View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ትምህርተ ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት

ወልድ ዋሕድ /ክፍል ፩/

 ሊቀ ካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ ደስታ /B.D./
በዴንቨር ኮሎራዶ፣ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና

የሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ


መግቢያ፦

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት መሠረታዊ እምነት «ተዋሕዶ» ነው። ተዋሕዶን የሚተረጉም ኃይለ ቃልም ፣ «ወልድ ዋሕድ» የሚለው ነው።

ወልድ ዋሕድ ለሚለው ሥያሜ መሠረቱ «ቃል ሥጋ ኮነ» የሚለው ቃለ ወንጌል ነው። ዮሐ ፩፥፲፬። ስለሆነም፣ የዚህ ዝግጅት ዐቢይ ርእስ /ዋና ርእስ/ ወልድ ዋሕድ እንዲባል ተመርጦአል።

በዚህ ዝግጅት የሚቀርቡ ንኡሳን አርእስተ ትምህርት በየርእሳቸው እየታተቱ የሚቀርቡ ሆኖ ጥናቱ በማስረጃ የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ አዘጋጁ ተገቢውን ጥረት ያደርጋል። ለወጣቱ ግንዛቤ ይሰጣል ተብሎ የሚታመንበት ዝግጅት እንዲሆንም በቀላል አገላለጽ ለማቅረብ ይሞክራል። የትምህርተ ሃይማኖት ምሥጢራዊ ይዘት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከአበው ሊቃውንት የትርጉም ዘይቤ እየተገናዘበ ይቀርባል።

የዝግጁቱ ዋና ዓላማ፣ ወጣቶች የትምህርተ ሃይማኖት ግንዛቤያቸውን እንዲያሰፉ ማድርግ በመሆኑ፣ የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ሊያዛቡ ከሚችሉ አዳዲስ አስተሳሰቦችና የግል አስተያየቶች ፍጹም ነፃ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ሆኖ እንዲቀርብ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረጋል። ከአንባቢያን ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ አስፈላጊው ትኩረት እየተሰጣቸው ተገቢውን መልስ እንዲያገኙ ማድረግ የአዘጋጁ ተቀዳሚ ተግባርና ግዴታ ነው። ይህን ዝግጅት የሚከታተሉ አንባብያንም እያንዳንዱን ኃይለ ቃል፣ በማስተዋል መከታተል፣ ምሥጢሩንና ቁም ነገሩንም በጥንቃቄ መቅሰም ይጠበቅባቸዋል። ጥበብና ማስተዋል የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጠን። ከእግዚአብሔር አጋዥነትና ረድኤት ውጪ ምንም ምን የሚሆን ነገር ስለሌለ፣ በተለይም ባሕረ ጥበባት የሆነውን ትምህርተ መለኮት ለማቅረብ መሞከር፣ ውቅያኖስን በእንቊላል ቅርፊት... ማለት በመሆኑ፣ የጥበባት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቡንና ማስተዋሉን እንዲሰጠን እንለምነዋለን።



ትምህርተ ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት

ትምህርተ ሃይማኖት መለኮታዊ ምሥጢርን የሚያስረዳ እንደመሆኑ ትምህርቱ ጥልቅ፣ ረቂቅና ምጡቅ ነው። ይሁንና በዚህ ዝግጅት ግን እንደ ትምህርቱ ጥልቀትና ምጥቀት ሳይሆን፣ እንደ አዘጋጁ የዕውቀት ውሱንነትና እንደ ተቀባዩ የአእምሮ ስፋት መጠን፣ ግልጽ በሆነ አቀራረብ ባጭር ባጭሩ ይቀርባል።



የሃይማኖት ትርጉም


ለመሆኑ ሃይማኖት ምንድን ነው?


ሃይማኖት ወይም እምነት ማለት ማመን፤ መታመን፤ የፈጣሪን ሕልውና ማወቅ፤ ከሃሊነቱን፣ መግቦቱንና ቸርነቱን መረዳት፤ መለኮታዊ እውነታዎችን በትክክል መቀበል፤ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥራ ፈጽሞ አለመጠራጠር፤ ጥርጥርን ከኅሊና ማስወገድ፤ ስለ ሰማያዊ ሕይወት ጽኑ ተስፋ ማድረግ በሚሉ አገላለጾች ይተረጐማል።


ሃይማኖት በረቂቅ ሐሳብ፣ በልብ ሰሌዳነት፣ የሚጻፍ የአእምሮ መጽሔት ነው። ሃይማኖት የኅሊና መሰላል በመሆኑ የዓለምን አስቸጋሪ ዳገት ይወጡበታል። ሃይማኖት የሕይወት መርከብ በመሆኑ ገፊውን ማዕበል ተቋቁመው ባሕሩን ይሻገሩበታል። ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙበታል። ዕብ ፲፩፥፮። ልክና መጠን፣ ወሰንና ዳርቻ የሌለው መለኮታዊ ባሕርይ የሚታየው፣ ሕልውናው ከሃሊነቱና መግቦቱ የሚታወቀው በሃይማኖት ነው።


ቅዱስ ጳውሎስ የሃይማኖትን ኃይል ሲተረጉም፦ «እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው።» ይልና በመቀጠልም «ነአምር ከመ ተፈጥረ ዓለም በቃለ እግዚአብሔር። ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ እናውቃለን።» ብሎአል። ዕብ ፲፩፥፩-፫። ሃይማኖት ፍጡርን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኝ የኅሊና መሰላል በመሆኑ ፍጡር የሃይማኖት መሰላሉና ድልድዩ ከተሰበረበት ወደ ፈጣሪው መድረስ ይሳነዋል፤ ሌላ መድረሻ ሌላ መንገድ ፈጽሞ የለውም።


የሃይማኖት ኃይል ልዩና ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኘው፣ ምድራዊ ባለሥልጣን የማይገዛውን የሚገዛ፣ በዓይነ ሥጋ የማይታየውን የሚያሳይ፣ በእጅ የማይዳሰሰውን የሚዳስስ፣ በሥጋዊ ጥበብ የማይመረመረውን የሚመረምር ምሥጢር መሆኑ ነው። ማቴ ፲፮፥፲፯።


ልዕልና ነፍስ /የነፍስ ልዕልና/ ክብረ ነፍስ የሚገኘው በሃይማኖት ነው፤ ከሃይማኖት ውጪ የሚሆነው ሁሉ ኃጢአትና በደል ነው። «ወኲሉ ዘይከውን ዘእንበለ አሚን ኃጢአት ወጌጋይ ውእቱ። በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢአትም፣ በደልም ነው።» ሮሜ ፲፬፥፳፫። የሚታይና የማይታይ፣ ግዙፍና ረቂቅ፣ ሁሉ ከማይታይ እንደሆነ ማለትም በመለኮታዊ ሥልጣን የተገኘ መሆኑን ያሳውቃል።


እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ መገኘት ምክንያት ሳይሻለት በከሃሊነቱ እምሀበአልቦ ፈጥሮታል። ይህን ማወቅ የሚያስችል ከሃይማኖት ውጪ ሌላ ጥበብ ፈጽሞ የለም። የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሽ የመሆን ዕድል የሚያገኘው በሃይማኖት ብቻ ነው። በዓለም ያለውን ሥርዓት በቀላሉ በምሳሌነት ማየት ይቻላል፤ ይኸውም የአንድን ሰው ሃብትና ንብረት ለመውረስ በቀላሉ ባለመብት መሆን የሚቻለው የባለጸጋው ወይም የባለሀብቱ ልጅ ሆኖ መገኘት ሲቻል ነው። በእግዚአብሔር መንግሥትም በሃይማኖት ልጅነትን ካላገኙ የመንግሥቱ ወራሽ መሆን አይቻልም።


«እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።» እንዳለ ጌታ በቅዱስ ወንጌል። ዮሐ ፫፥፭።


«… ስለዚህ ከእንግዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም። ልጅም ከሆንክ ደግሞ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።» ገላ ፬፥፬-፯።

ሃይማኖት በአማኙ ዘንድ ሦስት ነገሮች ተሟልተው እንዲገኙ ግድ ይላል። እነዚህም፦


፩. ትክክለኛ አረዳድ /እውነት/

፪. የልብ ንጽሕና /ቅንነት/

፫. መጥዎተ ርእስ፣ ማለትም ጥብዓት፣ ራስን መካድ፣ ራስን አሳልፎ ለሃይማኖት መገዛት ፈቃደ ሥጋን አሸንፎ መስቀልን መሸከም የሚሉ ናቸው። እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ያልተሟሉለት አማኝ ግብዝ ሃይማኖተኛ ይባላል።



ማስረጃ


«... እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ። አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል። …» ያዕ ፪፥፲፬-፳፪። ማር ፭፥፯። ጌታም በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይለናል። «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።» ማቴ ፯፥፳፩።


«ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ። መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።» ማር ፰፥፴፬። ሉቃ ፱፥፳፫። ማቴ ፲፥፴፰፣ ፲፮፥፳፬።


«ወኅሊናሁሰ ለነፍስትነ ሞተ ያመጽእ ላእሌነ፤ ወሕሊናሁሰ ለመንፈስ ሰላመ ወሕይወተ ይሁብነ። የሥጋችን ፈቃድ ሞትን ያመጣብናል /ያስፈርድብናል/ የነፍሳችን ፈቃዱ ግን ሰላምን ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን ድኅነትን ይሰጠናል። እስመ ኅሊናሁ ለነፍስትነ ፀሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ። የሥጋችን ፈቃዱ የእግዚአብሔር ጠላቱ ነውና ሞትን ያመጣብናል።» ሮሜ ፰፥፭-፰።

የሃይማኖት ዓላማውና ግቡ፣ ሀልዎተ እግዚአብሔርን ማሳወቅና ፍጡር በፈጣሪው ሕግና ትእዛዝ እየተመራ ዘለዓለማዊ ክብር እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ማቴ ፳፭፥፴፬።


ሀልዎተ እግዚአብሔርን ማወቅ ማለትም ቅድመ ዓለም የነበረ፣ በማዕከለ ዓለም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ ፈጣሪ፣ መጋቢ ሠራዒ፣ በመለኮታዊ ባሕርዩ ጸንቶ የሚኖር፣ ለመንግሥቱ ሽረት፣ ለሕልውናው ኅልፈት የሌለበት አንድ ፈጣሪ፣ አንድ አምላክ መኖሩን አውቆ ማመን ማለት ነው።


«እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላክህ እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው።» ዘዳ ፭፥፬።


የማይታይና የማይመረመር፣ የማይገሰስና የማይዳሰስ፣ ሕያወ ባሕርይ እግዚአብሔር በከሃሊነቱ ሁሉን የፈጠረ፣ በመግቦቱ ሁሉን የሚያስተዳድር፣ በቸርነቱ ሁሉን የሚጠብቅ አምላክ በመሆኑ ለፍጥረቱ የሚታወቅበት ገጽታ አንዱ ይኸው ነው። ሁሉን የሚገዛ፣ ሁሉን የሚያስተዳድር በመሆኑ ይቅርታውና መግቦቱ በሁሉም ላይ ነው።


«እስመ ቅንየትከ ወምልክናከ ላዕለ ኲሉ፣ ይሬስየከ ትሣሃል ላዕለ ኲሉ። ማለት በሁሉ ላይ ያለ ሥልጣንህና አገዛዝህ ሁሉን ይቅር እንድትል ያደርግሃል።» እንዲል።


«… እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።» ማቴ ፭፥፵፭።


በከሃሊነቱ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር የማይታይ፣ የማይመረመርና የማይዳሰስ፣ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ባሕርዩ ከሚገለጽባቸው አያሌ መገለጫዎች ጥቂቶቹን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል። እነሱም፦


፩. ፈጣሪ

፪. ከሃሊ

፫. ምሉእ

፬. ዘለዓለማዊ

፭. ቅዱስ

፮. ፍጹም

፯. ማእምር /አዋቂ/ ጥበበኛ የሚሉ ናቸው። እነዚህን በዝርዝር እንመለከታለን።

Written By: admin
Date Posted: 12/3/2011
Number of Views: 8493

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement