View in English alphabet 
 | Tuesday, September 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ትንሣኤ

“ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም”

እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ መዝ( ፸፯÷፷፭)

በቀሲስ አድማሴ መኮንን

 

በትራክት መልክ የተዘጋጀውን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ።

ታላቁ አባት ቅዱስ ኤፍሬም ሃይማኖተ አበው በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ ፵፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፮ ላይ ልዩ በሚሆን ድንቅ በሚያሰኝ መለወጥ ይስማማው በነበረ ሥጋ በተወለደው ልደት ወደ አልተለመደው ነገር /ወደ ሞት/  ወደ መስቀል ደረሰ ( ኢሣ ፱÷፮ _ ፯)::  እኛን የሚመስል ሥጋን ገንዘብ አደረገ ይኸውም ከሁሉ ጋራ አንድ ነው ከባህርያችን የተገኘው አንድ አካል አንድ ባህርይ የሆነ እርሱ ሕማም ሞት የሌለበት ሲሆን በሥጋ ባህርይ ኃጥያት ሳይኖርበት ታመመ ሞተ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጥያት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጥአት አደረግነው(፪ኛቆሮ ፭÷፳፩)“ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ኃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሣለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማትን እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም ነገር ግን የባርያውን መለክ ይዞ በሰው ምሣሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ “(ፊልጵ፪÷፭ _ ፱)“

አምላክ ቃል በሥጋ እንደ ታመመ በሥጋ ተሰቅሎ እንደሞተ ከሙታን ተለይቶ ለሚነሣ በኲር እንደሆነ እሱ ሕይወትን የሚያድል እንደሆነ የማያምን ቢኖር እርሱ የተለየ የተወገዘ ነው “አለ::  ምክንያቱም ትንሣኤ ሙታን እንዳለ ከሞት በኋላ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረት ሳይሆን መልካም የሠሩ ከመልካም ሥራቸው ጋር ለክብር ትንሣኤ ፤ክፉ የሰሩ ከክፉ ግብራቸው ጋር ለፍርድ ትንሣኤ ተነስተው እንደሚቀርቡ ዋጋቸውንም እንደሚያገኙ ያስገነዝበናል። ከአብ ተወልዶ የመጣ ቃልስ በመለኮቱ ሕማም ሞት የተለየበት ነው:: እርሱ ከህማም ከሞት የራቀ ነውና እርሱ ክቡር ነው:: የእግዚአብሔር ባህርይ የማይመረመር ነው:: እርሱ ለሁሉም ህይወትን የሚያድል ነው:: ይህ ባህርይ ከአብ ባህርይ የተለየ አይደለም ከአብ ጋር አንድ ነው እንጂ:: ስለ እኛ መከራን ይቀበል ዘንድ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሚታመም የሚሞት ሥጋን ለመዋኃድ ፈጠረ ሥጋንም ከእርሱ ጋር አንድ አደረገው:: ይኸው ለኛ ቤዛ ሆኖ መከራ ይቀበል ዘንድ ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ ሞትን የተቀበለው ነው:: ሁላችንንም ከሞት ከፍዳ ያድነን ዘንድ አምላክ ነውና በባህርዬ ስልጣኑም ለሥጋ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ መከራ ተቀበለ:: ለሙታን በኲር ሆነ::

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድህነተ ዓለምን ከፈጸመ ቦኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ:: ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስበሶ መቅረትን ሊያስቀር ነው:: በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ ይኸውም ዲያቢሎስ በአዳም ላይ ያጸናው የባርነት ቀንበርን ሰበረ:: በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ነጻ ያወጣቸው ዘንድ ነው መለኮት በተዋህዶ ከሥጋም ከነፍስ ጋር ነበር:: ለዚህ ነው መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለም /መዝ ፲፭÷ ፲ / ”ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱሱንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም ” ያለው ቅዱስ ጴጥሮስም ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ )እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ አመጸኞች አንድ ጊዜ በኃጥያት ምክንያት ስለ ሰው ልጆች ኃጥያት ተላልፎ በመሰጠት ሞትዋል በሥጋ ሞተ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ ያን ሥጋ ነፍስ እንደተለየችው መለኮት አልተለየውም በእርሱ ደግሞ መለኮት በተዋሐዳት ነፍስ ሄዶ በወህኒ ለነበሩት ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው “እለ ውስተ ሲኦል ጻዑ ወለእለ ውስተ ጽልመት ተከሰቱ “ በማለት ከሲኦል እስራት ነጻ እንዲወጡ ከጨለማው ግዞት እንዲላቀቁ ነገረ ድህነትን ሰበካቸው አስተማራቸው::

ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት 

በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት የቆየው በነቢዩ በቅዱስ ዳዊት ሥጋዬ በተስፋ ታድራለች በማለት የተናገረውን የትንቢት ቃል ሊስረግጠው እና ሊያጸናው ነው:: (መዝ ፲፭÷ ፱ ) ምስጢራዊ ትርጉሙም ፦ሦስት ሌሊት በመቃብር የወረደ መለኮት ነው ተስፋ ትንሣኤውም በተዋህዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኮት ነው ነቢዩ ሆሴም “ ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እርሱ ሰብሮናልና - በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው እርሱ ፈውሶናል መርገመ ሥጋን አስወግዶ ከሞት ወደ ህይወት አሸጋግሮናልና እርሱ መትቶናል፦እርሱ ይጠግነናል ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል በሦስተኛው ቀን ያስነሳናል” በማለት አበው መተርጉማን ያመሰጥሩታል በሦስተኛው ቀን ትንሣኤው መሆኑን አረጋግጧል(ሆሴ፮÷ ፲፪)።ይልቁንም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ከጻፎች ከሽማግሌዎች ከካህናት አለቆች ብዙ መከራ ይቀበል ዘንድ እና እንደሚገድሉት ከዚያም በሦስተኛ ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸዋል (ማቴ፲፮ ÷፳፩) ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ በቀር ምልክት አይሰጠውም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወል ዕጓለ ሕመያው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል ብሏቸዋል(ማቴ ፲፪÷፴፰_፵ )

ሞትን ድል አድርጎ ስለ መነሣቱ፦

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የተነሣው በታላቅ ኃይል እና ስልጣን ነው:: ይኸውም የባህርይ ገንዘቡ ነው:: ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሳት ዘንድ) አኖራለሁ ( በፈቃዴ እሞታለሁ ) ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም ላኖራትም(በገነት ነፍሴን በመቃብር ሥጋዬን ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት)ሥጋዬን ነፍሴን አዋህጄ ላነሣት ስልጣን አለኝ በማለት አምላካችን ድንቅ የሆነ የባህርያ ገንዘቡ በሆነው አምላካዊ ሥራውን የገለጸው ( ዮሐ ፲÷፲፯ )።

ታላቁ አባት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ” ተጨነቀ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም ሊታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም ” በማለት ተናግሯል:: እንዲሁ ይህም የትንቢት ቃል የሚያመለክተው በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ የትንቢት ቃል (ኢሣ፶፫፥፯) ቅዱስ ጴጥሮስም በኃይሉ በስልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነስቷል እርሱ የትንሣኤ እና የህይወት ባለቤት ነውና "ኢየሱስ አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት ዘየአምን ብየ እመኒ ሞተ የሐዩ ወኩሉ ዘሕያው ወየአምን ብየ ኢይመውት ለዓለም (ኢየሱስም ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል)" (ዮሐ፲፩÷፳፭) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ቃል ብቻ አላበቃም የህይወትን እራስ ገደላችሁ በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ እርሱን ግን እግዚአብሔር አስነሳው ለምን አለ ?ለሚሉ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን አበው ቅዱሳት መጻሕፍትን አጣቅሰው አራቀው ትክክለኛውን ምስጢር ተርጉመው አስተምረዋል።

እግዚአብሔር የሚለው የመለኮት መጠርያ ሲሆን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ሲጠራ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫው ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ ወውእቱ ቃል ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ ቃል ወዝንቱ እምቀዲሙ ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ (ዮሐ፩÷፪) ስለዚህ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው አንዲት በሆኑት በአብ በራሱ እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሳ ተብሎ ይተረጎማል ይታመናል ትንቢያትም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው (ወተንስአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለፀሮ በድህሬሁ) እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነሳ እንደሚነቃ ተነሳ የወይን ስካር እንደተወ እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹን በኋላው መታ መዝ( ፸፯÷፷፭)።

በአዲስ መቃብር ስለመቀበሩ፦ 

በእሥራኤል ባህል የአባቶቻቸው መቃብር ካረፈበት የመቅበር ልማድ አላቸው። ዮሴፍ የእስራኤልን ልጆች እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንስታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ ያማላቸው የአባቶቹ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አጽም ካረፈበት መቃብር ፈልጎ ነው ( ዘፍ ፶፥፳፭ )። ቤቴል የነበረው ሽማግሌም እንዲሁ ነበር የተናገረው (፩ኛነገ ፲፫፥፴፩)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ የቀበሩት እንደ እስራኤላውያን የቀብር ስርአት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት በአዲስ መቃብር ነበር ያም አዲስ መቃብር ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውን በንጹህ በፍታ ከፈነው ከአለት በወቀረው በአዲስ መቃብር አኖረው በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ (ማቴ ፳፯÷፶፱) ይኽም የሆነው እርሱ ባወቀ በራሱ ጥበብ ነው እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል ምክንያቱም በ፩ኛነገ፲፫÷፪ የኤልሳዕ አጽም አጠገብ የተቀበራው አጽም በነካው ጊዜ እንደተነሳ በራሱ ጊዜ ሣይሆን የቅዱሱ አጽም ነክቶት ነው እንጅ እንዳይሉ ይህንን ምክንያት ለማጥፋት ነው በአዲስ መቃብር የተቀበረው።

በዝግ መቃብር ስለመነሣቱ፦

ጌታችንን ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩትበኃላ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው ያ ሰው ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሎ በህይወቱ ያስተማረው ትዝ አለን እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስህተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት(ማቴ ፳፯፥፷፪-፷፮)። ጲላጦስም “እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው እነርሱም ድንጋዩን ከጠባቂዎች ጋር አትመው አስጠበቁ።
ታላቁ አባት ሄኔሬዎስም በሃይማኖተ አበው ክፍል፪÷፳፯ ዳግመኛ ትንሣኤ ሙታንን በተናገረበት አንቀጽ በዲዲስቅልያ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የምንሆን እኛ ምእመናን በወንጌል እንዲህ እናምናለን አሉ የታመነ ነው በተናገረውም ሐሰት የለበትም መዝ፹፱ ዳዊት እግዚአብሔር በነገር ሁሉ የታመነ ነው በሥራውም ሁሉ እውነተኛ ነው ብሏልና ከንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ሥጋን ፈጥሮ የተዋሐደ እርሱ ነው ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ሙታንንም ሁሉ የሚያስነሣ እርሱ ብቻ ነው እንዳለው (ሮሜ ፩÷፫_፭) በመስቀል መከራ እንደ ተቀበለ እንደሞተ እንደተቀበረ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እንዳዩት ተናገረ።

ቅዱስ አትናትዮስም ዳግመኛ እንዲህ አለ ፀሐይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ሁሉ በጨለማ ተያዙ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በእንጨት ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ ባለሟሉ መልአክም ዐላውያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ ከመላዕክት መካከል ወጣ የክርስቶስም ቸርነቱ በከለከላቸው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደው ከላይ እስከታችም ከሁለት አደረገው:: መላዕክትም ሁሉ ከሰማይ ሆነው እርሱን አይተው በአንድነት ሲቆጡ የአብ ምህረቱ የወልድ ትዕግስቱ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከላቸው ፀሐይ ብርሃኑን ነሣ ዓለምን በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ተወው:: ይህ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ብርሃን ታየ። ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ (መዝ ፸፫÷፲፪-፲፮ ፣ ፩ኛጴጥ፫÷፲፰- ፳) ሲኦል ተናወጠች መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት:: ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውን ሁሉ ጠበቀ ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ተወው። ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወርዳ ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሣትን አዳነች:: ሲኦልንም በዘበዘች ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች:: ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ:: ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች። በዚያችም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሱ)የብረት ቁልፎችም ተቀጠቀጡ (ፍዳ መርገም ጠፋ )ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃንን ነፍሳት ፈታች አለ:: ቴዎዶጦስ የተባለውም አባት “በህማሙ ህማምን ሊያጠፋ፣ በሞቱ ሞትን ሊያጠፋ የሰውን ህማም ገንዘብ አደረገ።” በማለት አስተምሯል:

አምላካችን እግዚአብሔር ከትንሣኤው ረድኤት በረከት ያሣትፈን!

የእናታችን ቅድስት ድንግልማርያም ምልጃ : የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት አይለየን።

 

 

 

 

 

አዘጋጅ፡-
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል
፳፻፭ ዓ.ም.

 

 

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !  አሜን


Written By: host
Date Posted: 5/3/2013
Number of Views: 8812

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement