View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ጥምቀተ ክርስቶስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

“ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን”
/ጸሎተ ሃይማኖት/

ጥምቀተ ክርስቶስ

ለጌታችን ሠላሳ ዓመት ሊሆነው ስድስት ወር ሲቀረው ፣ የሊቀ ካህናቱ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ከምድረ በዳ ወጥቶ ማስተማር ጀመረ:: ይህንንም ትምህርት የጀመረው ከፈጣሪው ባገኘው መልእክት ነው:: ሉቃ ፫፥፩ ዮሐንስም ከቆሮንቶስ ምድረ በዳ ወጥቶ በዮርዳኖስ ዙርያ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ በማስተማር የንስሐን ጥምቀት ማጥመቅ ጀመረ :: ሉቃ ፫፥፫ ሕዝቡም ትምህርቱን በመቀበል ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በንስሐ ጥምቀት ይጠመቁ ነበር:: ማቴ ፫፥፫ የትምህርቱን እውነተኛነት ባወቁ ጊዜ ዮሐንስን ክርስቶስ ነው ብለው ጠረጠሩ:: ሉቃ ፫፥፲፭ ዮሐንስም እንዲህ ሲል እውነቱን ነገራቸው " እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።  ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤  እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።" ዮሐ ፩፥፳

የዮሐንስ ጥምቀት
ምንም እንኳን ዮሐንስ ጥምቀትን ያጠምቅ የነበረ ቢሆንም የዮሐንስ ጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጥ ጥምቀት አልነበረም:: የሱ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር:: የዮሐንስ ጥምቀትን አቅምንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን እንዲህ ሱሉ ይገልጹታል::  እድፍ ቆሻሻ የያዘው ልብስ በውኃ ታጥቦ ነጽቶ ሽቱ ይርከፈከፍበታል:: ገላም ሲያድፍ በውኃ ታጥቦ ጽዱ ልብስ ይለብሳል:: እንደዚሁም ሁሉ የዮሐንስ ጥምቀት ተጠማቂዎቹ ኋላ በክርስቶስ ጥምቀት የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በቅተው እንዲገኙ ከኃጢያት መለየታቸውን ተለየን ማለታቸውን የሚገልጽ ምልክት ነው:: ራሱም አንዲህ ሲል መስክሯል "እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ...ከኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ግን በእሳት ያጠምቃችኋል.." ማር ፩ ፥፰ 

የጌታችን ጥምቀት
እንደ ቤተ ክርስትያናችን ዘመን አቆጣጠር ጌታችን የተጠመቀው በሠላሳ አመት ከ 13 ቀኑ በ 5531 ዓመተ ዓለም ጥር 11 ማክሰኞ ቀን ነው:: አጠማመቁም ይሄንን ይመስላል::ዮሐንስ ያስተምርበት በነበር ጊዜ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ:: ዮርዳኖስም ዮሐንስ ያጠምቅበት የነበረው ቦታ ነበር:: ጌታችንም ወደ ዮሐንስ ቀርቦ " አጥምቀኝ" አለው:: ዮሐንስም " እኔ በአንተ እጠመቃለሁ እንጂ አንዴት አንተ በኔ ትጠመቃለህ ? " በማለት መለሰ:: ጌታችንም " አንተ እኔን በማጥመቅ እኔ በአንተ እጅ በመጠመቅ የሰውነትን ሥራ እንፈጽም ዘንድ ይገባናል:: አጥምቀኝ " አለው:: እንደመልከ ጼዲቅ ሥርዓት አንተ የዘላለም ካህን ነህ መዝ ፻፥፬ ብርሃንን የምትገልጽ የቡሩክ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለን እያለ አጠመቀው:: ማቴ ፫፥፲፫ተጠምቆም ከውኃው ከወጣ በኃላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት ታይቷል:: አብም " “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ይህ ነው ብሎ ብሎ መስክሯል::ማቴ ፫፥፲፮

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ወልደ ማርያም የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ነው:: የባሕርይ አምላክ ነው:: ስለዚህ ጥምቀት ለሱ የሚጠቅመው ነገር የለም:: የተጠመቀው ግን ስለ ብዙ ምስጢራት ነው:: በመጀመርያ ትንቢቱን ለመፈጸም ነው:: አስቀድሞ እነ ቅዱስ ዳዊት ትንቢት ተናግረው ነበር:: " አቤቱ ውሆች አዩህ ተጨነቁም ቀላዮችም አዪህ ተንቀጠቀጡ"መዝ ፸፯:፲፮ ይሄንን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ:: በትንቢት እንደተነገረለትም ጌታችን ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ውሃው ከመካከሉ ተከፍሎ ወደፊትና ወድ ኋላ ሽሽቷል:: አሳትም እንዳነደዱበት ሆኖ ፈልቷል:: ሌላው ምክንያቱ የዮሐንስን ምስክርነት ለማስረዳት ነው:: ዮሐንስ " ከኔ በፊት የነበረ ከኔ የሚበልጥ ከኔ በኋላ ይመጣል" ብሎ በቃል መስክሮለት ነበርና ለሕዝቡ ተገልጾ እንዲታይና እንዲታወቅ ነው:: ስለዚህም ምክንያት የተጠመቀበት ቀን ኤጲፋንያ ተብሏል:: በግዕዝ ደግሞ አስተርእዮ ተብሏል:: መገለጽ : መታየት ማለት ነው::

የጥምቀት በዓል
የጌታችን የጥምቀት በዓል ዛሬም በሀገራችን ደምቆ ይከበራል:: በዋዜማው ታቦታቱ ከየአብያተክርስቲያናቱ ወጥተው በወንዝ ዳር ( የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ) በድንኳን ውስጥ ያድራሉ::የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ጌታ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው:: ሌሊት ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥራተ ቅዳሴውም ይፈፀማል:: ሲነጋ በወንዙ ዳር ጸሎተ አኮቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውሃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል::ይሄም የጌታችንን በረከተ ጥምቀት ለምእመናን ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁ ምእመናን እየመላለሰች ቤተ ክርስትያን አታጠምቅም:: ጥምቀት አንዲት ናትና::

ገሃድ

በዓለ ጥምቀት የሚከበረው ጥር 11 ቀን ነው:: ጥምቀት ረቡዕ ቢውል ገሃዱ ማክሰኞና ዓርብ ቢውል ገሃዱ ሐሙስ ለውጥ ሆኖ ይጾማል፤ በዓለ ጥምቀት የሚውልባቸው ረቡዕና ዓርብ አይጾሙምና።
እኛ የሰው ልጆች ሥርዓተ ጥምቀት እንዲፈጸምልን የሚያስፈልገው፡-
የልጅነት ጸጋን እናገኝ ዘንድ ነው፡፡ ዮሐ.1፥5

አስቀድመን ከሥጋ እናት አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ያለው፡፡ /ዮሐ.3፥3 እና 6/ በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል፡፡ ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን /የምንጣራበትን/ የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል፡፡” ብሏል፡፡ /ሮሜ.8፥15-16/ ጌታችንንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው የእግዚአብሔር ልጆች ይሁኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል፡፡ /ዮሐ.1፥11-13/
እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ፡፡ ይኸውም መጀመሪያው ከሥጋ እናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን መሆን ያስፈልጋዋል፡፡ ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና፡፡

ሥርየተ ኀጢአትን ለማግኘት
በአምልኮ ባዕድና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ከጥምቀት በአፍአ ሆነው የቆዩ ሰዎች ከነበረባቸው ኀጢአት ይነፁ ዘንድ ሥርዓተ ጥምቀት ተሠርታለች፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በ50ኛው ቀን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብቱ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ማደሩን የሰሙ አይሁድ፤ ከቅዱሳን ሐዋርየት ዘንድ ቀርበው የሚናገሩትን ቃለ እግዚአብሔር መስማት ጀመሩ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነቱን፣ በኃይለ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ወደ ሰማይ ማረጉን ነገሯቸው፡፡ አይሁድም ይህንን በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?” አሏቸው፡፡ ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡….” አላቸው /ሐዋ.2፥37-38/ ይህ የሐዋርያው ቃል የሚያስረዳን የጥምቀትን መድኀኒትነት ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው አባቶቻችን በሃይማኖት መግለጫቸው “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፥ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ማለታቸው ጥምቀት ከደዌ ነፍስ የምታድን መሆኗን መመስከራቸው ነው፡፡ /ጸሎተ ሃይማኖት/

ዘላለማዊ ድኅነት
የሰው ልጅ ድኅነት ቅጽበታዊ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና የድኅነት በር ከፋችና ሌሎችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለመፈጸም የሚያበቃን ምሥጢር ምሥጢረ ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ መመሪያ ውስጥ “ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት፡፡ ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ይደየን፡፡ ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ /ማር.16፥15-16/
እንግዲህ በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋና ክብር ሁላችን ልናስብ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ክብራችንን መጠበቅ ያሻናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
 
አዘጋጅ፡-
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል
ጥር ፳፻፭ ዓ.ም


Written By: host
Date Posted: 1/19/2013
Number of Views: 9436

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement