View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

“ወገብረ ሰላመ በዲበ መስቀሉ”

ወገብረ ሰላመ በዲበ መስቀሉ
በመስቀሉ ሰላምን አደረገ
 በቀሲስ ስንታየሁ ደምሴ

     መስቀል የሚለው ቃል የተገኘው “ሰቀለ” ከሚለው የግእዝ ቋንቋ ግሥ ነው፡፡ትርጓሜውም “የተመሳቀለ” ወይም “መስቀል” ማለት ነው፡፡

መስቀል ለክርስቲያኖች የሕይወትና የድኅነት ምልክት የሆነው መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
 
 በኦሪት መስቀል የመርገምና የመቀጫ መሣሪያ ሆኖ ይቆጠር ነበር፡፡ ”ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ እንዲሞትም ቢፈረድበት በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር” ዘዳ 21:22-23
 የጥንት ሮማውያን ወንጀለኞችን በመስቀል ተሰቅለው እንዲሞቱ ማድረግ ልማዳቸው ነበር፡፡ክርስቶስ ኢየሱስ ለድኅነተ ዓለም ከመሰቀሉ በፊት የእርግማን ምልክት የነበረው የመስቀል ታሪክ ጌታችን ከተሰቀለበት በኃላ ግን ታሪኩ ተቀይሯል፡፡PDF

ለምን ለመስቀል ክብር እንሰጣለን ?
 
  1. ሞት የተሸረበት ስለሆነ፡-
 በአባታችን አዳም ምክንያት ለ፶፭፻ ዘመን በአዳምና በልጅ ልጆቹ ላይ ሰልጥኖ የነበረው ሞትና ዲያብሎስ የተሻሩት በክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዝ የተጻፈውን የእዳ ጽህፈት ደመሰሰው፡፡ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል” ቆላ 2.14
 ስለዚህም ከአዳም ጀምሮ ለ፶፭፻ ዘመን የነበረው የሰይጣን ድል ማድረግ በክርስቶስ መስቀል ከንቱ በመሆኑ ሰይጣን መስቀል ባየ ቁጥር ኃይሉን እንደሚያጣና እንደሚዋርድ ጌታችን በመስቀሉ ማዳን ያመኑትን ሰዎች ሁሉ ጥንተ ጠላታቸው ሞታቸው በክርስቶስ መስቀል ሞት መዋረዱን አይተው ተገቢውን ክብር ይሰጡታል፡፡
 
  1. ሰላም ስለገኘንበት ፡-
ኣባታችን አዳም በድሎ የሰው ልጅ ክብሩን ሰላሙን አጥቶ ነበር፡፡ጌታችን ከተሰቀለ በኋላ ግን ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ ተመልሷል ፡፡ስለዚህም ሐዋርያው “በመስቀሉ ባፈሰሰው ደሙም ሰላም አደረገ” ቆላ1.20 “ጥል ጠፋ ሰላምን ለሰው ልጅ አጎናጸፈ፡፡ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ አስታረቀ” ኤፌ 2፡16 መስቀል ሠላማችን የተመለሰበት ስለሆነ እናከብረዋለን እንሳለመዋለን፡፡
 
 
 
  1. መንፈሳዊ ኃይል ስላገኘንበት፡-
የክርስቶስ ክቡር መስቀል ጠላታችን ዲያብሎስን የምንቀጠቅጥበት ኃጢአት ዓለምን የምናሸንፍበት ኃይል ያገኘንበት ነው፡ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው”፡፡1ኛ ቆሮ 1፡18 ለዚህም ነው በዘወትር ጸሎታችን “መስቀል ኃይላችን ነው ፡፡መስቀል ቤዛችን ነው፡፡ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው”  ብለን የምናመሰግነው፡
 
  1. መመኪያችን ስለሆነ ፡-
መስቀል ጠላት ድል የተነሳበት እኛም የቀደመ ክብራችንን ያገኘንበት በመሆኑ መስቀል ትምክህታችን ነው እንላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ዓለም ለኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ“ ገላ 6.14 እንዲል:: እኛም ክርስቲያኖች ይህን በመረዳትና በመገንዘብ እንዲህ እንላለን “ጸጋ ነሣእነ ወሕይወተ ረከብነ በኃይለ መስቀሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ኪያከ እግዚኦ ነአኩት ነሢአነ ጸጋ ዘእመንፈስ ቅዱስ” ትርጉሙም “ጸጋን ተቀበልን ድኅነትንም በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ኃይል አገኘን አቤቱ ከመንፈስቅዱስ የተገኘ ጸጋን ተቀበልን አንተን እናመሰግናለን፡፡”
 
በመስቀል አምሳያ በማማተብ የምናገኛቸው በረከቶች አሉ ፡-
እነዚህም ፡-
1.      ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ስለኛ መዳን የተቀበለውን ሞት እናስታውሳለን ፡፡ በዚህ ሃይማኖታችን እንመሰክራለን፡፡
2.     የተሰቀለው የክርስቶስ ገንዘቦች መሆናችንን በግልጽ እናውጃለን ስለ ክርስቶስ መስቀል በሰዎች ፊት አናፍርም ፡፡ነገር ግን በእርሱ እንከብራለን በእሱ እንመካለን የአምላካችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መሆናችንን በእርሱ ማመናችንና መገዛታችንን እንገልጻለን፡፡
3.     ስናማትብ ስመ እግዚአብሔርን እንጠራለን ይኸውም “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” እንላለን፡፡ ስለዚህም ባማተብን ቁጥር እስከ ዘለዓለም አንድ አምላክ በሆኑ በቅድስት ሥላሴ ማመናችንን እንገልጻለን ፡፡ ይህም ያለማቋረጥ የአብ፡የወልድ ፡የመንፈስቅዱስ ልጆች መሆናችንን እንድናስብ እድል ይሰጠናል፡፡
4.     ስናማትብ በሥጋ የተደረገልን ካሳ ማመናችንን እንመሰክራለን ይኸውም እጃችንን ከላይ ወደታች ከግራ ወደቀኝ በመውሰድ እናማትባለን:: በዚህም እግዚአብሔር ወልድ ከሰማያት መውረዱንና የሰው ልጆችን ከግራ ወደቀኝ ፡ከጨለማ ወደ ብርሃን ማሻገሩን እናስታውሳለን በዚህም በልባችን የሚሰሙን መንፈሳዊ ስሜቶች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡
5.     ስናማትብ ከጌታችን ጋር ያለንን ወዳጅነት እንገልጻለን ይኸውም “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” ገላ 2.20 ፤ “እርሱንና የትንሳኤውን ኃይል እንዳውቅ እንድንካፈል” ፊል3.10 ያለው የሐዋርያውን ቃል እናስታውሳለን፡፡
6.      በትእምርተ መስቀል ስናማትብ መስቀል የድል ምልክት ነውና የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን ይሞላል፡፡ ጠላትም ከአጠገባችን አርባ ክንድ ያህል ይርቃል:: “እክህደከ ሰይጣን” በማለት ጠላታችንን እንክዳለን የማይወደውንና የተሸነፈበትን መስቀል በማንሳት እናማትባለን፡፡
 
 እንግዲህ የማንኛውም እንቅስቃሴያችን መጀመሪያና መጨረሻ ለጸሎት በቆምን ቁጥር እንዲሁም አስፈሪ ነገሮችን ባየንና በሰማን ቁጥር በመስቀል አምሳያ እናማትባለን በእርሱም ኃይል እናገኛለን ፡፡
 
የመስቀሉ ታሪክና የበዓሉ አከባበር
 
 የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እርሱ ተሰቅሎ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ገቢረ ተአምራት ሲያደርግ ቆይቷል:: ነገር ግን አይሁድ በምቀኝነት የክርስቶስን መስቀል ኃይሉን የሚያስቀሩት መስሎአቸው በጉድጓድ ውስጥ በመጨመር  ቦታው ተራራ እስኪያህል ድረስ አፈርና ቆሻሻ ሞልተውበት ቀበሩት፡፡
 ከብዙ ዘመናት በኃላ ንግሥት ዕሌኒ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ጠፍቶ በመቅረቱ ታዝን ነበርና መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ አፈላልጋ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን አስወጣታለች:: ይሕንንም ለማዘከር ደመራ በመደመር እንዲሁም በዚያ ዘመን የምሥራች ዜና ከቦታ ወደ ቦታ ሊሸጋገር የሚችለው እሳት በማንደድ ስለነበር ችቦ በማብራት የመስቀልን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀንና መስከረም ፲፯ ቀን በታላቅ ሥነ-ሥርዓት እጅግ በደመቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታከብረዋለች፡፡ምንም እንኳን መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉ የተገኘበት ቀን የደስታ በዓል የሚደረግበት ቢሆንም ሁልጊዜ መጋቢት ፲ ቀን ጾመ ሁዳዴ ስለሆነ በዓሉን በሆታ በደስታ ለማክበር ቁፋሮ በተጀመረበት መስከረም ፲፮ እና ፲፯ በታላቅ ድምቀት ይከበራል ፡፡
 
 መስቀሉ ለአራቱ አህጉራት ተከፋፍሎ ሣለ የአፍሪካ ድርሻ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል በእግዚአብሔር ጥበብ፣ በደጋጎች ኢትዮጵያውያን ነገሥታት አጼ ዳዊት እና ልጃቸው አጼ ዘርዓያዕቆብ ጥረት መስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል በመቀጠልም መስከረም ፳፩ ቀን ግማደ መስቀሉ በግሸን ተራራ ላይ በክብር አረፈ፡፡ በየዓመቱ በዓሉ በድምቀት በግሸን ማርያም ይከበራል፡፡
 
የመስቀሉ ረድኤትና በረከት ይደርብን።
 
በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
የሰሜን አሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሥልጠና ክፍል
 
መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፪ ዓም

Written By: host
Date Posted: 9/24/2009
Number of Views: 9211

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement