View in English alphabet 
 | Thursday, October 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በቤተክርስቲያን አንድነትና በእርቀ ሰላሙ ዙሪያ የትምህርት እና የውይይት ጉባኤ በሲያትል ተካሄደ::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያንማኅበረ ቅዱሣን የአሜሪካ ማዕከል፣ በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ እና  በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት በዓለ ወልድ ማኅበር በሲያትል ከሚገኙት አራት ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ጋር በመተባበር በሲያትል እና አካባቢዋ የሚገኙ ካህናት አባቶች እና ምዕመናን ያሳተፈ የሁለት ቀን የትምህርት እና የውይይት ጉባኤ አካሄዱ።

በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ ጉባኤ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የተጀመረ ሲሆን የቅዳሜው መርሃ ግብር ከየአጥቢያው አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ዝማሬ አቅርበው ተጀምሯል። ከዝማሬው በመቀጠል አበው ለዚች ቅድስ ቤተክርስቲያን የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚያዘክር ስነ ግጥም ቀርቦአል።

በቅዳሜው የመጀመሪያ ትምህርተ ቀሲስ ዶር መስፍን ተገኝ “ይህ ህዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል” (ዘፀ 34፥10) በሚል ርዕስ የእግዚአብሔርን ቃል አስተላልፈዋል፣ በትምህርታቸውም ሰው በእግዚአብሔር ጽኑ እምነት ካለው የእግዚአብሔርን ስራ ሊያይ እንደሚችል አስረድተዋል:: እንደምሳሌም እንደ ራሄል ያሉትን የቀደሙትን የእምነት ሰዎች አንስተው ቅን ፍርድ ባጡ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር እንዳመለከቱ እና እግዚአብሔር ቅን ፍርድ እንደሰጣቸው አስተምረዋል::  በእኛም ዘመን የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ለማየት ድርሻን በአግባቡ መወጣት፣ በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት መኖር እና በጸሎት መትጋት እንደሚያስፈልግ አስተምረዋል::

በመቀጠልም የቀረበው ስነጽሁፍ ምዕመናን በዚህ ዘመን እያወከ ያለውን ከበግ ጋር ተመሳስለው መንጋውን ስለሚያምሱ ሃሣውያን በምሣሌ አዋዝቶ አስረድቷል። ስነጽሁፉ እንደመዝጊያ ምእመናንን ጥያቄ በመጠየቅ እነርሱም ዕለት ተዕለት በሚያጋጥማችው  የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ነቅተው መንጋውን ከሚያምሱ ተኩላዎች እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፏል።

በቅዳሜው መርሃግብር ሁለታኛውን ትምህርት መልአከ ሕይወት ቀሲስ ርገተቃል ይልማ የሰጡ ሲሆን፣ መምህሩ ትምህርታቸውን ከንጉስ ስለተላከ መልዕክተኛ ምሳሌ በመናገር ጀምረዋል። ይህ መልዕክተኛ  ከንጉስ መልዕክት ይዞ ለማድረስ በወቅቱ የመገናኛ አማራጭ ስላልነበረ በእግሩ ጉዞ እንደጀመረ እና መሀከል ላይ ሲደርስ ከድካሙ የተነሳ ጉዞውን መቀጠል እንዳለበት ወይንም መመለስ እንዳለበት ግራ እንደገባው፣ ሰዎችንም ሲጠይቅ የተለያየ አማራጭ እየሰጡት የበለጠ ግራ እንዳጋቡት በመግለጽ የእኛንም ሕይወት ከዚህ ሰው ጋር በማመሳል ‘’ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለን‘’ ገላ 6፡9   በሚል ርዕስ ሰፊ ትምሕርት ሰጥተዋል። በመጨረሻም ይህ ሰው በርትቶ ጉዞውን ቢጨርስ ከንጉሱ ሽልማትን እንደሚያገኝ እኛም በክርስትና ሕይወት የሚያጋጥመንን ፈተና ሁሉ ተቋቁመን ብንጓዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋን እንደምናገኝ አስረድተዋል። 

በመጨረሻም የቅዳሜው ውሎ ከፓርትላንድ ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤ/ክን በመጡት  ቆሞስ አባ ጌዴዎን አጭር መልዕክት በማስተላለፍ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎተ ምህላ ተጠናቋል።

              

የእሁድ መርሃግብር በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዝሙር የተጀመረ ሲሆን፣ ከመዝሙሩ ቀጥሎ መልአከ  ሕይወት ቀሲስ ርገተቃል “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” ኤፌ 42 -3) የሚለውን የቅ/ጳውሎስን ቃል መነሻ በማድረግ ስለ አንድነት አስፈላጊነት እና  የመንፈስ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሠፊ ትምህርት ሰጥተዋል። መምህሩ በዚህ ዘመን የአንድነት መጥፋት በቤተክርስቲያናችን ላይ ምን ያህል የከፋ ችግር እያደረስ እንደሆነ በእግዚአብሔር ቃል በመደገፍ አስተምረዋል። የቤተክርስቲያን አንድነት ሊያናጉ የሚችሉ ዋና ዋና  ጉዳዮች መናናቅ፣ በዘር/በሃረግ/በወንዝ ልጅ የተደገፈ ወገንታዊነት እና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ማለት እንደሆነ አብራርተው አስተምረዋል። አሁን በሲያትል የተጀመረው በአንድነት መሰባሰብ ተስፋ ሰጪ ስለሆነ ተጠናክሮ  እንዲቀጥል አሳስበዋል። በቤተክርስቲያን አንድነት እንዲመጣ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባው እና ድርሻ የለኝም ብሎ ወደኋላ ማለት እንደሌለበት አስተምረዋል። እሳቱን ለማጥፋት አቅም እንኳን ቢያንስ ወደ ልዑል እግዚአብሔር ማሳሰብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

መላከ ሣህል ቀሲስ አወቀ በሲያትል የደብረምህረት ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ ካቀረቡ በኋላ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን “ለቤተክርስቲያን አንድነት የእኛ ተጠያቂነት” በሚል ስለቤተክርስቲያን አንድነት ለውይይት በሚረዳ መልኩ ሰፊ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። የቤተክርስቲያን ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነ አበክረው ያብራሩት መምህሩ ቤተክርስቲያን እስክ አሁን እንዳልተከፈለች ወደፊትም እንደማትከፈል በማስረዳት የተለያየነው እኛ ባመጣናቸው አንድነትን በሚፈታተኑ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከምክንያቶቹም የተጠቀሱት

 • በሙሉ እምነት/በሃይማኖት/ ቤተ ክርስቲያንን አለማገልገል
 • በኣቋም መጽናት አለመቻል
 • ከቤተክርስቲያን ጥቅም የራስን ጥቅም ማስቀደም
 • ቤተክርስቲያንን ለሌላ ዓላማ መጠቀም/ለምሳሌ ለፓለቲካ ዓላማ/
 • እውነተኛ ዳኝነት/ፍርድ/ ውሳኔ መጥፋት ናቸው

ከላይ የተዘረዘሩት መክንያቶች የሚከተሉትን ችግሮች እንዳስከተሉ መምህሩ አብራርተዋል

 • ሁላችንም ወደ አስመስሎ  መኖር እንደመራን
 • የእርስ በእርስ አለመተማመን (ካህናት/ ምዕመናን)
 • ለቤተክርስቲያን ጥብቅና መቆም አለመቻል
 • ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ቤተከርስቲያንን አሳልፎ  መስጠት
 • በዘር፣ በፓለቲካ አመለካከት መለያየት
 • የቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት መባከን
 • የእምነቷ ተከታዮች ተስፋ መቁረጥ

አሁን ያለውን መለያየትን ለመቅረፍ ሁላችንም ልናደርገው የሚገባን ነገር እንዳለን መምህሩ አስረድተዋል:: ከጠቀሷቸው የመፍትሄ ሃሳቦች የሚከተሉት ይገኛሉ፥

 • በግልጽ መወያየት እንደሚያስፈልግ፣ መወያየት ምን ያህል ሃይል እንዳለው ሲያስረዱም የቀድሞ አባቶቻችንን “ኢትዮጵያውያን ከአዋቂዎቻቸው ወገን አለቃ አይሹሙ” የሚለውን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ተጥሎ የነበረውን እቀባ እንዴት መዋቅርን ሳያፋልሱ በውይይት እንዳስተካከሉ እና ቤተክርስቲያን ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላትን ግንኙነት ሳታቋርጥ የእራሷን አለቃ /ሊቀ ጳጳስ/ እንዳገኘች አስረድተዋል። በዚህ ዘመንም መወያየት እንጂ በትንሽ በትልቁ መለያየት እንደማይገባ አስረድተዋል።
 • ስለ ቤ/ክ ያለንን ወቅታዊ ግንዛቤ  ማሳደግ - የቤተክርስቲያንን ችግር ስንሰማ  መሰልቸት እንዴለለብን ችግሯን ስንሰማ  የአግልግሎት ጥሪ መሆኑን ማስተዋል እንዳለብን
 • በጋራ አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ይዘን በሚቀረን ጉዳይ የቤተ ክርስቲያንን መመሪያ እና ስርዓት መመሪያ ወይንም ዳኛ አድርገን ወደ አንድነት ለመምጣት ጥረት ማድረግ እንዳለብን
 • እራሳችንንም ማስተካከል እና መንፈሳዊ ህይወታችንን ማጠንከር እንዳለብን ተገልጿል
 • ምንም ነገር ከቤተክርስቲያን ሊበልጥብን እንደማይገባም ተብራርቷል

በመቀልም መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆኖ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ የጉባኤው ተሳታፊ ውይይት አድርጓል።  በርካታ የጉባኤው ተሳታፊዎችም ወደ አንድነት ለመምጣት መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ብዙ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ከተሰጡትም ሃሳቦች በከፊል፣

 • ሁላችንም በጸሎት እንበርታ
 • ይህ በሲያትል የተጀመረው የአንድነት ጉባኤ በሌላውም የአሜሪካ ግዛቶች ተጠናቅሮ  የሚቀጥልበትን ሁኔታ ሶስቱም ማኅበራት ባላቸው መዋቅር መስራት ቢችሉ
 • በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ለተከሰተው መለያየት እንደ አብይ ጉዳይ የሚነሳው የአራተኛው ፓትርያርክ ከስልጣን የወረዱበት እውነተኛው  ምክንያት በወቅቱ  በነበሩ አባቶችን  የሚታወቅ በመሆኑ አባቶች በእውነተኛ ወንደማማች መንፈስ ተነጋግረው ችግሩን ፈተው ለምእመናን እውነቱን እንዲነግሩን ማድረግ ቢቻል
 • ሁላችንም የምናወራው ስለቤተክርስቲያን አጠቃላይ ሰላም ቢሆን፣ ስለአጥቢያ እና ስለ አንድ ቤተክርስቲያን ብቻ ባይሆን
 • እንደወንድም እና እህት መቻቻል ብንችል
 • ፓለቲካን ቤተክርስቲያን ስንገባ ልክ እንደ ጫማችን እውጭ አውልቀን መግባት ብንችል

በመጨረሻም ጉባኤውን ስላዘጋጁት ሶስቱ ማኅበራት እና በአካባቢው የተሣተፉ የአራት ቤተክርስቲያን ስንበት ት/ቤቶችን አባላት በመወከል ዲ ብዙአየሁ ልመንህ ሰለ ጉባኤው ዝግጅት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያውም ስለሶስቱ ማኅበራት ማንንት እና ለቤተክርስቲያን እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት በአጭሩ ተብራርቷል፣ በዚህም መሰረት ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት 20 ዓመታት በቅ/ሲኖዶስ ፈቃድ አግኝቶ በተለያዩ  አገልግሎቶች በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቤተክርስቲያንን ትምህርት ስርዓተ ትምሕርት ቀርጾ ለግቢ ተማሪዎች እያስተማረ እንደሆነ፥ የአብነት ት/ቤቶችንም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆን እንደማሳያም በቅርቡ በ 5 ሚሊዮን ብር በጀት የአብነት ተማሪዎች የዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ የ ትምህርት እድል መስጠቱ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ማኅበሩ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የሬድዮ መርሃ ግብር እንደጀመረ  በቅርቡም የቴሌቪዥን መርሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ተገልጿል።

ማኅበረ በዓለ ወልድ ማኅበርም በሰሜን አሜሪካ ከተለያዩ ቦታ በመጡ አባቶች፣ እናቶች፣ እህቶች እና ወንድሞች በተለይም ደግሞ በተለያዩ  የኬንያ ከተሞች በስደት ይኖሩ በነበሩ ወገኖች እንደተመሰረተ በወቅቱ በነበሩት በሶስት ሊቃነ ጳጳሳት እውቅና ተሰጥቶት ሠፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ ማኅበረ  እንደሆነ ተገልጿል። ከአገልግሎቶቹም ውስጥ በኬንያ ኬናውያን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን እንዲያውቁ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ እንደሆነ፣ በአሜሪካ አኅጉረ ስበከቶችን ለማጠናከር ከአባቶች ጋር በተለይም የዲሲ እና አካባቢውን አኅጉረ ስብከት ለማጠናከር በሃሳብ በገንዘብ እንዳገዘ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ አድባራት እና ገዳማትን በመርዳት ሰፊ ስራ እየሰራ ያለ ስብስብ እንደሆነ ተገልጿል።

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ማኅበርም በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተነሳሽነት እንደተቋቋመ ተገልጾ ከ7ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ጀምሮ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እየተገኙ አካሄዱን እየመሩት ቤተክርስቲያንን እያገለገለ  ያለ ማኅበር እንደሆነ ተብራርቷል። የሰንበት ት/ቤት ከሚሰጣቸው ሰፊ አገልግሎቶች መካከል በኢትዮጵያ  የሚገኙ ገዳማትን በመርዳት እንዲሁም በኢትዮጵያ የተቋቋመውን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከምስረታው ጀመሮ  በሃሳብ እና በገንዘብ እያገዘ እንደሆነ ተገልጧል።

እነኝህ ሶስት ማኅበራት ከዚህ በፊትም አብሮ የማገልገል ልምድ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን እንደማሳያም የዝቋላ ገዳምን ለመርዳት ወደ $24,000 ከምዕመናን በማሰባሰብ እንደረዱ ተገልጿል።

የዚህ ጉባዔ ዝግጅት ወጪም በሶስቱ ማኅበራት እና ባአጥቢያው ባሉ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንደተሸፈነ ተገልጿል። በቀጣይም እንዲህ አይነት ጉባኤ ለማድረግ ተሳታፊዎች ሃሳብ እንዲሰጡ ተጋብዘው አንዳንድ ሃሳቦች ከተሰነዘሩ በኋላ በየሶስት ወሩ ቢደረግ የሚል የመነሻ ሃሳብ ላይ ተደርሷል።

በመጨረሻም መላከ ሣህል ቀሲስ አወቀ ኣባታዊ ምክር ካስተላለፉ በኋላ በጸሎት አሳርገዋል።


Written By: admin
Date Posted: 12/12/2012
Number of Views: 6139

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement