1. ማዕከሉ ስብከተ ወንጌልን በማጠናከር ረገድ የማኅበሩ አባላት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ያለውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በማጠናከር እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ የተለያዩ ጉባኤያትን በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በማዘጋጀት፣ ጉባኤያት የሚያዘጋጁ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በመርዳት፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ማኅበራት ጋር ጉባኤያትን በትብብር በማዘጋጀት፣ በየበዓላቱ በራሪ ጽሁፎችን በማዘጋጀት፣ በማኅበሩ ድረ ገጽ ላይ ትምህርታዊ ጽሑፎችን በማውጣት አገልግሎቱን በማጠናከር ላይ ይገኛል።
2. በማዕከሉ የአብነት ትምህርት ቤቶችና የቅዱሳን መካናትን ለመርዳትና ለማቋቋም በተደረገውም ጥረት በዋናው ማዕከል በዚህ ረገድ የተያዘውን የጠራ አካሄድ በመከተል ላለፉት ዓመታት በተከታትይነት እያደገ የመጣው የምእመናንና የአባላት ሱታፌ እጅጉን የሚያበረታታ ነው። በ2005 ዓ.ም. ብቻ ከ$76,000 በላይ ዶላር ለማሰባሰብ እና ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ወደ ዋናው ማዕከል ለመላክ ተችሏል።
3. በዚህ ዓመት ጉልህ ውጤት ከተገኘባቸው የአገልግሎት መስኮች በሚዲያ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው። የአሜሪካ ማዕከል ከማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያ ዋና ክፍል ጋር በመተባበር የጀመረውን የቴሌቪዥን አገልግሎት አድማስ ለማስፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል። የቴሌቪዥን እና የሬድዮ መርሃ ግብር የሚተላለፍበት ድረ ገጽ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መረጃ ድረ ገጽ፣ ገዳማትን በቀላሉ ለመርዳት የሚያስችል ደረ ገጽ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናትን በዓላት በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ድረ ገጽ አዘጋጅቶ እንዳቀረበ ተገልጿል።
4. መጪውን ትውልድና ሌሎችን ለመድረስ ቤተ ክርስቲያንን ለሁሉም (ኢትዮጵያዊያን ላልሆኑ ጭምር) ማስተዋወቅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋር ከሚስማሙ፣ በምስጢራት ከምንተባበራቸው ከሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር ለማገልገል የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ተገልጿል።
በአጠቃላይ በአሜሪካ ያለው የማኅበሩን አገልግሎት በየሥፍራው ያለውን የቤተ ክርስቲያንና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ እንዲሆን በማድረግ፥‘በውጭ ሀገር ያለው የማኅበሩ ተልዕኮ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ምእመኑን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ/ማጽናት እንዲሆን እና ማኅበሩ በውጭ ሀገር አገልግሎት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የተቀመጠውን ተግባራዊ ለማድረግ የአሜሪካ ማዕከል የበኩሉን እየሞከረ እንደሆነ ተገልጿል።
የዕቅድ አፈጻጸሙ እየቀረበ በጉባኤው ላይ የተገኙት መልአክ ሃይል ጌታሁን ያቀረቡት ያሬዳዊ ዜማ ለጉባኤው ድምቀት ሆኗል።
በመቀጠልም በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል አወቃቀር መሠረት በማዕከል ደረጃ ያሉ የክፍሎች እና በየግዛቱ ያሉ ንዑሳን ማዕከል የዕቅድ አፈጻጸም የቀረበ ሲሆን በቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም ላይ በአባላት ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በጉባኤው ላይ የተገኙ አባቶች በቀረበው ሪፖርት ላይ ያላቸውን ሃሳብ እና አስተያየት ሰጥተው የጠዋቱ መርሃ ግብር በምሳ እረፍት ተጠናቋል።
ቀጣይ ሪፖርቶችን ይዘን ስለምንቀርብ ተመልሰው ይጎብኙን።