View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ - ትርጉሙ - መልእክቱ

                                 
ጸሎት
በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

አንበርኒ ማርያም ውስጥ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሒትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ በጽጌሁ ሕይወት፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ ‹‹እንደ ማኅተም በልብህ፣ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ›› (መኃ 8÷6) ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ ‹‹አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተም ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት› እመቤታችንን ‹‹እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ›› በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ ‹‹በእንተ ርስሒትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት›› ይላል፡፡ ይኽም ማለት ‹‹አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ›› በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ ‹‹መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ›› እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡  

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረስዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ እኅሊ፣
ሥርዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ ‹‹ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ› ይላል፡፡ ጌታችን ‹‹እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም›› (ማቴ 17÷20) በማለት ላመነ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ብሎ ባበሰራት ጊዜ ‹‹ይህ እንደምን ይሆንልኛል›› አለች፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› ቢላት በፍጹም እምነት ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ - እንደቃልህ ይሁንልኝ›› በማለት ተቀበለች፡፡ ይህንንም ቅድስት  ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ ‹‹ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት›› (ሉቃ 1÷45) ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልዪልኝ በማለት የለመነው፡፡

 ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት፣
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፅት፣
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡

‹‹ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረ ኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽ በሐመልማል የታየ ማርያም ሆይ በእሳት አምሳል የታየ ጽጌ-ልጅሽ ኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡››

ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ (ዘጸ 3÷3)፡፡ ይህ የምሥጢረ ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ ሐመልማሉ የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱ አምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮት ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረጋጋት የሚያስረዳ ነው፡፡
 
ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርና የርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ መሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን ‹‹ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀቅ÷ ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ›› በማለት ያቀርባል፡፡ ይኽም ማለት ‹‹ያ ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴን ያስተስርይልኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ›› ማለት ነው፡፡
 
ዳዊት ‹‹በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል›› (መዝ 86÷7) ብሎ እንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ 

Written By: host
Date Posted: 12/18/2007
Number of Views: 6060

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement