እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
በትራክት መልክ የተዘጋጀውን የአማርኛ መልእክት ለማግኘት ይህንን ይጫኑ
To read about The Feast of the Transfiguration in English,
click here
በዓለ ደብረ ታቦር
በዲ/ን ተስፋዬ ከበደ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካሏት መንፈሳዊ በዓላት አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው። ይህ በዓል ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው። ደብረ ታቦር ወይም የታቦር ተራራ ጌታ በምድረ እስራኤል እየተዘዋወረ በማስተማር ላይ በነበረ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን ብርሃነ መለኮቱንና ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ነው።
ጌታችን በቂሳርያ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ብለው ይጠሩታል?” በማለት ከጠየቃቸው ከስድስት ቀናት በኋላ ዘጠኙን ሐዋርያት ከእግረ ደብር ትቶ ሦስቱን ማለትም ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን አስከትሎ ከርዕሰ ደብር ወጣ። በተራራው ላይ ሳሉ የጌታችን መልክ ተለወጠ። ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ በረዶ የነጻ ሆነ። በዚህ ጊዜ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን ገለጸ። ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ። ሙሴና ኤልያስን መምረጡ ስለምንድር ነው ቢሉ ሙሴ 570 ጊዜ ቃል በቃል ተነጋግሮ ባይህ እወዳለሁ ባለው ጊዜ ፊቴን አይቶ አንድ ሰዓት እንኳ መቆም፣ መቆየት የሚቻለው የለም ቢለው ይህ ከሆነማ ባለሟል መባሌ ምኑ ላይ ነው ሲለው መሥዋዕት ሆኜ በምቀርብበት ጊዜ እታይሃለሁ ብሎት ነበርና /ዘጸ ፴፫፥፲፰-፳፫/ ያንን ለመፈጸም፤ ኤልያስም እንዲሁ ተስፋ ነበረውና።
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው። ብትፈቅድስ ሦስት ዳስ እንሥራ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱን ለኤልያስ በማለት ተናገረ። ሙሴ ጠላት ይገድላል፣ ባሕር ይከፍላል፣ መና ያወርዳል፣ ውሃ ያፈልቃል፤ ኤልያስ ሰማይ ይዘጋል፣ ዝናብ ያቆማል፤ ክርስቶስ ቅዱሳኑ በጸጋ የሠሩትን ሥራ በባሕርይው ይፈጽማል፤ እነሱ ካሉ ሁሉም አለ ብሎ። ይህን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው። ወዲያውም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ” /በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት/ የሚል ድምጽ ተሰማ። እነጴጥሮስ ደንግጠው ወደቁ። ጌታ ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው። “ተነሱ አትፍሩ” አላቸው ዓይናቸውንም ገለጡ። ከተራራም ሲወርዱ ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጅ ከሙታን ተለይቶ እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው።
ዘጠኙን በእግረ ደብር ትቶ ሦስቱን አስከትሎ መውጣቱ ስለምንድር ነው ቢሉ ከዘጠኙ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን ሊያይ የማይገባው ይሁዳ ነበርና ብቻውን ቢተወው ከብርሃነ መለኮቱ ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት ይል ነበርና። ያስ ቢሆን ከተራሮች ሁሉ ታቦርን ስለምን መረጠ ቢሉ ዳዊት “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ” /ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል/ ብሎ ነበርና ያን ለመፈጸም ነው።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን በገለጸበት በታቦር ተራራ አካባቢ በጐቻቸውን አሰማርተው ይጠባበቁ የነበሩ እረኞች አካባቢው በብርሃን ስለተሞላ ገና ያልመሸ መስሏቸው በዚያው ቆዩ። ልጆቻቸው ወደየቤታቸው በጊዜ ባለመመለሳቸው ግራ የተጋቡት ወላጆቻቸው ዳቦ በመያዝና ችቦ በማብራት ወደተሰማሩበት ሥፍራ ሲሄዱ በደህና አገኟቸው። በዚህ ታሪክ መሠረት በሀገራችን ወጣቶች ቡሄ (ደብረ ታቦር) ከመድረሱ በፊት ጅራፍ እየገመዱ ያጮሃሉ። እናቶችም ለበዓሉ የሚሆን ሙልሙል ለመጋገር ስንዴ ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉና ሲያስፈጩ ይሰነብታሉ። በዓሉ እንደነገ ሊሆን እንደዛሬ በዋዜማው ነሐሴ 12 ቀን የየሰፈሩ ወጣቶች በየቤቱ እየዞሩ ቡሄ በሉ ሆ እያሉ ይጨፍራሉ። በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ሙልሙል ዳቦ እያነሱ ይሰጧቸዋል። በነጋታው ነሐሴ 13 ቀን ማታ የመንደሩ ሰው አንድ ላይ በመሆን ችቦ ያበራል።
በደብረ ታቦር በዓል ሰሞን የጅራፉ ጩኸት ድምፀ መለኮትን፣ ጩኸቱ ማስደንገጡ ደግሞ ሦስቱ ሐዋርያት በድምፀ መለኮት ደንግጠው መውደቃቸውን ያስተምረናል። የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ መብራቱ ደግሞ በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮትና ወላጆች ልጆቻቸውን ለመፈለግ ላበሩት ችቦ ምሳሌ ነው። በበዓሉ ዕለት የቅርብ እውቂያ ላለው እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጆች ልክ ዳቦ ይሰጣል። ይህም በዕለቱ ወላጆች ለልጆቻቸው ዳቦ ይዘው ለመሄዳቸው ምሳሌ ነው።
በሀገራችን በሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ደግሞ ደብረ ታቦር የተማሪዎች በዓል ነው። ተማሪዎች ቀደም ብለው “ስለደብረ ታቦር” እያሉ እህል፣ ጌሾና ብቅል ይለምናሉ። ሕዝቡም ባሕሉን ስለሚያውቀው በገፍ ይሰጣቸዋል። እነርሱም ጠላ ጠምቀው፣ ቆሎ ቆልተውና ዳቦ ጋግረው የደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚመጡ ምዕመናን ከቅዳሴ በኋላ ይጋብዛሉ። ይህ እስካሁን በመንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ባሕላችን ነው።
ስለዚህ ይህንን ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓልና ነባር ባሕል በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፉ ተገቢ ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አልባ ለማድረግ በየአቅጣጫው ለተነሱ ምንደኞች እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ታሪክና ባሕል በማስረዳት ክብሯ ተጠብቆ እንዲኖር መጣር ከሁላችንም ይጠበቃል። በደብረ ታቦር የታየው ድንቅና የማይረሳ ታሪክ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ አለበት። በተለይ በአሁኑ ጊዜ የቡሄ በሉ ጭፈራ ሳይቀር ታዋቂ ስፖርተኞችን፣ ዘፋኞችንና አርቲስቶችን ማወደሻ እየሆነ ስለመጣ “አንድ ሞኝ የተከለውን አምሳ ሊቃውንት አይነቅሉትም” እንደተባለ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ለቤተ ክርስቲያኑ መቆም አለበት። ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ፣ ማሳደግና ለዓለም ማስተዋወቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
ከደብረ ታቦር በዓል ረድኤትና በረከት ያሳትፈን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Written By: admin
Date Posted: 8/18/2011
Number of Views: 10908
Return