View in English alphabet 
 | Thursday, October 3, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

«ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም?»

/ኢሳ. ፶፰፥፫/
በቀሲስ ስንታየሁ አባተ

በኢሳያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን የተናገሩት ቃል ነው። እስራኤላውያን የሚጾሟቸው ብዙ አጽዋማት ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህልም ብናይ በሳምንት ሁለት ጊዜ በሳምንት ሁለት ቀን ይጾሙ እንደነበር በሉቃ. ፲፰፥፲፪ ላይ ያለው ቃል ያስረዳል። ማክሰኞና ሐሙስ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ ደብረ ሲና የወጣበትና ከዚያ የወረደበት ዕለት ለማሰብ እስራኤላውያን በሳምንት ሁለት ቀኖች ይጾሙ ነበር። በነቢዩ በዘካርያስ ትንቢትም ላይ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዝዟቸዋል «የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሀሤትም በዓላት ይሆናል ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ወደዱ።» ተብሎ ለእስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ዘንድ በነብዩ በኩል በተነገራቸው መሠረት የተጠቀሱትን ይጾሙ ነበር። /ዘካ. ፰፥፲፰-፲፱/።

በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን የእስራኤል ዘስጋ ታሪክ በምናይበት ሰዓት ብዙውን ጊዜ ሲጾሙ ብዙውን ጊዜ ሲጸልዩ በጾም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ፣ በጾም ችግራቸውንና ሐዘናቸውን ለእግዚአብሔር ለመግለጽ፣ በጾም የልቡናቸውን መሻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመቀበል ነበር።

እኒህን ሁሉ አጽዋማት ጊዜያቱን ጠብቀው ቢጾሙም እግዚአብሔር በምህረት አይኖቹ አላያቸውም መራቡ መጠማታቸውንም አልቆጠረላቸውም ስለዚህ በርዕሳችን እንደጠቀስነው «ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም» በማለት እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ዘንድ ምሬታቸውን ሲያቀርቡ እንመለከታለን። እስራኤል ጾመዋል ፣ደክመዋል፣ ራሳቸውንም አዋርደዋል፣ ሰውነታቸውንም አጎሳቁለዋል። ይሁን እንጂ የልቡናቸው መሻት ሰላልተፈጸመላቸው የጾማቸው ዓላማ ግቡን ስላልመታ ፍሬም ስላላፈራላቸው ወደ አባታቸው ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው «ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም?» ብለው እንደጠየቁት እናያለን።

ስለምን እግዚአብሔር አልተመለከታቸውም? በእውነት የዋሀን እንደሚያስቡት ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ሳይሆን ቀርቶ ነውን? እግዚአብሔር ጾምን የማይቀበል ሆኖ ነውን? አይደለም። 

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጠቀሰው ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ነው። የሰው ልጆች እንዲጾሙ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እነዲቀርቡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተሰጡት ትእዛዛትና ሕግጋት መካከል የመጀመሪያውና ቀዳሚ ትእዛዝ መሆኑን መጽሐፍ ቀዱስ ይነግረናል። /ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯/።

እግዚአብሔር ለአዳም ሁሉን ይገዛ ዘንድ በሁሉ ላይ ባለሥልጣን ገዥ ንጉሥ እንዲሆን አድርጎታል። ነገር ግን አዳምን ዓይኑ የተመለከተዉን ሰውነቱ የፈቀደውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ አላሰናበተውም። ለዚህ ነው ሥርዓተ ጾምን /ሕገ ጾምን/ የሠራለት። እግዚአብሔር አዳም እንዳይበላ የከለከለውን ዕፀ በለስን በምናይበት ሰዓት ለአዳም እንዲበላ ከተሰጡት ዕፅዋት መካከል ተለይታ ለዓይን የምታስጎመጅ ለጥበብም መልካም ሆና የተገኘች ነበረች። ጾም አብልጠን የምንወደውን የሚያምረንና ለሰውነታችን እርካታና ምቾት የሚያስገኘውን ሁሉ ለተወሰኑ ጊዜያት ወይም በዘላቂነት መተውን የሚመለከት መልካምና ደገኛ የሆነ የሃይማኖት ሥርዓት ነው።

ጾም ከጥሉላት ምግቦች ወይም ከእንስሳት ተዋጽኦ ራስን ገትቶ መቆየት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ጾም የመላ ሕዋሳት ተግባር ነው። ጾም በዚህ ምክንያት መላ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ማደርያነት ቀድሶ ማቅረቢያ ነው። እስራኤል ከዚህ ስለጎድሉ ነው እግዚአብሔር በነብዩ በኢሳያስ አድሮ «በውኑ እኔ የመረጥሁት ጾም ይኸ ነውን?» በማለት ለእስራኤል ጥያቄ መልስ የሰጣቸው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ያለዘርዓ ብእሲ በፍጹም ድንግልና ከተወለደ በውኃላ ብርሃነ ክብሩን በገለጠበት በደብረ ታቦር ተራራ ከቀዱሳን አበው መካከል የተመረጡ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ነበር። ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሁም ነብዩ ኤልያስ በዚያ የክርስቶስ ክብር ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠበት ተራራ ላይ ቆመው እናያቸዋለን። ይህን ሰማያዊ ክብር ለማየት የታደሉት እኒህ አበው በዘመናቸው 40 ቀንና ሌሊት ጾመዋል። በጾማቸውም በረከትን ተቀብለዋል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ በመጾሙ እስራኤል የሚመሩበት ሕገ ኦሪት ሠርቶላቸዋል ሕዝበ እስራኤል የሚባረኩበትን ጽላት ተቀብሏል። ነብየ እግዚአብሔር ኤልያስም ፈራሽ ሆኖ ሳለ በመጾሙ በመጸለዩ ለእግዚአብሔርም ክብር በመቅናቱ ሰማየ ሰማያት እንዳረገ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል።/፪ ነገስ. ፪፥፲፩/። ቅዱሳኑ በዘመናቸው በፈጸሙት መልካም ጾም የጌታችንን መለኮታዊ ክብር ለማየት በቅተዋል። ጾም በአግባቡ ቢጾሙት እግዚአብሔር እንደሚፈቅደው ሆነው ከተገኙ እግዚአብሔር ጾምን የሚቀበለው ሐዘንን ከልቡና የሚያርቅ እንባን ከዐይን የሚያብስ መሆኑን እናያለን።

ጾም እንዲህ ያለ ታላቅ ዋጋ የሚያሰጥ ቢሆንም እስራኤል ግን ጾመው ያገኙት ጥቅም አልነበረምና «ስለምን ጾምን» በማለት እግዚአብሔርን ይጠይቁታል።

ምክንያቱም ጾማቸው የጎደለው ኖሮ ነው ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው፣ ከእግዚአብሔር ሊያስታርቃቸው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት ቸርነትን ሊያመጣላቸው ያልቻለውና «ስለምን ጾምን» ብለው መጠየቃቸው አግባብ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርአት መሠረት ከዓመቱ ቀናት መካከል ከ235 ቀናት በላይ እንጾማለን። ይሁን እንጂ እንደ እስራኤል ዘሥጋ ሁሉ «ስለምን ጾምን?» የሚያሰኙ ሁኔታዎች አሉን። የበዛውን የዓመቱን ጊዜ በጾም አሳልፈናል በውኑ እግዚአብሔር ጾማችንን ተቀብሎአልን? ተመልክቶስ ቤታችንንና ሥራችንን፣ ልጆቻችንንና ሀብታችንን ባርኮአልን? ካልሆነስ ለምን? የጾምንበት ዓላማ ግቡን መምታቱንና አለመምታቱን ካየን በኋላ ለምን በሚል ጥያቄ አምላካችንን እንድናማርር አድርጎናል። መልካም ደገኛ የሆነውን ሥርአተ ጾም ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን የሚያዋርድ ሰው ሁሉ አጽዋጿሙ በእግዚአብሔር ፊት ምን እንደሚመስል ራሱን ሊጠይቅ፣ ሕይወቱንና ልቡናውን ሊመረምር ይገባል።

በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያንና በቤታችን ውስጥ ዛሬ እንደምናየው መከፋፈልና መለያየት፣ ረሃብና ደርቅ፣ በሽታና ስደት ነግሰው ዕለት ዕለት የምእመናንን ልቡና በትካዜ ተውጠው እናያቸዋለን። በየቀኑ ከምትወጣዋ ፀሐይ ጀርባ መልካም ዕለትን ከመናፈቅ ይልቅ እያንዳንዱ ዕለት መከራ ያመጣብን ይሆን? እያሉ የሚሰጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው። የዚህ ሁሉ መንስኤው እንደ እስራኤል ሁሉ መንፈሳዊነት የጎደለው ጾም ስለሆነ ነው። የቡዙዎቻችን ጾም እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሆኖ አለመገኘቱ ነው።

ከላይ እንዳየነው እስራኤላውያን በዓመት ውስጥ አራት ወራትን በሳምንት ሁለት ቀናትን ቢጾሙም ጾማቸው መንፈሳዊነት የጎደለው ነበር። እስራኤል ቢጾሙ የሰዓቱን እርዝማኔ እንጂ በዚያ በረዘመው ሰዓት ወስጥ ምን እያደረጉ እንደሆነ አያውቁም ምን ማድረግ እነደነበረባቸውም አያስተውሉም ነበር። ይህ ሁኔታ ዛሬ በምንጾመው ጾም ውስጥ የሚታይ ነው።

እስከ ስድስት እስከ ዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት ሰዓት እየቆየን እንጾማለን እንጂ በዓመቱ ያሉትን ሰባት አበይት የዐዋጅ አጽዋማት ዛሬ ደግሞ በግልና በፈቃድ የምንጾማቸውን የጳጉሜንና የጽጌን ጾም ጨምሮ መጾማችንን እንጂ በአጽዋማቱ ወራት ወቅትና ዕለት እንደ ምእመን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሊያድርገው የሚገባውን ነገር እያደረግን ነው ወይ? የሚለውን ነገር አናስተውለውም። የሚታየን መዋላችን ከምግብ መከልከላችንና ራሳችንን ማድከማችን እንጂ በነዚያ ሰዓታት ውስጥ በትሕትና ከወገኖቻችን ጋር በሰላምና በፍቅር መሄድ አለመሄዳችንን ስለማናስተውለው መንፈሳዊነት ይጎድለናል።

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን ሲጾሙ ጥል ክርክና ግፍ ማድረግን ከልቡናቸው አላራቁትም ነበር። ይጾማሉ በሚጾሙበት ሰዓት ግን ይጣሉ ነበር። ይጾማሉ በሚጾሙበት ሰዓት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ነበር። ይጾማሉ በተለይ በሚጾሙበት ወቅት በሠራተኞቻቸው ላየ ግፍ ያደርጉ፣ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ያስቀሩ፣ በግፍ ይበዘብዟቸው፣ ያስጨቋቸው፣ ያስመርሯቸው ስለነበር ይሄ ጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ያቀርባቸው ዘንድ አልቻለም። እስራኤል «ለምን አልሰማኸንም» በማለት ከእግዚአብሔር ጋር በተዋቀሱ ጊዜ እግዚአብሔር በነብዩ በኢሳያስ አድሮ እንዲህ ይመልስላቸዋል «በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁን ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እነደምትጾሙት አትጾሙም» በማለት እግዚአብሔር ወቅሷቸዋል።/ኢሳ. ፶፰፥፫-፬/።

ጾም የምንጣላበት ሳይሆን ሰላምን የምናደርግበት ነው። ጾም የምንከራከርበት ጊዜ ሳይሆን አንድ የምንሆንበት ጊዜ ነው። ጾም ግፍን የምናደርግበት ሳይሆን የግፍን ማሰርያ የምንበጥስበትና ከክፉ አድራጊነት ወደ በጎነት የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው።ይሄን ሳያገናዝቡ መጾም ጾማችንን መንፈሳዊነት የጎደለው ያደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን ሲጾሙ ለወገኖቻቸው ምሕረትን አላደረጉም ነበር። ጾም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን የምንለምንበትና የምንጠይቀበት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ዓይነ ምሕረቱን እነዲመልስ እዝነ ልቡናውን ወደ እኛ ንዲያዘነብል የማያልቀውን የቸርነቱን ሥራ እንዲሠራልን የምንጠይቅበት ጊዜ ነው።

ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና ይቅርታን እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም በጾማችን ወቅት ከሌላው ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ለወገኖቻችን ምሕረትን ልናደርግ ይገባል። ምሕረት ማድረግ ስንል ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል። እነዚህም ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ናቸው።

ምሕረት ሥጋዊ ፤ለአንድ ሰው በሥጋ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት ነው። ቀዶ ማልበስ ቆርሶ ማጉረስ ወዘተ ነው። የጎደለውን አይቶ መሙላት በተለይ በጾማችን ወቅት ከሌላው ወቅት በተለየ ሁኔታ ለሌሎች ምሕረት ማድረግ ይገባናል።

ምሕረት መንፈሳዊ ፤ ማለትም አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበትን ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻችት ነው። በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ፣ ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር የራቀውን በትምህርት በምክር በተግሳጽ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ነው። ከባልጀራው ጋር ተጣልቶ እግዚአብሔርን ያስቀየመውን በመካከላቸው እርቅ እንዲኖር ማድረግ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወቱ እንዳይጎሰቁል እንዳይደክምና ከጽድቅ እንዳይጎድል መርዳት ነው።

እንደ እስራኤል ሁሉ ከምሕረት የራቀ ጾም ይዘን እንደሆነ መልስ የማያስገኝ በመሆኑ በምንጾምበት ሰዓት ለወገኖቻችን ምሕረት ማድረግን የጾማችን ክፍል ልናደርግ ይገባል።

«እኔስ የመረጥሁት ጻም ይህ አይደለምን? የበደልን አስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ደሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቆቱትንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፥ የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሀል።» /ኢሳ. ፶፰፥፮-፱/ ተብሎ የተነገረው ቃል በጾማችን ወቅት ምሕረት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል።

እስራኤል ሲጾሙ ሥጋቸውን ከማስራብ በስተቀር ነፍሳቸውን በንስሐና በቃለ እግዚአብሔር አይመግቧትም ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና እንደ እግዚአብሔር ቃል የጾም ትልቁ ዓላማ ሥጋን ማስራብ ሳይሆነ ነፍስን በበጎ ነገር ማርካትና በበጎ ነገር ማጥገብን የግድ የሚመለከት ነገር ነው።

ጌታችን አርአያና ምሳሌ የሆነበት ዐቢይ ጾም ፈታኝ ወደእርሱ ቀርቦ እንዲመገብ ባዘዘው ጊዜ «ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ» በማለት እንደመለሰ በማቴ. ፬፥፬ ተጠቅሶ እናገኛለን።

በጾማችን ወቅት ምግበ ሥጋ በማጣት የደከመ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ቃለ እግዚአብሔርን የጠገበች ነፍስም ልትኖረን ያስፈልጋል። ያለዚያ ግን ምንም እንኳ ሥጋ ቢደክምም ነፍስ ከተራበች ኃጢአት ይሰለጥንባታል። በዚህ ምክንያት ጾማችን ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርበን ምሕረትና ቸርነትንም ሊያስገኝልን አይችልም። «የጠገበች ነፍስ የማር ወለላን ትረግጣለች፤ የተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።»/ምሳ. ፳፯:፯ /። ጽድቅን፣ ቃለ እግዚአብሔርን፣ ንስሐን የተራበች ነፍስ በሁሉም በጎ የሆነውን ፈቃደ እግዚአብሔር በመማር ያላወቀችና ከፈቃደ እግዚአብሔር የራቀች ነፍስ የመረረ ነገር፣ ኋጢአት፣ በደል፣ ክፋት ይጣፍጣታ። በኋጢአት በበደል በክፉ ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ባልሆነ ነገር ሁሉ ታስራ መከራዋን ታያለች። በቃለ እግዚአብሔር፣ በፍቅረ እግዚአብሔር፣ በንስሐ ፣በሥጋውደሙ የጠገበች ነፍስ ግን የዚህን ዓለም ተድላ ደስታ ምኞት ንቃ ትጠየፈዋለችና ከእግዚአብሔር ጋር አንድነቷን ታጠናክራለች።

በቅዱሳት መጻሕፍት ዜና ሕይወታቸው ተዘግቦ የምናገኘው ቅዱሳን ራሳቸውን አሳልፈው ለሞት እስከ መስጠት ዓለምን ንቀው ወደ በረሓ እስከ መመነን የሚደርሱት ነፍሳቸው በቃለ እግዚአብሔር የጠገበች በመሆኗ ነው።

ሊቀ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስና በሰብአ ነገሥታት ፊት በተጋደለበት ዘመን ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሊያታልለው ሞክሮ ነበር። በዚህ ዓለም የብዙዎች ስዎችን ልቡና የሚያነሆልሉና የሚያታልሉ ታላላቅ ገፀ በረከቶችን አቅርቦለት ነበር። ከነዚህም መካከል መኳንንቱና መሳፍንቱ የሚመኟት አንዲት ሴት ልጁን ሊድርለት ቃል መግባቱ ነበር። የመንግሥቱን እኩሌታም እንደሚሰጠው፣ ከእርሱ በታች ታላቅ ባለሥልጣን እንደሚያደርገው፣ በሰባ ሀገሮች ላይም እንደሚሾመው ቃል ገብቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ነፍሱን በእግዚአብሔር ቃል ያጠገበ አባት ነበርና ዱድያኖስ ያቀረበለትን ማባበያ ንቆ በሃይማኖት ጸንቶ ተገኝቷል።

እስራኤላውያን በጾማቸው ወቅት ሥጋቸውን ከማስራብ በስተቀር ነፍሳቸውን ያጠገቡበት ሁኔታ አልነበረም። ነፍሳቸውም ሥጋቸውም የተራበች ነበረች። ከዚህ የተነሳ ነው እግዚአብሔር ሊጎበኛቸውና ሊመለከታቸው ያልቻለው። ስለዚህ የእኛም ጾም እንዲህ እንዳይሆን በምንጾምበት ጊዜ ጾማችን የግድ ከንስሐ፣ ከሥጋ ወደሙ፣ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር አንድነት ሕብረት ያለው ሊሆን ይገባዋል። ሥጋን ብቻ አስርቦ ነፍስን የማያጠግባት ጾም መልስ የማያስገኝና የምሬተ ጾም ይሆንብናል።

በነብዩ በኤርምያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላዉያን የተወቀሱበትን ሁኔታ ስንመለከት አንድ ነገር እንድናስተዉል ያደርገናል። «እንዲህ ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሰሡምን? የሳተስ አይመለስምን? እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም ዕንቢ ብሎአል። አደመጥሁ ሰማሁም ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸዉም፦ ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አዉቃለች ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመውጣታቸዉን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም»።/ኤር. ፰፥፬-፯/።

እስራኤል በጾማቸው ወራት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሳቸውን ንስሐ አልተጠቀሙበትም ነበርና ነዉ እግዚአብሔር ያልሰማቸው። ስለዚህ በጾማችን ወቅት ከመብል መከልከል ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት ወደ እኛ እንዳይመጣ ያገደዉን ኃጢአት በንስሐ ልናስወግድ ይገባል።

የእስራኤል ጾም በልማድና በግብዝነት የተሞላ ነበር። ይህ ነዉ የልቡናቸው መሻት እንዳይፈጸም አንቆ የያዘው። ጾም ዓላማ ሊኖረው የሚገባ ድርጊት ነው። የሚጾም ሰው በጾሙ አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ፤ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት እንዲደረግለትና ለልዩ ልዩ ዓላማ ሲጾም የጾሙ ማዕከላዊ ዓላማ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር ሊጣጣም ይገባል።

ሥርዓቱ ስለተደነገገ ብቻ የሚጾም ጾም አላማዉን ግብ ማድረግ አይችልም። ልማዳዊ ብቻ ስለሚሆንም ዋጋ አያስገኝም። በመጽሐፍ ቅዱስ የጾሙ ሕዝቦችንና ግለሰቦችን ታሪክ በምናይበት ጊዜ ለጾማቸው ዓላማ ነበራቸው።

በዘመነ አስቴር የነበሩ አይሁድ ከክፉ ሀማ ምክር ይድኑ ዘንድ /አስቴ. ፬፥፲፮/ ፣ የነነዌ ሕዝቦች ከቁጣ እግዚአብሔር ያመልጡ ዘንድ /ዮና. ፫፥፭/፣ እነ ዳንኤል ምስጢር እንዲገለጥላቸው /ዳን. ፲፥፫/ ጾመዋል። ስለዚህ እኛም በምንጾምበት ወቅት እግዚአብሔር በእኛና በእርሱ መካከል ያለውን የአባትነትና የልጅነት መንፈስ እንዲያጠናክርልን፣ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን፣ ቀሪው የሕይወት ዘመናችንን እንዲባርክልን፣ በጾማችን ወቅት ሀገራችንን እንዲጎበኝልን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲጠብቅልን፣ ለቤት ክርስቲያን መሪዎች ሰላም ፍቅርና አንድነትን አድሎ ሕዝቡን በአንድ ልቡና እንዲመሩልን የመሳሰሉ ዓላማዎች ሊኖሩን ይገባል።

ከዚህ ዉጪ በልማድ ብቻ የሚደረግ ጾም ዋጋ የማያስገኝ ከንቱ ነው። ቀዱስ ጳዉሎስ የምታደርጉትን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉ በማለት እንዳሳሰበን ጾማችንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሰረት ባደረገ ሁኔታ ብንጾም ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት ቸርነትና በረከትን ያሰጠናል በማለት ሊሆን ይገባል።

እስራኤል ከሌላው ጊዜ የጾማቸውን ወቅት የሚገልጠውና የሚያሳየው አስቀድመው በፍስክ ወቅት ይበሉት የነበራውን ነገር ትተው የምግብ ለውጥ ማድረጋቸው ብቻ ነው። ሌላ የሕይወት ለውጥ አይታይበትም። በቤተ ክርስቲያን ያለን ምእመናንም ጾማችንን በምናይበት ሰዓት ከዚህ የተለየ ሆኖ አናገኘውም። ከፍስኩ ወቅት ሥጋና የሥጋ ተዋጽኦዎችን እንመገብ የነበርን ሰዎች በጾማችን ትተነዋል ይሁን እንጂ በእርሱ ፈንታ ሥጋችንን ሊያዳብሩ የሚችሉ ምትክ ምግቦችን ምናልባትም በፍስኩ ወቅት በተሻለ ሁኔታ እንመገባለን። ያም ሆኖ ከምግብ ከመከልከል ዉጪ ሌላ ለዉጥ በሕይወታችን አይታይም። የጾም ወቅት ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ልናሳይ የሚገባበት ወቅት ነው።

የጾም ወቅት ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ለአንደበታችን ልጓም የምናበጅበት ወቅት ነው። ባልንጀራን የሚያሳዝን ሰዎችን የሚያስከብር ዓላማዊ ሕይወትን የሚያደፈርስ በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሊሆን የሚችል ንግግርን ከአንደበታችን ልናርቅ የሚገባበት ወቅት ነው። የጾም ወቅት ንግግርን ብቻ ሳይሆን የአሠራርም ጭምር ለውጥ የምናመጣበት ነው። አስቀድመን እንሠራቸው የነበሩ የኃጢአት ሥራዎችን ትተን አባቶቻችን ቅዱሳን አበውንና እናቶቻችንን ቅዱሳን አንስትን በቅድስና የምንመስልበት ነው። የጾማችን ወቅት ፈቃድ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን የምናስገዛበት መልካዊ ባሕርያችን የሚያይልበት ወቅት ነው።/፩ ቆሮ. ፱፥፳፮-፳፯/።

በአጠቃላይ እንደ እስራኤል ዘሥጋ ዓይነት ጾም ጾመን «ስለምን ጾምን አንተም አልተመለከትኸንም» በማለት እንዳናማርር ጾማችን የምሕረትና የቸርነት ፍሬያት የሚገኙበት እንዲሆን የአጿጿማችንን ሁኔታ ልናየውና ልንመረምረው ይገባል።

እግዚአብሔር አምላካችን በነብዩ በኤዪኤል አድሮ «ጾምን ቀድሱ» ብሎ እንደነገረን ጾማችንን ከአሕዛብ ልማድና ከግብዝነት አካሄድ ለይተን እግዚአብሔር የሚገኝበትና ወድዶ ፈቅዶ የሚቀበለው ጾም ልናደርገው ይገባናል።/ኢዮ. ፪፥፲፭/። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የድግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Written By: useducation
Date Posted: 3/18/2011
Number of Views: 16904

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement