View in English alphabet 
 | Thursday, May 2, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ቅድስት ቴክላ

ይህች ቅድስት ከኒቆምድያ ሀገር በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ሐዋርያዊት የሆነች ናት። ቅዱስ ጳውሎስም ከአንጾኪያ ከተማ በወጣ ጊዜ፤ ወደ ኒቆምድያ ከተማ ሄደ። በዚያም ስሙ ስፋሮስ የሚባል ምዕመን ሰው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስን ወስዶ በቤቱ አኖረው፤ ብዙ አሕዛብም የሐዋርያው የጳውሎስን ትምህርት ይሰሙ ዘንድ በእርሱ ዘንድ ይሰበሰቡ ነበር።

ይህች ቅድስት ቴክላም በቤቷ መስኮት ተመለከተች፤ የሐዋርያውንም ትምህርት ሰማች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ፈታኝ ቀርቦ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። እርሱም መልሶ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ፤ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል።” ብሎ እንደመለሰለት እንዲሁም ትምህርቱን እያዳመጠች ሳትበላና ሳትጠጣ ሦስት ቀኖች ቆየች። ትምህርቱም በልቧ አደረ፤ አባትና እናቷ ቤተሰቦቿም ሁሉ አዘኑ። ከምክርዋም እንድትመለስ ሐዋርያው ጳውሎስንም እንዳትከተል ለመኗት፤ ነገር ግን አልሰማቻቸውም። /ማቴ. ፬፥፫-፬/።

አባቷም ዲማኖስና ርምጋኖስ ወደሚባሉ ዳኞች ሄዶ ከሰሳት፤ ከልጁም የሆነውን ሁሉ አስረዳቸው። እነርሱም ቢያስገድዷት አልተቀበለቻቸውም። ሁለተኛም አባቷ ወደ ንጉሡ ሄዶ ሐዋርያው ጳውሎስን ከሰሰው። ንጉሡም ወደ እርሱ አስቀርቦ ስለሥራው ጠየቀው፤ ነገር ግን የሚቀጣበት ምክንያት በላዩ አላገኘም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስንም እንዲያስሩት አዘዘ።

ጴጥሮስና እንድርያስ ዓሣ የሚያጠምዱበትን መረባቸውን ትተው ጌታን እንደተከተሉት፤ እንደዚሁም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አይቶ በጠራቸው ጊዜ አባታቸውንና ታንኳይቱን ትተው እንደተከተሉት ይህች ቅድስት ቴክላም ልብሶቿንና ጌጦቿን ከላይዋ አስወገደች። ወደ ቅዱስ ጳውሎስም ሄዳ ከእግሩ በታች ሰገደች በእርሱም ዘንድ እየተማረች ተቀመጠች። /ማቴ. ፬፥፲፰-፳/።

ወላጆቿም በፈለጓት ጊዜ አላገኟትም። በሐዋርያው ጳውሎስ ዘንድ እርሷ እንዳለች ሰዎች ነገሯቸው። በመኮንኑም ዘንድ ከሰሷት፤ እርሱም በእሳት እንዲያቃጥሏት አዘዘ። እናቷም ስለእርሷ ሴቶች ሁሉ እንዲገሰጹና እንዲፈሩ አቃጥሏት እያለች ጮኸች። ብዙዎችም የከበሩ ሴቶች በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት አምነው ነበርና። እርሷ ግን በሚያቃጥሏት ጊዜ ልቧን አጽንታ ቅዱስ ጳውሎስን ተመለከተችው።

ዳግመኛም ሲጸልይ ቅዱስ ጳውሎስን አወጡት፤ በላይዋም በመስቀል ምልክት አማተበ፤ ራሷንም ወደ እሳቱ ምድጃ ወረወረች፤ ሴቶችም ያለቅሱላት ነበር። እግዚአብሔር ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት እንዳዳነ ያን ጊዜ ብዙ ዝናብን በረድና መብረቅን ላከ። የእሳቱም ምድጃ እንደ ቀዝቃዛ ጠል ሆነ። ቴክላም ሮጣ ቅዱስ ጳውሎስ ተሰውሮ ወደ አለበት ቦታ ደረሰች። /ዳን. ፫፥፲፱-፳፯/።

ተስፋችንም ስለእናንተ ጽኑ ነው ስቃያችንን እንደተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን እንድትካፈሉ እናውቃለን። እንዲሁም በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽናኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለሆናችሁ፤ በልቤ ትኖራላችሁና ስለሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። /፪ኛ ቆሮ. ፩፥፯፣ ፊል. ፩፥፯/ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ፤ ቅድስት ቴክላም ቅዱስ ጳውሎስን ራሷን ላጭቶ ትከተለው ዘንድ ለመነችው፤ እንዲሁም አደረገላት።

ወደ አንጾኪያ ከተማም በሄደች ጊዜ ከመኳንንቶች አንዱ ሊያገባት ፈለገ። መልኳ እጅግ ውብ ነበረና እርሷም ዘለፈችው፣ ረገመችውም። እርሱም በዚያች አገር ገዥ በሆነ በሌላ መኮንን ዘንድ ከሰሳት። ሹሙም ለአንበሶች እንዲጥሏት አዘዘ። ዳንኤልን በአንበሳ ጉድጓድ በጣሉት ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ እንደዘጋ ሁሉ ቅድስት ቴክላንም እነዚያ አንበሶች እግሯን ይልሱ ነበር እንጂ ምንም አልከፉባትም። /ዳን. ፮፥፲፮-፳፬/።

ከዚያም በኋላ በሁለት በሬዎች መካከል አስረው በከተማው ውስጥ ሁሉ አስጎተቷት። ነገር ግን ምንም ምን ክፉ ነገር በላይዋ አልደረሰም፤ ከዚያም በኋላ ለቀቋት።

በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ስቃይ በእኛ ላይ እንደበዛ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። በማለት ሐዋርያው እንደተናገረው ወደ ቅዱስ ጳውሎስ በሄደች ጊዜ አረጋጋት፤ እንድትሰብክ አዘዛት። /፪ኛ ቆሮ. ፩፥፬-፮/።

ከዚያም በኋላ ቆሎንያ ወደሚባል ሀገር ሄዳ ሰበከች። ከዚያም ወደ ሀገሯ ሄዳ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማረች። አባትና እናቷንም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መለሰቻቸው።

ተጋድሎዋንም ፈጽማ ሐምሌ ሃያ አምስት ቀን በሰላም አረፈች። የሐዋርያነት አክሊልንም ተቀበለች። ሥጋዋም በግብፅ ደቡብ ሰንጋር በሚባል አገር እስከዛሬ አለ ከሥጋዋም ብዙ ድንቅና ተአምር ተገለጠ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ቴክላ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።


ምንጭ፦ መለከት መጽሔት ፲፫ኛ ዓመት ቁጥር ፯ ሰኔና ሐምሌ ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. /ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ ገጽ ፮፻፲ የተወሰደ/


Written By: admin
Date Posted: 7/24/2011
Number of Views: 4652

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement