View in English alphabet 
 | Wednesday, October 27, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

መስቀል:- ትርጉሙ፤ ክብሩ፤ ምሥጢሩ እና አከባበሩ

 
 «የመስቀሉ ኃይል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው»

1.   መግቢያ

 መስቀልና ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያና መስቀል የማይነጣጠሉ፤ ተለያይተው የማይቀርቡ ወዳጆች ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ምዕራፈ መስቀል፤ ልጆቿም የመስቀል ፍሬዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ያገኙትን የነገረ-መስቀሉን ትምህርት በልቦናቸው ሰሌዳ ጽፈው ለብዙ ሺህና መቶ ዓመታት ቆይተዋልና፡፡ በዘወትር ጸሎታቸውም «መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ፤ መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት» ማለታቸውም ይህንኑ ያጠይቃል፡፡

 « መስቀል» የሚለው ሥም ሲነሳ ከአማናዊ ትርጉሙ፤ በሱ ላይ ከተፈጸመው የድኅነት ተግባር በተጨማሪ በሰው ኅሊና የሚቀረፀው መስከረም በባተ በአሥራ ስድስት የሚለኮሰው ደመራ፤ በነጋው /በአሥራ ሰባት/ የሚደረገው ሃይማኖታዊና ባሕላዊ አከባበር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነገረ መስቀሉ ይነገራል፤ ይዘከራል፤ የመስቀሉ ትርጉም ይታወቃል፤ ባሕላዊ አከባበሩም የክርስትናን ሕይወት ያሣያል፤ ግዘፍ ነሥቶ ይገለጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን የመስቀሉ ልጆች ናቸው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
 
2.  ትርጉሙና ጥንተ ታሪኩ
 
መስቀል የሚለው ቃል «ሰቀለ» ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም የተመሣቀለ ማለት ነው፡ ለምሳሌ ሰው እጁን ወደጎን ዘርግቶ ሲቆም፤ አእዋፍ ሲበሩ የመስቀልን ቅርጽ ያሣያሉ፡፡ የመስቀልን ቅርጽ ይይዛሉ፡፡ ለሞት የሚያበቃ ማንኛውም መከራ እና አይሁድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዕለተዓርብ የተሰቀሉበት በ«ተ» ቅርጽ የተሠራው ዕጸ መስቀልም መስቀል ይባላሉ፡፡

ሰውን በመስቀል መስቀል የተጀመረው በፋርስ ነው፡፡ በፋርስ ሰዎች አምልኮት የመሬት አምላክ ኦርሙዝድ/ ORMUZD/ ይባላል፡፡ ወንጀለኛ በሀገራቸው ሲገኝ ቅጣቱን በመሬት የተቀበለ እንደሆነ አምላካቸው እንዳይረክስ ወንጀለኛውን ሁሉ በመስቀል ይሰቅሉት ነበር፡፡ ይህ አድራጎት እንደ ልማድ ሆኖ በሮማ ግዛት ሁሉ የተለመደ ሕግ ሆነ፡፡ በኦሪትም ሥርዓት በመ ስቀል ይሰቅሉት ነበር፡፡ በሮም ግዛት ሁሉ የተለመደ ሕግ ሆነ፡፡ በኦሪትም ሥርዓት በመስቀል / በስቅላት/ የሚቀጡ ሁሉ ርጉማን ውጉዛን ነበሩ፡፡ በፋርስ ግዛት ኃላም በሮማውያን አገዛዝ ሰልጥኖ ነበረው ሰዎችን በመስቀል የመስቀል ቅጣት ብዙ ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮችም ይጨምር ነበር፡፡

ወንጀለኛው ከመስቀሉ በፊት ይገረፋል፡፡ መስቀያውን ተሸክሞ እየተንገላታ ከከተማ ውጪ ወዳለ መስቀያ ቦታ ይወሰዳል፡፡ ሕማሙን ይረሣ ዘንድ የኢየሩሳሌም ሴቶች ሥቃዩን ለማደንዘዝ መጠጥ የጠጡታል፡፡ ከዚያም በመስቀሉ ላይ እጆቹንና እግሮቹን ይቸነከራል ወይም በገመድ ይታሠራል፡፡ ከራሱ በላይም ወንጀሉ ተጽፎ ይለጠፍበታል፡፡ የተሰቀለው ሰው የሚሞተው ደሙን በማፍሰስ ሳይሆን በልቡ ድካም በመሆኑ ብዙ ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው የምትለየው በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ ወንጀለኛውን ቶሎ መግደል ሲፈልጉም እግሮቹን ይሰብሩ ነበር፡፡ 

ክፉዎች አይሁድ መድኃኒታችን ኢየሰሱስ ክርስቶስን በሰቀሉበት ጊዜ ያደረጉትን ከላይ ከተዘረዘረው ጋር ማስተያየት ይቻላል፡፡ አስቀድመው ገርፈውታል /ማቴ 27÷26/ መስቀሉን አሸክመው አንገላተውታል /ዮሐ 19÷17-20/፡፡ በሰፍነግ ሆምጣጣ ነገር አጠጥተውታል/ ማነ27፡-34/፤ እግሮቹንና እጆቹን ቸንክረውታል፤ ጎኑን በጦር ወግተውታል /ማሐ 20÷25/፡፡ ክብር ምሥጋና ይግባውና የሰማይና የምድር ፈጣሪ መሆኑን ሳይገነዘቡ «ወንጀል ተናግሯል» ሲሉ « የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ» የሚል ጽሑፍ ከበላዩ ለጥፈውበታል /ዮሐ 19÷19/፡፡ ከርሱ አንድም አጥንት አይሰበርም የሚለው የነቢዩ የዳዊት ቃል ይፈጽም ዘንድ እንደሌሎች ወንጀለኞች እግሮቹ አልተሰበሩም /ማር 15÷44/ በራሱ ፈቃድ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ እንጂ፡፡ 

በዚህ መልኩ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት በኋላ የርጉማንና ውጉዛን መስቀያ የነበረው መስቀል የነጻነታችን አዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን፤ የክርስቲኖች የነጻነትና የድል ምልክት ሆኗል፡፡

ከሕገ እግዚአብሔር ከአምልኮተ እግዚአብሔር የወጡ ፋርሶችና ሮማውያን ወንጀለኞቻቸውን ለመቅጣት የመግደያ መሣሪያ ቢያደርጉትም መስቀል ከጥንት ጀምሮ በብዙ ምሳሌ የተገለጠ መሆኑን መጻሕፍት ቅዱሳት ይመሰክራሉ፡፡

የኖኅ መርከብ የተሠራችበት እንጨትና ሙሴ የፈርኦንን መሰግላን ድል ያደረገበት በትር የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡፡ አስቀድሞ ጻድቁ ያዕቆብ ልጆቹን ኤፍሬምንና ምናሴን አንዱን እጁን በሌላኛው ላይ አስተላልፎ /በመስቀል ቅርጽ/ የባረካቸውም በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርቶ ነገረ መስቀሉን ተረድቶ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም « ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኃቸው» /መዝ 59÷4/ ብሎ ምእመናን በክርስቶስ አምነው በመስቀል አማትበው ከማየ ሥራዌ ከማየ ድምሳሴ፤ ከኃጢአት፤ ከአምልኮ ጣኦት እንደሚድኑ፤ አጋንንትን፤ መናፍቃንን ፍትወታት እኩያትን ድል እንደሚየደርጉ ተናገረ፡፡

                                                                                             ዲ. ኤፍሬም እሸቴ


Written By: host
Date Posted: 12/19/2007
Number of Views: 6458

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement