View in English alphabet 
 | Thursday, March 28, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ቤተ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው?

ቤተ ክርስቲያን ሲባል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን ሲባል  ክርስቲያን ምእመናን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሲሆን ይችላል። የእነዚህንም አባባሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በሚቀጥሉት መግለጫዎች እንመልከት።

ምእመናን፦ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመኑ የክርስቲያን ሃይማኖት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕራፍ ፲፮፣፬- ፭ ላይ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ ካለ በኋላ፣ እነርሱን የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም ብሏል። እንዲሁም በቤታቸው ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ ብሏል።እዚህ ላይ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያን የተባሉትና በቤታቸው ያለችው  ቤተ ክርስቲያን የተባሉት ምዕመናን ናቸው እንጂ ሌላ አይደለም። በተመሳሳይ አባባል ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልእክቱ ምዕራፍ ፲፮፣፲፱ ላይ የእሲያ አብያተ ክርስቲያን ሰላምታ እንደሚያቀርቡ ገልጾአል። እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፳፣፳፰ ላይ ለኤፌሶን ካህናት ባደረገው የመሰናበቻ ንግግር “ጌታ በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ ብሏቸዋል።” እዚህም ላይ እንዳለፉት አባባሎች  ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የተባለው ምእመናን ለማለት ነው።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፦ ቤተ ክርስቲያን ሲባል ምዕመናን ማለት እንደመሆኑ ሁሉ በሌላ ጊዜ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማለት ነው።

ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ለበደለኛ ሰው ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ በደሉን ንገረው ቢሰማህ እንደገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ ባይሰማህ ግን ሁለት ወይም ሦስት ሰዎችን ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ። እነርሱንም አልሰማ ቢል ለቤተ ክርስቲያን ንገር ቤተ ክርስቲያንንም የማይሰማ ከሆነ እንደ አረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኅጢያተኛ ቁጠረው” (ማቴ፲፰፣ ፲፭ -፲፯)። እዚህ ላይ እንደተመለከተው ቤተ ክርስቲያን የተባለው በቤተ ክርስቲያን ስም ከፍተኛ ጉደይ የሚያደምጥ ተቋም መሆኑ ነው። ይህም የቤተ ክርስቲያን ምዕመን፣ ወይም የሃይማኖቱ ተወካይ ሆኖ እንደዚህ ያለ ክብር የሚሰጠው የቤተ ክርስቲያን መሪ በተናጠል ወይም መሪዎች በጋራ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ እንደ እነዚህ ተመሳሳይ አባባሎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፦ በሌላ ጊዜ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ስንል የአንድ አገር የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማለታችን ነው።

ለምሳሌ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ነበሩ። አቡነ ባስልዮስ በፓትርያርክነት ከመሰየማቸው በፊት በኢትዮጵያና በግብጽ አብያተ ክርስቲያን መካከል ብዙ ውይይቶች ተካሂደዋል። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆንዋ ቀርቶ የራስዋ ፓትርያርክ እዲኖራት ስምምነት ተደረሰ።

ከዚህ በላይ የተገለጸው አባባል የሚያመለክተው ውይይት ተደርጎ ወደ ስምምነት የተደረሰው በኢትዮጵያና በግብጽ አብያተ ክርስቲያን አስተዳደሮች መካከል ነው። የቤተ ክርስቲያንም አስተዳደር አብዛኛውን ጊዜ የሚመራው በጳጳሳት ሲኖዶስ ነው።ስለዚህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የግብጽ  ቤተ ክርስቲያን፣ ተብሎ በሚገለጽበት ጊዜ የየሀገሩን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ወይም አመራር ለማመልክት ነው።

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፦ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ ዐሥርና አንቀጽ ሠላሳ አምስት በሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ሥርዓቶች ላይ ለሕንጻው ቤተ ክርስቲያንም የሚል እናገኛለን። ቤተ ክርስቲያን መባሉ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበትና የምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓቶች የሚያከናውኑበት ቦታ  ስለሆነ ነው። በብዙዎቻችን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን በሚባልበት ጊዜ ይኸው የሚሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚካሄድበትና ለጸሎትም የምንሰበሰብበት ቦታ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደዚህ ላለው ቦታ ደግሞ እግዚአብሔር የተለየ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ለመረዳት ወደ መጀመሪያው መጽሐፈ ነገሥት ምዕራፍ ስምንትና ዘጠኝ የተመለከትን እንደሆነ የሚከተለውን ሁናቴ እናገኛለን። ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደስን አሰርቶ በጨረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ባቀረበው ጸሎት በቤተ መቅደስ ተገኝቶ የሚደረገው ጸሎት ሁሉ ተሰሚነትን እንዲያገኝ ብሎ ለለመነው ልመና እግዚአብሔር መልስ ሊሰጠው “በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቼአለሁ፣ ለዘላለም ስሜ በዚህ ያድር ዘንድ ይህን የሰራኽውን ቤት ቀድሼአለሁ፡ ዐይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ (፩ነገ ም ፱፡ቊ ፫)።


ስለዚህ እንደየንግግሩ አመጣጥ በመለየት ቤተ ክርስቲያን ሲባል ምእመናን፣ ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ወይም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ወይም ሕንጻ  ቤተ ክርስቲያን ማለት ሊሆን ይችላል።



የቤተ ክርስቲያን መሥራች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ ማንነት ሐዋርያቱን በጠየቃቸው ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው መልስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” በማለቱ ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ካመሰገነው በኋላ “አንተ አለት ነህ፣ በዚህ አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እመሰርታለሁ” ብሎታል።


ይህንንም በማለቱ የቤተ ክርስቲያን  መሥራች እርሱ ራሱ መሆኑን አረጋግጧል። አለትም የተባለው እምነቱ ነው። ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን የምትመሠረተው ማለት ክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታዮች ወይም ቤተሰብ መሆናቸው የሚታወቀው ጊታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ወይም ዓለምን ለማዳን የነበረበት መሲሕ እርሱ መሆኑን አምነው የእግዚአብሔር ልጅነት በተቀበሉ ምዕመናን ላይ ነው ማለት ነው። ይህን አባባል ሐዋርያው ቅዱስ ዩሐንስ ሲያረጋግጠው እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያምን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” (1 ዮሐ ፭፣ ፩)።


እንግዲህ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ሁሉ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው፣ ወልድን የሚክድ አብ የለውም። በወልድ የሚያምን በአብ ያምናል” (1 ዮሐ ም ፪ ቁ፪ ፳፫)።


የቤተክርስቲያን ደንቦችና ሥርዓቶች የተዘጋጁት የሐዋርያት ትምህርት በሆነው በዲድስቅልያና በዓለም ዐቀፋዊዎቹ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች ቢሆንም እንኳ በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጌታችን በመድኅኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህንኑም በሚከተሉት መግለጫዎች ይመለከቷል።


ቤተ ክርስቲያን ማለትእንደ ጉዳዩ አመጣጥ፣ ምእመናን፣ ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ወይም
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና፣ ወይም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን  መሆኑን ተገልጿል።

ከእነዚህ ከአራቱ ትርጉሞች አንዱ የሆነው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በተመለከተ ጌታችን መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንዳለ እንመልከት፦

“ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችችሁ በደሉን ንገረው፣ ቢሰማህ እንደገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ፣ ባይሰማህ ግን የሁለት ወይም የሦስት ስዎች ምስክርነት ስለሚጸና ሁለት ወይም ሦስት ስዎች ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ፣ እነርሱም አለሰማም ቢል ለቤተ ክርስቲያን ንገር፣ ቤተ ክርስቲያንንም የማይሰማ ከሆነ እንደ አረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኃጢያተኛ ቁጠረው” (ማቴ፲፰፣ ፲፭- ፲፯)።
ይህ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ራሱ በጌታችን አነጋገር ውስጥ መግባቱና ያም ቃል ስሞታ ሊነገረው የሚችል በምእመናን መካከል መንፈሳዊ ዳኝነትን ለመስማት የተደራጀ አንድ ተቋም የነበረ መሆኑን ያመለክታል። ያም ባይሆን ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ወደፊት ሊቋቋም ስላለው ስለቤተ ክርስቲያን መመሪያ እንደሰጣችው ያሳያል። በዚህም ሆነ በዚያ ያ አባባል የሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቤተ ክርስቲያንን የመሰረታት አስቀድሞ ዋጅቶአት መሆኑን ሲያመለክት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦

“መንፈስ ቅዱስ እናንተን የመንጋው ጠባቂዎች አድርጎ ሾሞአችኋል፣ እንግዲህ ለራሳችሁና ለመንጋው ተጠንቀቁ፣ ጌታ በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ” (ሐዋ ፳፣ ፳፰)።
ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጀት ጌታችን ደሙን ማፍሰስ ነበረበት። በደሙ የዋጃቸውን በቤተ ክርስቲያን አሰባሰባቸው። ይህም ማሰባሰቡ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረቱ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦

“ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናቸሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማእዘኑም ራስ የሆነው ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል። እናንተም እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን በክርስቶስ ትታነጻላችሁ” (ኤፌ ፪፣ ፲፱- ፳፪)።

“እነሱ ከሁሉም ነገር በፊት ነበር፣ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው፣ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፣” (ቆላ ፩፣ ፲፯-፲፩፰)።

“ሁሉንም ነገር ከሥልጣኑ ሥር አድርጎ አስገዛለት፣ በቤተ ክርስቲያንም ከሁሉ በላይ እንዲሆን ራስ አደረገው፣ ቤተ ክርስቲያን የእርሱ አካልና የእርሱ ሙላት ናት፣ እርሱ ሁሉን በሁሉ የሞላ ነው” (ኤፌ ፩፣ ፳፪ - ፳፫)።
ስለዚህ ከላይ በቀረቡት ልዩ ልዩ ማስረጃዎች መሠረት ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ዋጅቶአታል፣ አካሉ ነች፣ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፣ እንዲሁም መሥራችዋ ነው። ጌታችንም በደሙ ባይዋጃትና በእርሱ ላመኑት ልጅነትን ባይሰጥ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ባልተመሠረተችም ነበርና መሥራችዋ እርሱ ነው የሚባለው ስለዚህ ነው።


ምንጭ
ትምህርት መለኮት ገጽ 155-158፣ በዓሥራት ገብረ ማርያም 1994 ዓ.ም. ሦስተኛ ዕትም

Written By: admin
Date Posted: 2/13/2013
Number of Views: 9637

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement