View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

እንቁጣጣሽ፥ ፍቅር የወለደው ቃል

በሊቀኅሩያን ከፈለኝ ወልደጊዮርጊስ
በትራክት መልክ የተዘጋጀውን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ

እንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ዓውደ ዓመት፣ ዘመን መለወጫ፣ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ /ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱን/ እየተባለ ቢጠራም ሁሉም ያው አዲስ ዓመትን ከታሪክና ከትርጉም ጋር የሚገልጹ ስያሜዎች ሆነው እናገኛቸዋለን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በሦስት ሕግጋት ማለትም፦ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት /ብሉይ ኪዳን/ እና በሕገ ወንጌል /አዲስ ኪዳን/ ውስጥ ያለፈች ብቸኛ ሀገር ሆና በመገኘቷ ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር ለመሆን በቅታለች። ሕገ ልቡና ማለት የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የሚጠብቁትና የሚመሩበት የተጻፈ ሕግ ሳይኖራቸው ግን በልቡናቸው ማስተዋል ብቻ ይኖሩበት የነበረው ዘመን ሲሆን ይህም ከአዳም እስከ ሙሴ የነበረውን ዘመን የሚያካትት ነው። ሕገ ኦሪት ማለት ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች መመሪያ የሚሆን የጽሑፍ ትዕዛዝና ሕግ በሙሴ አማካይነት የሰጠበትና ሰዎችም በተሰጣቸው ሕግ መሠረት መኖር የጀመሩበት ዘመን ሲሆን ይኸውም ከሙሴ እስከ ጌታ ወደዚህ ዓለም በሥጋ መምጣት ጊዜ ድረስ ነበር። ሕገ ወንጌል ማለት ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ቆይታው ያስተማረው ትምህርት፣ የሰው ሥርዓት፣ ያደረገው ቃል ኪዳን ይህም በቅዱሳን ሐዋርያት ምስክርነትና ጽሑፍ እነሆ ለእኛ የጻፈው ወንጌል /የምሥራች/ የተሰጠበት ዘመን ሲሆን ይኸውም ከጌታ ልደት ወደፊት እስከ ዳግም ምጽአቱ የሚመጣውን ዘመን የሚያካትት ነው።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ሀገራችን በእነዚህ በሦስቱ ዘመናት ውስጥ በማለፍ የረጅም ጊዜ ታሪክና ቅርስ እንዲሁም ታላቅ የሆነ ልዩ ባሕል ያላት ብቸኛ ሀገር ከመሆኗም በላይ መስከረም አንድን የአዲስ ዓመት በዓል አድርጋ ማክበር የጀመረችው በኖኅ ልጅ በካም ዘመን ይኸውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት 2785 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ። መስከረም የሚለው ቃል ራሱ ከሁለት የግዕዝ ግሶች ተውጣጥቶ የተገኘ ቃል ሲሆን እነርሱም፦ መሐሰ = ቆፈረ እና ከረመ = ከረመ የሚሉት ሲሆኑ መሐሰ-ከረመ = መስ-ከረም ሆኖ ተገልጿል። ዝርዝር ትርጉሙ ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ እስከ ሰማይ ድረስ ሞልቶ የነበረውን ውኃ በሐኖስ፣ በውቅያኖስና በጠፈር ለሦስት ቦታ ከፍሎ ከወሰነው በኋላ ደረቁ ክፍል ይገለጥ ባለ ጊዜ መሬት ለስልሳ ተስተካክላ አባጣ ጐርባጣ ሳይኖራት መገኘቷን በማሰብ /ዘፍ. ፩፥፮-፲፣ ኩፋ. ፪፥፱/ አሁንም ክረምቱ አልፎ መስከረም ላይ ደመናው የሚገለጥበት፣ ደረቅ መሬት የሚታይበት የመጀመሪያው ወራት በመሆኑ በዚህ ተፈጥሯዊ ትርጉሙ እንኳ መስከረም ለአዲስ ዓመት የመግቢያ ወሩ ሆኖ እናገኘዋለን። /አለቃ አያሌው ታምሩ፣ “የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት”/። በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅሙ የታሪክ ጉዞዋ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ይዛ ካመጣቻቸው ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት መካከል አንዱና ደማቅ ሆኖ በየዘመኑ የሚከበረው ይኸው የእንቁጣጣሽ በዓል ነው።

የበዓሉ ድምቀት በሦስት ዓይነት መንገዶች የሚገለጥ ነው፦

  1. በቤተ ክርስቲያን በሚከናወነው ሥርዓተ ጸሎትና ዝማሬ
  2. በሕዝቡ ዘንድ በየባሕሉ ካለባበሱ ጀምሮ በሚከናወነው ድርጊትና
  3. በሐምሌና በነሐሴ ጠቁሮ የነበረው ሰማይ ብሩህ ሆኖ የሚታይበት፣ የደፈረሱት ወንዞችና ፏፏቴዎች ሁሉ ኩልል ብለው የሚጠሩበት፣ ሜዳና ተራራው ሁሉ አረንጓዴ ለብሶ በየመሃሉ በአደይ አበባ ፍንጥቅጣቂ ተውቦና ፈክቶ ዓይን የሚማርክበት፣ የጠወለጉት ጽጌያት ለምልመው፣ ዕንቡጦች ፈንድተው መዓዛቸው መላ ሀገሪቱን የሚያውድበት፣ ፍሬ የተሸከሙ የአዝርዕት ዛላዎች በየሜዳውና በየማሳው ላይ ሽው በሚለው ነፋሻ አየር ደፋ ቀና እያሉ ደረስንላችሁ በሚል መንፈስ የገበሬውንም፣ የከተሜውንም ልብ በተስፋ የሚሞሉበት፤ እውነትም አሮጌው በአዲሱ፣ ባዶነት በተስፋ የሚሞላበት ጊዜ በመሆኑ አዲስ ዓመት ደማቅ በዓል መባሉ ትርጉም ሰጪ ሆኖ እናገኘዋለን።
ወደ ጥንቷ ኢትዮጵያ ስንመለስ ደግሞ ይህንኑ የአዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ለሚወዷት እንደ እናት ለሚመለከቷት ንግሥታቸው ለንግሥት ሕንደኬ የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በራሳቸው ተነሳሽነት የከበረ ዕንቁ ለፍቅራቸውና ለአክብሮታቸው መግለጫ በሥጦታ ሲያበረክቱላት ላንቺ የሚገባሽ ለንግሥትነትሽ የሚመጥነው ዕጣ ክፍልሽ ዕንቁ ነውና ሲሉ በየዓመቱ ዕንቁ ዕጣሽ ወይም ዕንቁ ለጣትሽ በማለት ያበረክቱላት ስለነበር ፍቅር የወለደው ሥጦታ ፍቅር የወለደውን ቃል አስገኘና እነሆ እስከዛሬ ድረስ እንቁ-ዕጣሽ፣ እንቁጣጣሽ በሚለው ተለምዷዊ አነጋገር ተተክቶ አዲስ ዓመት በመጣ ጊዜ ሁሉ የጥንቱን ድንቅ ዘመን እያስታወሰን፣ አሁን ላለንበት ዘመን ደግሞ ፍቅርን እየሰበከንና እየቀሰቀሰን ይገኛል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታሪክም፣ የቅርስም፣ የጥበብም፣ የጀግንነትም፣ የኩሩነትም፣ የፊደልና የዜማም በአጠቃላይ የሁሉም ምንጭ በመሆኗ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ያላበረከተችው ሀብት፣ ያላስገኘችው ዝና የላትም። ቅዱስ መጽሐፍም ኢትዮጵያን ደጋግሞ የሚያነሳት በሃይማኖቷ ለእግዚአብሔር ባላት ፍጹም ተገዢነቷ ነው እንጂ ጠላቶቿ ወይም ምቀኞቿ ዛሬ ዛሬ በሚያወሩባት ዘመን ወለድ ወሬ አይደለም። በዚህ የተነሣ እንኳንስ የራሷ ዜጎች ቀርተው ዛሬ መላው ጥቁር ሕዝብ ባንዲራዋን እያውለበለቡ “ኢትዮጵያ የተስፋይቱ ምድራችን” በማለት የሚመኩባት ሀገሪቱ የክርስቲያን ደሴት በመሆኗና ቤተ ክርስቲያኒቱም የሁሉ ሙሉ ምንጭ መሆኗን በመረዳታቸው እነሆ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችና አሁን አሁን ደግሞ ነጮችም ጭምር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንከተላለን በማለት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እየከፈቱ የሃይማኖታችን ተከታዮችና ፈላጊዎች እየሆኑ በመገኘታቸው ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ ተረድቶ ብፁዓን አባቶችንና ሰባክያንን እየመደበ “ከበረቴ ያልሆኑ በጎች አሉኝ እነሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል” /ዮሐ. ፲፥፲፮/ የተባለላቸውን ሁሉ በማስተማር፣ በማጥመቅና በማቁረብ ዕለት ዕለት የክርስቶስን ቤተሰቦች በማብዛትና በማበራከት ላይ ይገኛል።

ታዲያ ይህ እውነታ ያልተዋጠላቸው፣ ይህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊነት አዝማሚያ ያስደነገጣቸው የውጭ ጠላቶች ቤተ ክርስቲያኒቱንም ሆነ ሀገሪቱን በጦርነት ርብርብ ሞክረው ቢያቅታቸው ለጥቅም በተገዙና በይሁዳ መንገድ በተጓዙ በራሷ ዜጎች  የዛሬ ሆድ መሙላታቸውን እንጂ የነገው ትውልድ ኃላፊነት ጨርሶ በማይሰማቸው፣ ገንዘብ እንጂ እግዚአብሔር አምላክ ያልሆናቸው፣ የጠላት ቡትቶ እንጂ የራሳቸው መልካም ነገር ሁሉ የሚያሳፍራቸው የትውልድ አረሞች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አርጅታለችና እናድሳታለን፣ ኋላ ቀር ሆናለችና ዘመነኛ እናደርጋታለን በማለት የገዢዎቻቸውን ምኞትና ሐሳብ ለማስፈጸም እነሆ ሳይሆኑ የሆኑ በመምሰል ቀሚሷን አጥልቀው፣ ወንጌሏን ጨብጠው፣ መስቀሏን አንጠልጥለው በዐውደ ምሕረቷ፣ በአስተዳደር ቤቷ ሁሉ ሳይቀር ተሰግስገው እነርሱ ከውስጥ፣ የቁራሽ ጌቶቻቸው ከውጭ በመሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሊንጧት ቢሞክሩም በአለቱ ላይ በክርስቶስ ደም ላይ ተመስርታለችና አትወድቅም አትናወጥም። እንኳንስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ልትለወጥ ልትታደስ ቀርቶ መልካሙ ኢትዮጵያዊ ባሕላችንና ወጋችን እንኳ ፈጽሞ አይቀርም ምክንያቱም በብዙ ፈተና ውስጥ አልፎ እስከዛሬ አለና ነው።

ለዚያውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንዲቷን ሃይማኖት አስመልክቶ ሲያስጠነቅቅ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም” /፩ኛ ቆሮ. ፫፥፲፩/ ብሏል:: ወንጌላዊው ዮሐንስ ደግሞ በመልእክቱ ላይ እንደጻፈው “እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።” /፩ኛ ዮሐ. ፪፥፳፬/ ተብሎ እየተነገረን ምቀኞቻችን ግን እነሆ የዘላለም ሕይወት ሊያሳጡን እየታገሉ ይገኛሉ። የመውጊያውን ብረት መቃወም ለማን እንደሚብስበት ማየት ከፈለጉ ይቀጥሉ እንኳንስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ሊለወጥ ሊታደስ ቀርቶ ተፈጥሮ እንኳ እየታደሰ ወደ ሌላ ነገር ሲቀየር አልታየም። እነሆ አዲስ ዘመን እንቁጣጣሽ በየዓመቱ ሲመጣ ለሜዳ ተራራው ውበት የሚያጐናጽፉት አደይ አበቦች እንኳ ቢጫነት ቀለማቸውን ቀይረው ጽጌረዳ ወደ መሆን አይለወጡም በየዓመቱ ያው ናቸውና። እንግዲያስ ሊለወጥ ሊታደስ የሚገባው ወይም ተሐድሶ የሚያስፈልገው ለማን ነው? ቢባል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚነግረን በኃጢአት መንፈሳዊ ሕይወቱ ላረጀ ለደቀቀ የሰው ልጅ ሁሉና በተለይ ደግሞ በሐሰትና በማታለል ትምህርት ተጠልፎ የሚጠልፈውን ሁሉ /ኤፌ. ፬፥፲፬/ ሲሆን በምክሩም መጨረሻ “ፊተኛ ኑሯችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ በአእምሯችሁም መንፈስ ታደሱ” /ኤፌ. ፬፥፳፪/ በማለት ይነግረናል።

በመሆኑም በኃጢአት ያረጀው፣ በክህደት የጎሰቆለው፣ በገንዘብ ጥቅም የታወረው ሁሉ ካለፈው ዘንድሮ ከዘንድሮውም በሚመጣው ዓመት ጉድለቱን እያስተካከለ በመንፈሱ፣ በኑሮ ዕቅዱ እየተሻሻለና እየታደሰ ሊመጣ የሚገባው እርሱ ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም። ዛሬ በዓለም ዙሪያ እንደሚታየውና እንደሚሰማው ከአንዲቷ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ወጥተው እንደ አሸን የፈሉት የክርስትና ድርጅቶች ነን ባዮች ሁሉ እምነታቸውን አድሰው አድሰው የደረሱበት ደረጃ ቢኖር ከተፈጥሮ  ሥርዓት ውጭ ወጥተው በግብረ ሰዶም የሚኖሩትን ከማጋባታቸውም በተጨማሪ እንስሳትንም “የክርስትና ጥምቀት” በማጥመቅ ላይ ባሉበት ዘመን ላይ ደርሰዋል። እንግዲህ የዛሬ ተሐድሶዎች ለእኛም የደገሱልን ይህንን ዕጣ ነው። የጌቶቻቸው ዕድገት እዚህ ድረስ መድረሱን እየሰማንና እያየን ነውና።

ይልቁኑስ የራቀው ቀርቦ፣ የከዳው አምኖ፣ በጥቅም የሰከረው ሰክኖ፣ ፍቅር ያጣው ፍቅርን ገንዘብ አድርጎ፣ የበደለው ንስሐ ገብቶ፣ ቤተ ክርስቲያኑን ሊሸጥ የሚያስማማው እርሱን ትቶ በማያወላውል አቋም ቆርጦ ቢነሳ የጥንቷን ኢትዮጵያ ከነሃይማኖታዊ መገለጫዋ በትዝታ ብቻ ሳይሆን በእውነታው ዓለም ውስጥ በገሀድና በደስታ ይኖርባታል፣ ይኮራባታል፣ ይመካባታል። የዚያን ጊዜ እንደቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ መንግሥት ከሕዝብ ጋር፣ ቤተ ክህነቱም ከምዕመናን ጋር የጠበቀ ፍቅርና መተሳሰብ ስለሚኖረው ይሄም ትውልድ በተራው እንቁጣጣሽን የመሰለ ፍቅር የወለደውን ሌላ አዲስ ቃል በመፍጠር ለትውልድ ሊያበረክት ይችላል።

እግዚአብሔር በጽኑ ሥልጣኑ ቤተ ክርስቲያናችንን እና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን። አሜን።

እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን!


Written By: admin
Date Posted: 9/9/2012
Number of Views: 3621

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement