View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም - ጾም

(በመሐር ቸሬ አበበ)
በፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ አንቀጽ 15 እንደተገለጸው ቅዱሳን አባቶቻችን ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም የሚያደርግ የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ የለመነውም ልመና መልስ እንዲኖረው እጅግም የሰይጣንን ፍላጻ ወይም ጦር ለመስበር የሚያስችል ኃይል ያለው መሣሪያ ጾም ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር «በእግዚአብሔር አምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እናድርግ፣ በእርሱም ዘንድ ጾምን አወጅኩኝ። ስለዚህ ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን እርሱም ተለመነን፡፡» እንዳለ የሰው ልጅ የነፍሱን ነገር በማሰብ በጾም እግዚአብሔርን ሊለምን ሊማጸን የሚፈልገውን ሁሉ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ከነቢዩ ዕዝራ የምንማረው በጾም ለሕዝብና ለራስ ለምኖ ዋጋ ማግኘትን ነው፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ «ይህ ነገር ያለጾምና ያለጸሎት አይወጣም» /ማቴ.17.2/ ሲል የሚያስረዳን ትልቅ ምስጢር አለ፡፡ እርስ በእርሳችን የሚያጣላን የሚያቀያይመን ይባስም ብሎ ከአምላካችን ጋር እንድንለይ የሚያደረገውን በዐይናችን የማናየውን የዘወትር ጠላታችን ሰይጣንን ድል መንሳት የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ለዚህም ነቢዩ «ጾምን ለዩ ምህላንም አውጁ» እንዳለ /ኢዩ.2.11/ የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ለማስገዛት ጾምን በራሱ ላይ ሊያውጅ ወይም ሊያነግሥ ይገባል፡፡
 
በብሉይ ኪዳን ዘመን እጅግ ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን በጾም የጠየቁትን ሁሉ አግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ እስራኤልን በሚመራበት ወቅት አሕዛብ እንዳይሰለጥኑበት፣ ወገኖቹም እስራኤል የአሕዛብን አምልኮት ተከትለው ከአምላካቸውከእግዚአብሔር ዘንድ እንዳይለዩ፣ እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ፣ በተለይም ዘወትር ለመንፈሳዊ ጉዟቸው የሚያሰፈልጋቸውን ሕጉ የተጻፈበትን ቅዱስ ታቦት የተቀበለው 40 ቀንና 40 ሌሊት በሲና ተራራ በመጾም በመጸለይ ነበር፡፡
 
ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስም ይህችን ረብ ጥቅም የሌላትን ጊዜያዊና ኃላፊ ዓለም ትቶ የሚበልጠውን መንፈሳዊውን ዓለም ለማግኘት ወደ ሰማይ ያረገው በጾም ኃይል ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል መንፈሳዊ ኃይል ተሰጥቶት ታላቋን የባቢሎንን ከተማ በማናወጥ በሥጋ ሐሳብና ኃይል የማይቻለውን ድንቅ ነገር ማድረግ የቻለው የአናብስትን አፍ የዘጋው በጾም በጸሎት ነው፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም ሳይቀሩ ከነበልባል እሳት የዳኑት በጾም ኃይል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
 
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የማስተማር ተግባሩን ሳይጀምር ለሥራው ሁሉ ተቀዳሚ ያደረገው ጾምን ነው፡፡ በጾሙም ወቅት ዲያብሎስ ስለተፈታተነው በቀረበለት ፈተና ሁሉ ድል ነሥቶታል፡፡ ከዲያብሎስ የቀረቡለትም ፈተናዎች ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ነበሩ፡፡ ክርስቶስም በስስት የመጣውን በትዕግሥት፣ በትዕቢት የመጣውን በትሕትና እንዲሁም በፍቅረ ንዋይ የመጣውን በጸሊአ ንዋይ ዲያብሎስን ድል ነስቶታል፡፡ ማቴ.1.1ጠ11፡፡
 
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመው ዐቢይ ጾም የምንማረውም የኃጢአት ሁሉ ሥር የሆነውን ዲያብሎስን ድል መንሣት ሲሆን ይኸውም በጾም፣ በጸሎት፣ በትዕግሥት፣ በትሕትና፣ በሃይማኖት፣ በጸሊአ ንዋይ ወይም ገንዘብን በመጥላት ወዘተ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለሆነም በዚህ ታላቅ የጾም ወቅት ሁላችንም ትችት፣ ሐሜት፣ ቅናት፣ ተንኮል ወዘተ ፍላጎቱ የሆነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ለነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ ፈቃድ በማስገዛት የሥጋ ፈቃዳት የተባሉትንም በማሸነፍ የፈቲው ጾርንም በማድከም ከልብና በሃይማኖት ልንጾም ይገባል፡፡ ብዙ ሰዎች ከጊዜያዊ እህል ውኃ ይጾማሉ ወይም ያስቀድሳሉ ይጸልያሉ ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን በመጾማቸው በመጸለያቸው በሃይማኖታቸው በትዕግሥታቸው በትሕትናቸው ሲጸኑ ዲያብሎስንም ድል ሲያደርጉ ብዙም አይታዩም፡፡ይኸው በሽታ በብዙዎቻችን ዘንድ አንዳንዴም ቢሆን ይከሰታል፡፡ ግን ለምን ይሆን? ጾማችን የግብዞች ጾም ሆኖ ይሆን? ለታይታና በልምድ እየጾምን ይሆን?
 
ይህ መዋዕለ ጾም ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ በጠባብ በር ወደ ተመሰለው ፈቃደ ነፍስ ለመግባት ሊሽቀዳደሙበት የሚገባ ወቅት ነው፡፡ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ «ብፁዓን ይርኅቡ ወየጸምኡ በእንተ ጽድቅ እስመ እሙንቱ»፤ ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.5.6/፡፡ ስለጽድቅና ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉ ከሚባሉት እየቀነሱ ለጦም አዳሪዎች የሚሰጡ ብፁዓን ይባላሉ፡፡ በመንግሥተ ሰማያት አይራቡምና፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ገንዘብ ሳይሰስቱ ለተራቡ የሚሰጡ፣ በትሕትናቸው ብዙ መንፈሳውያን የትሕትና ሰዎችን የሚያፈሩ በትዕግሥታቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔርእንዲቀርቡ ምክንያት የሚሆኑ ሰዎች ይህን መዋዕለ ጾም አስበውታል የጾም ትርጉሙም ገብቷቸዋል ማለት ያስችላል፡፡ እየጾሙ፣ እየሰበኩ፣ እየዘመሩ፣ እያስተማሩ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ከሌላቸው ክርስቶስን መስለውታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም በራሳችን ላይ ይህን ዐቢይና የጌታ ጾም ስናውጅ ትርጉም ያለው ለንስሐ የሚያበቃ ጾም እንዲሆንልን ፍቅራችን፣ መተሳሰባችን ሊጨምር ይገባዋል፡፡
 
ሁላችንም እንደ ዘኬዎስ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን። የምንወጣበት ዛፍ ግን እጅግ ያስፈራናል፡፡ ሁሉንም በእግዚአብሔር እንድንችለው ትሕትና፣ ፍቅር ሃይማኖት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲሁም አቅማችንን በማወቅም ደረጃ ብዙ ይቀረናል፡፡ ሰው ሁል ጊዜ ታናሽ እንደሆነ ክርስትናውም ዕለት ዕለት ማደግ እንዳለበት ካላመነ እጅግ ከባድ አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡
 
እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ የለም፣ የማይኖርበትም ጊዜ የለም ለኃጢአተኛም ይሁን ለጻድቅ ሰው እግዚአብሔር ቅርብ ነው፡፡ በድለን በደላችንን በመንገር የሚደመስስልን ቸር አምላክ፤ ኃጢአት ሠርተን በኃጢአታችን የሚያጠፋን ይቅር ባይ ታጋሽ ጌታ ስለሆነ እግዚአብሔርን ከምንምና ከማንም በላይ በፍጹም ፍቅር መቅረብና መማጸን ይገባናል፡፡
 
በዚህ በእርሱ ስም በከበረና በሚጠራው የጾም ወራትም በጸሎትና በምጽዋት በትዕግሥትም ይቅር በመባባል ወደ እግዚአብሔርመቅረብ አለብን፡፡ ጾም ከደዌ ሥጋና ከደዌ ነፍስ ለመፈወስ የምንችልበት መንፈሳዊ ኀይል ስላለው የሚሰጠውን ጥቅም ማወቅና መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይህም ከሆነ በጾም ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም ያስችላል ማለት ነው፡፡ ጾመን የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን በዚህ ለሥጋችንም ፈቃድና ሐሳብ ሳይሆን ለነፍሳችን ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድናስብ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Written By: host
Date Posted: 2/8/2010
Number of Views: 6005

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement