View in English alphabet 
 | Wednesday, May 1, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ቆይታ ከመላከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ ጋር

መላከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ ከማኅበረ ቅዱሳን መስራች አባላት አንዱ ሲሆኑ የመጀመሪያው የማኅበሩ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል። ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ የደቡብ ምሥራቅ፣ እና የመካከለኛው አሜሪካ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት የራቸስተር ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የዚህ ዕትም የሐመረ ኖኅ እንግዳ አድርገናቸዋል፤ ተከታተሉን።


ሐመረ ኖኅ
፦ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የት እና እንዴት ጀመሩ?

መልአከ ጽዮን፦ በቅድሚያ ወደ መልሱ ከመሄዴ በፊት በክርስትና ሕይወት አገልግሎት የፈጸሙ ሰዎች መንፈሳዊ አገልግሎታቸው የሚገለጠው ከሞቱ በኋላ በሌሎች ሰዎች አማካይነት ነው። ምክንያቱም፦
1ኛ) ሥራውን የሚሠራው ልዑል እግዚአብሔር ስለሆነ ሊመሰገን የሚገባውም እሱ በመሆኑ፣
2ኛ) ሠሪዎቹ በውዳሴ ከንቱ እንዳይወድቁ የእግዚአብሔር ጥበቃ በመሆኑ፣
3ኛ) አንድ ሰው እስኪሞት መጨረሻው ምን እንደሚሆን ስለማይታወቅ፣
በእኔ እምነት በማኅበሩ ምሥረታ እና በአገልግሎት ላይ የተፈጸመውን ሁሉ ሌሎች ቢመሰክሩ ይመረጣል በሚል ራሴን ከሚዲያ ሳሸሽ ኖሬያለሁ ይሁን እንጂ መታዘዝ ከመስዋእት ይበልጣልና የሐመረ ኖኅን ትዕዛዝ እና ጥያቄ በመቀበል መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የጀመርኩት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ ደብረ መድኃኒት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው። ይኸውም አባቴ ቄስ ወርቁ ዳርጌ እና አያቴም መምሬ ወልደ ጊዮርጊስ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በመሆናቸው እኔንም ገና የ7 ዓመት ልጅ እያለሁ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የድቁና ማዕረግ እንድቀበል አደረጉ። ከዚያም በድቁና በማገልገል ላይ እያለሁ በ1974 ዓ.ም. በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና የካህናት ማሰልጠኛ ገብቼ ከታላቁ አባት ከብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተምሬያለሁ:: ይህ ሕይወቴን የለወጠበት እና የቤተ ክርስቲያኔን አገልግሎት በተገቢው መንገድ የተረዳሁበት ዘመን ነበር ማለት እችላለሁ። ከዚያ ቀጥሎም በደብራችን ሰ/ት/ቤት ካቋቋምን በኋላ  በሰላሌ አውራጃ በፍቼ ከተማ ዙሪያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በአራተ ማርያም፣ ኪዳነ ምህረት እና መድኃኒዓለም ሰ/ት/ቤት የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት ሰጥቻለሁ። በአ/አ ሀገረ ስብከትም በምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም በተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ደብር ሰበካ ጉባኤ አገልግሎት ገብቼ ሰጥቻለሁ።

ሐመረ ኖኅ፦ የማኅበረ ቅዱሳንን አመሰራረት እንዴት ያስታውሱታል?

መልአከ ጽዮን፦ ማኅበሩ የተመሰረተው በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። በእርግጥ ሰዎች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ያውም በተናቁት እና  እዚህ ግቡ በማይባሉ ሰዎች ልዑል እግዚአብሔር ሥራ ሲሠራ እንመለከታለን። ስለዚህም በእኔ እምነት ማኅበረ ቅዱሳን ስያሜ ሳያገኝ ሥራ መሥራት የጀመረው በ1977 ዓ.ም. ነው፤ በ1984 ዓ.ም. ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ እውቅና ያገኘበት ዘመን ነው። 

ከማኅበረ ቅዱሳን ምሥረታ ጀምሮ አሁን እስካለው አገልግሎት እልፍ አዕላፍ አባላት በተለያየ ዘመን እና ስፍራ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በማኅበሩ አገልግሎት፣ በግቢ ጉባኤ፣ በወረዳ ማዕከላት፣ በንዑስ ማዕከላት በመሳተፍ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያከናወኗቸው ተግባራት በብዙ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚጻፍ እና ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ነው።

ከሁሉ በፊት ቅድመ ማኅበረ ቅዱሳን (ከ1977 ዓ.ም. በፊት) ለማኅበሩ መመሥረት የነበሩት ነባራዊ ሁኔታዎችን ስንቃኝ፦ 
•    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ኖሮት በዩኒቨርሲቲ እና በኮሌጆች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን እምነት እና ሥርዓት በማስተማር እና አገልግሎት እንዲሰጡ በማስተባበር የሚመራ አካል አለመኖሩ፣
•    በወቅቱ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እግዚአብሔር የለም የሚለው ንድፈ ሀሳብ በግል የሚሰበክበት እና ትውልዱ ሁሉ እምነቱን  እና  ሥርዓቱን የዘነጋበት የረሳበት ወቅት መሆኑ፣
•    በኢትዮጵያ የነበረው የወጣቶች ማኅበር “አኢወማ” ብቻ እንዲጠናከር እንጂ በሕግ ሌላ ማኅበር እንዲቋቋም ያልተፈቀደ በመሆኑ፣
•    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኋላ ቀር፣ ጎታች፣ ፊውዳል አድኃሪያንን ወክላ የምትበዘብዝ ተደርጎ የሚወሰድበት  ወቅት በመሆኑ፣
•    የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሆኖ ነጠላ ለብሶ ቅዳሴ ማስቀደስ፣ ዲያቆንም ሆነ ካህን መሆን እንደ ኋላ ቀር የሚቆጠርበት ዘመን በመሆኑ፣
•    በአንፃሩ በወቅቱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆን እንደ ዘመናዊ እና ትክክለኛ እምነት ተከታይ ሆኖ የሚቆጠር በመሆኑ፣
•    በተለይ በግቢ ውስጥ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም ማለትም የጾም ምግብ እንኳን ባለመዘጋጀቱ ምክንያት ተማሪዎች ጾም መጾም አለመቻላቸው፣
•    በሌላ በኩል ደግሞ በ1977 ዓ.ም. ከየክፍለ ሀገሩ በሰ/ት/ቤት ሲማሩ የነበሩ በዩኒቨርሲቲው መርሐ ግብር መግባታቸውና በእግዚአብሔር ፈቃድ መገናኘታቸው፣
•    ከዚያም በ1977 ዓ.ም. በተለይ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና የካህናት ማሰልጠኛ ሰልጥነው የወጡት ወደ ዩኒቨርሲቲ መርሐ ግብር መግባታቸው እና ከብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር እንዲገናኙ ድልድይ መፍጠራቸው በምሥረታው ወቅት የነበሩ ነባራዊ ሁኔታዎች ናቸው።

አጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩና ከነዚህም ጋር ተጓዳኝ የነበሩ ጉዳዮች ስለነበሩ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሆኖ ማኅበር መመሥረት የማይታሰብ ነበር። ነገር ግን ፈቃደ እግዚአብሔር በደረሰ ጊዜ ማኅበሩ በእግዚአብሔር ቸርነት እንዲመሠረት አደረገ።

ከ1977 ዓ.ም. – 1984 ዓ.ም. ያለው የማኅበሩ ቅድመ ምሥረታ ሲቃኝ ለማኅበሩ ምሥረታ ዐበይት ምክንያት የሆኑትን እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።

ሀ) በአ/አ ዩኒቨርሲቲ ትንሿ የግቢ ጉባኤ የጽዋ ማኅበር መመሥረት፦ በ1977 ዓ.ም. በአ/አ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ስድስት ኪሎ ሕንጻ ቁጥር 505 ዶርም ቁጥር 028 ውስጥ ታህሳስ 19 ቀን በቅዱስ ገብርኤል ስም በአምስት ወጣቶች የጽዋ መርሐ ግብር ተመሥርቷል።


ለ) በ1977 ዓ.ም. በወጣቶች ወደ መተከል እና ጋምቤላ የተደረገው የከፍተኛ ት/ት ተቋማት የመንደር ምሥረታ ዘመቻ፦ በዘመቻው የየተቋማቱ ተማሪዎች እንዲገናኙ እና በየግቢዎቻቸው ስላሉት መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ሀሳብ ለመለዋወጥ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በዚህ ዘመቻ በተለይ በመተከል በዕለተ ሰንበት ከአንድ ትልቅ ዋርካ ሥር በግቢው ሲፈጸም የነበረው የጸሎት መርሐ ግብር እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሳይቋረጥ ይከናወን ነበር። ይህም ለዛሬው የማኅበረ ቅዱሳን መመሥረት እና ህልውና አስተዋጽዖ ከነበራቸው ትዝታዎች አንዱ ነው።

ሐ) የመጀመሪያዎቹ የቅድመ ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ተመራቂዎች ልዩ መርሐ ግብር፦ በ1980 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አጠገብ በሚገኘው በምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም በተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፣ የቀድሞው ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም የበላይ ጠባቂ፣  ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ኤፍሬም የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የደመቀ የምረቃ መርሐ ግብር ተፈጽሞ ቤተ ክርስቲያን በብጹዓን አባቶች አማካይነት አደራዋን ሰጥታለች። ተመራቂዎችም አደራውን በደስታ ተቀብለዋል። ይህም ከምረቃ በኋላ አባላትን ዳግመኛ ወደ አገልግሎቱ ስቦ የሚያመጣ ነበር።

መ) በ1983 ዓ.ም. ወደ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የተደረገ ዘመቻ፦ በዚሁ ዓመት በመንግሥት ትዕዛዝ በአገሪቱ በሚገኙ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ብላቴ የማሠልጠኛ ካምፕ እንዲገቡ ሲሆን ከአገሪቱ ሁሉም ተቋማት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ሁሉ በዚህ ስፍራ እንዲሰበሰቡ ተደረገ። በየግቢዎቻቸው የጀመሩትንም መንፈሳዊ መርሐ ግብር በአንድነት ለማካሄድ እና ለመመካከር ዕድል አገኙ። ዓበይት በዓላትን ለምሳሌ የትንሳኤ እና የእመቤታችንን የልደት በዓል በማክበር የተጀመረው መርሐ ግብር ተጠናክሮ ወደ ሙሉ የግቢ ጉባኤ መርሐ ግብር አደገ። በወቅቱ ከዘመቱት ተማሪዎች መካከል ቀደም ብለው በዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛ ከብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የተማሩ ምሩቃን በመኖራቸው በዝዋይ ይሰጥ የነበረውን ኮርስ በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ የሁሉም ተቋማት ተማሪዎች ሊሰጥ ቻለ። የመንግስት ለውጥ ሆኖ ወታደራዊ ስልጠናው ሲበተን ተማሪዎች ወደየግቢዎቻቸው ሲመለሱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን ለመቀጠል እና በቅ/ሚካኤል መታሰቢያነት የዝክር መርሐ ግብር ለማድረግ ብጽዓት ገብተው ተለያዩ።

ሠ) በ1983 መጨረሻ እና በ1984 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በምሥረታው ወቅት የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት፦ በ1983 ዓ.ም. ሐምሌ 19 ቀን በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የሙት ዓመት መታሰቢያ ቀደም ሲል በግቢ ጉባኤ ተምረው የተመረቁ፣ በግቢ ጉባኤ በመማር ላይ ያሉ እና በዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛ ገብተው የወጡ አባላት በአንድነት በተገናኙበት ወቅት ቀደም ሲል በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተጀምሮ የነበረው መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በወቅቱ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ እና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል አማካኝነት መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር የሚያስተባብሩ የኮሚቴ ሰዎችን መርጦ ተለያየ። ጉባኤውም በመስከረም 1984 ዓ.ም. በተጠናከረ መልክ ሁሉም እንዲገናኝ እና አንድ ማኅበር እንዲመሠረት ወሰነ፣ በዚህ የቀጠሮ ቀንም በጉባኤው ላይ ሦስት አካላትን እናገኛለን፦

ሀ) በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ገብተው ተመርቀው የወጡ የዝዋይ ደቀ መዛሙርት ማኅበር አባላት፣
ለ) ከግቢ ተመርቀው ወጥተው በማርያም ጽዋ ማኅበር ስም ይሰባሰቡ የነበሩ አባላት፣
ሐ)ከብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ገብተው ከወጡ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በማኅበረ ሚካኤል ስም ያሉ አባላት።

ከሦስቱም አካላት ሰዎች ተመርጠው አንድ አካል፣ አንድ ደንብ እንዲቀርጹ እና በተቀናጀ በተዋሐደ መልኩ አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፣ የተመረጡት አባላትም ውህደቱን እንዲያፋጥኑ እና የማኅበሩን ደንብ እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በዚህ መሠረት ውህደቱ እጅግ እልክ በሚያስጨርስ ሁኔታ በአዳር ፕሮግራም በመወያየት እና በመመካከር ስምምነት ላይ ተደረሰ።

ይህንንም በወቅቱ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ የበላይ ኃላፊ በሆኑት በብጹዕ አቡነ ገብርኤል አማካይነት በተለይ የማኅበሩን ስያሜ አስመልክቶ የተለያዩ አማራጮች ቀርበው ነበር። ለአብነት ያህልም ማኅበረ ማርያም፣ ማኅበረ እስጢፋኖስ፣ ማኅበረ ጎርጎርዮስ፣ በኋላም አባላቱ የተገናኙበትን ዓላማ መሠረት በማድረግ ማለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስተ ቅዱሳን ሰለሆነች፣ ቅዱስ ሚካኤልም ሆነ በየግቢው በጽዋ ማኅበር የሚደረገው ቅዱሳን ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት የሚዘከሩት ሁሉ ቅዱሳን በመሆናቸው የተዋሕዶ እምነትን የሚያስፋፋ እና ቅዱሳንን የሚያዘክር እንዲሆን ስያሜው ማኅበረ ቅዱሳን ይሁን የሚለው ሃሳብ ቀርቦ የሁሉም ሰው ልቦና በደስታ ተቀብሎት ሰለጸደቀ ወደ አገልግሎቱ ተሰማርቷል።

ሐመረ ኖኅ፦ በምሥረታው ወቅት እና ከምሥረታው በኋላ የእርስዎ ድርሻ ምን ነበር?

መልአከ ጽዮን፦ ሥራውን የሚያከናውነው ልዑል እግዚአብሔር ነበር፣ ምህረቱን እና ቸርነቱን ከኔ ከባርያው ሳያርቅብኝ ፈቃዱ ሆኖ  በዕድሜዬ ከምሥረታው ጀምሮ እስከ አሁን በአገልግሎት አልተለየሁም። ልዑል እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ሰው የማያውቃቸው ብዙ ወንድሞች እና እህቶችን መሣሪያ አድርጎ ሥራውን የሠራው እሱ ነው። ለማኅበሩ በተለያየ ዘመን እና ቦታ በአካል የሞቱለት የታሰሩ የተሰደዱ ከሥራቸው የተባረሩ እና ልዩ ልዩ ጽዋትወ መከራ የደረሰባቸው አባላት እጅግ ብዙ ናቸው። ሁሉም የየራሱን አሻራ ጽፎ ለታሪክ እንደሚያስቀምጠው ይጠበቃል። ከዚሁ አንጻር የእኔ ድርሻ  ከ1977 ዓ.ም. ከዶርም የጽዋ መርሐ ግብር ጀምሮ በመተከል ሰፈራ ጣቢያ ዛፍ ጥላ ሥር፣ በ6 ኪሎ  ግቢ ጉባኤያት፣ በተምሮ ማስተማር ዛፍ ጥላ ሥር ከዚያም በየመኖሪያ ቤታችን አዳር መርሐ ግብር ተሳትፌያለሁ።

ማኅበሩ ከምሥረታው በፊት፣ ሲመሠረት እና ከምሥረታው በኋላ በተሰጠኝ ኃላፊነት እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ማኅበሩ በአባቶች ዕውቅና እንዲያገኝ፣ የማኅበሩ አገልግሎት መዋቅር እንዲጠናከር፣ በማኅበሩ ላይ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚቀርበውን ፈተና ለማሸነፍ ከወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም ከአባቶቼ ጋር በመመካከር ከኔ የሚጠበቀውን ለማድረግ ሞክሬያለሁ። በተለይ በሰሜን አሜሪካ ያለውን አገልግሎት መዋቅር እንዲዘረጋ እና እንዲጠናከር የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ።

በ1979 እና 1980 ዓ.ም. ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እኔ ያወቅኩትን እንዲያውቁ ከብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር አገናኝቻቸዋለሁ። በ1980 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹን 12 ሠልጣኞች ወስጄ ዝዋይ አድርሻለሁ።

በተለይ ሦስቱ አካላት አንድ ሆነው ማኅበረ ቅዱሳን የሚለውን ስያሜ እንዲያገኙ በተደረገው ጥረት ከወንድሞቼ እና እህቶቼ ጋር የበኩሌን ድርሻ አበርክቻለሁ። በምሥረታው ወቅትም በተመረጡት ኮሚቴዎች ሁሉ ተመርጬ አገልግያለሁ። እስከ 1984 ባሉና  ከምሥረታው በኋላም ከ1984 እስከ 1991 ዓ.ም. በማኅበሩ ሰብሳቢነት የተጣለብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ሞክሬያለሁ። ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን አሜሪካን ማዕከል ለአራት አመታት በማዕከሉ ሰብሳቢነት አገልግዬ ከአራት ዓመታት በኋላም አሁንም በድጋሚ የሰሜን አሜሪካ ማዕከል ሰብሳቢ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ።

ሐመረ ኖኅ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።  ያከናወናቸውን ተግባራት ካነገበው አጠቃላይ ዓላማ  አንፃር እንዴት ይመዝኗቸዋል?
 
መልአከ ጽዮን፦ ማኅበሩ በበኩሌ ካነገበው አጠቃላይ ዓላማ አንፃር ስመዝነው፣ በእግዚአብሔር ቸርነት ከኔ ትውልድ በኋላ ሊፈጽም ይችላል ብዬ የምመኘውን ተፈጽመው ተመልክቼ የተደሰትኩባቸው ሲኖሩ፣ በኔ በደካማው ዓይን ሊያከናውናቸው እና ሊታወቅባቸው ይገባል የምላቸው አንዳንድ ተግባራት ላይ ደግሞ የዘገየበትን ሂደት አያለሁ።

ማኅበረ ቅዱሳን ያነገበው የመጀመሪያ ዓላማ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅ የስም እና የልምድ ክርስቲያን መሆኑን ትቶ ክርስትናን በሕይወት በመኖር የመንግሥተ ሰማያትን ክብር ለመውረስ መዘጋጀት ዋናው ሲሆን ማኅበሩ ትምህርተ ወንጌልን፣ ተዋሕዶ ሃይማኖትን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን  በማሳወቅ በሕይወት እንዲተገብሩ በማድረግ ሰፊ ተግባራትን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ትውልዱ የእምነቱ ተረካቢ እንዲሆን ማዘጋጀት እና የማንነት መታወቂያው የሆነውን ሃይማኖቱን አውቆ ጠብቆ የማስጠበቅ፤ ከውስጥም ከውጭም ያለውን ፈተና እና ጠላትን በመከላከል ይህንንም ቤተ ክርስቲያንን ከሥር ነቅለው ለማጥፋት ከሚጥሩ የተሐድሶ መናፍቃን ጀምሮ  ከውጭ በገሃድ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ለማጥፋት ከሚረባረቡት ክፍሎች ጋር ተፋጦ አንዳንዴም ብቻውን በመፋለም ላይ የሚገኝ ነው። ብዙ አገልግሎት የመፈጸሚያ ጉልበቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን ሁሉ ይሻሙታል፤ አንዳንዴም ጠላት እየቀደመ  የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሕልውና እያናጋ የማኅበሩንም አገልግሎት ለማደናቀፍ ጉሮሮ ለጉሮሮ የመተናነቅ ያህል ተግባር ይፈጽምበታል።

ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያን ገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች ተጠብቀው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማደረግ ላይ ይገኛል፤ ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የምርምር እና የጥናት ምንጭ በመሆኗ ይህ በስፋት ያልተሰራበት ወደ ፊት ግን ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ የሚገባው ዘርፍ ነው። የቤተ ክርስቲያን እምነት ቀኖና  እና ትውፊት እንዲጠበቅ እና ለትውልድ እንዲተላለፍ ይህም ተግባር የማኅበሩ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተግባር እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር በመንፈሳዊ እና በዘመናዊ መሳሪያዎች እንዲደራጅ፣ በመንፈሳዊ እና በዘመናዊ ት/ት የሠለጠኑ ባለሙያዎች እንዲበዙ በማድረግ፣ ብጹዓን አባቶች፣ ካህናት እና ምዕመናን ያካተተ በንቁ እና በጉልህ የሚሳተፉ የቤተ ክህነት አባላትን ማፍራት ማኅበሩ በዐብይ ትኩረት ሊሰራው የሚገባው ጉዳይ ነው።

በተለይ ሁልጊዜ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኝነት እና የመፍትሔው አካል መሆን ያስፈልጋል ምክንያቱም ከውጭ ሆኖ ብዙም መፍትሔ ማምጣት አይቻልምና በውስጥ ገብቶ፣ ሆኖ በመገኘት ግን መፍትሔ መስጠት ይቻላል። በዚህ በኩል ማኅበሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ ማኅበሩ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽመው በልዑል እግዚአብሔር መሪነት በመሆኑ በሁለት አሥርት አመታት ውስጥ ማኅበሩ ዓለም አቀፋዊ ሆኖ በአገር ውስጥ እና በውጭ ሰፊ መዋቅር ዘርግቶ በማስተባበር ከውስጥ አባላቱን ለአገልግሎት በማሰለፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመናድ እና ለማዳከም የሚረባረቡትንም ከውስጥ እና ከውጭ በመከላከል ጉልህ የሆነ አሰተዋጽዖ አበርክቷል።

ማኅበሩ ዓላማውን አንግቦ ተግባራቱን መፈጸሙና በሕሊናዬም ሁሌ የሚመጡ ሦስት ዐበይት ሂደቶች ሚዛናቸውን ጠብቆ መጓዝ የማኅበሩ ሥራ ምንጊዜም የልዑል እግዚአብሔር ሥራ መሆኑን የሚያረጋግጥና በአድናቆት የሚያስገርም ነው። ይኸውም፦ 

1ኛ) እንደ ሕጉ እና ወጉ ደንብ ቀርጾ፣ ዓላማ ሰጥቶ፣ በዚህ በኩል ሂዱ ብሎ  የሚመራ እና መነሻው መሆን ያለበት ከበላይ  ነው። ይህ ስብስብ በአብዛኛው ወጣቶች የተሰባሰቡበት እንደመሆኑ ከባህሪም አንጻር ስሜታዊነት እና ችኩልነት የሚንጸባረቅበት በሆነ ነበር ነገር ግን ደንብ ቀርጾ ሁሉንም ይዞ ወደ ቤተ ክህነት መግባት ታላቅ ምሥጢር ነው። ከበላይ ሳይጠብቅ ይህን ብናቀርብ በመዋቅርም ሆነ  በአገልግሎት ይህ ቢሆን ይጠቅማል ሕገ ቤተ ክርስቲያንንም ጠብቆ መሄድ ይኖርበታል በማለት ተጨንቆ  እና ተጠቦ ራሱን በመግዛት ይህንን ከበላይ አካላት ሊፈጸም የሚገባውን ተግባር ራሱ አከናውኗል።

2ኛ) የማኅበሩ ጠላቶች የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ናቸው። ስለዚህም ከነዚህ ጋር ታላቅ ተጋድሎ እየፈፀመ መረጃዎችን በተጨባጭ አሰባስቦ ለሊቃውንት ጉባኤ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ እያቀረበ ውሳኔ እንዲያገኝ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱንም የማኅበሩንም ህልውና ጠብቆ ብዙ ተግባራትን መፈጸሙ የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ብዛት ነው ።

3ኛ) ዛሬ እንኳን በማኅበር ሁለት እና ሦስት ሰው ሆኖ መጓዝ በሚከብድበት ጊዜ ይህ ሁሉ እልፍ አእላፍ የማኅበሩ አባላት በቋንቋ፣ በዘር፣ በቦታ በማይገናኙበት ሁኔታ አንድ ሆነው፣ ዓላማውን ተገንዝበው፣ ወደው ፈቅደው በተግባር ላይ ማዋላቸው፣ በሚገጥማቸውም ፈተና ሁሉ ጸንተው መጓዛቸው እጅግ የሚያስደንቅ ነው።ሌላው ማኅበሩ ወገናዊነቱ የቤተ ክርስቲያን እንጂ የማንም የምንም ወገን መሣሪያ ሆኖ አያውቅም ወደ ፊትም አይሆንም።

ሐመረ ኖኅ፦ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል የረጅም እና የአጭር ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ምን ናቸው?

መልአከ ጽዮን፦ የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ከተቋቋመ ገና 12 ዓመቱ ነው። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ጥቂት የማይባሉ መንፈሳዊ አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ይገኛል። ሰሜን አሜሪካ በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት አንጻር ሲታይ ባህሪው፦

1)    የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሀገር ውጭ በስደት፣ በዲቪ ሎተሪ፣ በስራ፣ በት/ት እና በልዩ ልዩ  ምክንያት በብዛት የሚኖርበት ሀገር በመሆኑ፣

2)    ቤተ ክርስቲያን  3 አህጉረ ስበከት ብታዋቅርም መዋቅሯ ገና እስከ አጥቢያ ድረስ ተዋቅሮ በማዕከላዊነት የምትመራበት ሁኔታ ገና ያልተመቻቸ መሆኑ፣

3)    የአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን ቀድመው ስለመጡ በፈቃዳቸው በሀገሩ ካለው “የቤተ እምነት” መብት አንጻር አጥቢያቸውን ያቋቋሙ በመሆኑ እና ይህንም የሰበካ ጉባዔ በቃለ አዋዲው ለመምራት ብዙ መሟላት የሚገባቸው ተግባራት መኖራቸው፣

4)    በተለይ የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚ ኃይሎች ዋና ምንጫቸው በዚህ  የሚገኝ በመሆኑ፣

5)    የአሜሪካ ሲኖዶስ በሚል ሌሎች አባቶች የሚገኙበት እና እነዚህንም የሚደግፉ እና የሚከተሉ ምዕመናን ተለይተው በብዛት የሚገኙበት ሀገር በመሆኑ፣

6)    በሀገር ውስጥ ካለው ውጭ  ቤተ ክርስቲያን በሁሉም አመለካከት እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ባላቸው ኃይሎች በተቻለ መጠን ምዕመናንን ለማግኘት እና ለመያዝ የሚጠቀሙበት ስልት፣ የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን እና ኃላፊነት ይዘው ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ያሉበት ሁኔታ በመሆኑ፣ 

7)    በሀገር ቤት ከተሰየመው ይትበሃል ውጭ ቤተ ክርስቲያን በመድኃኒዓለም ወይም በእመቤታችን  በቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወይም በቅዱሳን መላዕክት እና በጻድቃን ሰማዕታት ስም ከመጠራት ይልቅ በግል የአቶ፣ የወ/ሮ፣ በዘር የእነ እገሌ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ  የሚጠራበት ሀገር በመሆኑ፣

8)    ቤተ ክርስቲያን የአገልጋይ አባቶች፣ ሊቀ ጳጳሳት ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና በአጠቃላይ አገልጋይ ካህናትን  በተመለከተ የአገልግሎት ድርሻቸው ታውቆ በተገቢው ክብራቸው እና አገልግሎታቸው ታውቆ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን የሚሰጡበት ሁኔታ የግንዛቤ ችግር ያለበት በመሆኑ በትክክል በሀገረ ስብከት መዋቅር ተጠብቆ ሳይሆን ከፊሉ ገለልተኛ ከፊሉ ስደተኛ በሚል ደረጃ ላይ ያለበት ሁኔታ በመሆኑ ይህም የትኛው  እውነተኛ ካህን፣ ሥልጣነ ክህነቱን ጠብቆ የሚያገለግለውን እና የማያገለግለውን ለመለየት የሚያስቸግርበት ሁኔታ በመሆኑ።

በአጠቃላይ በሰሜን አሜሪካ የማኅበሩ የረጅም ጊዜም ሆነ የአጭር ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎቹ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁሉ ተግባር ማከናወን ነው።

ከትኩረት አቅጣጫዎቹ ውስጥ፦
•    አባላቱን፣የማዕከሉን መዋቅር ማጠናከርና ማደራጀትን፣
•    በቀጣና እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሚሰጡትን መንፈሳዊ አገልግሎት ይበልጥ ማቀናጀት፣
•    በሰው ኃይል፣ በጽ/ቤት፣ በገንዘብ እና በማቴሪያል ማኅበሩን ማደራጀት፣
•    ከሰ/ት/ቤ አንድነት፣ ከልዩ ልዩ  መንፈሳዊ ማኅበራት ጋር በጋራ እና በውህደት በማገልገል እና በመሥራት ችግሩን እንዲቀረፍ ማድረግ፣
•    የቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስበከቱ መዋቅር እንዲጠናከር እና በቃለ አዋዲው የተቀመጠለትን ኃላፊነት እንዲወጣ ማስቻል፣
•    የዋናው ማዕከል አገልግሎት ከማዕከሉ የሚጠብቀውን ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት መሥራት፣
•    ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከትም ሆነ በአጥቢያ ደረጃ ከማኅበሩ ጋር እንዲሰራ እና እንዲፈጸም የሚጠየቀውን ማሟላት
•    ቤተ ክርስቲያን በግል፣ በጋራ፣ በቤተሰብ፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በፖለቲካ ወዘተ… ምክንያት ተለያይታ መከራ የሚታይበት በመሆኑ ይህ ልዩነት ጠፍቶ አንድነት እና ውህደት እንዲፈጠር የሚያደርግ ማንኛውንም ተግባር መፈጸም፣
•    በሰሜን አሜሪካ ያለው ሕዝበ ክርስቲያን እምነቱን፣ ስርዓቱን እና ትውፊቱን አውቆ ፣ ሕይወቱን በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር እየመራ ነፍሱን እንዲያድን ማድረግ፣
•    ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ ትውፊቱን እንዲጠብቅ ብሎም ለትውልድ እንዲያስተላለፍ የማድረግ ኃላፊነት ዕቅድ ነድፎ  በስትራተጂ ማስፈጸም፣
•    በተለይ በአሜሪካ የሚወለዱ ሕፃናት እምነት፣ ሥርዓታቸውን እና ትውፊታቸውን አውቀው ማንነታቸውን እንዳይረሱ ማድረግ፣
•    በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በአስተዳደር ምክንያት የተፈጠረውን ብሎም ወደ ሃይማኖት እና ሥርዓት ልዩነት ሊያድግ የሚችል ለትውልድ የሚተላለፍ የመለያየት አደጋ የሚጠፋበትን ለዚህም የማኅበሩ አባላት እንደ ድልድይ ሆነው በማገልገል ውግዘቶች ተነስተው ዕርቀ ሰላም የሚወርድበትን ማንኛውንም ሁሉ ትኩረት በመስጠት መሥራት፣ 
•    የአሜሪካ ማዕከል ከዋናው ማዕከል ቀጥሎ ለአገልግሎት የተመቻቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው፣ በማዕከሉ ከዋናው ማዕከልም ጽ/ቤት ማለትም 

o    ጽ/ቤት፣ መኝታ ክፍሎች
o    አዳራሽ፣ ሥልጠና በአጭር እና በመካከለኛ ሊያሰጥ የሚያስችል
o    ቤተ መጻሕፍት፣ አድባራት እና ገዳማት፣ የአብነት ት/ት ቤቶችን ሆነ በተለይ በሀገር ቤት ገጠር (ዐውደ ርዕይ)
o    ቤተ ክርስቲያንን  የሚያሳዩ ቋሚ ዐውደ ርዕዮችን
o    የማኅበሩን ታሪክ፣ የአገልግሎት ድርሻውን  እና የወደፊት ራዕዩን የሚያመለክት

•    ቤተ ክርስቲያን በህዝቡ ኑሮ  ያላትን ጉልህ ድርሻ እና ከካህናት፣ ከምዕመናን የሚጠበቀውን ኃላፊነት ማሳያ እና ናሙናዎችን የያዘ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ በቀላሉ ሊረዳው የሚችል ናሙና ወዘተ… እንዲኖር ትኩረት በማድረግ መሥራት፣
•    የዋናው ማዕከል አገልግሎት በተለይ በገንዘብ አቅሙ እንዲጠነክር ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው።

ሐመረ ኖኅ፦ ለአባላት የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

መልአከ ጽዮን፦ የማኅበሩ  አባላት ምን ጊዜም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው። ይኸውም ማኅበሩ  ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰጠውን ኃላፊነት በተለይ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ በየደረጃው ባሉት የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ አባላት ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይኸውም በተለይ በቤተ ክርስቲያን እንዲመጣ የሚፈለገውን ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለማምጣት፣ ድክመቶችን ለማረም እና ለማስተካከል፣ ልዩ ልዩ ቀዳዳ እና ክፍተቶችን ለመድፈን ከማኅበሩ አባላት ሌላ አካል ይመጣል ብሎ ማሰብ ወይም ሌላ ኃይል መጠበቅ አይገባም። ሁሉም አባላት በሰ/ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባዔ፣ በክህነት እና በምዕመንነት  ቤተ ክርስቲያን ከኛ የምትጠብቀውን ሁሉ የሕይወት፣ የጉልበት፣ የገንዘብ እና የእውቀት አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል።  ቤተ ክርስቲያን ግራ የተጋባውን ዓለም ወደማወቅ እና አምላኩን አመስግኖ ትዕዛዙን እንዲፈጸመበት ያቋቋማቸው ተቋማት እንደ አብነት ት/ቤቶች፣ ገዳማት እና አድባራት ያሉትን በዘመናዊ መልክ ተደራጅተው እና ተጠናክረው ከአገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁሉም መዳን እና መትረፍ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ማድረስ በጊዜው ከማኅበሩ አባላት የሚጠበቅ ድርሻ ነው።

ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትዳከም፣ ያላትን መንፈሳዊ በረከት ላጡት እንድታደርስ፣ ሀብቷም እንዳይባክን እና እንዳይመዘበር ይኸውም በገዛ ልጆቿ መሣሪያነት እንዲፈጸም የሚደረገው የተቀነባበረ የማፍረስ ተልእኮ መገታት ይኖርበታል። መናፍቃን በውስጥ ተሐድሶ  በውጭ ደግሞ በተለያየ ዘርፍ ቤተ ክርስቲያን እንድትደክም የሚያደርጉትን ርብርብ የመናፍቃን ድርጅቶች እና አላውያንን ሁሉ የማኅበሩ አባላት በግንባር ቀደም ሰማዕትነት እየተቀበሉ መከላከል እና ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። የማኅበሩ  አባላት ብቻ ሳይሆኑ በ9ኛ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ እንደተወሰነው ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ልጆችም በልዩ ልዩ መልኩ ተሰባስበው እና ተደራጅተው ያሉ ተቋማት ሁሉ በጋራ እና በአንድነት ሆነው ቤተ ክርስቲያናቸውን  እንዲጠብቁ ግንባር ቀደሙን ድርሻ ይዘው ተሳትፎአቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።  ቤተ ክርስቲያን መላውን ዓለም የምትመራ እንጂ የምትመራ አይደለችም። ልጆቿም ቢሆኑ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ማለትም ቤተሰባቸውን፣ መንደራቸውን ክልላቸውንም ሆነ አገራቸውን  በኃላፊነት በመምራት ግልጽ ድርሻ ሲያበረክቱ የቆዩ መሆናቸውን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያመለክተናል። ዛሬም ቢሆን በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሀገር ደረጃ እንደ  ቤተ ክርስቲያን ልጅነት እና እንደ ሀገር ዜግነት የበይ ተመልካች ወይም በገዛ ቤት እንግዳ መሆን የለባቸውም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ በአገር ደረጃ በግንባር ቀደም ገብተው ማገልገል እና መገልገል መብትም ግዴታም መሆኑን አባላት አውቀው በዚህ ጉዳይ ትልቁን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሀብት በአግባቡ እና በሥርዓቱ እንድትጠቀምበት፣ ሀብቷም  ከምዘበራ እና ከብክነት እንዲድን አባላት በአንክሮ  ሊያዩት የሚገባ ጉዳይ ነው። በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያንን በልማት በኩል ማለትም ትውልዱን በሥነ ምግባር አንፃ ማሳደግ፣ በየትኛውም አንጻር ያላትን ሀብት በዘመናዊ መልኩ አልምታ ለራሷም፣ ለሀገርም ሆነ ለዓለም በረከቷን እና ወንጌልን የምታስፋፋበትን ሁሉ ተግባር እንድታከናውን አባላት በተለያየ  ምክንያት ተበትነው ባሉበት ሁሉ ይህንን ተልእኮ የማስፈጸም ኃላፊነት አለባቸው።

ሐመረ ኖኅ፦ ጊዜዎን ሰውተው ለጥያቄዎቻችን መልስ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። ረጅም እድሜ፣ የተሳካ የአገልግሎት ዘመን እግዚአብሔር እንዲሰጥዎ እንመኛለን።

መልአከ ጽዮን፦ አሜን።

ምንጭ፦ ሐመረ ኖኅ ኤሌክትሮኒክስ መጽሔት ፯ኛ ዓመት ቁጥር ፩ ታኅሣሥ ፳፻፫ ዓ.ም.


Written By: admin
Date Posted: 7/18/2011
Number of Views: 3496

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement