View in English alphabet 
 | Tuesday, April 16, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ሀብተማርያም

በዚችም ቀን (ሕዳር ፳፮) የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትዮጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ አገሩ የራውዕይ በምትባል በስተምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው፤ በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚች አገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው። እጅግም ሀብታም ነበር፤ ብዙ ንብረትም አለው በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ። ይቺም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት። ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋህነትን ትሕትናን ፍቅርን ትዕግሥትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን።

በእንደዚህም ሳለች ጌታችን በወንጌል ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋን ምን ይጠቅመዋል እንዳለ ላንች በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሽ የሚል ሐሳብ መጣባት። ከዚህም በኋላ ወጣች ፈጥናም በሀገርዋ ትይዩ ወደሆነ ምድረ በዳ ደርሳ ወደመካከሉ ገባች። በዚያም በረሀ አራዊት እንጂ ሰው አይኖርበትም። በዚያም ደጃፍዋ የተከፈተ ታናሽ ዋሻ አግኝታ ምንም ምን ሳትነጋገር ወደ ውስጧ ገብታ ቆመች የዳዊትንም መዝሙር የሚጸልይ ሰው አይታ ደነገጠች። እርሱም ባያት ጊዜ ፍርሀትና መንቀጥቀጥ በላዩ ወረደበት በመስቀል ምልክት በላይዋ አማትቦ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ እንዳልሸሸችም አይቶ ሰው መሆንዋን አወቀ፤ በአወቀም ጊዜ እንዲህ ብሎ ገሠጻት “ወደዚህ ምን አመጣሽ ለእኔ እንቅፋት ልትሆኝ ነውን አሁንም ከዚህ ፈጥነሽ ሒጂ” አላት።

እርሷም አባቴ ሆይ አንተ እንዳሰብከው አይደለሁም። እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዩ ነኝ እንጂ በእርሱ ፍቅርና በእናቱ በእመቤቴ በቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር ያለኝን ሁሉ ትቼ ንቄ ከዓለም ወጥቼ ወደዚህ መጣሁ፤ በዚህ ቦታም ከአራዊት በቀር ሰው እንዳለ አላወቅሁም አሁንም አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ወደ ሌላ ቦታ እሔዳለሁ አለችው።

በዚያንም ጊዜ ከርሷ የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት እንዲህ አላት “ዜናው ወደ ዓለም ሁሉ የሚወጣ በሕይወተ ሥጋም እያለ የብዙዎች ስዎች ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣ እንደመላእክትም ክንፎች ተሰጥተውት ወደ አርያም ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትና የሦስትነትን ምሥጢር የሚያይ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ወደቤትሽ ተመለሽ” አላት። ቅድስት ዮስቴናም ከዚያ ሽማግሌ ባሕታዊ ይህን በሰማች ጊዜ አድንቃ የፈጣሪዬ ፈቃዱ ከሆነ ብላ ወደቤቷ ተመለሰች።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ፀንሳ ይህን ደም ግባቱ መልኩ የሚያምር ልጅን ወለደች። በእናትና በአባት ቤትም ታላቅ ደስታ ሁኖ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ለዘመዶቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ታላቅ ምሳ አደረጉ እነርሱም በጠገቡ ጊዜ እነርሱንም ሕፃኑንም መረቋቸው።

ሕፃኑም አርባ ቀን በሆነው ጊዜ እንደ ሕጉና እንደ ሥርዓቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ካህኑም ተቀብሎ በአጠመቀው ጊዜ ስሙን ሀብተ ማርያም ብሎ ሰይሞ ለክርስትና አባቱ ሰጠው። ሕፃኑም ጥቂት በአደገ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ሲሉ ሰምቶ ሕፃን ሀብተ ማርያም በልቡ ይቺ ጸሎት መልካም ናት እኔም መርጫታለሁ በዚህ ዓለም ስሕተትን አስቦ ከመሥራት በሚመጣውም ዓለም ከገሀነም እንደምድንባት አውቃለሁና አለ። ይህንንም ብሎ የሚሠራውን ማንም ሳያውቅበት ይህን ጽሎት ከማዘውተር ጋር ሌሊቱን ሁሉ በመስገድ ይጸልይ ነበር።

ከዚህም በኋላ አባቱ የበጎች ጠባቂ አደረገው በአንዲት ዕለትም በጎችን እየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ ጠባቂዎች እሸት ተሸክመው መጥተው ና እንብላ አሉት እርሱ ግን ከወዴት እንዳመጣችሁት የማላውቀውን አልበላም አላቸው፤ እነርሱም በቁጣ ዐይን ተመልክተው ተጠቃቀሱበት። እሸቱንም በልተው ከጨረሱ በኋላ የከበረ ሕፃን ሀብተ ማርያምም ታላቅ ዝናም ስለመጣ ወደየቤታችን እንመለስ ከዚህ የምንጠለልበትና የምንጠጋበት ቤት ወይም ዋሻ የለምና አላቸው። እነርሱም እኛ የማናየውን የሚያይ ሌላ ዐይን አለህን በሰማይ ፊት ምንም ደመና ሳይኖር ሀገሩም ብራ ሆኖ ሲታይ እንዴት ይዘንማል ትላለህ አሉት። እርሱም እኔ የማውቀውን እናንተ አታውቁትም ግን ወደ ቤታችሁ ግቡ አላቸው። እረኞችም ባልሰሙት ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ በጎቹን እያስሮጠ ወደ ቤቱ ገባ። ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ታላቅ ዝናም መጣ ነፋሳትም ነፍሱ መብረቆችም ተብለጨለጩ ነጎድጓድም ተሰማ ደመናትም ተነዋወጹ፤ ይህ ሁሉ በላያቸው ሲወርድ መሸሸያ አላገኙም።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ እረኞችም አብረውት ነበሩ። አንድ የበግ ጠባቂም መጥቶ የወጣት ሀብተ ማርያምን በትር ነጠቀውና ሔደ ብላቴና ሀብተ ማርያምም “በትሬን ለምን ትቀማኛለህ” አለው። እረኛውም በትዕቢት ቃል “በጉልበቴ ነጥቄሃለሁ” አለው። ብላቴና ሀብተ ማርያምም “እኔ ኃይል የለኝም ነገር ግን በጎቼን የምጠብቅበትን በትሬን እንዳትወስድብኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም አምልሃለሁ” አለው። ያም የበግ ጠባቂ “እምቢ አልኩህ” አለው። ብላቴናው ሀብተ ማርያምም “አንድ ጊዜ በፈጣሪዬ ስም አማልኩህ ከእንግዲህ ወዲያ ደግሜ አላምልህም በአንተ ላይ የሚደረገውን ራስህ ታውቀዋለህ” ይህንንም ተናገሮ ዝም አለ። በዚያንም ጊዜ ያ የበግ ጠባቂ በአየር ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ። “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሀብተ ማርያም ማረኝ” እያለ ይጮህ ጀምረ። የልዑል እግዚአብሔርን ስም አቃልሏልና ተሰቅሎ ዋለ። እረኞች ሁሉም አይተው አደነቁ ፈሩትም። “ይህን ሰነፍ ማርልን እግዚአብሔር ያደረገልህን ኃይል አይተናልና አሁንም ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ይቅር በለው” አሉት። ብላቴናው ሀብተ ማርያምም በውኑ እኔ የሰቀልኩት ነውን በእግዚአብሔር ስም አማልኩት እንጂ የኃይሉን ጽናት በላዩ ሊገልጥ እርሱ እግዚአብሔር ሰቀለው አሁን እርሱ ከፈቀደ ያውርደው እርሱ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና። ይህንንም በተናገረ ጊዜ ወርዶ በእግሩ ቆመ ወደርሱም መጥቶ ሰገደለት። ከረጂም ዘመናትም በኋላ ስሟ አለአድባር ወደምትባል ገዳም ሔዶ ከዚያም የምንኵስናን ሥርዓትና ሕግ በአበምኔቱ በተመረጠ አባ መልከጼዴቅ እጅ ተቀበለ። ከዚያም ቅዱሳን መነኮሳት ወደሚኖሩበት ሔዶ ታላቅ ታጋድሎ ጀመረ።

እርሱም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል፤ በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግምባሩ አሸዋ እስቲነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል፤ ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር። ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ። አርባ አርባ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ። በባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ።

ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም በአስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ ተገልጦ መጣ። ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያዉ ሁነው እያመሰገኑት ነበር። “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን” አለው። በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ፤ ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና “ጽና ኃይልህን ላድሳት ላጠፋህ አልመጣሁምና ተጋድሎህና ድካምህም ሁሉ በኢያሩሳሌም ሰማያዊት እንደ ተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ። እነሆ እኔ በጎ ዋጋህን በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ፤ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀመጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሔድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ” አለው።

ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው። ክብር ይግባዉና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ርሱ መጥቶ “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን። ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ እረፍት ልወስድህ ነው እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና አንዱ ስለ ድንግልናህ ሁለተኛም ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኵስናህ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ አምስተኛው ስለ አኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥክ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ስጠሁህ እሊህ ሰባቱ አክሊላትም ለየአንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው። መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማፀኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ አምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሃን ልብስን ሥውር የሆነ መና እሰጥሃለሁ” አለው። መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው “ወዳጃችን ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን” አሉት። አባታችን አባ ሀብተ ማርያምም “በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው” አለ።

ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና “የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ” አለው። “መታሰቢያህን የሚያደርገውን በስምህ ለቤተክርስቲያን መባ የሚሰጠውን ስምህንም የጠራውን ወደዚች አገር አገባዋለሁ አራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሽህ አደረግሁልህ ይኸውም ካንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆችህ መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቼሃለሁ”። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋዋ ተለየች ፤ ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት። በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ።

እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

Written By: admin
Date Posted: 12/7/2013
Number of Views: 12708

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement