View in English alphabet 
 | Friday, June 14, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ዜና ስብከተ ወንጌል

“ወንጌል ለእርስዎና ለብዙዎች” በሚል ርዕስ የማኅበሩ የሲያትል ንዑስ ማዕከል የካቲት 1 እና 2 ቀን 2006 ዓ/ም ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የስብከተ ወንጌል መርሐግብር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በስኬታማ ሁኔታ ተጠናቋል።

ትምህርተ ወንጌልን ለአካባቢው ምዕመናን ለማስተላለፍ እንደዚሁም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወንጌልን በተጠናከረ መልኩ በዓለም የሚሰማበትን እድል ለመመካከር ታስቦ በተዘጋጀው በዚህ መርሐግብር ላይ በሲያትልና አካባቢው የሚገኙ የአድባራት አስተዳዳሪዎች: ካህናትና ምዕመናን: የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና የተለያዩ  የኅብረተሰቡ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በሁለቱ ቀናት ጉባኤ ላይ
መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው ሰፋ ያሉ ትምህርቶች ተሰጥተዋል።

ክፍል 1 ትምህርት "እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ" (ማቴ.3÷8), 

ክፍል 2 ትምህርት ("ምን እናድርግ?")

በሊቀመዘምራን ይልማ ኃይሉ 
እና በሰንበት ት/ቤት መዘምራን የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች ቀርበዋልየዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር ለሚለው የጉባኤው አላማ፣ ”ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያናችን አገልግሎት ታላቅ ዕድል“ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን። ቤተ ክርስቲያን ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቷን ለማስፋፋት እያደረገች ያለችው ጥረት ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በንጽጽር ቀርቦ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ተብራርቷል።

ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነቱ በበኩሉ በዘርፉ እየሠራቸው ያሉት ሥራዎችም ተገልጸዋል። ከነዚህም መካከል በህትመት ውጤቶች ፥ በድረ ገጽ/ website/ ፥ በራዲዮና ቴሌቪዥን ፥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ደረጃ የጀመራቸው ሥራዎች ተጠቅሰዋል : በተለይም ካለፈው 2004 ዓ/ም ጀምሮ ማኅበሩ በየሳምንቱ ዓርብ  በራድዮ እና በየሳምንቱ እሑድ በቴሌቭዥን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ስርጭት: ዝግጅቱ ከተላለፈም በኋላ (http://EOTC.TV/ ) በሚለው ድረ ገጽ ለህዝብ የሚተላለፈው መርሐግብር ከሚሊዮን በላይ ምእመናንን እያገለገለ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አገልግሎቱን በቀጣይም የበለጠ ለማጠናከር በማኅበረ ቅዱሳን በዋናው ማዕከል እየተሠሩ እና የታቀዱ ሥራዎች በቪዲዮ ቀርቧል።

በማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ ማዕከልም በተለይ በውጪ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ትኩረት ባደረገ መልኩ ሚዲያውን ለማጠናከር እንደታሰበ እና በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሳምንት አንድ ሰዓት የሚቆይ የኢንተርኔት ቴሌቪዥን ለመጀመር እንደታሰበ ተገልጧል።

በዚሁ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ ማዕከል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ያዘጋጀው “ተዋሕዶ” የተሰኘው የስልክ መጠቀሚያ ፕሮግራም/አፕሊኬሽን/  ተመርቆ ለምዕመናን አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓል።

በመርሐግብሩ ላይ ከተደረገው ገለጻ መረዳት እንደሚቻለው ”ተዋሕዶ“ በሚል ሥያሜ የተለቀቀው የስልክ መጠቀሚያ ፕሮግራም/APPLICATION/ በአምስት ዋና ዋና ዘርፎች የሚከተሉትን ጥቅሞች ለምዕመናን እንደሚሰጥ ተገልጿል።
1.    ቴሌቪዥን እና ራዲዮ:- የተላለፉ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ መርሐ ግብር በቀላሉ ከስልክ ላይ መከታተል ያስችላል
2.    ግጻዌ - በቀላሉ የቤተ ክርስቲያንን አጽዋማት፣ በዓላት እና የቅዳሴ ምንባቦችን ለማውጣት ያስችላል
3.    የአብያተ ክርስቲያናት መፈለጊያ - ከስልክዎ ላይ በቀላሉ በአቅራቢያዎ ያለውን ቤተክርስቲያን አድራሻ የሚጠቁም እና የመንጃ አቅጣጫውን የሚያሳይ። ለጊዜው የአሜሪካን አብያተ ክርስቲያናት መረጃ እንደያዘ በቀጣይ ግን በሌሎች ክፍለ ዓለማት ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን የማስገባት ዕቅድ እንዳለ ተገልጿል።
4.    የጸሎት መጻህፍት - ለጊዜው ውዳሴ ማርያም እና ውዳሴ አምላክ፣ በቀጣይ ሌሎች መጻህፍትን ለማስገባት እንደታሰበ ተገልጿል።
5.    መዝሙራት፣ ስብከቶች ለማዳመጥ በሚመች መልኩ ተቀናጅተው ከተዋሕዶ አፕ ላይ ማግኘትም እንደሚቻል ተገልጿል።

Android እና የ iPhone አፖቹ ለመጠቀም ዝግጁ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን። በ iPhone አፑ  ላይ የቴሌቪዝን እና የራዲዮ እንዲሁም የጸሎት መጻህፍቱ ሥራ እንዳልተጠናቀቁ ነገር ግን በዚህ ወር መጨረሻ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑ ተገልጿል። የተሠሩ የስልክ ፕሮግራሞች እንዴት እንደሚጠቀሙ ከዚህ ቪዲዮ ላይ ማግኘት ይችላሉ።

በዚሁ ጉባኤ ላይ ሚዲያውን እና ቴክኖሎጂ ነክ ሥራዎችን ለማጠናር የተጀመረው ተግባር ተበራቶ እንዲቀጥል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በቀሲስ ግርማ አስተባባሪነት ተደርጎ ምዕመናን ለአገልግሎቱ $33,000.00 እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል።

ከሚከተለው የቢዝነስ ካርድ ላይ ለታዳሚ ምእመናን የተበተነ ሲሆን፣ ከካርዱ ላይ ያለውን QR CODE ከስማርት ስልክ ላይ (Android QR Reader, iPhone QR reader and Windows QR reader) ስካን በማድረግ በቀላሉ የማኅበሩን የፌስ ቡክ ገጽ በመከተል የሚተላለፉ መልዕክቶችን መከታተል እንደሚችሉ ተገልጿል።


 
በአጠቃላይ ጉባኤው የእግዚአብሔር ቸርነት የታየበት፣ የምእመናን ሕይወት በንስሐ ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠበት፣ ምእመናን እግዚአብሔርን በዝማሬ  ያመሰገኑበት፣ ምእመናን ለአገልግሎቱ የበለጠ የተነቃቁበት፣ ቤተ ክርስቲያን በሚዲያው እና  በቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ምዕመናን የታዩበት ነው።
በጉባኤው ፍጻሜ ላይ የሲያትል ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክን አስተዳዳሪና የካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ መልአከ አርያም ቀሲስ አወቀ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የማኅበረ ቅዱሳን ሲያትል ንዑስ ማዕከል


Written By: host
Date Posted: 2/15/2014
Number of Views: 7210

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement