ይህን መዝሙር እያሰማን እርቅና ሰላም የተደረገበትን የልደት በዓል ስናከብር በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከልም የተጀመረውም የእርቅ ሒደት ፍሬ እንዲያፈራ ልናበረክተው የሚገባንን አስተዋጽዖ ሁላችንም ባለን ድርሻ እና ኃላፊነት ልንወጣ ይገባናል:: ሁሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ይህ የመለያየት ግንብ ፈርሶ ወደ ቀደመ ታሪካችን እና ክብራችን እንመለስ ዘንድ፣ ምስጋናችንም በአንድ መንፈስ ወደ አርያም ያርግ ዘንድ ለእርቀ ሰላሙ የምንችለውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል::
ጌታችን ብርሃነ ልደቱን በገለጸባት በዚያች የተመረጠች ሌሊት ቅዱሳን መላእክት እና የአዳም ልጆች ታርቀው በአንድ መንፈስ አዲስ ምስጋና እንደተቀኙ ሁሉ እኛም በአስተደዳደር የተለያየችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መታወቂያዋ እና ክብሯ ወደ ሆነው ወደ አንድነትዋ እንድትመለስ ተስፋችንን የፍቅር መሠረት በሆነ በልዑል እግዚአብሔር አድርገን፣ ተማኅጽኖአችንን ወደ አርያም ልናሳርግ ይገባል::
ይህ ጥሪ የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ጥሪ አይደለም:: የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባል የሆን ክርስቲያን ሁሉ የሚመለከት ጥሪ ነው:: ስለሆነም ሁላችንም የልደቱን በዓል ስናከብር አንድነታችንን እየናፈቅን፣ የእርቅ ሒደቱም እንዲፋጠን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን ተሳትፎ እያደረግን ሊሆን ይገባል:: የእርቅ ሂደቱን የሚያስተባብሩትንም አካላት በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልንደግፋቸው ይገባል::
በማይመረመር ረቂቅ ጥበቡ ከእመቤታችን ነፍስ እና ሥጋን ነስቶ ብርሃን ልደቱን የገለጸልን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በፍጹም አንድነት እንደዘመሩት መላእክትና እረኞች እኛም በስሙ የተጠራን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በአንድነት ሆነን የምንዘምርበት እና የምስጋና መስዋዕት የምናሳርግበትን ጊዜ እንዲያቀርብልን እንመኛለን:: ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳንም የእርቁን ሒደት በትኩረት እየተከታተለ ለተፈጻሚነቱም የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑን እየገለጽን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብርሃነ ልደቱ ረድኤት በረከት ይክፈለን እንላለን::
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል