View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በማኀበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል በሎስ አንጀለስ ያቀረበው ዐውደ ርእይ ሪፖርታዥ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኀበረ ቅዱሳን ጥር 22 እና 23 2002 ዓ.ም በሎስ አንጀለስ ያቀረበው ዐውደ ርእይ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች አስታወቁ:: ቅዳሜ ጥር 22 ቀን 2002 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ከሎስ አንጀለስ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ ከላስ ቬጋስ ቅዱስ ሚካኤል ወቅድስት ኪዳነ ምሕረት እንዲሁም ከፖርትላንድ በተጋበዙ ቆሞሳትና ቀሳውስት በጸሎት ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በቆየው በዚሁ ዐውደ ርእይ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን መመልከት እንደቻሉ ታውቋል::

በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የማኀበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ፀሐፊ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ እንደገለጹት ማኀበረ ቅዱሳን የመጀመሪያውን ዐውደ ርእይ በአዲስ አበባ ማሳየት ከጀመረበት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባና በየክፍላተ ሀገሩ በተደጋጋሚ በማሳየት ብዙ ሰዎችን በተለየ አቀራረብ ማስተማሩንና ይህንኑ የማስተማር ዘዴ በመጠቀም በአውሮፓ እና በአሜሪካ ልዩ ልዩ ስቴቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እና የሌላ ሀገር ተወላጆችን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና መንፈሳዊ ቅርስ በማስተማር ላይ የሚገኝ መሆኑን አብራርተዋል:: አክለውም “ኤግዚቢሽን” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል “ዐውደ ርእይ” የሚል አቻ የግእዝ ቃል ከሊቃውንት ጋር በመመካከር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ማኀበሩ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች (ሚዲያዎች) ይህንን ቃል በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል::

በአሥራ አንድ ክፍሎች የቀረበው ይህ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ዜማ፤ ቅዱሳት መካናት ፤ ቅዱሳት ሥዕላት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ፤ ንዋያተ ቅድሳት፤ የዘመን አቆጣጠር፤ ቤተ ክርስቲያን በዳያስጶራ፤ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች፤ ቤተ ክርስቲያን ነገ እና ማኀበረ ቅዱሳን የሚሉ አርእስት የነበሩት ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል በተመደቡ ገላጮች አማካይነት ስንዱ እመቤት ተብላ ስለምትጠራው ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች፤ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ጠለቅ ያለ ገለጻ በመስጠት የዐውደ ርእዩ ታዳሚዎች ጥሩ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል::

በዐውደ ርእዩ ላይ የተገኙት አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ እጅግ  መርካታቸውንና ስለ ቤተ ክርስቲያን የማያውቁትን ብዙ ነገር እንደተማሩበት ገልጸው፤ እንዲህ ዓይነቱ ዐውደ ርእይ በየስድስት ወሩ ቢደረግ ብዙዎችን ለማስተማር እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:: የሌሎች ሀገራት ተወላጅ የሆኑት ጎብኚዎችም በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ትምህርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል::

አዘጋጆቹ ዐውደ ርእዩ ካለቀ በኋላ እንደገለጹት ሁሉም ነገር በተሳካ መልኩ በመጠናቀቁ እግዚአብሔርን አመስግነው፤ በተለይም የሌሎች ሀገር ዜጎች በዐውደ ርእዩ ተማርከው ጓደኞቻቸውን እየጠሩ በማምጣት ሁለት ሶስት ጊዜ እየደጋገሙ ሲመለከቱ በማየታቸው መደነቃቸውን ገልጸዋል:: 

በዚህ ታላቅ የዐውደ ርእይ ዝግጅት ላይ ከማኀበረ ቅዱሳን የሎስ አንጀለስ ቀጣና ማዕከል ጎን ለጎን የአጥቢያው የቅድስት ሥላሴ ወገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን  ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፤ ከላስ ቬጋስ፣ ከሳንሆዜ እና ከዋሽንግተን ዲሲ የመጡ የማኀበሩ አባላትም ተሳትፎ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል::
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው ማኀበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ታሪክ እንዲሁም ቅርስ በዐውደ ርእይ (በኤግዚቢሽን) መልክ በማቅረብ ማስተማርን በሰፊው እንደሚጠቀምበት ይታወቃል::  


Written By: host
Date Posted: 2/7/2010
Number of Views: 5738

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement