View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የቅዱሳን መሰወር (ኅብአተ ቅዱሳን)

የሰው ልጆች ወደ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ አገልግሎት ባዘነበሉ መጠን ቸርነት የባሕርዩ የሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የተለያየ መንፈሳዊ ብቃትን ይሰጣቸዋል፤ ሰማያዊ ምሥጢርን ይገልጥላቸዋል። ቅዱሳን በሥጋቸው በምድር ለጸሎት ቆመው ነፍሳቸው በተመስጦ ገነት መንግሥተ ሰማያት ተነጥቃ ሄዳ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ታመሰግናለች። እንዲሁም በአካል እንደ ነቢያቱ ሄኖክና ኤልያስ በመወሰድ እስከ ጌታችን ዳግም ምጽአት መዳረሻ ቀን በመሰወር እንደሚኖሩ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል።

«መሰወር» የሚለው ቃል የግእዝ ግሱ «ኀብአ»፦ «ሰወረ፥ መሰወር»፤ «ተኀብአ»፦ «ተደበቀ፥ ተሰወረ፥ ራቀ፥ ረቀቀ» ማለት ሲሆን በጥቅሉ ለዓይን እንዳይታይ እንዳይገኝ ሆነ፤ ለምሥጢርም ከሆነ ለአእምሮ ረቀቀ ማለት ነው ።

«መሰወርን» የምንዳስስበት ሃይማኖታዊ ጠገግ ወይም አድማስ በሥጋ ለባሽነት የኖሩትን የሰው ልጆችን በጽድቅና በቅድስና መሰወር የሚያካትት ነው። በዚህም መሠረት ከሰው ልጆች ወገን፦ በቅድስናቸው ብቃት፥ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ እስከ ምጽአት ድረስ በሥጋቸው በብሔረ ሕያዋን እንዲሰወሩ፤ ከሰው ልጆች ዓይን ለጊዜው ለአስፈላጊ ሁኔታ እንዲሰወሩ፤ ከመደበኛ መልካቸው ለጊዜው ሌላ ሰው በመምሰል እንዲሰወሩ፤ መከራ እንዳያገኛቸው የሰወራቸውና ከሞቱ በኋላ ቅዱስ ሥጋቸውን የሰው ልጆች እንዳይቀብሯቸው የተሰወሩት ወዘተ ይገኙባቸዋል።

እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት አንድ ሰው ለመሰወር የተለያዩ የብቃት ደረጃዎች ላይ መድረስ አለበት። ደረጃዎቹም ሊገኙ የሚችሉት ሃይማኖትን ከምግባር ጋር በማጽናት፣ በጾም፣ በጸሎትና በትሩፋት ማጌጥን ይጠይቃል። የብቃት መዓርጋቱም በሦስት ዐበይት መዓርጋትና በዐሥር ንዑሳን ደረጃዎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ዐቢይ መዓርግ ንጽሐ ሥጋ ይባላል። በውስጡም ጽማዌ፣ ልባዌና ጣዕመ ዝማሬን ያጠቃልላል። «ጽማዌ»፦ ከአንደበት ከሚወጣ ኃጢአት መቆጠብና ንግግር አለማብዛት፤ «ልባዌ»፦ ፍጹም መንፈሳዊ እና እውነት የሆነውን ነገር በሚገባ ማስተዋል፤ «ጣዕመ ዝማሬ»፦ የእግዚአብሔርን ምሥጢር በንቃትና በተመስጦ ሆኖ በዜማ ላህይ በማመስገን መትጋት ነው።

ሁለተኛው ዐበይት የብቃት መዓርግ ንጽሐ ነፍስ ነው። ቅዱሳን ወደዚህ መዓርግ የሚደርሱት የመጀመሪያውን ሲያልፉ ነው።

በውስጡም አንብእ፣ ኩነኔ፣ ፍቅርና ሁሰትን ያጠቃልላል። «አንብእ» ከመንፈሳዊ ተመስጦ የተነሳ እንደምንጭ /ሰን ውኃ/ ከቅዱሳን ዓይን እንባ የሚፈስበት ደረጃ ነው። «ኩነኔ» ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በመንፈሳዊ ጥበብ የማስገዛት ደረጃ ነው። «ፍቅር» በቅዱሳኑ ዘንድ የሰው ልጆችን ዘር ሁሉ እኩል የመውደድ ደረጃ ነው። «ሁሰት» በዚህ ደረጃ ቅዱሳኑ በቅርብም በሩቅም ማንኛውንም ክንውን በዓይነ ሥጋ ሳይሆን በዓይነ መንፈስ ማየት ነው። ይህም የቅዱሳን መላእክትን እንቅስቃሴ /ተልእኮ/ እስከማወቅ ያደርሳቸዋል።

ሦሰተኛው ዐቢይ የብቃት መዓርግ ንጽሐ ልቡና ነው ። ይህ የመጨረሻው የፍጹምነት ደረጃ ነው ። በውስጡም ንጻሬ መላእክት፣ ተሰጥሞ ብርሃን፣ ከዊነ እሳት ይገኙበታል። «ንጻሬ መላእክት» በዓይነ ሥጋ ቅዱሳን መላእክትን በያሉበት ዓለማት መመልከት ነው። «ተሰጥሞ ብርሃን» በእግዚአብሔር ልዩ የባሕርዩ ብርሃን መመሰጥ ሲሆን «ከዊነ እሳት» ደግሞ ቅዱሳን ሰዎች በእሳታዊነት ጸጋ ከነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የሚደርሱበት ደረጃ ነው።

ከላይ እንዳየነው በእነዚህ የብቃት መዓርጋት ውስጥ ያሉ ቅዱሳን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከሚሰጧቸው ጸጋዎች አንዱ መሰወር ነው። የመሰወር ጸጋውም የተለያዩ ሁኔታዎች አሉት። እንደሚከተለው እንመለከተዋለን።

፩. በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ለጊዜው መሰወር

ይህ የመሰወር ጸጋ በዓለመ ሥጋ መካከል ሳሉ አስፈላጊ ለሆነ ሁኔታ አብረው ካሉት ሰው ለጊዜውም ቢሆን አለመታየት ነው። ይህን ዓይነት መሰወር በጾም በጸሎት ተወስነው፥ በብሕትውና ያሉ ቅዱሳን ከፈቃደ እግዚአብሔር ውጪ ሊያዩአቸው የሚመጡትን ሰዎችና በክፉ የሚመጡባቸው ሰዎች እንዳያገኟቸው የተሰጣቸው የመሰወር ጸጋ ነው። ይህንንም እውነታ ለቅዱሳኑ ማድረግ እንደሚቻላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። ለዚህም አብነት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። በግእዙ «ወዘንተ ብሂሎ እግዚእ ኢየሱስ ሖረ ወተኃብኦሙ»፤ ትርጉሙም፦ «ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው።» /ዮሐ. ፲፪፥፴፮፤ ሉቃ. ፳፬፥፴፩/። ከላይ ያለውን ንባብ ስንመረምር ጌታችን ሲያስተምር በጊዜው በጉባኤው ላይ የተገኙት አይሁድ ትምህርቱን በመቃወም ሊገድሉት ፈልገው፥ ሊይዙት ነበር። ጌታችን ግን ራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት ጊዜ ስላልደረሰ ከአጠገባቸው እያለ ተሰወረባቸው ። በአጠገባቸው አልፎ በመካከላቸው ሲሄድ ማየት እንዲሳናቸው አደረጋቸው።

ለቅዱሳኑም ይህን ጸጋ ሰጥቷቸዋል። በእነርሱ አድሮባቸው ይኖራልና ይሰወራሉ። «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።» /ዮሐ. ፲፬፥፲፪/። በግብረ ሐዋርያት መጽሐፍ ላይ ይህን ታላቅ ተአምር በተግባር እናየዋለን። ሄሮድስ በቤተ ክርስቲያን ላይ መከራ ባጸናባት ዘመን የዮሐንስ ወንድም ቅዱስ ያዕቆብን በሰይፍ በማስገደል፤ አይሁድን ይበልጥ ደስ ለማሰኘት ቅዱስ ጴጥሮስን ከፋሲካ በኋላ ሊያወጣላቸው ሌሊትና ቀን ቆመው በሚጠብቁት ወታደሮች አስከበበው። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ሰለ እርሱ አጥብቆ ይጸለይ ነበር። ሄሮድስ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳያመልጥ ፈጽሞ ስለፈለገ በሁለት ሠንሠለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል እንዲተኛ አስደረገ። በተጨማሪም በሩ እንዳይከፈት ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው በተጠንቀቅ ይጠብቁ ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስን ሊያወጣው በመጣው የእግዚአብሔር መልአክ አማካይነት ተቀስቅሶ ከሁለቱ ጠባቂዎች መካከል ሲነሣ ያየው ጠባቂ የለም። ሠንሠለቶቹ ከእጆቹ ሲወልቁና ሲወድቁ ያስተዋለው አልነበረም። በተለይ የሚገርመው በሩን በተጠንቀቅ ደጁ ላይ ሆነው ይጠብቁ የነበሩ ጠባቂዎች በሩ ተከፍቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲወጣ ሊያዩት አልቻሉም። ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ያለች የእግዚአብሔር የመሰወሪያው ጸጋ ጠብቃዋለችና ነው። የእግዚአብሔር መልአክ ባለበት የእግዚአብሔር ቸርነት አለና። ሲነጋም ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን «ምን ነካው? ወዴት ጠፋ?» ብለው ታወኩ። ምክንያቱም በሩ ሳይከፈትለት፥ በቁልፉ እንደተቆለፈ ሆኖ ወታደሮች በተጠንቀቅ ሳሉ ወዴት ሄደ ይበሉ? እነርሱ አላወቁም እንጂ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በጸሎት ትማፀን ስለነበር የእግዚአብሔር መልአክ ለሞት ከጠበቁት ወታደሮች ዓይን ሰውሮ አውጥቶታል። ወዲያውም ወደ ማርቆስ እናት ቤት በመሄድ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ነግሯቸዋል። ከዚህም እግዚአብሔር በፈለገ ጊዜ እንደወደደ ቅዱሳኑን ለጊዜውም ቢሆን የመሰወር ብቃት እንደሚሰጣቸው እንረዳለን። /የሐዋ. ፲፪፥፮-፲፱/።

፪. የመገለጥ ጊዜ እስኪደርስ ሌላ ሰው በመምሰል መሰወር

ለዚህም ምሳሌ የምናደርገው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በትንሣኤው ዕለት በመቃብሩ የተገኘችው መግደላዊት ማርያም ዘወር ብላ ጌታችንን አይታው ነበር። ነገር ግን አላወቀችውም። እንደውም የአትክልት ጠባቂ መስሏት ነበር። ፈቃዱ እስኪሆንም ልታውቀው አልቻለችም። ከጭንቀቷ የተነሣ «ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ» በማለት ራሱን ትጠይቀው ነበር። ፈቃዱ በሆነ ሰዓት «ማርያም» ብሎ በመጥራት እንድታውቀው አደረጋት። /ዮሐ. ፪፥፲፩-፲፯/።

የኤማሁስ ሰዎችም ታሪክ ተመሳሳይ ሁኔታን የያዘ ነው። ስድሳ ምዕራፍ ቀኑን ሙሉ እስከምሽት ቃሉን እየሰሙ ፊቱን እያዩ ቢጓዙ በፈቃዱ እርሱን ለማየት እንዲበቁ እንጀራ ቆርሶ እስኪሰጣቸው ሊያውቁት አልቻሉም። በዓይናቸው ፊት እያዩት ሳለ እርሱ መሆኑ ተሰውሮባቸው ነበር። «ቆርሶ ሲሰጣቸው ዓይናቸው ተከፈተ። ዐወቁትም። ወዲያውም ከዓይናቸው ተሰወረ።» /ሉቃ. ፳፬፥፲፫-፴፭/። ጌታ ለወደደው በወደደው ጊዜ ይገለጣል፤ ለሌላው ይሰወራል። በአንድ ጊዜና እይታ ሳሉም የሰዎችን የተሰወረውን የማወቅን ብቃት ይለያያል። ይህንንም በጥብርያዶስ ባህር ዓሣ በማጥመድ ላይ ያደሩ ሐዋርያት ታሪክ በሚገባ ያስረዳናል። ሲነጋም «ጌታ እኮ ነው» በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ ሲነግረው ሊረዳ ችሏል። በኋላም በየደረጃው ሁሉም ሐዋርያት ሊያውቁት ችለዋል። /ዮሐ. ፳፩፥፬-፲፬፤ ፩ኛ ሳሙ. ፫፥፩-፲፬/።

ለሰው ልጆችም እንደብቃታቸው መጠን ይህች ጸጋ ተሰጥታቸዋለች። ነቢዩ ኤልሳዕ ከሩቅ በሶርያ ቤተ መንግሥት የሚደረገውን በጸጋ እግዚአብሔር የማወቅ ደረጃ ደርሶ ነበርና የሶርያ ንጉሥ የመከረውንና ያቀደውን እያወቀ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረውና እስራኤልን ከአደጋ ይጠብቅ ነበር። የሶርያ ንጉሥ ይህን ባወቀ ጊዜ ጭፍሮቹን ልኮ ነቢዩ ኤልሳዕን እንዲይዙት አስከበበው። ነቢዩ ኤልሳዕም የሶርያ ጭፍሮች ዓይኖች እርሱ ያለበትን ቦታ እንዳያውቁት፥ ዓይነ ስውርም እንዲሆኑ ጸለየ። እግዚአብሔርም የነቢዩ ኤልሳዕን ጸሎት ሰማ። ነቢዩ ኤልሳዕም እንደሌላ ሰው እንዲመስላቸው አደረገ። ነቢዩ ኤልሳዕም እንደሌላ ሰው ሆኖ «ኤልሳዕ ያለበትን ቦታ ላሳያችሁ» ብሎ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው። እንደገናም «ዓይኖቻቸውንም ግለጥ» በማለት ጸለየና በሰማርያ መካከል መሆናቸውንና መርቶ ያመጣቸው ነቢዩ ኤልሳዕ መሆኑን እንዲለዩ አደረጋቸው። እዚህ ላይ ነቢዩ ኤልሳዕ የበቃ ሰው በመሆኑ በጸሎቱ የሶርያ ወታደሮቹን እየመራቸው ሲመጣ እርሱ እንደሆነ እንዳያውቁት፥ ያለበትንም ቦታ እንዳይለዩ አደረጋቸው። ይህም የእርሱ ማንነት እንዲሰወራቸው በመኾኑ ነው።
እንደዚሁም ጻድቁ ገብረ ክርስቶስ ከሙሽርነቱ ቦታ በእግዚአብሔር ተጠርቶ ከቤተሰቦቹ በተለየ ጊዜ የአባቱ ጭፍሮች እርሱን በፍለጋ እንዳያገኙ ሰውነቱ እንዲለወጥ ጸለየ። እግዚአብሔርም እርሱ እንደሆነ እንዳይታወቅ በቁስል ሸፈነው። በዚህም ሁለት ነገር እንዲያገኝበት አድርጎታል። አንደኛው ከቤተሰቦቹ እንዲሰወር ሁለተኛው በመከራው ዋጋ እንዲያገኝበት የእግዚአብሔር ሙሽራው ሆኗልና። ዐሥራ አምስት ዓመት በሰው አገር፣ ዐሥራ አምስት ዓመት በአባቱ ደጅ ሲተኛ ያወቀው የለም። እዚህ ላይ መረዳት ያለብን ምንም እንኳ በቁስል ቢመታ በአንድ ምልክት ቤተሰቦቹ ሊያገኙት ይችሉ ነበር። የእግዚአብሔር ጸጋው ሸፍናዋለችና ይህን ያህል ዓመት በደጃቸው ሆኖ ተሰውሯቸው ኖሯል።

፫. ልዩ መሰወር

እስራኤላውያን እግዚአብሔርን በመበዳላቸውና ከኃጢአታቸው አልመለስ በማለታቸው፣ ለባቢሎናውያን አሳልፎ ሰጣቸው። በመካከላቸው ግን ከነቢዩ ኤርምያስ ጋር ለእስራኤል ሕዝብ መልካም ያደርጉና ለእግዚአብሔር ታዛዦች የሆኑ «የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን» ይሉ የነበሩ ነቢዩ ባሮክና ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክን ከመከራና ከግዞት እግዚአብሔር እንደሰወራቸው እንመለከታለን። ይህ እንዲሆን ነቢዩ ኤርምያስ ወደ እግዚአብሔር ስለ ሦስት ነገር በጸሎቱ አመለከተ። በመጀመሪያ ስለንዋያተ ቅዱሳቱ መሰወር እንዲህ ብሏል «አቤቱ ጌታዬ፥ ይህችን አገር በጠላት እጅ አሳልፈህ እንድትሰጣት የባቢሎን ወገኖች እንዲይዟት እነሆ ዛሬ አወቅሁ። ...ስለምናገለግልበት ንዋያተ ቅዱሳት ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ጌታም «እርሱን ወስደህ ለምድር በቤተ መቅደስ አደራ ስጣት፤ አንቺ ምድር በውሆች ላይ የፈጠረሽ የሰገነት ክፍልም የከፈለሽ የፈጣሪሽ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተሽ፥ ጌጥሽን ተቀበይ፤ ዘሩባቤል እስኪመጣ ድረስ ገንዘብሽን አደራ ጠብቂ በላት» አለው። ባሮክና ኤርምያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤ የሚያገለግሉበትን ዕቃ ሁሉ ጌታ እንዳዘዛቸው ለምድር ሰጧት። ምድርም ያን ጊዜ አደራ ተቀብላ ዋጠች። ይህም ምድር የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅዱሳት መሰወሯን፥ መደበቋንና መሸሸጓን ያመለክታል።

ሁለተኛም «…ለኢትዮጵያዊው ሰው ለአቤሜሌክ የማደርገውን ግለጥልኝ፤ ...እርሱ ከረግረግ ጉድጓድ ውስጥ አወጣኝ፤ እንዳያዝን የአገሪቱን ጥፋት ያይ ዘንድ አልወድለትም» በማለት ጸለየ። ጌታም ለኤርምያስ «ወደ አግሪጳ የወይን ቦታ በዚህ ተራራ ጎዳና አቤሜሌክን ላከው፤ ሕዝቡን ወደ አገራቸው እስክመልሳቸው ድረስ እኔ እሰውረዋለሁ።» አለ። በነጋውም ኤርምያስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አቤሜሌክን እንዲህ ብሎ አዘዘው «ወደ አግሪጳ የወይን ቦታ ለታመሙ ወገኖች ትንሽ በለስን አምጣ ብሎ ላከው። …አቤሜሌክም ኤርምያስ ከላከው ቦታ በቀትር ጊዜ በለሱን አመጣ፤ ጽፍቅ ያለች ዱርንም አገኘ፤ ጥቂትም ያርፍ ዘንድ በጥላዋ ሥር ተቀመጠ፤ በለስ ያለባትን ሙዳይ ተንተርሶ ስድሳ ስድስት ዓመት ተኛ። ሲነቃም «ገና ራሴን ይከብደኛል፤ እንቅልፌን አልጨረስኩምና ዳግመኛ ጥቂት ብተኛ በጎ ነገር ነው» አለ። ያን ጊዜም በለስ ያለበትን ሙዳይ ከፈተ በለሶችም በሙዳዩ ውስጥ አዲስ ሆነው ወተታቸውም ሲፈስ አገኘ። «ተመልሼ እንዳልተኛ እንዳልዘገይም አባቴ ኤርምያስ እንዳይነቅፈኝ እፈራለሁ» አለ። ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሲገባ አገሩን ሊያውቀው አልቻለም በስድሳ ስድስቱ ዘመን ዛፎች በቅለው ደን ሆኖ ነበርና።

ሦስተኛም እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ «ባሮክን ግን በኢየሩሳሌም ተወው አለው» ባሮክም ስድሳ ስድስቱን ዘመን በመቃብሩ ስፍራ ባለው የመቃብር ቤት ተሰውሮ አሳለፈ። ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ አቤሜሌክን ወደ ባሮክ መርቶ ወሰደው። ባሮክም በመቃብር ቤት ተቀምጦ ነበር።» /ትንቢተ ኤር. ፴፱፥፲፭-፲፰፤ ተረፈ ባሮክ ፪፥፭-፲፫፣ ፫፥፩-፲፫፣ ፬፥፪/ በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። ከአቤሜሌክ ተአምራዊ እንቅልፍ ምን እንረዳለን? «እግዚአብሔር እሰውረዋለሁ» እንዳለ ከጠላቶች ሰውሮታል።

የሚገርመው ነገር አቤሜሌክ ራሱ ከራሱ ተሰውሮበታል። ስድሳ ስድስት ዘመን እንደ ጥቂት ደቂቃ አሳልፎ በመነሳቱ ከስድሳ ስድስቱ ዘመንም /ከጊዜ/ ተሰውሯል። የተኛው ጫካ ውስጥ ነበር፤ ከአውሬ፣ ከዝናብ፣ ከብርድ፣ ከፀሐይ ወዘተ ተሰውሯል። በላዩ ላይ ሣር በቅሎበት አልጠፋም። የእግዚአብሔር ተአምራዊ ጸጋው ከጥፋት ሰውራዋለች። «ወሰወረኒ በምኀባአ ጽላሎተ» ትርጉሙም «በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና» እንዳለ ቅዱስ ዳዊት። /መዝ. ፳፮፥፭/።

፬. ብሔረ ብፁዓን

ከኻያው ዓለማት ውስጥ የኾነች /ከመሬት ወገን የምትመደብ/ ስውር ምድር ብሔረ ብፁዓን ናት። እንደ ገድለ ዞሲማስ አገላለጽና ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት፥ በዚህች ቦታ ተሰውረው የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸውን ለፈቃደ እግዚአብሔር ያስገዙ ናቸው። በውስጧም ቅዱስ ጋብቻን መፈጸም የሚችሉና ዘርን ለማሰቀረትና ለመተካት ልጅን መውለድ ይችላሉ። ለኃጥአን ያልተፈቀደች የማትገባም ቦታ ናት።

፭. ደብር ቅዱስ

ከምድር ወገን ሆና የተለየች ሥፍራ ናት። አዳም በበደለና ከገነት በወጣ ጊዜ ገነትን በማየት ይጸጸት ዘንድ በዚህች ሥፍራ አኑሮታል። መጽሐፍ ቅዱስ /ብሉይ ኪዳን/ ይህችን ቦታ «ደብር ቀዱስ፣ ከፍ የለች ሥፍራ» በማለት ይጠራታል። /ሄኖክ ፬፥፸፩/። አዳም ከአቤል ሞት በኋላ የተወለደለት ሴት ከነልጆቹ ይኖር እንደ ነበርና በኋላም በኖኅ ዘመን የቃየንን ሴቶች ልጆች በማየት ስተው መውረዳቸውን በዘፍጥረት ትርጓሜ እንረዳለን። «የእግዚአብሔር ልጆችም /በደብር ቅዱስ የሚኖሩ የሴት ልጆች/ የሰውን ሴት ልጆች /የቃየንን ልጆች/ መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ ከመረጧቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።» /ዘፍ. ፮፥፪/ ይላል።

እነዚህ የቃየንን ሴቶች ልጆች በኃጢአት ተመኝተው ቅዱስ ሥፍራቸውን ጥለው በመውረድ የወለዷቸው ልጆች ኃያላን ነፍስ ገዳዮች፥ ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሆኑ። እግዚአብሔር ምድርን በእነርሱ ምክንያት አጠፋት።
ጻድቁ ሄኖክም ስለ እነርሱ መሳትና ስለ ደብር ቅዱስ ቅድስና እንዲህ ይላል «ከፍ ያለ ደብር ቅዱስን ዘላዓለም ጸንቶ የሚኖር መንግሥተ ሰማያትን ስለምን ተዋችሁት» /ሄኖክ ፬፥፳፩/፤ «ቀድሞ የንጽሕና መሠረት የነበሩ እነዚህም በዚህ ዓለም ክፉ ልጆች ይሆናሉ። ክፉ ልጆች ይባላሉ» /ሄኖክ ፬፥፹፫/ ብሏቸዋል። በተጨማሪም መልካም ሥራን በመልካም ቦታ እንዲሁም ጸሎትን መጸለይ የተዉትን የሴት ልጆች እንዲህ ይላቸዋል «እናንተ ለሰው ልተለምኑ ይገባችሁ ነበር። ሰው ግን ለእናንተ ሊለምንላችሁ አይገባችሁም ነበር» በማለት የሴት ልጆች ሳይስቱ በደብር ቅዱስ ቢቆዩ ኖሮ ለሰው ልጆች እየጸለዩ እነደሚኖሩ ገልጿል። ነቢዩ ሄኖክ በብሔረ ብፁዓን ይኖሩ የነበሩትን ከብሔረ ሕያዋን ሄዶ የነገራቸው፥ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚራራ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ጥፋት አይወድምና የሴት ልጆች ከነበሩበት ቦታ የሚያስወጣ ምኞት ተጸናውቷቸው በነበረ ጊዜ ምን አልባት ይመለሱ እንደሆን ያሰተምራቸውና ይመክራቸው ዘንድ ነው ። እግዚአብሔር ትእዛዙን ለነቢዩ ሄኖክ የገለጸለት በቅዱሳን መላእክት በኩል ነበር። /ሄኖክ ፬፥፮-፯፣፳፮/።

፮. ብሔረ ሕያዋን

በዚህ ቦታ የሚኖሩ ቅዱሳን ሰዎች በዘመናቸው መልካም ሥራን በማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ሰዎች ናቸው። ከእነዚህም በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚታወቁት መካከል ዋነኛዎቹ ነቢዩ ሄኖክና ነቢዩ ኤልያስ ናቸው። ስለነቢዩ ሄኖክ በመጽሐፈ ሲራክ ላይ «ሄኖክ እግዚአበሔርን ደስ አሰኘው፤ እግዚአብሔርም እርሱን ከሞት ሰወረው፤ ንስሃ ለሚገቡ ሰዎች አብነት ሆነ» ተብሏል /ሲራክ ፵፬፥፲፮/። በተሰወረ ጊዜም ከሰው ልጆች ያወቀ የለም። እርሱም በብሔረ ሕያዋን ለመግባት የመጀመሪያው ሰው ነበር። መጽሐፍ «ከነገር ሁሉ አስቀድሞ ሄኖክ ተሰወረ፤ ከሰውም ልጆች በተሰወረበት ቦታ ሳለ የሚያውቀው አልነበረም። ይሙት ይዳንም የሚያውቅ የለም» /ሄኖክ ፬፥፩-፪/ እንዲል /ዕብ. ፲፩፥፭-፮፤ ዘፍ. ፭፥፳፪-፳፬/።

ነቢዩ ሄኖክ ከመሰወሩ በፊት በአኗኗሩ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሰማያት ምሥጢር የተገለጡለት ከእግዚአብሔር የተማረ ነበር። በመጽሐፈ ኩፋሌ «ስሙን ሄኖክ አሉት፤ እርሱ አስቀድሞ በዚህ ዓለም ከተፈጠሩ ሰዎች ይልቅ መጻሕፍትንና ትምህርትን ጥበብንም ተማረ፤ የዘመኑን ጊዜ ያውቅ ዘንድ እንደወራቸው ሥርዓት የሰማይን ምልክት በመጽሐፍ ጻፈ።» /ኩፋሌ ፭፥፳፪-፳፫፤ ይሁዳ ፲፬-፲፭/ በማለት ይገልጸዋል።

በተጨማሪም ቅዱስን መላእክት የሰማይን ምሥጢር እያስጎበኙ ገልጠውለታል። እርሱም ከምድር ወደ ሰማይ በመነጠቅ በተመሥጦ ተረድቶታል። «ከነዚያ ወራት በኋላ በነፋስ ሰረገላ ተነጥቄ ነበርና፥ መላእክትም ወደ ምዕራብ ወስደውኝ ነበርና፥ በዚያ ቦታ የተሰወሩትን ራዕዮች አየሁ» /ሄኖክ ፲፬፥፩/ በማለት ይገልጾዋል።
ነቢዩ ኤልያስም ከደቀ መዝሙሩ ነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ እግዚአብሔር በእሳት ሰረገላ ወስዶታል። ከመወሰዱ በፊት ሙት በማንሣት፣ ሰማይ ዝናም እንዳይሰጥ በመለጐም እንደገናም ዝናምን በጸሎቱ በማዝነብ ወዘተ ተአምራት በማድረግ ለአምላኩ ቀናዒ መሆኑ ተመስክሮለታል። /፩ኛ ነገ. ፲፰፥፲፮-፵፮፤ ፪ኛ ነገ. ፪/። ከእርሱ ቀድሞ የተሰወረ ጻድቁ ሄኖክ ስለ ኤልያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ገልጿል «የእስራኤል ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤልን ጸባዖት ነቢያት ጠርቶ አስተምሩ ብሎ ላካቸው፤ እስራኤል ይገድሏቸው ጀመር። ከነቢያት አንዱ ኤልያስ ከሞት ዳነ፤ ሞት አላገኘውም፤ ፈጥኖ ሄደ፤ በእስራኤል ከተማ አስተማረ። እስራኤል ሊገድሉት ወደዱ። የእስራኤል ገዥ እግዚአብሔር ከእስራኤል እጅ አዳነው ። ወደ እኔም አምጥቶ አኖረው።» ይላል።

እንግዲህ በብሔረ ሕያዋን የሚኖሩ በብሉይ ኪዳን እንደነነቢዩ ሄኖክና ነቢዩ ኤልያስ ያሉት ናቸው። በሐዲስ ኪዳንም በወንጌሉ የተነገረላቸውና ከእነርሱም በኋላ ብዙ ቅዱሳን እንዳሉ መጻሕፍት ያስረዱናል። ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ወንጌላዌው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌላቱ ገጸ ንባብ ስሙ ሳይጠቀስ በምልክት፥ በትርጓሜ ወንጌል ላይ ደግሞ በስሙ ተጠቅሶ ወደ ስውራኑ መኖሪያ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደተነጠቀ ይገልጽልናል። ለዚህም ቅዱስ ሉቃስ «እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ» /ሉቃ. ፱፥፳፯/ በማለት ሲጠቅስ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ስለራሱ «ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱ ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ «ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?» ያለው ነበር። ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን «ጌታ ሆይ ይህስ እንዴት ይሆናል?» አለው። ኢየሱስም «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ» አለው። ስለዚህ ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?» አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።» /ዮሐ. ፳፩፥፳-፳፫/ በማለት ይገልጻል። በትርጓሜውም፣ በገድሉም፣ በስንክሳሩም ይህን መነሻ አድርገን ቅዱስ ዮሐንስ ከእነሄኖክና ኤልያስ ጋር በብሔረ ሕያዋን እንደሚኖር እናረጋግጣለን።

እነዚህ በብሔረ ሕያዋን ተሰውረው የሚኖሩ ቅዱሳን በአንዳንዶች ዘንድ «እዚያ ምን ይሠራሉ?» የሚል ጥያቄ ሊያሥነሳ ይችላል። በመጽሐፈ ሄኖክ ከመላእክት ጋር በቅዳሴ እንደሚያመሰግኑ እንደሚከተለው ተገልጿል። «ሥራውም ሁሉ በተሰወረበት ወራት በቅዳሴያቸው ከሚተጉ ቅዱሳን መላእክት ጋርና ከቅዱሳኑ ጋር ነበር።» በተጨማሪም «እኔም ሄኖክ ገናና ጌታን በአራቱ ማዕዝነ ዓለም የነገሠ እግዚአብሔርን አመሰግነው ጀመር» /ሄኖክ ፬፥፴፬/ በማለት ከተግባሩ አንዱ ምስጋና እንደሆነ ይገልጽልናል። እንዲሁም ቅዱሳኑ ከመላእክት ጋር ስለሰዎች ልጆች ድኅነት እንደሚነጋገሩና ነቢዩ ሄኖክ ወደ ደብር ቅዱስ ይሄድ ዘንድ በመላእክት እንደተነገረው እርሱ ከጻፈው መጽሐፍ እንረዳለን። «…ለቅዳሴያቸው የሚተጉ መላእክት እነሆ ይጠሩኛል። ...ለኃጢአት ለሚተጉ ሰማያዊ መዓርጋቸውን መንግሥተ ሰማያትን አጥተው ከሴቶችም ጋር ለጠፉ የቃየል ልጆችም እንደሚያደርጉ ላደረጉ ለደቂቀ ሴት ሄደህ ንገር አለኝ...» /ሄኖክ ፬፥፮-፯/ በማለት ቅዱሳን መላእክት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመምጣት ሄኖክ ወደ ደቂቀ ሴት ከጥፋታቸው እነዲመለሱ እነዲነግራቸው ከእግዚአብሔር ተልከው ነግረውታል። እርሱም የተላከውን መልእክት ሊያስተላልፍ ወደ ደቂቀ ሴት እንደ ሄደና እንደነገራቸው «እውነት ነገር ያለበት ይህን ቃል እናገር ዘንድ በደብር ቅዱስም ለነበሩ በኃጢአታቸው ለሚተጉ ለደቂቀ ሴትም አስተምር ዘንድ ጀመርሁ» /ሄኖክ ፬፥፳፮/ በማለት በዚያም ያለውን የቃለ እግዚአብሔር የማስተማር ተልእኮውን ይገልጽልናል።

በአጠቃላይ በብሔረ ሕያዋን ምስጋና፣ ቅዳሴ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መነጋገር፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር መነጋገር፣ መጸለይ፣ ስለሰው ልጆች ድኅነት ማሰብ ወዘተ እንዳለ እንረዳለን።

በተጨማሪም በብሔረ ሕያዋን በሚኖሩ ቅዱሳን መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ግርማ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር እንደተገለጠ ከወንጌሉ እንረዳለን። /ሉቃ. ፱፥፳፰-፴፮፤ ማቴ. ፲፯፥፩-፰፤ ማር. ፱፥፪-፰/። ይህም በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነቢዩ ኤልያስ በሥጋው እንዳረገ ስለሚያውቁ ከጌታችን ወደዚህ መምጣት ጋር ተጋጭቶባቸው የጌታችንን አምላክነት እንዳይክዱ ለሐዋርያቱ ከነቢያት አንዱ ኤልያስን ከመሰወሪያው ከብሔረ ሕያዋን በማምጣት እንዲያዩት አድርጓቸዋል። ይህንንም በማየት ቅዱስ ጴጥሮስ «እኔ ማነኝ?» ለሚለው ጥያቄ ጌታችን አምላክ እንጂ ነቢዩ ኤልያስ እንዳልሆነ «አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» በማለት አረጋጧዋል።

ስውራን ቅዱሳን /ኅቡአን ቅዱሳን/ በፍጻሜ ዘመን ወዳለንበት ምድር መጥተው እንደሚገለጡና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መስክረው በአውሬው /ሐሳዌ መሲሕ/ ሰማዕትነትን እንደሚቀበሉ መጻሕፍት ያስረዱናል። በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ቅዱስ ዮሐንስን ጌታችን «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ምን አግዶህ?» ብሎታል። ይህም ማለት በብሔረ ሕያዋን እስከምጻት መዳረሻ /ጌታ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ/ ሳይሞት ይኖር ዘንድ እንደፈቀደለት እንጂ ጭራሹኑ አይሞትም አላለውም። /ዮሐ. ፳፩፥፳፪-፳፫/። በሐሳዌ መሲሕ ዘመን በእውነተኛ ምስክርነቱ ሰማዕትነትን እንደሚቀበል፣ ነፍሱ ከሥጋው እንደሚለይ ያስረዳናል። ስለነቢያቱ ሄኖክና ኤልያስም ዮሐንስ በራዕዩ «ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች» በማለት የሐሳዌውን መሲሕ ክሕደት በመቃወም ምስክነታቸውን እንደሚሰጡ፥ በምድር ላይ ያሉትን ሕዝቦች እንደሚያስተምሩና ታላላቅ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ከትርጓሜ ራዕየ ዮሐንስ እንረዳለን። /ዮሐ. ራዕ. ፲፩፥፬-፲፫/።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፦ የሐመር መጽሔት ፲፫ኛ ዓመት ቁ. ፭ መስከረም/ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ለድረ ገጽ እንዲመች ሆኖ በከፊል የተወሰደ

Share |

Written By: host
Date Posted: 2/6/2011
Number of Views: 13145

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement