View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው

(ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ አለማየሁ)

የጌታችን እና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ለማወቅ  የአምላክነትን የመለኮትንና የባህሪይን ትርጉምና ምሥጢር በትክክል መረዳት ያስፈልጋል:: ከዚህም ጋር አምላክ  ሰው የሆነበትን ምሥጢርና ምክንያት በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው:: አምላክ ማለት ፈጣሪ ገዥ  ፈራጅ መጋቢ ሠራዒ ከሃሊ ማለት ነው:: አምላክነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነም እግዚአብሔር ብቻ  በመሆኑ  እሱ ብቻ የባሕርይ አምላክ ይባላል::  ፈጣሬ ዓለማት አምጻኤ ዓለማት መጋቤ ዓለማት እሱ ብቻ ነው::  ከእግዚአብሔር በቀር አምላክነት የባሕርዩ የሆነ ማንም የለም:: ኢሳ ፵፭፥፳፩- ፳፪  ፩ኛ ቆሮ ፰፥፬-፮
ሌሎች የባሕርያቸው ባልሆነ ስያሜ አማልክት እየተባሉ ቢጠሩም “አማልክት ዘበጸጋ” የጸጋ አማልክት እየተባሉ ይጠራሉ:: አማልክት ዘበጸጋ ያልሆኑትም “አማልክት ሐሰት” ሐሰተኛ አማልክት ይባላሉ እንጂ ባሕርያዊ ከሃሊነትና መለኮታዊ ሥልጣን ፈጽሞ የላቸውም ::

ዘጸ ፯፥፩ :: ዘሌ ፲፱፥፬ :: መዝ ፵፱፥፩ , ፹፩፥፩-፯ :: ኢሳ ፵፥፲፰-፲፱  ሐዋ ፲፯፥፯-፳፱

የቅዱስ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክነት መገለጫው መለኮቱ ነው፤ መለኮት ማለትም ሥልጣን ልዩና ክቡር ስም፤ ከፈጣሪ በቀር ማንም ፍጡር ሊጠራበት የማይችል እግዚአብሔር ብቻውን ፈጣሪ ፥ ከሃሊ በቃሉ ፥ ገዥ አምላክ አማልክት እግዚአ አጋእዝት ንጉሠ ነገሥት፥ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው፥ ዘለዓለማዊ፥ ወጣኔ ኩሉ፥ ፈጻሜ ኩሉ፥ መላኤ ኩሉ ፥ምሉእ ውስተ ኩሉ መሆኑ የሚታወቅበት ሥልጣኑ ባህርየ መለኮት ነው::

መለኮት :- ቅድስት ሥላሴን አዋሕዶ እግዚአብሔርን አንድ አምላክ ሦስት አካላት የሚያሰኝ የአካል የግብርና የስም መሠረት ነው:: አካላት ከባሕርያቸው ከመለኮት ስምን ይነሳሉ እንጂ ባሕርየ መለኮት አይከፈልም:: ባሕርየ መለኮት ሳይከፈል ለእግዚአብሔር ሦስት አካላት ሦስት ስም ሦስት ግብር አለው:: የአካለ ሥላሴ የባሕርይ አንድነት ምሥጢርም በመለኮት ይገለጻል:: “እሉ ሠለስቱ አካላት ፍጹማን ዲበ መንበረ ስብሐት ወእኁዛን በጽምረተ አሐዱ መለኮት ዘውእቱ አሐዱ ብርሃነ ዘይሠርቅ እምኔሁ::”  ሥላሴ :- እሊህ ሦስቱ አካላት በጌትነት (በፈጣሪነት) በክብር ፍጹማን ናቸው : በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው :: ይኸውም ሦስትነት (ሥላሴ) ከእርሱ (ከመለኮት) የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው:: በዓለሙ ሁሉ ምሉዕ ነው:: እንዳለ ቅዱስ አግናጥዮስ (ሃይ አበው ዘአግና)

ባሕርይ:- የአካል የስምና የህላዌ ጥንት የግብር መሠረት ነው:: ባሕርየ እግዚአብሔር (ባሕርየ መለኮት) እንደ ፍጡር ባሕርይ ከአባት ወደ ልጅ  አይከፈልም ፤ አይቀዳም::  በመሆኑም አብ ወልድን ይወልደዋል ብሎ አይቀድመውም  አይበልጠውም ማለቱ ባሕርየ መለኮት ፈጽሞ የማይከፈል ባሕርይ መሆኑን ያረጋግጣል::  የማይከፈለው ባሕርየ መለኮት ግዙፉንና ረቂቁን የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም እም ሀበ አልቦ ፈጥሮ መግዛት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣንና ከሀሊነት ነው:: መጽ.ጥበ ፲፪፥፲፫-፲፮:: ዘፍ ፩፥፩ ዮሐ ፩፥፩-፫

ቃል ሥጋ ኮነ

የምሥጢረ ሥጋዌ ጥንቱና መሠረቱ “ቃል ሥጋ ኮነ” ነው:: ጥንትና ፍጻሜ የሌለው ጥንትና ፍጻሜ እሱ ራሱ የሆነ ብሉየ መዋዕል አካላዊ ቃል በፈቃዱ ከልዕልናው  ወርዶ ባሕርየ ሰብእን ከአካሉ አዋሕዶ ለመለኮታዊ ባሕርዩ በሚገባ ልደት ተወልዶልናል:: ለዚሁም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ (ተፈጠረ) ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለእርሱ አልሆነም :: …… ቃልም ሥጋ ሆነ :: ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ  በእኛ አደረ :: ….. ” ብሎአል:: ዮሐ ፩፥፩-፲፬ ሁሉን የፈጠረ ሁሉ በእርሱ የሆነ አምላክ ወልደ አምላክ ሥግው ቃል በተለየ አካሉ ጠባይዓተ ሥጋንና ባሕርያተ ነፍስን ገንዘብ አድርጎ ንጽሕተ ንጹሐን  ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ለእመ አምላክነት መርጦ በክበበ ትስብእት ሲወለድ የተዋሕዶው ምስጢር ሰው ሆኖ የመወለዱ ነገር ምን ይረቅ ምን ይደንቅ ይባላል:: (፩  ጢሞ ፫፥፲፮) ለዚሁም አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰውሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይረቃል ተብሎአል::  አምላክ በሥጋ ሲወለድ አካለ መለኮት ወደ አካለ ሥጋነት ወደ ግዘፍ ሳይቀየር አካለ ሥጋ  ወደ አካለ መለኮትነት ወደ ርቀት ሳይለወጥ አንዱ ባሕርይ ወደ ሌላ ከዊንነት ሳይለወጥ ሳይፋለስ ሳይበረዝ ሳይቀላቀል  በፍጹም ተዋሕዶ ወልድ ዋሕድ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎአል:: ቅድመ ሥጋዌ ወልደ አብ የተባለው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ቃል ሥጋ ኮነ ከተባለበት ዓረፍተ ዘመን ጀምሮ ሥግው ቃል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎአል:: (“አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” መዝ ፪፥፮-፯: “ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው: የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል::” ሉቃ ፩፥፴፭)
የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር ዋና ምክንያት በበደሉ ምክንያት ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ተፈርዶበት በፍዳ ተይዞ በግብርናተ ዲያቢሎስ ስር ወድቆ ፥ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረውን የሰው ዘር ወደ ጥንተ ክብሩ ይመልስ ዘንድ ነውና ኂሩቱና መሐሪነቱ ከፈታሒነቱ ጋር በማይቃረን ጥበቡ ሰው ሆኖ ሰውን ይዋጅ ዘንድ ወዶ ፈቅዶ ተወልዶልናል:: ገላ ፬፥፫-፭:: ሮሜ ፭፥፮-፲፯::

•    የመወለዱ ምክንያት ሰውን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ነውና አምላክና ሰው በመሆኑ አማኑኤል ተብሏል::
•    ንጉሠ ነገሥት እግዚአ አጋእዝት ካህን ሊቀ ካህናት በመሆኑ ክርስቶስ መሲሕ ተብሏል:: 
•    የዓለም መድኅን በመሆኑ ኢየሱስ ተብሏል:: እነዚህም ስሞች ስመ ሥጋዌ ይባላሉ :: “አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ”  የመባሉ ምሥጢር ዕጹብ ድንቅ ረቂቅ ምጡቅ የሚያሰኘውም ባሕርየ መለኮት ከባሕርየ ሥጋ ሳይቀላቀል በአካለ ቃልና በአካለ ሥጋ ውላጤ ሳይኖር በፍጹም ሰውነትና በፍጹም አምላክነት መወለዱ ነው:: በዚህ ምሥጢር ተዋሕዶ አካልን ከባሕርይ ባሕርይን ከአካል ሳይቀላቅሉ ለይቶ አጥርቶ ማወቅ የክርስቲያን ሁሉ የእምነት ግዴታ ነው:: ይህን ጠንቅቆ ማወቅ ካልተቻለ ባሕርይ ያለአካል አካል ያለባሕርይ ህልውና የለውም ወደሚል መደምደሚያ ይወስድና “ሥላሴ ሰው ሆኑ” የሚል የምሥጢር ተፋልሶና የእምነት ሕፀፅ ያስከትላል:: ትክክለኛው ግን አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ባሕርየ ሰብእን ተዋሕዶ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ መወለዱን አምላክ ወልደ አምላክ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ ነው:: ይህን ጠንቅቆ ለማወቅም የሦስቱም አካላት የግብር ከዊንነት ለይቶ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል:: (ሃይማኖተ አበው ዘአግናጥዮስን ይመልከቱ)

 ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ አምላክ ሰው የመሆኑ ምሥጢር የተፈጸመው በአካለዊ ቃል ብቻ ነው::  የሥጋዌ ነገር ለአካለ አብና ለአካለ መንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ አይሰጥም:: ዮሐ. ፩፥፲፬:: ለመንግሥቱ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ለማዳን በሰጠው ተስፋ ድኅነት መሠረት ተወለደ ሲባልም የባሕርይ አምላክነቱንና ሥጋዊ ልደቱን የሚያረጋግጥ ትንቢት ተነግሮለት ሱባኤ ተቆጥሮለት ፈጣሪነቱንና የባሕርይ አምላክነቱ በቅዱሳት መጻሕፍት ተረጋግጦለት እንጂ ልደቱ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አልነበረም:: እግዚአብሔር ወልድ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የእግዚአብሔር ነቢያት ከተናገሩለት ትንቢት ጥቂቱን እንመልከት::

  • “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወልድም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች::” ኢሳ ፯፥፲፬
  • “ሕፃን ተወልዶልናል:: ወልድም ተሰጥቶናል:: አለቅነቱም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል::” ኢሳ ፱፥፮
  • “ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ::ከጥንት ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማነው? ያሳየሁም የተናገርኩም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? :: ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም:: እኔ ድንቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ:: ከእኔም በቀር ማንም የለም:: ..” ኢሳ ፵፭፥፳፩-፳፪
  • “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ አለቃ (ገዥ) የሚሆን ይወጣልኛልና::” ሚክ ፭፥፪


የትንቢቱ ፍጻሜ

    እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሰጠው ተስፋ ድኅነት በደረሰ ጊዜ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ተወለደ ሲባልም ለአካለዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ሁለት ልደት አለው ማለት ነው:: ይኸውም:-

1ኛ ዘመናት የማይቆጠሩለት አዝማናት የማይወስኑት ብሉየ መዋዕል አካለዊ ቃል ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ያለ እናት በቃልነት አምሳል ተወልዶ ወልደ አብ የተባለበት ቀዳማዊ ልደቱ::

2ኛ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ በተናገሩለት ትንቢት መሠረት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ያለ አባት በመወለድ ወልደ ማርያም የተባለበት ልደትነው:: ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፈጣሪዋን በመውለዷ ምክንያት እመአምላክ ወላዲተ ቃል ድንግል ወእም ያሰኘበት ደኃራዊ ልደቱ ነው:: “ቀዳማዊ ልደቱ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደቱ” እንዲል::

አካላዊ ቃል ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደበት ቀዳማዊ ልደቱ እንደ ደኃራዊ ልደቱ ዘመን የሚቀመርለት ሱባኤ የሚቆጠርለት ትንቢት የሚነገርለት ባይሆንም ባሕርይ ዘእም ባሕርይ መወለዱን በማረጋገጥ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ገልጸዋል:: ለምሳሌም መዝ. ፪፥፯ , ፻፱፥፪ , ሉቃ ፫፥፳፩-፳፪, ዮሐ፩፥፳፱, መመልከት ይቻላል:: የባሕርይ አምላክ ኢየሱ
ስ ክርስቶስ በተነገረለት ትንቢት መሠረት ተወልዶ ዓለምን ማዳኑን መጻሕፍተ ሐዲሳት አምልተው አስፍተው ጽፈዋል:: ከብዙ በጥቂቱ :-

  • “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ (ተፈጠረ) ከሆነውም  (ከተፈጠረውም) አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም' (አልተፈጠረም) ….. ቃልም ሥጋ ሆነ:: (ሰው ሆነ) ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ:: … ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን:: ” ዮሐ፩፤፲፬ ዘፍ. ፩፥፲፫
  • “ዘመኑ በደረሰም ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም ላከ ከሴትም ተወለደ በኦሪትየታዘዘውን ሕግም ፈጸመ በኦሪት የነበሩትን  ይዋጅ ዘንድ እኛም የልጅነትን ክብር እናገኝ ዘንድ:: ገላ ፬፥፬-፭
  • “... ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን::” ሮሜ ፱፥፭, ኢሳ ፵፭፥፳፩-፳፪
  • “በእውነት ታላቅ ነው የአምላክ ምሥጢር አምላክ በሥጋ ተገለጠ:: …” ፩1ኛ ጢሞ ፫፥፲፮ ( ይህን ኃይለ ቃል ለማግኘት በ1879 ዓ.ም የታመውን የጥንቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስና (king james Version የእንግሊዘኛ  መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት ያስፈልጋል)
  • “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ::” ሐዋ ፳፥፳፰
  • “የእግዚአብሔር ልጅ (እግዚአብሔር ወልድ) ሰውሆኖ ዕውቀትን እንደሰጠን እናውቃለን:: እውነተኛ እግዚአብሔርን እናውቀው ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አለን:: እሱም በእውነት እግዚአብሔር ነው:: ”  ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳ ፊሊ ፪፥፭-፯
  • “... ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘለዓለምእስከ ዘለዓለምድረስ ሕያው ነኝ”  ራእ ፲፯፥፲፰ ዘጸ ፫፥፲፫-፲፬ ዕብ ፲፫፥፰

እንግዲህ ጥልቅና እሙን ከሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ውቅያኖስን በጭልፋ ያህል አቅርበናል:: ለወደፊቱ ግን ዕድሉ ከገጠመን በስፋት በምልአት ለመጻፍ እንሞክራለን:: እስከዚያው ወልድ ዋሕድ በምትል የከበረች ሃይማኖታችን እስከመጨረሻው ያጽናን አሜን !

ምንጭ: ፍኖተ ሰላም መጽሔት ጥር ፲፱፻፺፱  ዓ/ም

 


Written By: host
Date Posted: 4/16/2011
Number of Views: 8778

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement