View in English alphabet 
 | Wednesday, April 24, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

እረኞች ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ

 

ሕዝ 347
                      መምህር ዕርገተ ቃል ይልማ

ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ሕዝቅኤል ከጌታ ልደት 597 ዓመት በፊት የተነሳ ነቢይ ነው፡፡ይህ ታላቅ ነቢይ የእሥራኤል ልጆች ወደ ባቢሎን ተማርከው በስደት በሄዱ ጊዜ

ከምርኮኞች አንዱ በመሆን እስራኤላውያን የደረሰባቸውን መከራና ስቃይ በዐይኑ ለማየት ጩኸታቸውንም በጆሮው ለመስማት ችሏል፡፡ ኢየሩሳሌም ለከፋ ውድቀት ከመዳረጓ በፊት ሕዝቡ ራሳቸውን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር እነዲያቀርቡ መክሯል፡፡ይሁን እንጂ ከበደላቸውና ከኃጢአታቸው ተመልሰው በጽድቅ መንገድ ሊጓዙ ስላልቻሉ የተለያየ መከራ ደረሶባቸዋል፡፡

 
          በነበሩበት የስደት አገር ውስጥ ይደርስባቸው ከነበረው ልዩ ልዩ መከራ የተነሳ ተስፋ ቆርጠው እንደ ተበተኑ በጎች ተበትነን እንቀራለን ባሉበት ሰዓት እራሱ እግዚአብሔር እረኛ ሆኖ ከተበተኑበት ሥፍራ እንደሚሰበስባቸው የተሰበሩትንም እንደሚጠግን የተለያዩትንም መንታዎች አንድ እንደሚያደርግ ታላቅ የሆነ የተስፋ ቃል ለሕዝቡ ሰጠ፡፡
 
          እግዚአብሔር ቀደም ባለው ጊዜ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ከህናትን ነቢያትንበሥጋዊው አስተዳደር ነገሥታትንና መሳፍንትን እረኛ ሆነው በኃላፊነት ሕዝቡን በቅንነት በፍቅርና በታማኝነት እንዲመሩ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር፡፡ይሁን እንጂ እነዚህ እረኞች ከበጎቹ የሚገኘውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ እንጂ ለበጎቹ ደንታ ቢስ ስለነበሩ «እራሳቸውን ለሚያሰማሩ እረኞች ወዮላቸው እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውም ጮማውን ትበላላችሁ ጠጉሩንም ትለብሳላችሁ የወፈሩትን ታርዳላችሁ በጎቹን ግን አታሰማሩም የደከመውን አላጸናችሁም የታመመውን አላከማችሁም የተሰበረውን አልጠገናችሁም የባዘነውን አልመለሳችሁም በኃይልና በጭቆናም ገዛችኋቸው» ሕዝ 34፡4፡፡በማለት ስለበጎቹ እስራኤላውያን ሲል እረኞች የነበሩትን ከህናትንና መሪዎቻቸውን ወቅሷል፡፡
 
          እረኞች ስለበጎች ደንታ ቢስ ሆነው በመገኘታቸውና አራዊት ለተባሉ ጨካኝ ገዢዎች ተላልፈው በመሰጠታቸው የበጎቹ ባለቤት «እኔው እራሴ እረኛ እሆናቸዋለሁ» ባለው መሠረት «መቶ በጎች ያሉት ሰው አንዱ በግ ብትጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የጠፋችውን አንዷን በግ ለመፈለግ አቀበቱን የማይወጣ ቁልቁለቱን የማይወርድ ማነው ባገኘውም ጊዜ ደስ ይለዋል» ብሎ ጌታችን እንደተናገረው ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክትን ትቶ የጠፋውን የሰው ልጅ ለመፈለግ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ተለያይቶ የነበረውን የሰው ልጅ አንድ አደረገ ለበጎች ድምጹን አሰማ ከበጎች ፊት በመሄድ አርአያ ሆነ በጎቹ እንዲያውቁት አደረገ፣  በየስማቸው ጠራቸው፣  ስለበጎች ሲል ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ይህ የእውነተኛ እረኛ ተግባር መሆኑንም በተግባር አሳየ የምንደኝነትና የቅጥረኝነት መንፈስ ያለው እረኛ ከሆነ ግን ከበጎቹ የሚገኘውን ጥቅም እንጂ በጎቹን አይፈልግም፣ በአውሬ ሲበሉ አይጨንቀውም፣  ቢበተኑ አይገደውም፣  ከበረቱ እንደወጡ ቢቀሩ አያሳስበውም፡፡ የበጎቹ ባለቤት ግን ስለበጎቹ ያስባል በደመና ይሁን በጨለማ ከተበተኑበት ሥፍራ ይሰበስባል፣  ነጣቂ አውሬ ተኩላ ቢመጣ ስለበጎቹ ሲል ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡
 
ዳዊት በልጅነቱ የአባቱ የእሴይን በጎች በሚጠብቅበት ሰዓት በጎቹን ለመብላት አንበሳና ድብ ይመጡ ነበር አስፈሪ የሆኑ አራዊትም ቢሆኑ ከኋላ ይከተልና በጉን ከአፋቸው ሳይቀር ያስጥል እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል 1ሳሙ፡17፡34፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ የዳዊት ተሞክሮ ሕዝበ እስራኤልን መሪ በነበረበት ወቅት ከእግዚአብሕር ታዝዞ በመጣ መልአክ ብዛት ያላቸው እስራኤላውያን በመቅሰፍቱ ሲመቱ «የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል;» 1ኛ ዜና 21፡17 በማለት ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
          ስለበጎቹ ሲል መከራ መስቀሉን የተሸከመው የተንገላታውና ብዛት ያላቸውን መከራ የተቀበለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ በጎቹ «የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፣  በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም» ማቴ 15፡12 በማለት ይናገራል፡፡ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ታላቅ ተልዕኮ ፈጽሞ ወደ አባቱ ሊሄድ ሲልም በጎቹን እንዲሁ አልተዋቸውም እንደእርሱ ሆነው የእርሱን ሥራ እንዲሠሩ ከመረጣቸው መከከል አንዱ የሆነውን ቅዱስ ጴጥሮስን ከአንዴም ሦስት ጊዜ «ትወደኛለህ;» የሚል ጥያቄ አቅርቦለት «እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ» ብሎ ፍቅሩን ስለገለጠለት ግልገሎቼን አሰማራ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን አሰማራ በማለት ህጻናትንና አረጋውያንን እንዲያሰማራ ወጣቶችን እንዲጠብቅ ታላቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ዮሐ 21፡17
 
          ይህ ቃል ለጊዜው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረ ቢሆንም እስከ ዓለም ፍጸሜ የሚነሱ የእግዚአብሔርና የሕዝብ አገልጋይ የሆኑ ከህናትን ይመለከታል፡፡ እነዚህ አገልጋዮች «እረኞች ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ» እንደተባለው ዛሬ ኣባግዐ እግዚአብሔር የሆኑ ምዕመናን ያሉበትን ሕይወት በመቃኘት አብዛኛውን እረኞች ምን ያህል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ አንድ እረኛ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጣ የሚባለው በጎቹን ከበረቱ ይዞ ጠዋት አውጥቶ ማታ ስለመለሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ስለበጎቹ ሕይወት የሚያስብና የሚጨነቅ መሆን አለበት፡፡«እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣  በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል» መዝ 22 የሚለው ቃል ጥበቃን ብቻ ሳይሆን መግቦትንም ጭምር ያሳየናል፡፡ከህናት በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ለመንጋው መጋቢዎች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ለነዚህ በጎች በየጊዜው የሚያስፈላጋቸውን ለሕይወታቸው ተስማሚ የሆነውን ምግበ ነፍስ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲሰሙ፣  ወደ ሥጋው ደሙ እንዲቀርቡ ማድረግ አለባቸው፡፡« እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሠጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝ ልባም ባሪያ ማን ነው;» ብሎ ማቴ፡24፡45 መጠየቁ ለዚህ አገልግሎት የሚሰለፈው ከህን መንጋዎቹን በተገቢው ቦታ ማኖር በተገቢው ሰዓት ተገቢውን ማዕድ ለጌታው ቤተሰቦች ለተባሉ ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ለመመገብ ተጠሪ ሆኖ ለመጠበቅና መጋቢ ለመሆን አስተዋይና ታማኝ መሆን አለበት፡፡
 
          ዛሬ ዛሬ በአገር ቤትና ይበልጥም ደግሞ በውጭው ዓለም ለመንጋው ደንታ ቢስ የሆኑ የምንደኝነትና የቅጥረኝነት መንፈስ በብዛት የሚታይባቸው፣  የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጡ፣  ለበጎቹ ምእመናን ሕይወት ሳይሆን ከምእመናን ጊዜያዊ የሆነ ጥቅምን መሻት ዓላማ አርድርገው የተነሱ፣  ስለ በጎቹ ከበረት ቤተ ክርስቲያን ወጥተው በመናፍቃን መወሰድ፣  ስለመንጎች መለያየትና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው መድረቅና መጎስቆል ምንም ግድ የማይላቸው፣  ቢሰበሩ ለመጠገን ቢደክሙ ለማበረታታት ከቤተ እግዚአብሔር ቢርቁ ለመፈለግ ከበጎቹ ፊት ቀድሞ ለመሄድ የሚችሉ ካህናት ለማግኘት መቸገራችን «እረኞች ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ» የሚለውን ቃል እንድናስተጋባ ያስገድደናል፡፡
 
          እረኞች እረኝነታቸውን በሚገባ መወጣት ስላቃታቸው ጅራት ራስ ሆኖ እግር እራስን በማከኩ በውጩ ዓለም ያሉ አብዛኞቹ አብያተክርስቲያናት የተመሠረቱበትን የቤተክርስቲያን ዓላማ የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ ላያቸው ሲታይ በመንፈሳዊ ካባ ተሸፍነው መንፈሳዊ ቢመስሉም በውስጣቸው ግን ከእግዚአብሔር መንግሥት ይልቅ የተለያዩ ፖለቲካዊ የውይይት እንቅስቃሴ የሚታይባቸው፣  ከአንድነት ይልቅ መለያየት ጎልቶ የሚንጸባረቅባቸው፣  ከክርስቲያናዊ ሕይወት ይልቅ ማኅበራዊ ሕይወት የበዛባቸው፣  እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል ለመናገር በፍርሃት የተሞሉ፣  በረቱን ቀንዳም የሆኑ በጎች የሚያዙበት የሚናዝዙበት፣  እረኛው ባዕድ የሆነበት፣  እረኛው የእነርሱን ቃል እንዲሰማ መመሪያ የሚሰጥባቸውና የማሰማሪያውን ሥፍራ ቤተ ክርስቲያንን የሚያደፈርሱ ቀንዳቸውን አሳድገው የሚዋጉትን አውራ በጎች ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ላይ የዐመጽ ተግባር የሚፈጽሙትን፣  በትምህርቷና በቀኖናዋ ላይ ትችት የሚሰነዝሩትን፣  በቸልታና በምን አለብኝነት የሚያዩ እረኞች ካህናት በዝምታቸው «ወየውላችሁ» ከሚለው ወቀሳ ለመዳን አይችሉም፡፡
 
          ሥርዓት ሲፈርስ ሕገ እግዚአብሔር ሲጣስ ዝም ማለት «ዕውቀትን ጠልተሀልና እኔም ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሀለሁ»፡፡ ሆሴ 4፡6 የሚለው ቃል በእንደነዚህ ዓይነት እረኞች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
 
          እረኞች ከህናት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከበጎቹ ባለቤት የተሰጣቸውን ቦታ ይዘው   በታማኝነት ለመንጋው አርአያ በመሆን የታመመውን በማከም የደከመውን በማበርታት የጠፋውን በመፈለግ ለምእመናን መልከም አርአያነትን ቢያሳዩ ክብራቸው ታላቅ ይሆናልና፡፡ «በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጎብኙት ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ የእረኞችም አለቃ በሚገኝበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ፡፡ 1ኛ ጴጥ 5፡2-3 እንዲል፡፡
 
መልከም እረኛ ሆኖ መገኘት ከሁሉም አባቶች ይጠበቃል ለዚህ ደግሞ ኃይሉን ጥበቡንና ማስተዋሉን እግዚአብሔር እንዲሰጥ ዘወትር መጸለይ ያስፈልጋል፡፡
 
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!                                     
 
 
በኢ///ቤተክርስቲያንበሰ//ቤቶችማደራጃመምሪያ
 
በማኀበረቅዱሳንየሰሜንአሜሪካማዕከልየትምህርትናሥልጠናክፍል
 
ታህሳስ 2000 .

Written By: host
Date Posted: 12/28/2009
Number of Views: 8573

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement