View in English alphabet 
 | Saturday, April 20, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ስለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚያስረዳው “በእንተ ስማ ለማርያም” የተሰኘው ዐውደ ርዕይ በሲያትል ለሕዝብ እይታ ቀረበ

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል “በእንተ ስማ ለማርያም” (ስለ እመቤታችን ማርያም ! ) በሚል መሪ ቃል ያሰናዳው በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ላይ ያተኮረው ብዙኃን የቤተክርስቲያን ልጆች የተሳተፉበት ዐውደ ርዕይ በሲያትል ንዑስ ማዕከል አዘጋጅነት መጋቢት 7 እና መጋቢት 8 2005 ዓ/ም በሲያትል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ለሕዝብ እይታ ቀርቧል::  

ዐውደ ርዕዩ ቅዳሜ መጋቢት 7 2005 ዓ/ም በሲያትልና በአቅራቢያው ካሉ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የሰባካ ጉባኤ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው  እንግዶች በተገኙበት ደመቅ ባለ ሥነ ሥርዓት ተከፍቷል::
በዚሁ ወቅት  በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል  መልእክት በዲ/ ተገኔ ተክሉ  የቀረበ ሲሆን በመክፈቻው ላይ በተገኙ ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተለያየ አስተያየት ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀን ክፍት ሆኖ የቆየውን ዐውደ ርዕይ  ከ300 በላይ ምእመናን የተመለከቱት ሲሆን ከተሰበሰበውን አስተያየት  የብዙኃኑን ስሜት የነካ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ዓውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን በዕለቱ ቀረበው ከነበሩት ፕሮጀክቶችን  መካከል እየመረጡ የወሰዱ ሲሆን በኦንላይን በተዘጋጀው የልገሳ ድረ ገጽ (http://www.gedamat.org)  ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ዐውደ ርዕዩ የሚከተሉት 7 ክፍሎች ነበሩት

1.    የአብነት ት/ቤት ታሪክ
በዚህ ክፍል ስለ አብነት ት/ቤት ከስሙ ትርጓሜ ጀምሮ፣ አብነት ት/ቤት ምን ማለት እንደሆነ፣ ምን አይነት ትምህርት በውስጡ እንደሚያጠቃልል፣ እንዴት እንደተጀመረ፣ በኢትዮጵያ ስለነበሩ እና ስላሉ የአብነት ት/ ቤቶች ያሳየ ክፍል ነው።
አብነት ማለት አባትነት ማለት ሲሆን በአብነት ትምህርት ውስጥ መምህሩ በእውቀት አርአያነት፥ ተማሪው ደግሞ በትህትና አርአያነት ልክ እንደ አባት መምህሩ ለትውልዱ ተማሪው ደግሞ ለጓደኞቹ እና በአካባቢው ለሚኖረው ማኅበረሰብ በህይወቱ በማስተማር አብነት እንደሚሆን ተገልጿል።
የአብነት ትምህርት ጀማሪው እግዚአብሔር አዳምን በቃል በማስረዳት እንደጀመረው፣ ከዛም በሙሴ በጽሁፍ እንደተጠናከረ፣ በመቀጠልም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር እንዳጸናው ተገልጿል።
ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶችም በትእይንቱ ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኙ ሲሆን፥ መቼ እንደተመሰረቱ፣ በአብነት ትምህርት ላይ የነበራቸው እና ያላቸው ፋይዳ በሰፊው ተገልጿል። እንዲሁም እነኝህ የአብነት ት/ቤቶች ያፈሯቸው ታላላቅ ሊቃውንት እንደ አለቃ አያሌው ታምሩ : አለቃ  አካለወልድ እንዲሁም ከእነ ቅዱስ ያሬድ ጀምሮ እነማን እንዳስተማሩባቸው ተገልጿል።

2.    የአብነት ት/ቤቶች የሥርዓተ ትምህርት አደረጃጀት
በዚህ ክፍል የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት ምን አይነት ይዘት እንዳለው ተገልጿል። በገለጻውም መሰረት የአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ራሳቸውን በቻሉ የትምህርት ዘርፎች (የጉባኤ ቤቶች)በተከፋፈለና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መሆኑ ተገልጿል።    የጉባኤ ቤቶች የሚባሉትም ንባብ ቤት ፣ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መጻሕፍት ቤት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ  ባሕረ ሓሳብ (አቡሻሐር) እና አክሲማሮስ ራሳቸውን በቻሉ ጉባኤ ቤቶች ይሰጡ እንደነበር ተመልክቷል።

3.    የአብነት ት/ቤቶች አስተዋጽኦ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር
የአብነት ት/ቤቶች ለቤተክርስቲያን ታላላቅ መምህራን እና ሊቃውንትን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንዳላቸው የተብራራ ሲሆን፣ ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መኩሪያ የነበሩ እነሎሬት ጸጋዮ ገብረ መድኅን እና ሃዲስ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ሰዎችን እንዳፈሩ ተገልጿል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የሼክስፒር ሶኔት የሚባለው በለ 14 መስመር የቅኔ ስልት ከቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት ጋር በማነጻጸር የቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት በተሻለ ሁኔታ ሃሳብን ለመግለጽና ለማመስጠር እንደሚያገለግል ተብራርቷል።

4.    አኗኗር በአብነት ት/ቤት
በዚህ የትእይንት ክፍል ውስጥ፣ የአብነት ተማሪው ከቤቱ ከትምህርት ከወጣ በኋል ተምሮ አንድ ደረጃ  እስኪደርስ አኗኗሩ ምን እንደሚመስል እና የሚያጋጥሙት ፈተናዎች ምን እንደሚመስሉ በስዕል፣ በድምጽ እና በቪዲዮ ቅንብር ተብራርቷል።
በተለይ ተማሪው ምግቡን ለማግኘት ከውሻ፣ ከተፈጥሮ እና ከበሽታ ጋር ምን ያህል ግብ ግብ እንደሚገጥም  በአብነት ት/ቤት ሕይወት ባለፉ ሊቃውንት እና የአብነት ተማሪዎች የቪዲዮ ምስክርነት የተገለጸበት ሁኔታ ልብን የሚነካ  ነበር።

5.    የአብነት ት/ቤቶች ያጋጠሙአቸው ዋና ዋና ችግሮች እና መንስኤዎቻቸው
በዚህ ክፍል ውስጥ፣ እነኝህ ለቤተክርስቲያን እና ለሃገር ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት መፍለቂያ የሆኑ የአብነት ት/ቤቶች በአሁኑ ሰዓት የተጋረጠባቸውን ፈተናዎች በተጠኑ መረጃዎች፣ በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ በተደገፈ ሁኔታ ለታዳሚው የቀረበ ሲሆን፣ የተማሪውን እና የመምህራኑን ቸግር የሚያሳዮ ቪዲዮዎች ሲቀርቡ በትዕይንቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ ምእመናን ሃዘናቸውን መቆጣጠር ተስኖአቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ መፍትሄ እንዲሰጥ ሊረዳ ይችላል በሚል የችግሮቹ መንስኤዎች በሰፊው ተብራርተዋል። ከመንስኤዎቹም ውስጥ የምእመናን አቅም ማነስ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት የአብነት ትምህርቱን አስተዋጽኦ ያለማገናዘብ ተጠቅሰዋል።

6.    የአብነት ትምህርት ቤቶች ነገ
አሁን በአብነት ት/ቤቶች ላይ ያጋጠመው ችግር እንዳለ ከቀጠለ በቤተ ክርስቲያን እና በሃገር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ  በዚህ ክፍል የተብራራ ሲሆን፣ በችግሩ ምክንያት ከፊታችን የተጋረጠውን አደጋ  እንዳይከሰት ለመከላከል በዚህ የትዕይንት ክፍል ውስጥ የመፍትሔ ሃሳብ ይሆናሉ የተባሉ ሃሳቦች ተጠቁመዋል። መፍትሄዎቹም ተማሪዎቹን በተመለከተ፣ መምህራኑን በተመለከተ፣ ገዳማቱ እና አድባራቱን፣ የመማሪያ ቁሳቁስን በተመለከተ በሚል እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን በተመለከተ በዝርዝር ቀርበዋል።

7.    ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት ት/ቤቶች ያደረገው እና እያደረገ ያለው አስተዋእጽዎ
በዚህ ክፍል ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ለምን ትኩረት አድርጎ  እየሰራ እንደሆነ፣ አሁን እየተሰሩ እና የታቀዱ ስራዎች፣ የታዩ ውጤቶች እና ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚል ሰፊ ገለጻ የተሰጠ ሲሆን  አያይዞም ማኅበሩ እየሰጠ ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት  በመደገፍ  በማጠናከርና ከማኅበሩ ጎን በመሆን ሁሉም ክርስቲያን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ያስገነዘበ ነበር::
በዚህ ክፍል ውስጥም በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ገዳማትን በቀላሉ በአንድ ጊዜ ስጦታ ወይንም በየወሩ በሚቆረጥ ስጦታ ለመርዳት የሚያስችለው ድረ ገጽ http://www.gedamat.org  ተዋውቋል።

ባጠቃላይ “በእንተ ስማ ለማርያም” በሚል የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት የአብነት ትምህርት ቤቶች በቀጣይና ዘመኑን በዋጀ መንገድ ሊቀጥሉ የሚችሉበትን ስልት መቀየስና አስፈላጊ መሆኑን ያመላከተና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመሆን በስፋት መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ ነበር ::


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: host
Date Posted: 3/22/2013
Number of Views: 15067

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement