View in English alphabet 
 | Tuesday, September 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

“የ፭ቱ ታቦታት የቀይ ምንጣፍ ጉዞ” በሲያትል ከተማ

                 “የ፭ቱ ታቦታት የቀይ ምንጣፍ ጉዞ” በሲያትል ከተማ

በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሲያትል ከተማ የሚገኙት አምስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የደብረ መድኃኒት ቅዱስ አማኑኤል ወአቡነ አረጋዊ ፤ የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ፤ የደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ወደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ፤ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል እና የደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ከሁለት ሺህ በላይ ምዕመናን በተገኙበት ጥር ፲  እና ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም (January 18/19 2014) በታላቅ ድምቀት አከበሩ::

በዋዜማው ቅዳሜ  ጥር ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው በታላቅ ዝማሬና እልልታ ከተነሱ በኋላ በደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ወደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ደብር ተገናኝተው የጥምቀተ በዓል ሥነሥርዓት ወደሚፈጸምበትና በታዋቂው ጥቁር አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ ወደተሰየመው አዳራሽ (KING HALL) ዑደት ተደርጓል::

በወቅቱም የሲያትል ከተማ ፖሊሶች በሞተር ሳይክል አጅበውና መንገድ እየመሩ : የትራፊክ መንገዱን ሥርዓት በማስያዝ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል::  ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ሕጻናትና አረጋውያን በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሆታ በእልልታና በመዝሙር ታቦታቱን እያጀበና እያከበረ የተጓዘ ሲሆን በከተማው የሚገኙት ወጣቶች ደግሞ ታቦታቱ የሚያልፉበትን መንገድ በማጽዳትና ለክብረ በዓሉ የገዙትን ትላልቅ ቀያይ ምንጣፎች እየተሽቀዳደሙ በማንጠፍ ይረባረቡ ነበር::  ይህም ሁኔታ የምዕመናኑና የወጣቶቹን የእምነት ጽናትና ፍቅር የሚገልጥ የተከታዩን ትውልድ የእምነት ተረካቢነት የሚያሳይ ታላቅ አጋጣሚ ነበር::ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ከደረሱ በኋላ ዋዜማ ተቁሞ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወረብና ያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ ያላቸው መዝሙሮች ቀርበዋል:: ቀጥሎም በዓሉን የተመለከተ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ ሰርኾተ ሕዝብ ተደርጓል:: ሌሊቱን በሀገራችን እንደሚደረገው ታቦታቱ ባደረቡት ሥፍራ አረጋዊያንና ወጣቶች የሌሊቱ ቁር ሳይበግራቸው ማደራቸው ሌላው የሃይማኖት ጽናት መግለጫ ነበር።

በማግስቱም እሑድ ጥር ፲፩  ቀን ፳፻፮ ከሌሊቱ 9 ሰዓት (3:00 AM ) ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት (6:00pm ) ማህሌት ተቁሞ ምስጋና ሲደርስ ያደረ ሲሆን  ከዚያም ጸሎተ ኪዳን ደርሶ ቅዳሴ ተገብቷል:: ከቅዳሴው በኋላ “ ... አንተ ሰበርከ ርእሰ ከይሲ በውስተ ማይ ወአንተ ቀጥቀጥከ አርእስቲሁ ለከይሲ : ወወሀብውኮሙ ሲሳዮሙ ለሕዝበ ኢትዮጵያ  “ አንተ በውሃ ውስጥ የእባብን/ሰይጣን/ ራስ ሰበርህ አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ : ለኢትዮጵያ ሕዝብም ምግባቸውን ሰጠኻቸው መዝ 73 (74)፥ 14  :: በሚል ምንባብ መነሻ ሰፋ ያለና በዓሉን የተመለከተ ቃለ ወንጌል ተሰጥቷል:: 
በመቀጠል በአበው ካህናት ማዩ ተባርኮ ምዕመናን ጸበል ተረጭተዋል:: በመጨረሻም የ፭ቱ አድባራት ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን “ ኅዲጎ ተስአ ወተሰአተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባሕር : ገብኣ ወወጽአ በሰላም” የሚለውን ወረብ እጅግ በአማረና በሠመረ ሁኔታ አቅርበው እንደፈጸሙ ታቦታቱ በታላቅ ዝማሬና እልልታ ወደየመንበረ ክብራቸው ተሸኝተዋል:: 
በዘንድሮው ዓመት በሲያትል ከተማ የሚገኙት አምስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የመስቀልንና የጥምቀት በዓልን በጋራ የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ በማዋቀር በታላቅ ቅንጅትና ትብብር ያከበሩበት ሁኔታ በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ምዕመናን እጅግ ያስደሰተ : የቅድስት ቤተክርስቲያንን አንድነትና ታላቅነት ያሳየ ነው:: ወደፊትም በከተማው ውስጥ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ለቅድስት ቤተክርስቲያን እድገትና መስፋፋት “እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ : እንደ አንድ ልብ መካሪ “ በመሆን በጋራ እንዲመክሩ : እንዲወያዩና እንዲሠሩ ትልቅ መሠረት የጣለ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች ቦታዎችም አርአያነት ያለው ነው::  በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባራት በበለጠ ቅንጅትና ዝግጅት ቢከናወኑ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አልፎ ለሌሎች ኢአማንያን ማዳረስ የሚቻልበትን ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዘገባ: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን
የሲያትል ንዑስ ማዕከል
ጥር 11 ቀን 2006 ዓ/ም (January 19 2014)


Written By: host
Date Posted: 1/20/2014
Number of Views: 5537

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement