View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ - ትርጉሙ - መልእክቱ

 
ታሪክ
በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሄድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥእልኪ ድንግል እዘይን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡
 
ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልቧ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስላዘነባት ልጅ ሳትወልድ ሞተች (ሳሙ 6÷12-23)፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ ‹‹ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ›› ዳዊት ‹‹ለእመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ››፤ ‹‹ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ፣ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ - ሜልኮል በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ ይሁን›› የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የእመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያክል የተረገሙ ይሆኑ? እነዚህም ‹‹በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ›› (መዝ 30÷18) ባለው ርግማን የተረሙ ናቸው፡፡
 
እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ሥቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣሕል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ ስዕምተ፡፡

አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ድኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያገኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር ብሎ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባዔ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው (ለአውሎጊስ) እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደሉ የማይፈርድ ጭርሱን ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከሥዕለ ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ እመቤታችን ልጇን ወዳጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡

አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ ‹‹ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ›› ማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባን እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡
 
ኦ ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢተኃሥሢ፣
እመንበረ ላዕክኪ ቢምዕር ከመገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣ 
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡

የእመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው እጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል ‹‹ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው›› ቢሉት ‹‹እኔም እንደርሰ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ፣ ከእርሱ በምን አንሳለሁ?›› በማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ታሪክ ነው፡፡

‹‹ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጂ፣ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ፣ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተበቀልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኵያን ኀጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን (ማለት የልጅሽን) ኀይል ይዘሽ ተነሽ›› በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም እመቤታችን እኛንም ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡
 
በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒኪ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አጺዋ፣
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጤዋ፡፡
 
አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋች ገነትን ‹‹እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣ ያለ አንቺ ጽጌ (ያለ ክርስቶስ) በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም›› (ዘፍ 3÷24)፡፡ ‹‹ካንቺ በተገኘ በክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች›› ይላል፡፡
 
በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ ክርስቶስ ሰው መሆንና በመስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ ክርስቶስ ደግሞ ከእመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት ‹‹መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ›› (ኢሳ 46÷1) እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽዮን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡  

Written By: host
Date Posted: 12/18/2007
Number of Views: 6349

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement