View in English alphabet 
 | Tuesday, September 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

መጻጉዕ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“አላ ሰብእ አልብየ” ሰው የለኝም (ዮሐ 5፥7)


በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ከፈለኝ ወልደጊዮርጊስ


ቤተ ሳይዳ ወይም ቤተሰዳ ማለት የምህረት ቤት ማለት ነው አምስትም መመላለሻ ያላት ማለትም አምስቱ አዕማደ ምሥጢር የሚገኝባት በነዚህ ሁሉ ድህነትን የምትሰጥ ናትና ቤተሳይዳ የምህረት ቤት ናት። አምስቱ አዕማድም የተባሉትም 1) ምስጢረ ሥላሴ 2) ምስጢረ ሥጋዌ 3) ምስጢረ ጥምቀት 4) ምስጢረ ቁርባን እና 5) ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን የሚባሉ ናቸው። እንግዲህ ወደዚች የምህረት ቦታ፣ የፀበል ቦታ በመጀመሪያ ሄዶ የተገኘ፣ ገብቶ የተጠመቀ፣ ካለበት ሕመም ሁሉ ፍጹም ጤነኛ ይሆናል። ይህም ሰው 38ዓመት ሙሉ በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ወደ ጸበሏ የሚወስደው፣ በርትቶ ጸንቶ ጠብቆ በሰው ፊት የሚያስገባው ሰው አጥቶ ለብዙ ዘመናት በተስፋ መቁረጥ ላይ ይገኝ የነበረ ነበር።

 

ጌታችን ደግሞ ወደዚህች ምድር የመጣው የታሰሩትን ሊፈታቸው፣ የታመሙትን ሊፈውሳቸው የሞቱትን ሊያስነሳቸው በጨለማ የነበሩትን ሊያበራላቸው ነውና ሕመማችን ሊሸከምልን ነውና ወደዚ ሰው እራሱ ሄደ ቀረበ ለምን? ነቢዮ ኢሳይያስ (በም 53፥4) እንደገለፅልን “ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ” (ደዌያችንን ተቀበለ ህማማችንንም ተሸከመ) ብሏልና። እራሱ ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስም (ማቴ11፥28) ላይ “እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደኔ ኑ እኔ አቀልላችኋለሁ” ብሏልና። ትንቢቱ ሊፈፅም የተናገረውንም ሊያሟላ ወደዚ ሰው ሄደ ቀረበ እናም “ትፈቅድኑ ትሕየው” ልጄ ሆይ ልትድን ትወዳለህን? ልትድን ትፈቅዳለህን? አለው ወገኖቼ እስቲ አስቡት! እንኳንስ 38ዓመት ያህል ሕመምን ተሸክሞ የኖረ ይቅርና ሁለት ቀን ሆዱን የቆረጠው፣ ላንዲት ሰዓት ራስ ምታት የሚበጠብጠው፣ ወይም የጥርስ ሕመም አስጨንቆት የሚያንቆራጥጠው እንኳ መድሃኒት ፍለጋ፣ እረፍት ፍለጋ፣ ሐኪምን ፍለጋ ለመፈለግ ይሯሯጥ የለም እንዴ? ለምን? ሊድን ነዋ፣ እፎይ ሊል ነዋ በሽታ እኮ አይጣል ነዋ፦ ያለጊዜ ይቀጫል፣ ተስፋን ያጨልማል፣ ሥለዚህ እንዲህ ያለ መድኃኒት፣ እንዲህ ያለ ሃኪም እንደዚህ ባለ ቦታ አለ ሲባል መሮጥ ነው፣ ቀድሞ ወረፋ ይዞ መገኝት ነው። ይሄ ሰው ግን እንዳይሮጥ በምን እግሮቹ፣ እንዳይንቀሳቀስ በየትኛው ጡንቾቹ ብቻ ተስፋው ሞቶ፣ ሰውም አጥቶ በአልጋ ተኝቶ 38ዓመት ኑሮ እንበለውና ኖሮ። በዚህ ሁኔታ የነበረው ያሰው” ልትድን ትወዳለህን” የሚል ቃልን ሲሰማ ምን ተሰምቶት ይሆን? ምንስ ታስቦት ይሆን? አዎ ስሜቱ ቀዝቃዛ፣ የመዳን ተስፋው ደንዝዞ ተስፋም ቆርጦ አዬዬ እኔማ ሰው የለኝም አለ። አዎ ወገኖቼ! ሰው ለሠው ያስፈልገዋል፣ ለችግራችን፣ ለኑሮም፣ ለምክር ሰው ያስፈልገናል፣እንጨት እንኳን አንድ ብቻውን አይነድም ሁለት ሦስት ሲሆን ነው፣ ብቻውን እንኳ አንድ እጅ አያጨበጭብም ሁለተኛውም ሲኖር ነው። ሰው ለሠው መድኃኒቱ ነው ። እግዚአብሔርም አባታችንን አዳምን ብቻውን ይሆን ዘንድ አይገባም ሲል ሌላ ረዳት ሰው ፈጠረለት እናታችንን ሔዋንን፧ ምክንያቱም ሰው ያለ ሰው መኖር አይችልምና ነው። ዛሬ ብዙዎች ከሰው ተለይተን፣ ከወገን ወጥተንና ተለይተን ብቻችንን መኖር ይሻለናል ይላሉ። የብቸኝነት ዳገት እየቧጠጡ የአውሬነትን ኑሮ እየመረጡ ይታያሉ። አራዊት እንኳን በሕብረት ይኖራሉ ሰው ግን ከሰው ልለይ ይላል ይሄ ሐሰት ነው። ቢታመም ወደ ሃኪም መሄድ አይቀርም፣ ቢርበው መብላቱ አይቀርም፦ ሃኪሙም ሆነ ገበሬው ግን ለኑሮው እንዳስፈለጉት ይዘነጋል። ይህም ሰው ሰው የለኝም ሲል በሰው ዕርዳታ ሊድን ይችል እንደነበረ ተገንዝቦ ነበረ። ብቻውን መዳን አለመቻሉንም አውቆት ነበር። ሰው ጠፍትቶ ግን አልነበረም። ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ (በም2፥1-11) ላይ እንደገረን በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዘ አንድ ሰው ነበረ አራቱ ዘመዶቹ በአልጋ ላይ ተሸክመውት ጌታችን ወዳለበት ቦታ ይዘውት መጡ ስለሕዝቡም ብዛት ወደ ጌታ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣሪያ ነድለው አነሱና ሽባው የተኛበትን አልጋ በገመድ አወረዱት። ጌታችን ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን ፈወሰላቸው። የዚህ ሰው ድህነት የተገኘው በሰዎች ዕምነት ነበረ የ38ቱ ዓመት በሸተኛም ያጣው ሰው  ሳይሆን ዕምነት ያለው፣ የሚራራ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር ያጣው። ሥለዚህም ከነበሽታው ኖረ። ዛሬም እንዲሁ ነው ። ሰው ያስፈልገናል ዕምነት ያለው ሰው፣ ቅዱስ ሰው፣ፃድቅ ሰው፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆምልን ሰው ያስፈልገናል እግዚአብሔር የሚሰማው። ምክንያቱም ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው(መዝ 33፥15) “እስመ አዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር ኅበ ፃድቃኑ ወእዝኑሂ ኅበ ሥዕለቶሙ” የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደፃድቃን ጆሮቹም ወደጩኸታቸው (ማለት ወደ ልመናቸው፣ ወደ ጸሎታቸው፣ ወደ አማላጅነታቸው) ናቸው ይለናልና። ሥለዚህ ጸሎታቸውን የሚሰማላቸው፣ ልመናቸውን የሚቀበላቸው፣ አማላጅነታቸውን እሺ የሚላቸው ፃድቃን ያስፈልጉናል፣ የእነሱ ጸሎታቸው፣ እንባቸው ድውይን ይፈውሳል፣ ሙታንንም ያስነሳል የሃገር ሰላምንም ይመልሳል። ማርያምና ማርታ የጌታ ወዳጆች የሐዋርያት አገልጋዮች ነበሩ ወንድማቸው ቢሞት እውነተኛ እንባ አለቀሱለት። ጌታቸውንም ለመኑት ስለእምባቸው አልአዛርን ወንድማቸውን ከመቃብር አስነሳላቸው ከሞት ወደ ሕይወት መለሰላቸው። የ38ዓመቱ በሽተኛ በእንደዚህ ዓይነቱ ቤተሰቦች እና ሰዎች የተከበበ በመሆኑ “ሰው የለኝም” አለ። ወገኖቼ ለመሆኑ ዛሬ እኛ ሰው አለን ስንል በምን መለኪያ አይተን ይሆን በየትኛው መስፈርት መዝነን ይሆን? ባለን ጊዜ የሚወደንን፣ ባማርን ጊዜ የሚያፈቅረንን፣ በሰጠን ጊዜ የሚያመሰግነንን፣ በሞላልን ጊዜ የሚቀርበንን፣ ሰው ይሆን? አይደለም ባጣን ጊዜ ገሸሽ የሚልብንን፣ በጎሰቆልን ጊዜ የሚጠላንን በጐደለብን ጊዜ ላይኑ የሚፀየፈንን፣ በታመንን ጊዜ የሚሰለቸንን ሰው ሰው አለን ልንል አንችልም። ነገር ግን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸውን፣ ለሃገር ለወገን የሚሰማቸውን፣ ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚገዳቸውን ጸሎታቸው የሚሰምርላቸውን፣ ጸጋ እግዚአብሔር ያላቸውን ፃድቃንን ቅዱሳንን “ሰዎች አሉን” የሚቆሙልን፤ ሰዎች አሉን የሚያማልዱን ልንል እንችላለን:: አቡነ ተክለሃይማኖት አሉልን የሚለምኑልን፣  ክርስቶስ ሰምራ አለችልን የምትማልድን ፤ ከሁሉም በላይ እመቤታችን አለችልን በቃልኪዳኗ የቆመችልን እንላለን። ጌታችን ግን የሰዎችን እምነት አይቶ ሽባውን ተርትሮታል። የእመቤታችን ልመና ሰምቶ በላዔ ሰብን ምሮታል። የነማርታን ዕንባ አብሶ አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል “የፃድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ ኃይልን ታደርጋለች” (ያዕ 5፥16) ሥለዚህም ወገኖቼ እግዚአብሔር ቅዱስ ሰው አያሳጣን፣ በዓላማ የጸኑ የቤተክርስቲያን አባቶችን አያሳጣን ያን ጊዜ ነው “ሰው አለን” ማለት የምንችለው። ብንበድል የምንታረቅባቸው፣ ብንርቅ የምንቀርብባቸው፣ ብንታመም የምንድንባቸው በፊት ቅዱሳን ሐዋርያትን ዛሬ ደግሞ በእግራቸው የተተኩ አባቶችን እግዚአብሔር ሰጥቶናል። ስለዚህም ሰዎች አሉን ወደ ቤተሳይዳ፣ ወደ ምህረት ቦታዋ ወደ ቤተክርስቲያን የሚያስገቡን በፀበሏ የሚነክሩን በጸሎታቸው የሚያጠነክሩን እንላለን።


ይቀጥላል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: admin
Date Posted: 3/31/2013
Number of Views: 7392

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement