View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ሁለቱ የጾም ዓላማዎች

ጾም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጉዟችን ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት።
1.    የትህርምት ጾም፦
ቅዱስ ጳውሎስ የሥጋ ሥራዎች እና የነፍስ /የመንፈስ/ ፍሬዎች በዘረዘረበት በገላትያ መልዕክቱ “ሥጋ በመንፈስ ላይ፣ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፤ ሁለቱም እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ።” በማለት በሁለቱ መካከል ያለውን የማያቋርጥ የፈቃድ ልዩነትና ጦርነት ገልጾታል። /ገላ ፭፥፲፯/።

መንፈሳዊነት ማለት ነፍስን ለመንፈስ ቅዱስ /ለእግዚአብሔር/ ሥጋን ደግሞ ለነፍስ ማስገዛት ማለት ነው። ስለዚህ የአንድ መንፈሳዊ ሰው ጉዞ /ሕይወት/ በሠረገላ ሊመሰል ይችላል። አንድ ሠረገላ ነጂ፣ ፈረስ፣ ልጓም እና የሚጐተት ጋሪ አሉት። የሠረገላው ነጂ እግዚአብሔርን /መንፈስ ቅዱስን/ ይወክላል። ነጂው በልጓሙ ፈረሱን እንደሚቆጣጠረው መንፈስ ቅዱስ የልባችንን ሃሳብ በማቅናትና በማስተካከል ሕይወታችንን ይመራል። ፈረሱ በነጂው በታዘዘው መሠረት ጋሪውን ይጐትታል። ነፍሳችንም ሥጋችንን በመቆጣጠርና በመምራት ትክክለኛውን ሥራ እንዲሰራ ታደርጋለች። ፈረሱ ለነጂው የማይታዘዝ ከሆነ የሠረገላውን ጉዞ እንደሚያበላሸው ነፍሳችንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማትሰማ /የማትማር/፣ በዚህም ለመገዛት የማትፈቅድ /የማትወስን/ ከሆነ መንፈሳዊ ሆነን መኖር አንችልም።
ጋሪው ያልተስተካከለ ከሆነና ፈረሱ ጋሪውን ለመጐተት የሚቸገር፣ ሲጐተትም በአግባቡ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ጉዞው የተሳካ አይሆንም ስለዚህ መስተካከል አለበት። በተመሳሳይ ሁኔታ ሥጋችንም ለነፍሳችን ፈቃድ የማይገዛ ከሆነ፣ ንጽሕናን ስንፈልግ ወደ ዝሙት፣ ትዕግስትን ስንፈልግ ወደ ቁጣ… በግድ የሚመራን፤ እንደምንመኘው ሆነን እንዳንኖር የሚያደርገን ከሆነ ሥጋችንም መስተካከል አለበት። ሥጋ ተስተካክሎ ለነፍስ እንዲገዛ የሚደረግበት “ጋራዥ” ደግሞ ጾም ነው። ለዚህ ዓላማ የምንጾመው ጾም ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጃል። የአንድ ወይም የሁለት ቀናት ጾም ሥጋን ለነፍስ ያስገዛል ማለት ያስቸግራል። የሳምንታትን፣ የወራትን፣ እና የዓመታትን ትግል፣ ረጅምና በትዕግስት የሚደረግ ጥረትን ይፈልጋል። ሳምንታትን፣ ወራትን፣ ዓመታትን፣… የሚፈጅ ትግል ይፈልጋል ስንል ግን እነዚህን ጊዜያት ያለምንም ምግብ እንኖራለን ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን በምንጾምባቸው ወራት ከቀኑ የተወሰኑ ሰዓታትን /የተወሰኑ ቀናትን/ ያለ ምግብ እንቆይና ከዚያ በኋላ ደግሞ የምንበላውን መጥነን እንበላለን፤ በጾሙ ወራትም ከጥሉላት እንከለከላለን።
ስለዚህ በዚህ ዓይነት ጾም ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ጠቅላላውን የጾም ወራት “ጾም” በማድረግ ብቻ ነው። በጾሙ ወራት ባሉት ቀናት እስከተወሰነ ሰዓት ብቻ እየጾሙ ከዚያ በኋላ እስኪጠግቡ ድረስ እየበሉ ማካካስ በጾሙ ተጠቃሚ እንዳንሆን ያደርገናል። ቀኑን ሙሉ እየገነባን ማታ ማፍረስ ይሆንብናል። ስለዚህ በመብላታችን ውስጥም ጾማችን መቀጠል ይኖርበታል። ይህን ያህል ጊዜ፣ ወራት ወይም ሳምንታትን ጾምን ማለት የምንችለው እነዚያን ሳምንታት ወራት በሙሉ በትህርምት ስናሳልፍ ነው። በአጽዋማቱ መካከል ያሉት ቅዳሜዎችና እሁዶች እንኳን የምንበላውን መጥነን በመብላት ትህርምታችንን መቀጠል አለብን። ሳምንቱን እየገነቡ በሳምንቱ መጨረሻ ማፍረስ እንዳይሆንብን። በገድላቸው የምናውቃቸው ቅዱሳንና ዛሬም በየገዳማቱ ያሉ መነኮሳት ዓመቱን በሙሉ በትህርምትና በጾም የሚያሳልፉት ለዚህ ነው። ይህ ዓይነት ጾም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ስለሆነ ክርስቲያኖች ሁሉ በደስታና በፈቃዳችን ልንጾመው የሚገባን ነው። ቅዱሳን አባቶቻችንም በእውነት ዘመናቸውን በሙሉ በዚህ ዓይነት ጾም አሳልፈውታል፤ ተጠቅመውበታልም።
እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን በዝለትና በመዘናጋት ሳንጾምና በጾም ሳንጠቀም እንዳንቀር የዚህን ዓይነት ጾም የምንጾምባቸውን የዐዋጅ አጽዋማት አዘጋጅታለች። /ጾመ ነቢያት፣ ዐብይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ፍልሰታ፣ …/።  ጾመ ድኅነትም /የረቡዕና የዓርብ ጾም/ በየሳምንቱ ሁለት ቀናት እየመጣ ሕይወታችን ልቅ እንዳይሆን የሚያደርግና ወደ ትህርምት የሚገፋን ጾም ነው።
የትህርምት ጾም ከኃጢአት ርቀን የመንፈስ ፍሬዎች አፍርተን ለመኖር ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ስለሆነ፤ እነዚህን አጽዋማት ጨምረን በተገቢ ሁኔታ መጾም ይገባናል።
2.    የዝግጅት ጾም፦
ሁለተኛው የጾም ዓላማ ዝግጅት ነው። ሥጋ ወደሙ ስንቀበል፣ ሌሎቹንም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ስንፈጽም /ንስሐ፣ ተክሊል…/፣ በዓላትን ስናከብር ከፍ ያለ ተመስጦ ትኩረትና መንፈሳዊነት ያስፈልጋል። ሃሳባችን በተለያዩ ነገሮች በሚሰረቅበትና በሚከፈልበት ዓለም እየኖርን ይህንን ዓይነት ስሜት ወዲያው ማምጣት ስለሚያስቸግረን ከድርጊቶቹ በፊት ዝግጅት ማድረግ አለብን። ከነዚህ ዝግጅቶች አንዱ ጾም ነው። እየጾምን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ እየተዘጋጀንበት ስላለነው ጉዳይ በማሰብና በመወያየት ኃጢአታችንንና ደካማነታችንን እያሰብን በማዘንና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን በማድረግ ራሳችንን ወደሚፈለገው መንፈሳዊ ስሜት እናደርሳለን። በጾማችን ጊዜ የሚሰማን ረሃብ ለምንዘጋጅለት ጉዳይ ያለንን ናፍቆትና ረሃብ ይወክላል።
ለዚህ ዓላማ የምንጾመው ጾም ከምንዘጋጅላቸው ነገሮች በፊት ለጥቂት ጊዜ የሚጾም ርዝመቱ እንደምንዘጋጅለት ነገርና እንደየሰዉ ሁኔታ ይለያያል። በነዚህ ጊዜያት ግን ሙሉ በሙሉ ከምግብ እንከለከላለን። የዝግጅቱ ጊዜ ከተጠናቀቀ የምንዘጋጅለትን ነገር ከፈጸምን በኋላ (ሥጋ ወደሙ ከተቀበልን፣ በዓላትን ካከበርን) ግን እንደ ትህርምት ጾም ጾሙ አይቀጥልም። የምንበላውን የምግብ ዓይነትም አንወስንም፤ ዝግጅታችንን፣ የሐዘን ጊዜያችንን ጨርሰናልና በረሃብና ሐዘን አንኖርም። በፈጸምናቸው ምሥጢራትም ሆነ በምናከብራቸው በዓላት የተቀበልነውን ደስታ እናጣጥማለን እንጂ። ከሥጋ ወደሙ በፊት የምንጾማቸው 18 ሰዓታት፣ ከጥምቀት በዓል በፊት የምንጾመው ጾመ ገሃድ ለዝግጅት ጾም ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።
«ኦ እግዚአብሔር አምላክነ ንስእለከ ከመታብርህ አእይንተ አልባቢነ ከመናእምር ወንሌቡ ሕግጋቲሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ወከመ ታጥብ አነ ከመንፌጽሞሙ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሕግጋት እናውቅና እናስተውል ዘንድ የልቦናችንን ዐይን ታበራልን እንድንፈጽማቸው ታስጨክነን ዘንድ እንለምንሃለን።»
ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት ቁጥር ፫፤ ሰኔ ፳፻፪ ዓ.ም.
Share |

Written By: host
Date Posted: 2/24/2011
Number of Views: 7006

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement