View in English alphabet 
 | Tuesday, April 23, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዐረፉ

የከምባታ፣ ሐድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዐረፉ፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በደረሰባቸው ሕመም ሳቢያ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 13 ቀን 2002 ዓ.ም ዐርፈዋል፡፡

ሥርዓተ ቀብራቸው ሰኔ 15 ቀን 2002 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት አባቶችና ምእመናን በተገኙበት በምሁር ኢየሱስ ገዳም ተፈጽሟል፡፡ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ያስተዳድሩት በነበረው ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኘው እዣና ወለኔ ወረዳ /ምሁር ኢየሱስ ገዳም አካባቢ/ ከአባታቸው ከመምሬ ክንፈ ሚካኤልና ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለ ማርያም በ1951 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የምሁር ኢየሱስ ገዳም ቄሰ ገበዝ የነበሩት አባታችው በዚያው ፊደልና የቁጥር ትምህርት አስተማሯቸው፡፡

በመቀጠል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሔድ ቅኔ፣ መዝገበ ቅዳሴና ሌሎች ትምህርቶችን ተምረዋል፡፡ ከተማሩባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በዚሁ ማሠልጠኛ በመምህርነትና በአስተዳዳሪነትም አገልግለዋል፡፡

የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልአይ መንኩሰው ቅስና የተሾሙ ሲሆን፤ በ1987 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የኤጲስ ቆጶስነት መዓርግ ከተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡

ኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ዐረፍተ ሞት እስከገታቸው ድረስ የከምባታ፣ ሐድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከትንም በተጨማሪነት በሊቀ ጳጳስነት አገልግለው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

እንደዚሁም ከ1997 ዓ.ም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡


Written By: host
Date Posted: 6/22/2010
Number of Views: 11395

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement