View in English alphabet 
 | Thursday, May 2, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ዜና ትምህርተ ወንጌል!

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል የሲያትል ቀጣና ማዕከል በዘንድሮው ዓመት በዕቅድ ከያዛቸው ሦስት ዐቢይ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት የመጀመርያውን ጉባኤ ቅዳሜ ኅዳር 23 2004 ዓ/ም (December 3, 2011) እና እሑድ ኅዳር 24 2004 ዓ/ም (December 4, 2011)  በተሳካ ሁኔታ አካሄደ።

በዚህ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክን የሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ : የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች:  የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ፣ ካህናት ፣ ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት መዘምራን እና በሲያትልና አካባቢዋ ካሉ ከተሞች የመጡ ምዕመናን ተሳትፈዋል።  ለሁለት ቀናት በተካሄደው የትምህርተ ወንጌል ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ማዕምራን ለይኩን ተስፋ በተለያዩ ርዕሶች ትምህርት የሰጡ ሲሆን ከደብረ ሠላም ቅዱስ ሚካኤል፣ ከደብረ መድኃኒት ቅዱስ አማኑኤል ወአቡነ አረጋዊ እና ከደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም  አብያተክርስቲያናት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በአንድነት ያሬዳዊ መዝሙሮች አቅርበዋል። በእለቱም ሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ ተሳታፊዎችን በሚያነቃቃና ባሳተፈ ሁኔታ የመዝሙር  አገልግሎት ሰጥቷል። በጉባኤውም ላይ “ክፉዎች ሠራተኞችን እወቁባቸው” በሚል  ርእስ  የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ላይ እየሰሩ ያሉትን የጥፋት ሥራ የሚያሳይ የድምጽና ምስል ዝግጅት ለጉባኤው ተሣታፊዎች ቀርቧል። በወቅቱም ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን : የአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች አንድነት ጉባኤ: የሰባክያን ጥምረትና ሌሎችም ችግሩን የተረዱ ወገኖች በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ላይ በመናፍቃን የተዘረጋውን የጥፋት ሥራ ለመከላከል እያደረጉ ስላለው ተጋድሎ እንዲሁም  በጥቅምት 2004 ዓ/ም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንኑ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶበት ከተወያየ  በኋላ  ስለወሰናቸው ውሳኔዎች ገለጻ ተደርጓል። ከገለጻውም በኋላ በነበረው የውይይት  መርሐግብር ተሳታፊዎቹ መናፍቃን ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በተለያየ መንገድ ለማዳከምና አስተምህሮዋን ለመቀየር : የተተኪ አገልጋይ ዲያቆናት: ካህናትና መምህራን መፍለቂያ የሆኑትን ገዳማትና አድባራትን የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመበረዝ እያደረጉ ያለውን ክፉ ሥራ በተመለከተ ያደረባቸውን የቁጭት ሀሳብ ገልጠው የመፍትሔ እርምጃ ያሉትንም: አቅርበዋል: : በመጨረሻም  ምዕመናንን ሃይማኖታቸውንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያናቸውን ጠብቀው ማስጠበቅ የሚችሉት ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ሲያገኙ በመሆኑ በማኅበሩ የተጀመረው የቤተክርስቲያንን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የማጠናከር እንቅስቃሴ  በየደረጃው ካሉ የቤተክርስቲያን አካላት ጋር በመቀናጀት ተስፋፍቶ እንዲቀጥል : በየደብሩ ያሉ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎችና ሰባክያነ ወንጌልም  ለምዕመናን ወቅትና ሥርዓትን የጠበቁ ትምህርቶች በየጊዜው በስፋት እንዲሰጥ እንዲያደርጉ ከምዕመናን ሀሳብ ተስጥቷል። እንደዚሁም ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤት የስብከተ ወንጌል ባልተዳረሰባቸው  ጠረፋማና ሌሎችም አካባቢዎች የስብከተ ወንጌል ለማስፋፋትና አሥር አኅጉረ ስብከቶችን ለማጠናከር የጀመረውን “ሁለት ሺህ አሥራ አንድ" የሚባለውን የስብከተ ወንጌል ፕሮጀክት የወንጌል ማኅበርተኛ በመሆን እና የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ቋሚና ጊዜያዊ ፕሮጀክቶችን በመርዳት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦ  ከጉባኤተኛው ጥሩ ምላሽ ተሰጥቷል።

በጉባኤውም ላይ ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር  በቀጣና ማዕከሉ ገዳማትንና አድባራትን ለመርዳት ተዘጋጅቶ የነበረው የቶምቦላ ዕጣ ወጥቶ  በቦታው የተገኙ እድለኞች ስጦታቸውን ከብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እጅ  ተቀብለዋል። በመጨረሻም ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ሰጥተው ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘገባ፦ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል

         የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል

Written By: admin
Date Posted: 12/12/2011
Number of Views: 5434

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement