View in English alphabet 
 | Saturday, April 20, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ኪዳነ ምሕረት

ኪዳን የሚለው ቃል ተካየደ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ተማማለ፣ ተስማማ፣ ውል ገባ ማለት ነው፡፡ ኪዳነ ምሕረት ማለትም ደግሞ የምሕረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ስለሰው ልጆች ይቅርታ የገባላት ቃል ኪዳን ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት፣ ለሚያከብሩት፣ ለሚወዱትና ለሚወዳቸው ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ኪዳናትን ሰጥቷል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ከሚጠቀሱት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንመልከት፡፡

1- ኪዳነ ኖኅ

 የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ በሔዱ ቁጥር ኃጢአታቸውም እንዲሁ እየበዛ በመሔዱ በውኃ መጥለቅለቅ እንዲጠፉ ባደረገ ጊዜ ጻድቁ ኖኅ የሚድንበትን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው፡፡ ኖኅም እንደታዘዘው መርከብን ሥራ፡፡ በየወገናቸው ተባዕትና አንስት እየሆኑ በመርከብ ውስጥ ገብተው እንዲድኑ አደረገ፡፡ የጥፋት ውኃም ካለፈ በኋላ እንደገና እንዲበዙና ምድርን እንዲሞሏት እግዚአብሔር ፈቀደ፡፡ ምድርንም ዳግመኛ በንፍር ውኃ እንዳያጠፋት ለጻድቁ አባታችን ኖኅ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ «ቃል ኪዳኔንም ለአንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ልባሽ ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውሃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውሃ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር አለ በእኔና በአንተ መካከል ካንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ለዘላለም የማደርገው የቃልኪዳን ምልክት ይህ ነው፡፡ ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ፡፡ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል፡፡» /ዘፍ.9:13-16/፡፡ ይህም ቃል የጸና ሆኖ ምልክቱ /ቀስተ ደመናው/ እስከ ዛሬ ድረስ በግልጥ ሲታይ ይኖራል፡፡

 

2- ኪዳነ አብርሃም

 አብርሃም ከሣራ ልጅ ባለመውለዱ እያዘነ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር ተገልጦ «አብርሃም ሆይ አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው» አለው፡፡ እሱም « አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ ምን ትሰጠኛለህ ዘር አልሰጠኸኝም ወራሽም የለኝም» ባለው ጊዜ ልጅ እንደሚወልድ ዘሩም ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ እንደሚበዙና ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ያለውን ምድር ለዘሩ እንደሚያወርሰው ቃል ገባለት፡፡ አብርሃምም አምኖ ተቀበለ እንዲሁም ተፈጸመለት /ዘፍ.15:1.7/፡፡

 

3- ኪዳነ ዳዊት

 በነቢዩ ዳዊት አፍ «ኪዳን ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ከወዳጆቼ ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ» መዝ 88:2 ፡፡ ካለ በኋላ ለእርሱም የሰጠውን ቃል ኪዳን እንመለከታለን ይኸውም ዳዊትን ከሌሎች ወገኖቹ አብልጦ በመረጠውና የብዙ ወገኖቹ መሪ አድርጎ ባስቀመጠው ጊዜ ዳዊት ለፈጣሪው ቅን አገልጋይና ፍጹም ታማኝ በመሆኑ ልበ አምላክ እስከመባል ድርሷል፡፡ «ለአገልጋዬ ለዳዊት ማልሁ ዘሩንም ለዘለዓለም አጸናለሁ» ብሎም ምሎለታል መዝ 88:5 ፡፡ ዘሩንም ለዘለዓለም አጸናለሁ ማለቱም ለጊዜው ለልጁ ለሰሎሞን ይሁን እንጂ ኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሱ ዘር ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን ማዳኑን ሲያስረዳ ነው፡፡ ይህም አዳም በፈጸመው በደል በተጸጸተ ጊዜ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ቃል ኪዳን ገብቶለት ስለነበር ጊዜው ሲደርስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ትንቢቱም እንደተፈጸመ ያረጋግጣል፡፡

 እግዚአብሔር አምላክ ለቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን ያደረገው ቃል ኪዳን እጅግ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፋችን ውስጥ ማጠቃለል አይቻለንም፡፡ እናም ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ በመመለስ ጌታችን ምደኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ለእናቱ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰጣታትን ቃል ኪዳን እንመልከት፡፡

 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ በሰጠ ጊዜ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ነፍሱን በገዛ ፍቃዱ ከስጋው ከመለየቱ በፊት ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር /ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ/ ከመስቀሉ ሥር ስለነበር እናቱ ድንግል ማርያምን ያጽናናት ዘንድ «ነዋ ወልድኪ እነሆ ልጅሽ ወነያ እምከ፤ እነኋት እናትህ » በማለት አደራ ሰጥቶታል፡፡ /ዮሐ.19:26/ ዮሐንስም እመቤታችንን ወደ ቤቱ ወስዶ ካስቀመጣት በኋላ የእናትነት አንጀቷ አልችልላት ስላለ በየቀኑ እየሔደች በልጇ መቃብር በጎልጎታ ላይ እንባዋን እያፈሰሰች ትጸልይ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እንደተለመደው እያነባች ስትጸልይ ልጇ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክትን አስከትሎ ወደ እርሷ ወረደ፡፡

 «ስምሽን የጠራ፣ ቤተክርስቲያንሽን የሠራ፣ በስምሽ የተራበ ያበላ፣ የተጠማውን ያጠጣ፣ የታረዘውን ያለበሰ፣ ያዘነውን ያረጋጋ፣ ወይም ውዳሴሽን የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ሴት ልጁንም ሆነ ወንድ ልጁን በስምሽ የሰየመውን ሁሉ እምርልሻለሁ» (ዘሰኔ ጎልጎታ) ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ ይህም የገባላት ቃል ኪዳን የጸና ነው፡፡ ጌታችን ምደኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ የተናገረውን የማያስቀር እውነተኛ አምላክ እንደሆነ በቅዱስ መጸሕፍ « አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ ለሚወዱህና ትዕዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንና ምህረትን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምለክ ሆይ...» ተብሎ ተጽፏል፡፡ እርሷም ልመናዋና ጸሎቷ ስለሰዎች መዳንና መመለስ ስለነበር አመስግና ቃል ኪዳኗን ተቀብላለች፡፡

 ይህንንም ቃል ኪዳን የተቀበለችው ከክርስቶስ እርገት በኋላ የካቲት 16 ቀን ስለሆነ፤ ቤተክርስቲያን ባለበት ቦታ ሁሉ በተላቅ ድምቀት ሲከበር ይኖራል፡፡ ይህም ዕለት ከእመቤታችን ታላላቅ በዓላት አንዱ በመሆኑ ምእመናን ሁሉ በደስታና በተስፋ መታሰቢያዋንም በማድረግ ከላይ የተዘረዘሩትን ክርስቲያናዊ ተግባራት በመፈጸም ሊያከብሩት ይገባል፡፡

 ለእርሷ የተሰጠው ቃል ኪዳን ለመላው ምእመናን ስለሆነ በእርሷ አማላጅነት ያገኘነውን ተስፋ ለመቀበል እኛ ደግሞ ለተጎዱትና ተስፋ ለሌላቸው ወገኖቻችን እንዲሁ አዛኞችና ሩኅሩሆች መሆን ይጠበቅብናል፡፡

  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ተወልዶ ዓለምን በማዳኑ መድኃኔዓለም ተብሏል፡፡ እርሷም የዓለም ድኃኒት መገኛ በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም ተሰኝታለች፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ልናመሰግናት፣ የጸጋ ስግደት ልንሰግድላት፣ ልናከብራትና ልናገናት ይገባናል፡፡ ዛሬ በአፀደ ሥጋ ያለነው ብቻ ሳንሆን በእርሷ ተማጥነው በአማላጅነቷ ድነው በአፀደ ነፍስ ያሉት ነፍሳትም አንቺን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር በሰማይ ምስጋና ይድረሰው፤ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆን በአንቺ ምክንያት የዘለዓለም ሕይወትን አገኝተናል እያሉ ሲያመሰግኑዋት ይኖራሉ፡፡

 ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ቃል ኪዳን ጠብቀውና አክብረው ያለፉ ቅዱሳን አባቶቻችን የዘለዓለም ክብርን እንዳገኙ ሁሉ እኛም ቃሉን ብንጠብቅ ይጠብቀናል፡፡ ብናከብረው ያከብረናል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርንም ሆነ የድንግል ማርያምን ስም በመጥራትና በመሐላ የተዋዋልነውን ቃል ኪዳን የምናፈርስ፣በሐሰት የምንናገር በጥቅም ተደልለን ሌላውን የምንጎዳ ከሆነ የተሰጠንን ቃል ኪዳን ዘንግተናል፡፡

 «የማይረባውን ቃል ይናገራሉ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፡፡ ስለዚህ በእርሻ ትልም ላይ መርዛም ሥር እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል» ሲል ነቢዩ ሆሴዕ እንደተናገረው በምሕረት ፋንታ መቅሰፍትን በሥርየት ፋንታ መርገምን የምናመጣ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ሆሴዕ 10:4

 በዚህ ዓለም እርስ በእርሳችን የምናደርጋቸው ውሎችና ቃል ኪዳኖች ፈርሰው ቢገኙ ውል አፍራሽ ወገን በሕግ ፊት ቀርቦ በመረጃ ሲረጋገጥበት ቅጣቱን ተቀብሎ ውላቸው በሕግ የጸና እንደሚሆን ከእግዚአብሔርም የተቀበልነውን ቃል ኪዳን አፍርሰን ከተገኘን የሠራናቸው ክፉ ሥራዎች መረጃ /ምስክር/ በመሆን ያስፈርዱብናል፡፡ በወንጌል «ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም » ማቴ 24:35 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡

 ስለዚህ የቤተ ከርስቲያን ልጆች የሆንን ምእመናን በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ለእናቱ ለድንግል ማርያም በሰጣት ቃል ኪዳን መሠረት በመጠቀም በረከት ለማግኘት እንሽቀዳደም፡፡ ቃሉን ጠብቀን በሕጉ ጸንተን በመኖር በክርስቶስ ይቅር ባይነት በእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንድንወርስ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አምላከ ሰማያት ወምድር


Written By: host
Date Posted: 8/22/2009
Number of Views: 12932

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement