ ከወተት፣ ከቅቤ መለየት ብቻ ጾም መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ከውፍረታቸው ጥቂት የቀነሱ እንደሆነ #ጾሙ አከሳኝ$ ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ይህ ግን በጭራሽ የጾም ዓላማ አይደለም፡፡ ዓላማው ለፈቃደ ነፍስ ለመገዛት፣ በዚህም ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ፣ በትህትናም ከተናቁት ጋር አብሮ ለመዋል (የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታመሙትን በመርዳት) በእነዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ስለራሳችንና ስለሌሎች (ስለ ተጨነቁ፣ ስለ ታሥሩ፣ ስለ ተሠደዱ በጦርነት ስለሚሰቃዩ…ስስ) ከእግዚአብሔር ምሕረትን መለመን ነው፡፡ በተጨማሪም፡-
1. እግዚአብሔርን ለመለመንና ከእርሱም በረከትን ለመቀበል፡- እንደ ዕዝራ እና አስቴር ስለራሳችን፣ ስለ ልጆቻችንና ወዳጆቻችን ምሕረት ለመለመን፣ (ዕዝ.8÷21፣ ኢሳ. 4÷3፣16)2. ለመጸጸት ንስሐ ለመግባት፡- እንደ ነነዌ ሰዎች ከእግዚአብሔር ለመታረቅ፣ (ዮና. 3÷8-10)፡፡ እንደ ዳንኤል (በድለናል፣ አምፀንማል፣ አሁን ግን ይቅር በለን) በማለት፣ (ዳን. 9÷5-8)፡፡

 3. ለአገልግሎት፡- ቅዱሳን ሐዋርያት ወደየክፍለ ዓለሙ ለስብከተ ወንጌል ከመለያየታቸው በፊት ጾመዋል፡፡ ልናበረክት ስላቀድናቸው መንፈሳዊ ሥራዎች በቅድሚያ ልንጾም ይገባናል (የሐዋ. 13÷2-3)፡፡

 ለ. ጾም ከምን?
ከላይ የተጠቀሰውን ጾም ፍጹም ለማድረግም ወቅት ተለያይቶለት ይጾማል፡፡ ይህም ለተወሰኑ ጊዜያት ከጥሉላት ምግቦች (ከሥጋ፣ ከወተት፣ ከቅቤና ከተመሳሳይ ውጤቶች) እና ከሚያሰክር መጠጥ ነው፡፡
 
ቅዱስ ዳዊት በጾሙ ጊዜ #ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ$ (መዝ.108÷24) እና ነቢዩ ዳንኤልም #በዚያም ወራት እኔም ዳንኤል ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፣ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም$ (ዳን.10÷3) እንዳሉ ከጥሉላት እንከለከላለን፡፡
ሆኖም ግን አንዳንድ ሰዎች የዓሣን ሥጋ እንደ ሥጋ ባለመቁጠር ይሁን ወይም ሌላ መበላት እንዳለበት ሲከራከሩ ይታያሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በጾም ጊዜ ጥሉላት የሌሉበት ምግብም ቢሆን በመጠን ይበላ እያለች (ዳንኤል ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም እንዳለ) የዓሣ አለመበላት እንደ ጥያቄ ሊነሳ አይገባውም፡፡ እንዲሁም በእነዚህ የተቀደሱ የጾም ጊዜያት ክርስቲያን ሁሉ ከሚያሰክር መጠጥ የመለየት ግዴታ አለበት፡፡ ነቢዩ ዳንኤል (ጠጅም በአፌ አልገባም) ያለው ይህንኑ ለማጠየቅ ነው፡፡ የራስን መንፈሳዊ ሕይወትም ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት መካከል የምግብ ማካካሻ ማድረግ የማይገባ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ያስፈልገዋል፡፡
 
ሐ. ጾምን እንዴት እንቀበለው
ጾም መጣብን ተብሎ የሚፈራና የሚማረር ሳይሆን በመጣልን ተብሎ በጉጉት የሚናፈቅ ዕድሜ የሚለመንለት የሥጋና የነፍስ አስታራቂ ሽማግሌ ነው፡፡ የጾም ቀናት መንፈሳዊ ኃይል ማግኛና ስንቅ ማከማቻ ሲሆኑ ለሥጋ ፈቃድ ደግሞ የሞት ጊዜያት ናቸው፡፡ ጾምን የሚጾም ሰው የሚከተሉትን ቁም ነገሮች በሕሊናው ማስቀመጥም ያሻዋል፡፡
 
1. ዕለት ተዕለት የማይቋረጥ ጾም ያም የአንደበት፣ የዓይን፣ የእጅ፣ የእግር፣ የሕሊና ወዘተ…ጾም ነው፡፡
·         አንደበት - ከሃሜት፣ ከስድብ፣ ከሽሙጥ፣ ከሽንገላ፣ ምስጢር ከማባከን፣
·         ዓይን፡- ዓይቶ ለዝሙት፣ ለስርቆት፣ ከመመኘት፤
·         እጅ፡- ከመማታት፣ ከመግደል፣ ከመስረቅ፣ ሱጋራና ሀሺሽ ከመጨበጥ ጉቦ ከመቀበልና ከመስጠት፤
·         እግር፡- ወደ ዝሙት፣ ስካር፣ ዘፈን፣ ወዘተ…ቦታ ከመሄድ፤
·         ኀሊና፡- ከምቀኝነት፣ ከቅንዓት፣ መጾም ነው፡፡
2. ዓላማና ይዘቱ መንፈሳዊ መሆኑን፡- እንደ ግዴታ፣ ብዙ ሰው ስለ ጾመው ብቻ፣ ወይም ለመወደስ (ጿሚ ለመባል) የሚጾም መሆን የለበትም፡፡
 
3. የጸጸትና የልብ ንጽሕና ጊዜ መሆኑን - ‹‹ወደኔ ተመለሱ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› (ዘካ. 1÷3) እንዳለ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን ሥራ መፈፀሚያ፣ በደልን አምኖ በኃጢአት የጎሰቆለች ነፍስንም በንስሐ፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የሚያነጹበት ጊዜ ነው፡፡
 
4. ለነፍስ ምግብ ማግኘ ጊዜ መሆኑን - ከሥጋዊ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ በጾም ወራት የዕለታቱን ቅድስና፣ ታሪክ እና ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ሥርዓቶች በማወቅ የተዉትን የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች ከማሰላሰል ይልቅ ለነፍስ የሚሆነውን ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን እያጣጣሙ መንፈሳዊ ሕይወትን ለማለምለም መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
 
እንዲህ ያለውን ጾም የጾሙት (ሙሴ፣ አስቴር፣ ሠለስቱ ደቂቅ) ከእህል ከውኃ በመከልከላቸው አማሩ፣ ተዋቡ፣ ፊታቸው አበራ እንጂ ለበሽታና ለሞት አልተዳረጉም (ዘፍ. 34÷24-35፣ አስቴ.2÷17 እና ዳን.1÷12-15)፡፡
 
መ. ጾምና ንስሐ
ሰው በጾም፣ ሥጋውን ለኃጢአት ከሚያነሣሣ ከማንኛውም ምኞት ይከለከላል፡፡ በዚህም ጊዜ የራሱ ኃጢአት ከፊት ለፊቱ በመስተወት ውስጥ እንዳለ ምስል ቀርቦ ይታየዋል፡፡ ፈጥኖም ለንስሐ ይዘጋጃል፡፡ #በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ$ እንዳለ ሐዋርያው (2ኛ ቆሮ.13÷5) ማንነታችንን፣ ትናንትናና ዛሬ ምን መሆን አለበት? ብለን የምንጠይቅበት ወቅት ነው፡፡ እግዚአብሔር ጾማችንን እንዲቀበለው ራሳችንን እንመርምርና ካለፈው የኃጢአት ኑሮ እንላቀቅ፡፡ ያን ጊዜም ፈጥኖ ይምረናል፡፡
 
#እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፣ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፣$ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፣ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል$ (ኢሳ.59÷1-2)፡፡
 
የጾምና የንስሐን ግንኙነት ስናነሳ የነነዌ ሰዎች ትዝ ይሉናል፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዮናስን እንዲህ ብሎት ነበር፡፡ #…ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ$ (ዮና.3÷8)፡፡ ይህንን ቃል ካስተላለፈ በኋላም እንዳያጠፋቸው እግዚአብሔርን አንድ ነገር አሸንፎታል፡፡ ያንንም ነቢዩ እንዲህ ሲል ተናግሮታል #እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ$ (ዮና.3÷10)፡፡ እነዚህ ሰዎች ምሕረት ያገኙት ማቅ ስለለበሱ፣ አመድ ስለነሰነሱ ወይም ሦስት ቀንና ሌሊት ከንጉሡ እስከ ሌላው፣ ከሰው እስከ እንስሳው ከእህል ከውሃ ስለተከለከሉ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በፊት ይህንንም ለማድረግ ያስገደዳቸውን ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውን (መጸጸታቸውን) ስላየ እንጂ፡፡ ከዚህ አባባል የጾም መጀመሪያው ንስሐ (ጸጸት) መሆኑን እንረዳለን፡፡
 
ስለዚህ እኛም በጾማችን ወቅት ስለ ኃጢአታችን ንስሐ እየገባን ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ይገባናል፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ትረሳኛለህ?›› ከማለት ይልቅ ‹‹እስከመቼ እረሳሃለሁ? እስከ መቼስ በተቀደደ መጋረጃ ፊቴን እሰውራለሁ?›› ማለት ይገባናል፡፡
 
ነፍሳችንን ከአሁኑ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ አንጽተን ልባችንን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እናድርጋት፡፡ ከተዘፈቅንበት የኃጢአት ባሕርም እንውጣ፡፡ በንስሐ ያለንም መንፈሳዊ ተጋድሏችንን እንጨምር፡፡ ይህን ለመፈጸምስ ከአሁን (ከዛሬ) ሌላ ምን የተሻለ ጊዜ አለን? ከዕድሜያችን ላይ አንዲት ሴኮንድ ባለፈች ቁጥር ሞት ወደ እኛ÷ እኛም ወደ ሞት እየተጓዝን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ በዋዛ ፈዛዛ የምናሳልፋቸው ጊዜያት ሊኖሩን አይገባም፡፡ መጽሐፍ #እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው$ ይላልና (2ኛ ቆሮ.6÷2)፡፡

 እግዚአብሔር ጾማችንን የድል ያድርግልን፡፡


Written By: host
Date Posted: 12/16/2007
Number of Views: 10264

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement