View in English alphabet 
 | Tuesday, May 7, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ቅድስት ሣራና ወንድሟ አባ ሞይስስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ ሞይስስና እኅቱ ሣራ በሰማዕትነት ያረፉበት ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፤ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል፤ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት አይቻለውም” በማለት እንዳስተማረ የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው መልካም ፍሬን እንዳፈራው ዛፍ ደጎችና እጅግም ባለጸጎች ነበሩ። /ማቴ. ፯፥፲፯-፲፰/

የከበረ ሞይስስ ወላጆቹ ካረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊድራትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት፣ እርሱም ወደ ገዳም ሔዶ ሊመነኩስ አሰበ። ይህን ሐሳቡን በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት “እኔን ልትድረኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ” አለችው። እርሱም “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” እንዲል የከበረ ሞይስስም እኅቱን ሣራን “እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኩስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም፤ የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ” አላት። /ማቴ. ፲፮፥፴፱/

እርሱም “ምንኩስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሽውን አደርግልሻለሁ” አላት። ቅድስት ሣራም መልሳ “ለነፍስህ የምታደርገውን ለእኔም እንዲሁ አድርግ፤ እኛ ሁለታችን ከአንድ ባሕርይ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና” አለችው።

የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋር ተነሣ “ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ። መዝገብህ ባለበት ልብህ ድግሞ በዚያ ይሆናልና።” እንዳለ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንድ ባለጸጋ ቀርቦ “የዘለዓለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው እርሱም ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው።” … ጎበዙም ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ ደግሞስ የሚጎድለኝ ምንድን ነው? አለው። ጌታችን ኢየሱስም ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሒድና ያለህን ሽጠህ ለድሆች ስጥ መዝገብም በሰማይ ታገኛለህ መጥተህም ተከተለኝ አለው።” ሰማያዊ መዝገብን የሻቱ እነዚህ ቅዱሳንም ፍጹም መሆን ስለፈለጉ ገንዘባቸውን ሁሉ ለድሆችና ለምስኪኖች በተኑ። /ማቴ. ፮፥፲፱-፳፩፣ ፲፱፥፲፮-፳፪/

ከዚያ በኋላ እኅቱ ሣራን ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለው የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት፤ እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይተያዩ ዐሥር ዓመት ኖሩ።

በሊቀ ጳጳስ አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነስቶ የክርስቲያን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ፤ ከመነኮሳት ገዳማትም ብዙዎች የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ። በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት።

እኅቱም ሣራ በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች ሔዳ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት። እመ ምኔቷም ጸለየችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት። እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናብታቸው ወደ ወንድሟ ሔደች። በጎዳናም አገኘችውና እርስ በእርሳቸው ሰላም ተባባሉ። ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኮንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። መኮንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው፤ ከዚህም በኋላ ነሐሴ ሃያ ስድስት ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ፤ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።


ምንጭ፦ መለከት መጽሔት ፲፫ኛ ዓመት ቁጥር ፰ ነሐሴ ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. /ከመጽሐፈ ስንክሣር ዘወርኀ ነሐሴ ገጽ ፮፻፴፩ የተወሰደ/

Written By: admin
Date Posted: 8/30/2011
Number of Views: 5038

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement