View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጉባኤ ተካሔደ

የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጉባኤ ተካሔደ

• 20ኛ የምሥረታ በዓሉም ተከበረ

(ዴንቨር፣ ኮሎራዶ)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከሉ በየዓመቱ የሚያካሒደው ጠቅላላ ጉባዔ የዚህ ዓመት ስብሰባ ግንቦት 18-19/2004 ዓ.ም በኮሎራዶ ግዛት የዴንቨር ከተማ ተካሔደ። በመላው አሜሪካ ከሚገኙ 11 ንዑሳን ማዕከላት (ቀጣና ማዕከላት) እና 2 ግንኙነት ጣቢያዎች የመጡ አባላት በተሰበሰቡበት በዚህ ጉባኤ ላይ ከዋናው ማዕከል የተወከሉ ሦስት ልዑካን፣ የካሊፎርኒያና የምዕራብ ስቴቶች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ፣ አበው ካህናት እና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በዓመታዊ አገልግሎት ሪፖርትና ዕቅድ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሒዷል።

በቅዳሜ ውሎው የ2003-2004 ዓ.ምሕረት የአገልግሎት ዘመን የአገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ውይይት ተደርጎበታል። ዓመቱ ማኅበሩ አገልግሎት የጀመረበት 20ኛ ዓመት እንደመሆኑ ያንን ለማዘከር የተዘጋጁ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል። “ማኅበረ ቅዱሳን በ20 ዓመት አገልግሎቱ ያተመው አሻራ” (The Legacy of Mahibere Kidusan) እና “የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በሰሜን አሜሪካ” የሚሉት ጥናታዊ ጽሑፎቹ ማኅበረ ቅዱሳን በሰጣቸው አገልግሎቶች እና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባበረከታቸው ዐበይት ነጥቦች ላይ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን በሰ/አሜሪካም ደረጃም ያለፈበትን፣ የሠራውን እና ሳይሠራው የቀረውን በዝርዝር በማንሣት ውይይት ተደርጎበታል።

በቅዳሜው ታሪካዊ ዳሰሳ ላይ ተመርኩዞ በቀጠለው የእሑዱ ጉባኤ ማኅበሩ በተለይ በሰሜን አሜሪካ ሊከተለው ስለሚገባው የአገልግሎት መስመር ስልታዊ ማሳያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በሚቀጥለው ዓመትም መሥራቸው የሚገባው አገልግሎት ዝርዝር ቀርቦ ጉባኤው አጽድቆታል።

ለጉባኤው ድምቀት ሰጥተው ከነበሩት አጀንዳዎች አንደኛው በሆነው በዋናው ማዕከል ልዑካን ሪፖርት ማኅበሩ በመላው ዓለም እየሰጠ ባለው አገልግሎት የፈጸማቸው ተግባራት የቀረቡ ሲሆን ጉባኤተኛው በከፍተኛ ደስታ ተቀብሏቸዋል። በጠረፋማ የአገራችን አካባቢዎች እየተሰጠ ያለው ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ውጤቱ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው የገለጡት ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ የሦስተኛውን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የዘወትር ጥያቄ በማስታወስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው በየዓመቱ በሚደረገው የመንበረ ፓትርያርኩ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ “የዳር አገሯ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ናት?” ይሉ እንደነበር በማስታወስ በጠረፋማ አካባቢዎች የሚካሔደው ሐዋርያዊ አገልግሎት ታላቅ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል። “ዳሩ እሳት፣ መሐሉ ገነት” የሚለውን አባባል እውነታ በማጉላት “ዳሩ ሁል ጊዜ እሳት መሆን የለበትም፤ ዳሩንም ገነት ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።

ጉባኤው 20ኛውን ዓመት ለማዘከር ባዘጋጀው መርሐ ግብር ከማኅበሩ ምሥረታ ጀምሮ ለነበሩ አባላት ማስታወሻ ተሰጥቶ ታሪኩን፣ አነሣሡን እና አገልግሎቱን እንዲሁም አባላቱ የከፈሉትን መሥዋዕትነት አስታውሷል። ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ እግዚአብሔር ለዚህ ትውልድ ያደረጋቸውን ገቢረ ተዓምራት በማንሣት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው ሲል ጉባኤተኛው ስብሐተ እግዚአብሔር አድርሷል። ታሪኩን ያስታወሱትና ልብ የሚነካ እና አባላቱን በዕንባ እንዲሰሙ ያደረገ ትምህርት የሰጡት መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው “ዝንቱ ነዳይ ጸርኀ ወእግዚአብሔር ሰምዖ - ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው” (መዝ. 33፤) ያለውን የቅ/ዳዊት ቃል አንስተው “ዝንቱ ማኅበረ ቅዱሳን ጸርኀ ወእግዚአብሔር ሰምዖ፤ ይህ ችግረኛ ማኅበረ ቅዱሳን ጮኸ - እግዚአብሔርም ሰማው” ሲሉ አስተምረዋል።

ጉባኤው እስከ እኩለ ሌሊት በዘለቀው ረዥም የዕለተ እሑድ ጉባኤው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን በማሳለፍ፣ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ በመምረጥ እና በአዲስ መንፈስ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተገባውን ቃል ኪዳን በማደስ በሚቀጥለው ዓመት በሜኔሶታ በሚደረገው 15ኛው የማዕከሉ ጉባኤ ላይ ለመገናኘት በመቅጠር “ያብጽአነ አመ ከመ ዮም” በሚል መዝሙር ተፈጽሟል። የዓመት ሰው ይበለን።


Written By: host
Date Posted: 5/28/2012
Number of Views: 5522

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement