View in English alphabet 
 | Wednesday, April 24, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ

ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር - ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና የመስቀሉን አከባበር አጀማመር፣ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ባሕላዊ ትውፊቱን ለመመልከት እንሞክር፡፡

የመስቀል በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የዕውራንን ዓይን እያበራ፣ ልዩ ልዩ ደዌ ያደረባቸውን እየፈወሰ ተዓምራት በማድረጉ በሰቀሉት ሰዎች ዘንድ ባሳደረው ቅንዓት በአልባሌ ሥፍራ፣ በከተማ ጉድፍና ጥራጊ ማከማቻ ውስጥ ተጥሎ ለ300 ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ ተፈልጎ የተገኘበት ታሪካዊ በዓል ነው፡፡ ቅዱስ መስቀሉ ለሦስት ምዕት ከተቀበረበት የቆሻሻ ሥፍራ የተገኘው በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ሲሆን የበዓሉም መከበር ይህንኑ ይዘክራል፡፡
 
ንግሥት እሌኒ ከመንፈሳውያን አበው (አረጋዊውን ኪራኮስን ያስታውሷል) በተነገራት መሠረት ያዘጋጀችው የደመራ እንጨትና በደመራው ላይ የተደረገው የዕጣን ጢስ ወደላይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አመልክቷል፡፡ በዚያው ላይ ቁፋሮ ተካሂዶ መስቀሉ ተገኝቷል፡፡ መስከረም 17 ቁፋሮ የተጀመረበት፣ መስቀሉ ተገኝቶ ከወጣ በኋላ በስሙ የተሠራው ቤተመቅደስ የገባበትና ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት ቀን በየዓመቱ በስብሐተ እግዚአብሔርና በመንፈሳዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በዋዜማው መስከረም 16 ደመራ ይደመራል፣ ጸሎተ ወንጌል ይደርሳል፣ መዝሙርና ሽብሸባ ይቀርባል፡፡ በመጨረሻም ደመራው ይለኮሳል፡፡
 
ንግስት ዕሌኒ በመስከረም ማስቆፈር የጀመረችው የቆሻሻ ክምር ተንዶ መስቀሉ የተገኘው በመጋቢት 10 ቀን ቢሆንም በወርኃ ጾም (ያውም በዐቢይ ጾም) ተድላ ደስታ ማድረግ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ በመሆኑ የመስቀሉን በዓል ማክበር የማይቻል ሆነ፡፡ በአበው ውሳኔም ቁፋሮው የተጀመረበትና ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት መስከረም 17 በደስታና በተድላ እንዲከበር ተደረገ፡፡ የመስቀሉ መገኝት ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ደስታ ቢሆንም በአገራችን በኢትዮጵያ ያለው ሃይማኖታዊና ባሕላዊ አከባበር በሌሎች ዘንድ የለም፡፡ አገራችንን ከሌሎች የተለየች ያደረጋትም ይህ የበዓል አከባበርና በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ገንዘብ ልናደርገው የቻልነው ግማደ መስቀል (የመስቀሉ የቀኝ ክንፍ ስባሪ) በአገራችን መኖር ነው፡፡
 
በአጼ ዳዊት ዘመን የመጣው ግማደ መስቀል መጀመሪያ በመናገሻ ከተማ ምዕራባዊ እርከን በምትገኘው አምባ (መናገሻ) ማርያም ገዳም ካረፈ በኋላ ለዘለቄታው እንዲቀመጥ የተወሰነው ሌላ ቦታ በመሆኑ በራዕይና በልዩ ልዩ ሁኔታ በተገለጸው ምልክት መሠረት በተፈጥሮ አቀማመጧ የመስቀል ቅርጽ ባላት በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ገዳም ሊቀመጥ ችሏል፡፡
 
ከዚህ መንፈሳዊ ትርጉም ጎን ለጎንም የመስቀሉ ልጆች የሆኑት የኢትየጵያውያን ባሕላዊ የአከባበር ትውፊት ክርስቲያናዊ ትርጉምም ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም፡፡ የደመራ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ሁሉ ምዕመናን ተሰብስበው በየቋንቋቸው እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ ከጥቢ ጋር የተያያዘ ዝማሬ («ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ» ዓይነት) በማቅረብ በዕልልታና በሆታ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡ 

ደመራው በችቦ እሳት ተለኩሶ አመድ እስኪሆን ከተቃጠለ በኋላ ሕዝቡ አመዱን በጣቱ በመንካት ግንባሩ ላይ የመስቀል ቅርጽ ያበጃል፡፡ ትርኳሹን እየተሻማ ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡ ይህም የአከባበር ትውፊት ጥምቀተ ክርስትና በሌላቸው ብዙ ሕዝቦችም ዘንድ ሲፈጸም መታየቱ ቤተክርስቲያናችን ከጊዜ ብዛት በደረሱባት የተለያዩ ችግሮች ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለማስፋፋት ባልቻለችባቸው ቦታዎች የቀደሙ አበው ጥለውት የነበረው የወንጌል መሠረት በሕገ ልቡና ተጠብቆ መቆየቱን የሚያመለክት ነው፡፡


Written By: host
Date Posted: 12/19/2007
Number of Views: 9191

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement