View in English alphabet 
 | Sunday, May 5, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

“የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ 4፥3)

ሐዋርያዊት የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥት ለ2000 ዓመታት በላይ ልጆቿ ስታውጅ እና ስታበስር ኖራለች:: በተለይም የራሷን ፓትርያርክ ሰይማ ከእራሷ ልጆች ኤጲስ ቆጶሳትን እየሾመች አገልግሎቷን መምራት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በስብከተ ወንጌል እና አስተዳደር በኩል ተሰፋ ሰጪ ውጥኖች ታይተዋል:: ከውጪና ከውስጥ በሚነሱ ፈተናዎች ምክንያት የሚጠበቅባትን አመርቂ እርምጃ መራመድ ግን አልቻለችም::  በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ ምእመናንን በምግባር በሀይማኖት አጽንቶ ከበረት ውጭ ያሉትን የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት በጎችን ወደ በረቱ ማምጣትና የተከታዩንም ቁጥር ከፍ ማድረግ ይጠበቅባታል:: ሆኖም ግን በተለይ ከ20 ዓመታት ወዲህ ተከስቶ ቀስ በቀስ እያደገ የመጣው እና እስከ መወጋገዝ ደረጃ ላይ የደረሰው የብፁዓን አባቶች ልዩነት የወቅቱ አውራ የቤተ ክርስቲያን ችግር ሆኖ በጉልህ ይታያል::

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ከመሠረታት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ተለይቷት አያውቅም:: ሆኖም የፈተናው ቅርጽ እና ይዘት እንደየጊዜው ልዩ ልዩ ነው:: ከምንጊዜውም በላይ ግን በኬልቄዶን ጉባኤ ላይ እግዚአብሔር ከሰጣቸው አደራ ይልቅ ለራሳቸው ክብር በተጨነቁ ልዮናውያን ምክንያት የተከሰተው መለያየት እና መወጋገዝ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዝ ነው ለማለት ይቻላል::

በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት አንድ የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ተቋማዊ አቋሟ ተከፋፍሎ የነበረው የመተባበር እና የአንድነት መንፈስ ጠፋ:: በምትኩም የውድድር እና የክፍፍል መንፈስ ተፈጠረ:: የክርስትና  ማዕከል ለነበረችው ቁስጥንጥንያ መንበር አቅም መዳከም እና በእስልምና  መወረር ክፍፍሉ ትልቅ አስተዋጽዖጾ አድርጓል:: ዘግይቶ  የተከሰተው ሉተራዊ እንቅስቃሴም ክፍፍሉ የወለደው አስከፊ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽታ ነው::  የሉተርን ተቃውሞ  ይዘት ተከትሎ  በአሁኑ ዘመን በክርስትና ስም ሕግጋተ እግዚአብሔር በገሃድ እየተጣሱ ያሉት፤ በምዕራቡ ዓለም አብያተ እምነት እየተዘጉ ወደ ጭፈራ እና መጠጥ ቤትነት እየተለወጡ ያሉት፤ በአንድ መንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር በአሁኑ ጊዜ በብዙ የሥጋ ፍላጎት የተለያየ ትርጉም እየተሰጠው ያለው እና ከዚህ ጋር ተያይዘው እየተከሰቱ ለሚታዩ  ችግሮች ዋና መነሻቸው በኬልቄዶን ጉባኤ የተፈጠረው ክፍፍል ነው:: በዘመነ ሐዋርያት ከክፍፍሉ በፊት በዓለም ድንቁርና እና ጨለማነት ተስፋ ያልቆረጠች ቤተ ክርስቲያን፤ በዘመነ ሰማእታት ሰይፍ እና እሳቱን በጽንዓት ታግሳ ያሸነፈች ቤተ ከርስቲያን፣ ከክፍፍሉ በኋላ እርስ በእርስ በሚወጋገዙ መሪዎች ተሞላች:: የዚህ ሁሉ  ችግር መነሻ የታወቀና አንድ ሆኖ ሳለ የተሳሳቱት ወገኖች ራስ ወዳዶች እና ከስህተታቸው መመለሰ የማይፈልጉ እልኸኞች ስለነበሩ የችግሩ ውጤት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ዘርፈ ብዙ ለመሆን በቅቷል:: በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖታዊ ልዩነቱ በሰው ሰውኛ ሊፈታና አንድ ለመሆን ወደማይቻልበት ደረጃ በማደጉ በልዩነት አንድነት ወደሚባለው አስተሳሰብ ተደረሰ::

ከላይ ያተትነው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የልዩነትን አስከፊ ገጽታ በአጭሩ ለማውሳት ያህል እንጂ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ላለፉት ዓመታት የዘለቀው ልዩነት ከዚህ ታሪክ ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ አይደለም:: ምክንያቱም በዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል የተከሰተው ውግዘት መነሻው አስተዳደራዊ ልዩነት መሆኑ ነው። ሆኖም ግን ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጣስ ምክንያትነት በሃይማኖት አንድ የሆኑ ወንድማማቾች ተወጋግዘው መለያየታቸው  የቤተ ክርስቲያናችን ዘመናዊ ታሪክ ጥቁር አሻራ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል። አሁን ያለውን አስተዳደራዊ ችግር ባለበት ደረጃ መፍትሔ ለመስጠት እና ይህን አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ለመዝጋት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አላስፈላጊ የሆኑና  የሚያዘናጉ ምክንያቶችን በማስወገድ፣ የተቀላጠፈ እና የማያዳግም የመፍትሔ ውሳኔ አሳልፈው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው:: አለበለዚያ ልዩነቱ ሳይፈታ በተራዘመ ቁጥር ችግሩ ወደሌላ ደረጃ የማይሸጋገርበት ምክንያት አይኖርም:: ይህም የመፍትሔውን ዋጋ እጅግ እያከበደው ይሄዳል::

ስለሆነም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን የተከተሰውን ይህንን መለያየት በእርቀ ሰላም ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረትና አባቶቻችን ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ማንሣታቸው ብሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊጀመር መሆኑ መሰማቱ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ሁሉ ያስደሰተ ነው::  ውጤቱንም በታላቅ ጉጉትና ተስፋ እየጠበቁት እንደሆነ ግልጽ ነው:: ችግሩን ለመፍታትም ካለፈው ይልቅ መጪውን፣ ጊዜያዊውን ሳይሆን ዘላቂውን፣ ሥጋዊውን ሳይሆን መንፈሳዊውን መንገድ መከተሉ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ይህን በተመለከተ ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳንም በውግዘቱ ማግስት ለዘኃለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ ዕቅበት በሚል ርዕስ ባወጣው ርዕሰ አንቀጽ ለተከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሔ አመላካች የሆነ መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል።

ለቀጣዩ  ትውልድ በአንድነት ሆኖ የተጠናከረ ሥራ የሚሠራበትን መሠረት እንጂ የልዩነት አጥር አበጅተንበት የሥራ ጊዜውን እንዳናባክንበት ዛሬ ጊዜያችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል:: መቸም ተወደደም ተጠላም ችግሩ የተፈጠረው አሁን በሕይወት ባለነው ሰዎች እንደሆነ ማንንም ምስክር እና ዳኛ ሳንጠይቅ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ እስከ ማኅበረ ምእመናን እንደየ ኃላፊነታችን መጠን ሁላችንም ስለችግሩ ምንጭ እና ውጤት የምናውቅ፤ እንዲሁም ለመፍትሔውም በተለያየ ደረጃ ኃላፊነት መውሰድ የምንችል ቋሚ ምስክሮች ነን። ይህንን ማወቃችን ደግሞ  መፍትሔውንም ለመስጠት ብዙ ውጣ ውረድ ሳይጠይቀን ነገሩን በቅንነት ይዘነው በቀላሉ ማስተካከል ያስችለናል:: ቀዳሚውን እና ተከታዩን የሚወስነው እግዚአብሔር ቢሆንም የሁላችንም ምድራዊ ኑሮ በዐረፍተ ዘመን የተገታ ነው:: ስምና  ታሪክ ግን መልካም ይሁንም አይሁን ሲወሳ ይኖራል:: ስለዚህ በተሰጠን ጊዜ ይህንን በዘመናችን የተከሰተ መጥፎ የታሪክ አሽክላ ለማስወገድ የየራሳችንን በጎ አስተዋጽዖ በማበርከት በእግዚአብሔርም በትውልድም ዘንድ ተገቢውን መልካም ዋጋ ልናገኝበት ይገባል ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም መክፈል የሚገባንን መስዋእትነት መክፈል ባልቻልን መጠንና ለእርቀ ሰላም የምንዘገይበት እያንዳንዷ ቀን የልዩነት ታሪካችንን እድሜ እየጨመረች እንደምትሄድ ልንገነዘብ ይገባል:: ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በእርሷ  የምትለያይ መንግሥት አትጸናም” (ማቴ 15፡25) እንዳለ የልዩት ዘመን በጨመረ መጠን አሁን ካለው በባሰ የቤተ ክርስቲያን እድገት እየተደናቀፈ፤  ኃይላችንም እየተበታተነ ለአሕዛብ መሣለቂያ ለጠላትም መሳቂያ መሆናችን የማይቀር ይሆናል::

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሴተ ሐሙስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ሰብስቦ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ካቀበላቸው በኋላ ሰፊ የማበረታቻ እና  የማንቂያ  ትምህርት ሰጥቷቸዋል::  ከትምህርቱ እና ከመመሪያው ዋና ዋና ጉዳዮች ቀዳሚው ሐዋርያቱ የእርስ በእርስ ፍቅር እንዲኖራቸው የሚያዝ ነው:: (ዮሐ 15):: ጌታችን ሐዋርያት እንዲፋቀሩ ብቻ አስተምሮ  አልተዋቸውም:: በአስቆሮቱ ይሁዳ መሪነት ለመጡት ወታደሮች በፈቃዱ እራሱን አሳልፎ  ከመስጠቱ በፊት ስለሐዋርያቱ ወደ ባሕርይ አባቱ ባሳረገው ጸሎት ሐዋርያት ከዓለም እንዲጠበቁ ብቻ ሳይሆን በእርሱ በጌታችን እና በባሕርይ አባቱ በእግዚአብሔር አብ መካከል ፍጹም አንድነት ህልው እንደሆነ ሁሉ በእነሱም በሐዋርያት መካከል የሐሳብ ልዩነት እንዳይኖር አሳስቧል:: (ዮሐ 17 : 11):: ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችንም ይህንኑ ስለ ፍቅር የተሰጣቸውን መመሪያ የአገልግሎታቸው መገለጫ አድርገው ተጠቅመውበታል:: የቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችንን መንበር የወረሱ ብፁዓን አባቶቻችንም ይህንኑ የጌታችንን መመሪያ ተከትለው የጀመሩትን የእርቅ ሂደት በቅርብ ጊዜ ፈጽመው ደስታችንን ፍጹም እንደሚያደርጉት ተስፋችን ጽኑ ነው:: አሁንም ዋናው የመፍትሔ ቁልፍ ያለው በአባቶቻችን እጅ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። ስለሆነም የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ጠብቀው የተጣመመውን ማቅናት፤ የተዛባውን ማስተካከል የሚጠበቀው በዋናነት ከመንጋው ጠባቂዎች ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ነው።  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አባቶቻችን  የአገልጋዮችና የመላውን ምእመናንና ስሜት አገናዝበው ወደ ዕርቀ ሰላም ለመሄድ ያሳዩት አዝማሚያ የሚያስመሰግናቸው ነው።

እንግዲህ ተወጋግዞ ማዶ ለማዶ  መተያየቱ ለጠላት ካልሆነ ለማንም አይጠቅምም:: ስለሆነም ጠላት እንዲያፍር እግዚአብሔርም ደስ እንዲሰኝ አባቶቻችን የእርቅ ሂደቱን ምሩልን፤ በየደረጃው ያለን የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ፈለጋችሁን እንከተላለን:: ባለፉት የመለያየት ዘመናት ከመነሻው ጀምሮ  በሂደቱ ውስጥ የተበደሉ ወገኖች በቡድንም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፤ ሆኖም በፊት የደረሰባቸውን በደል ከኅሊናቸው ፍቀው ይቅር የሚሉት  ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም በመሆኑ በእርቅ ሂደቱ ውስጥ የግል ብሶታቸው እንቅፋት ሊሆን አይገባውም:: እንኳን ለዚህ ለታላቅ ዓላማ መሣካት ቀርቶ  በግል ደረጃ  በሚካሄድ ሽምግልና እንኳን የመታረቅ ዋናው መገለጫው ያለፈውን ቅሬታ ከልብ ፍቆ በእውነት መንፈስ እና በቀና ልቡና የፍቅር ሕይወትን ገንዘብ ማድረግ ነው:: ስለሆነም የተወሰኑ ሰዎች ላይ በማተኮር የችግሩም ይሁን የመፍትሔው ባለቤቶች እነሱን ብቻ አድርገን ሳንመለከት ሁላችንም በቤተ ክርስቲያን ባለን የተሳትፎ  መጠን እንደየደረጃችን ለአንድነቱ ልንተጋ ይገባናል::

ማኅበረ ቅዱሳንም የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሂደት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እውን እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት በሚችለው ሁሉ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ለሁለቱም ወገን ላሉት ወገኖችና የዕርቀ ሰላም ሂደቱን በማስተባበር ላይ ለሚገኙት ኮሚቴዎች  እና መላው ምእመናን እያረጋገጠ ለዕርቀ ሰላሙ እውን መሆን ሁላችንም በጸሎት እንድንተጋ ያሳስባል::

እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ያጽናልን። አሜን።


Written By: admin
Date Posted: 12/24/2011
Number of Views: 8988

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement