View in English alphabet 
 | Thursday, March 28, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ - ትርጉሙ - መልእክቱ

 
ምሥጢር
በዚህ ርዕስ ጉዳይ የምናየው በብሉይና በሐዲስ የተነገረውን እያመሰጠረ፣ በብዙ አምሳልና ትንቢት ይነገር የነበረውን የአምላክን ከድንግል መወለድ፣ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር እያዛመደ የሚናገረውን ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናያለን፡፡

ብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዑ ለአብርሃም አብ፣
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ፣
ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ፣
ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ››
 
ትርጉም
‹‹አሕዛብ በአንቺ የተባረኩብሽ፣ የአብርሃም የግዝረትና የዘሩ ምልክት አንቺ ነሽ፡፡ የድንግልናሽ ጽጌ በግዕ (በግ) የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ማርያም ሆይ የተወደደውን ኮከብ የወለድሽ የያዕቆብ ምሥራቅ ነሽ፡፡››
 
እግዚአብሔር አብርሃምን ከሀገሩና ከወገኑ ተለይቶ እርሱ ወደሚያሳየው ሀገር እንዲሄድ ካዘዘው በኋላ ‹‹በዘርከ ይትባረኩ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር፤ በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ› (ዘፍ 12÷3) ብሎ ቃል ኪዳን፣ ከአሕዛብ የሚለይበትና እግዝአብሔርን የሚያመልክ መሆኑ የሚታወቅበት ምልክት የሚሆን ግዝረትን ሰጠው፡፡ እንዲህ ሲል፡- ‹‹በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፡፡ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ በእኔና በአንተ ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል›› (ዘፍ 17÷9-11)፡፡ ‹አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ› የሚለው ተስፋ በይስሐቅ አልተፈጸመም፡፡ ምክንያቱም በሰው ላይ የተጣለው ርግማን በይስሐቅ አልተወገደም÷ በይስሐቅ የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ በተሰዋና ዓለምን ባዳነን ነበር፤ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መምጣትና መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ስለዚህ ያ በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ተብሎ ለአብርሃም የተነገረው ተስፋ የተፈጸመው ክርስቶስ ከእመቤታችን በድንግልና ሲወለድ ወይም ሰው ሲሆን ነው፡፡ አምላክ ሊዋሐደው የሚችል ንጹሕ ሥጋና ነፍስ ይዛ ተገኝታ ለአብርሃም የተነገረውን ተስፋ እንድናገኝ አድርጋለችና፡፡

 ለአብርሃም የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ያን ጊዜ ያመነና ያላመነ የሚለው በግዝረት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል መለያው ምልክቱ ጥምቀት ነው፡፡ ከአሕዛብ የሚለየንን፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች የሚያደርገንን ጥምቀት ተጠምቆ ‹‹ተጠመቁ›› ያለንን ክርስቶስን ያገኘነው ከእመቤታችን በመወለዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው፡-

‹ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርሁ ለአብርሃም አብ› ያለው፡፡
 
ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአብርሃም ዘር ነው (ዕብ 2÷16)፡፡ ክርስቶስን ያስገኘች እመቤታችን የአብርሃም ዘር መሆኗን ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ አንድ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ በእርሷ አማናዊ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡
 
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ
ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርዓው ኮከብ፡፡
 
ይስሐቅ ለመሥዋዕት በቀረበ ጊዜ ከመሞት ያዳነው በግ ከዚህ መጣ ሳይባል በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል (ዘፍ 22÷13)፡፡ አብርሃም በጉን ሰውቶ የታሰረውን ይስሐቅን ፈትቶታል፡፡ ይስሐቅ የዓለሙ ምሳሌ ሲሆን በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በጉ የተያዘበት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉ በዕፀ ሳቤቅ ታስሮ እንደተገኘ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ነው፡፡ ያ በግ ቤዛ ሆኖ ይስሐቅን ከሞት እንዳዳነው ሁሉ ክርስቶስም ስለ ዓለሙ ኃጢአት ሞቶ ለዓለሙ ቤዛ ሆኖአል (ዮሐ 3÷16-17)፡፡
 

ደራሲው የተምሳሌቱን መፈጸም ካስረዳ በኋላ ‹ወምስራቅ ዘያዕቆብ. . .› ይላል፡፡ በለዓም ‹‹ኮከብ ይሰርቅ እምያዕቆብ፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ኃጢአተኝነትንም ከእስራኤል ያስወግዳል…›› ብሎ ትንቢት የተናገረለትን ኮከብ የወለደች እርሷ መሆኗን የሚያስረዳ ነው (ዘኁል 22÷17፣ ኢሳ 27÷9፣ 59÷20፣ ሮሜ 11÷26)፡፡

ሰመዩኪ ነቢያት እስርእዩ ኅቡአተ፣ 
ገነተ ጽጌ ዕፁተ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፣ 
እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተዳዊት ትእምርተ 
ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ 
ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ፡፡ 

ትርጉም
‹‹ምሥጢርን ያዩ ነቢያት የተዘጋች የምሥራቅ በር የታተመች ገነት እያሉ ጠሩሽ፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በኢሳይያስ አማካኝነት በግልጽ ተናገረ፡፡››
 
ከሩቅ ያለውንና ወደፊት የሚሆነውን በትንቢት መነጽር አቅርበው ያዩና ሥውሩ ምሥጢር የተገለጠላቸው ነቢያት ‹‹ገነተ ጽጌ ዕፁተ፣ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፤ የታተመች ፈሳሽ የተዘጋች የምሥራቅ በር›› እያሉ ጠሩሽ፡፡
 
ሰሎሞን በመኃልዩ፡- ‹እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈች ገነት÷ የተዘጋች ምንጭ፣ የታተመች ፈሳሽ ናት›› ይላታል፡፡ በዚህም እመቤታችንን፡-
ሀ/ በተቈለፈች ገነት
ለ/ በታተመች ምንጭ መስሏታል፡፡ ለምን?
 
ሀ/ የተቈለፈች ገነት
በውስጥዋ አትክልት ሲኖር ነገር ግን ወደዚህች ቦታ የሚደርስ የለም፣ ተቈልፏልና፡፡ እመቤታችንም በንጽሕናና በድንግልና የታጠረች ስለሆነች ከእርስዋ የተወለደ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
 
የተክል ቦታ ዘር ሳይዘራባት ወይንም ተክል ሳይተከልባት እንዲሁም የሚንከባከበው ሳይኖር ሊያፈራ አይችልም፡፡ ይህች ገነት ምንም ነገር የማይደርስባት የተቆለፈች ስትሆን አትክልት ግን አለባት፡፡ እመቤታችንም በድንግልናና በንጽሕና የፀናች ስትሆን እንበለ ዘር (ያለ ወንድ ዘር) ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡
   
ለ/ የታተመች ምንጭ
ምንጩ የታተመ ሲሆን ነገር ግን ውኃ ያለው ነው፡፡ እመቤታችንም በድንግልና የፀናች ስትሆን በእናትነት ክርስቶስን ወልዳለች፡፡ ሕዝቅኤልም ‹‹ወርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ፣ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦኦ ዘእንበለ እግዚአ ኃያላን ቦአ ውስቴታ ወወጽኣ…››፡፡
 
‹‹ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል› አለኝ›› ይላል (ሕዝ 4÷1-3)፡፡
 
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ማለቱ ከሦስቱ አካል አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ፍፁም ሰው ሆኖ ከእርስዋ ተፀንሶ ተወልዷልና ነው፡፡
 
ይህ ሕዝቅኤል ያየው ሕንፃ በጥሬ ትርጉሙ ተወስዶ ቤተ መቅደስ ነው እንዳይባል ቤተ መቅደስ የሚሠራው ሕዝቡ አምልኮቱን ሊፈጽምበት ስለሆነ ከተሠራ በኋላ ለምን ይዘጋል? ‹በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ› እንዲል (ዘጸ 25÷8)፡፡ 

ይኸው ነቢይ ስለ ቤተመቅደስ በተናገረበት ቦታ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የደኅንነቱን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት›› ይላል (ሕዝ 46÷12)፡፡ ሰሎሞንና ሕዝቅኤል ስለ እርስዋ የተምሳሌትነትና በትንቢት የተናገሩላት እርስዋ ድንግል ማርያም መሆኗን ከዘከረ በኋላ ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔርም ምልክት መስጠቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡

‹‹እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለብተ 
ዳዊት ትእምርተ ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዱ ሕይወት 
ኢሳይያስኒ ነገረ ከሡተ›› ይላል፡፡ 

ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች›› (ኢሳ 7÷13-14) በማለት እግዚአብሔር ሰውን ይቅር የማለቱና የሰጠውን ተስፋ የመፈጸሙ ምልክት የእመቤታችን ክርስቶስን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለድ መሆኑን ተናገረ፡፡
 
መልአኩ ለእረኞች የጌታችንን መወለድ ብሥራት ከነገራቸው በኋላ ሄደው እንዲያገኙት ሲልካቸው ‹‹ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፣ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ›› ነበር ያላቸው (ሉቃ 2÷12)፡፡ ሰብአ ሰገልም ‹‹ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት›› (ማቴ 2÷11)፡፡ የድኅነታችን ምልክት የክርስቶስ በድንግልና ከእመቤታችን መወለድና መታየት ነው፡፡ እኛም እንደ ሰብአ ሰገል እውነተኛውን ክርስቶስን የምናገኘው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ምልክትም ናት፡፡ ክርስቶስን በእኛ ባሕርይ ከመውለዷም በላይ በስደቱ፣ በመዋዕለ ትምህርቱ፣ በስቅለቱ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ሲያድል ሁሉ አልተለየችም፡፡ ስለዚህ እኛም ረቂቅ ምሥጢርን ዐይተው በተለያየ ስያሜ እንዳመሰገኗት ነቢያት ልናመሰግናት ይገባል፡፡ ይኸውም የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፡፡ እርስዋማ ምን ጊዜም የተመሰገነች ናት፡፡
 
ማዕረረ ትንቢተ ማርያም ዘመነ ጽጌ እንግዳ
ወዘመነ ፍሬ ጽጋብ ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ
ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁ ለይሁዳ
ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊብ ፀዓዳ፡፡
 
ትርጉም
በመከር ጊዜ አበባ፣ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡ ‹የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ፣ የኤልዳ ነቢይ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዐዳ ወተት ይፈሳል ብሎ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፣ ተፈጸመ፡፡ እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውን ‹አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል› የሚለው ቃል እውነት ሆኗል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ› በማለት ተናግሮአል (ዮሐ.4÷37-38)፡፡ ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ ለፍሬ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነም ‹ማዕረረ ትንቢት› የትንቢት መካተቻ ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች› እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ በአበባ ትመሰላለች፡፡
 
ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ ‹ወዘመነ ጽጌ እንግዳ - እንግዳ የሆነ አበባ› አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ‹ብኪ ተአምረ ዘይቤ ነቢየ ኤልዳ፣ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውጋሪሁ ለይሁዳ፣ ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊበ ፀዓዳ›› በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡
 
ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኅብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጐበኛቸውና ረሃቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ ‹ብዙ መብል ትበላላችሁ÷ ትጠግቡማላችሁ፣ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፣ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ÷ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ÷ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ› (ኢዩ 3÷18፣ 2÷26)፡፡
 
‹ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአግሪሁ ለይሁዳ 
ጸቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ›

ያለው ይህም ማለት ነቢዩ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮችና ኮረብቶች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል÷ ይመነጫል ያለው በአንቺ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ክርስቶስን በወለደች ዕለት መሪሩ ጥሞ፣ ይቡሱ ለምልሞ ተገኝቷል፡፡ ይህ ለጊዜው ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከእርስዋ በነሣው ሥጋና ደም ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ከልጅነት ተራቁቶ፣ በረሀበ ነፍስና በጽምዓ ነፍስ ተይዞ የነበረውን የሰው ልጅ ከጐኑ ውኃን ለጥምቀት፣ ሥጋውንና ደሙን ምግበ ነፍስ አድርጎ የአምስት ሺህ አምስት መቶውን ዘመነ ረሀብ እንዳስወገደልን ያስረዳል፡፡

አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እምአንክሮ
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ
እለ ያማስኑ ለዓፀደ ወይንነ ወፍሮ
ናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ
 
ትርጉም
‹‹እመቤታችን ማርያም ሆይ አርምሞሽ ከማድነቅ በላይ ሆነ÷ በማድነቅ የማይፈጸም ሆነ፡፡ … የወይን ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች ለማጥመድ (ለመያዝ) ፍጠኚ፡፡›
 
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው ነበር›› (ሉቃ.2÷51) ሲል የእመቤታችን አርምሞ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ ገልጿል፡፡ እመቤታችን ማንም ፍጡር ያልሰማውን ብሥራተ መልአክ የሰማች÷ ለማንም ያልተደረገውን በድንግልና መጽነስና መውለድ የታደለች÷ ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲመሰገንባት የመላእክትን ቅዳሴ የሰማች ፈጣሪዋን የመገበች፣ ከሰው ወገን ይቅርና ከሱራፌልና ከኪሩቤል የሚበልጥ ክብርና ጸጋ የታደለች ስትሆን እርሷ ግን በዚህ ዓለም ስትኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ከማኖር በስተቀር ይህንን አየሁ÷ ይህንን ሰማሁ አላለችም፡፡ ሔዋን ዕፀ በለስን ወደ መብላትና ጸጋዋን ወደማጣት ያደረሳት ለእርስዋና ለአዳም ብቻ የተነገረውን ምሥጢር አውጥታ ለዲያብሎስ በመናገርዋ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን ሁሉን በልቧ መዝገብ በመያዟ የተመሰገነች ሆነች፡፡
 
ከክርስቶስም ሆነ ከእመቤታችን የተማርነው አርምሞን ነው፡፡ ክርስቶስን ጲላጦስና ሊቃነ ካህናቱ ከየት መጣህ? ማነህ? ትምህርትህስ ምንድነው? እያሉ ሲጠይቁት ዝም ነው ያላቸው፡፡ ልሰቅልህ ሥልጣን አለኝ ሲለው ብቻ ነው መልስ የመለሰለት፡፡ ስለዚህ እኛም ከአባታችን ከክርስቶስና ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያየነውን አብነት ማንሣት ይገባናል (ዮሐ.19÷2፣ ማቴ.27÷14)፡፡
 
የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የእመቤታችንን አርምሞ ከአደነቀ በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹እሥግሩ ለነ ቈናጽለ ንዑሳነ እለ ያማስኑ ዓፀደ ወይንነ - የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን›› (መኃ.2÷15) እንዳለ የወይን ቦታ የተባለ የሕግ መጠበቂያ ልባችንን ሊያበላሹ ውር ውር የሚሉትን በቀበሮ የተመሰሉ መናፍቃንንና አጋንንትን እንድታስታግስልንና እንድታስወግድልን ይጸልያሉ፡፡
 
ትመስል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ
ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ
ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ
እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ
ለእለ በሰማይ ወምድር ዘከንኪ ዕረፍተ፡፡
 
‹‹ማርያም ሆይ እናትሽ (ሐና) ጽጌያት የተፈጠሩባትን ሦስተኛዋን ቀን፣ ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛውን ቀን (ረቡዕ)፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን የፈጸመባትንና ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡››
 
እግዚአብሔር በዕለተ ሠሉስ (በ3ኛው ቀን) ዕጽዋትን ፈጠረ (ዘፍ.1÷13)፡፡ ከእነዚህ ዕጽዋት ጽጌያት (አበቦች) ከጽጌያት ደግሞ ፍሬ ይገኛል፡፡ ቅድስት ሐናን ጽጌያት በተፈጠሩበት በዕለተ ሠሉስ÷ እመቤታችንን በጽጌ፣ ጌታን ደግሞ ከጽጌው በተገኘው ፍሬ መስሏቸዋል፡፡ በአራተኛው ቀን (በዕለተ ረቡዕ) ፀሐይንና ጨረቃን፣ ከዋክብትን ፈጠረ፡፡ ሐናን በዕለቱ፣ እመቤታችንን በፀሐይ መሰላቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን (በሰንበት) ለሰው ሁሉ ዕረፍት እንዲሆን ለአብነት እግዚአብሔር አረፈ ተባለ፡፡ በዚህች ዕለት ሰው ሁሉ ከሥጋዊ ድካምና ውጣ ውረድ አርፎ ፈጣሪውን እያመሰገነ ይውላል፡፡ በእመቤታችንም ሰው ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ አርፎ ተግባረ ነፍስ እየሠራ ፈጣሪውን ‹ወሠርዓ ሰንበተ ለሰብእ፣ ዕረፍተ ሰንበትን ለሰው ዕረፍት ሠራ› እያለ ሲያመሰግን ይውላል፡፡
 
በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ
ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ
ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ
ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ
ወበጸዳሉ አብርሃ ጽልመተ
 
ትርጉም
‹‹በአንቺ ላይ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ለሰው የአካሉን ሦስትነት ገለጸ÷ አስረዳ፡፡ ድንግል ሆይ ጽጌሽ (ልጅሽ) ተአምራቱን ገለጸ÷ አስረዳ፡፡ በብርሃኑም ጨለማን አራቀ፡፡››
 
እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን በግልጽ ያሳየው በእመቤታችን÷ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ነው፡፡
ሀ/ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበሥራት እንዲህ አላት ‹መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ፣ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ - መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል÷ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል›› (ሉቃ.1÷35)፡፡
 
መንፈሰ እግዚብሔር ብሎ መንፈስ ቅዱስን፣ የልዑል ኃይል ብሎ ወልድን፣ ልዑል ብሎ አብን በማንሣት ሦስትነታቸውን አስረዳ፡፡ እመቤታችን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ ሊዋሐድ፣ አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ እናት ለመሆን እንድትበቃ በማድረግ ሦስቱም ተሳትፈዋል፡፡
 
ለ/ በዮርዳስ ‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ÷ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው› አለ፡፡ (ማቴ.3÷16-17)፡፡ 
ወልድ በተጠማቂነት÷ አብ በደመና ሆኖ ልጄ ነው እያለ ሲመሰክር÷ መንፈስ ቅዱስ ደግመ በርግብ አምሳል ሲወርድ በአንድ ጊዜ ታይተዋል፡፡ አንድ ገጽ የሚሉ ሰባልዮሳውያን ላይጠገኑ ተሰበሩ፡፡ አንዱ ራሱ በተለያየ ስም ተጠራ እንዳይሉ በአንድ ጊዜ ሦስቱም በየራሳቸው መገለጫ ወልድ በተዋሐደው ሥጋ÷ አብ በደመና÷ መንፈስ ቅዱስ በርግብ ተገለጡ፡፡
 
ሐ/ በደብረ ታቦርም አብ በደመና ሆኖ ‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት› በማለት ተናግሮአል (ማቴ.17÷1-8፣ 2ኛጴጥ.1÷17-19)፡፡
 
ዕፀ ደንጐላ ዘቈላ ወአኮ ዘደደክ
ዘጸገይኪ ጽጌ በማዕከለ አይሁድ አሥዋክ
ተአምረ ድኂን ማርያም ዘልማድኪ ምሒክ
መሐክኒ ለምእመንኪ እምፃዕረ ኵነኔ ድሩክ
ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ
 
ትርጉም
‹እሾህ በሆኑ አይሁድ መካከል ያለሽ የደጋ ያይደለሽ የቆላ የሱፍ አበባ ማርያም በአንቺ መታመኔ በከንቱ እንዳይሆንብኝ እኔን ምእመንሽን (የታመንኩብሽን) ከክፉ ኩነኔ አድኝኝ÷ አንቺ ምሕረት ልማድሽ ነውና፡፡›
 
በመኃልይ መጽሐፉ ሰሎሞን ‹ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማዕከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኅቤየ በማዕከለ አዋልድ፣ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ÷ እንዲሁ አንቺ ነሽ› ይላል (መኃ 2÷2)፡፡
 
የቆላ ሱፍ ዙሪያውን እሾህ ቢከብበውም ከማበብና ከማፍራት ወደኋላ አይልም፡፡ እመቤታችንም ብዙ ተአምር እያለ በማያምኑና ሁልጊዜ ምልክትን በሚፈልጉ በክፉዎች አይሁድ መካከል መሆኗ በሃይማኖት ከማበብና ፍሬ ትሩፋት ከመሥራት አልከለከላትም፡፡ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግልም የሰሎሞን የትንቢት ቃል እመቤታችን በአይሁድ መካከል ፍሬ ክርስቶስን በማስገኘቷ መፈፀሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህን ትንቢቱንና ፍጻሜውን ካስረዳ በኋላ ‹መሐክኒ ለምዕመንኪ እምፃዕረ ኵነኔ ድሩክ፣ ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ - በአንቺ እናትነትና ቃል ኪዳን የምታመን እኔን ከክፉ ፍርድ አድኝኝ፤ በአንቺ መታመኔና አንቺን ተስፋ ማድረጌ ለከንቱ አይደለምና በማለት ጸሎቱን ያቀርባል፡፡
 
እስከአሁን በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው የማኅሌተ ጽጌ ድርሰት እጅግ በጣም በምሥጢርና በኃይለ ቃል የታጀበና ልዩ የሆነ ውበትና ጣዕም ያለው ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የሚቻለው እንዳለ ግእዙን ማንበብ፣ መረዳት ሲቻል ነው፡፡ እንኳን በግጥም መልክ የተደረሰ ድርሰት ይቅርና ተራ ንባብና ድርሰት እንኳን ሲተረጉሙት መንፈሱን መልቀቁ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ይህ የቅኔ ዓይነት አካሄድ ያለው ድርሰት ሲተረጐም እየተፍረከረከ ትክክለኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ፍዝ ይሆናል፡፡
 
መልክዐ መልክዖችን መተርጐም ችግሩ ይህ ነው፡፡ የአማርኛው ትርጉም መልእክቱን አልችል ይላል፡፡ ሆኖም የማኅሌተ ጽጌን መንፈሱን ለመግለጽና ስለ ምንነቱ መጠነኛ ግንዛቤ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ለመግለጽ ተሞክሮአል፡፡
 
ይህም የእግዚአብሐርን ጸጋ ሁላችንም በመቅረብ እንድናውቅና ማኅሌተ ጽጌ በመጸለይና ማኅሌቱን በመቆም የእመቤታችንን በረከትና ረድኤት የልጇን የክርስቶስን ምሕረት ለማግኘት ያበቃናል፡፡ ለዚህም እመ አምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ አትለየን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚብአሔር  

Written By: host
Date Posted: 12/18/2007
Number of Views: 7405

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement