View in English alphabet 
 | Friday, June 14, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ትንሣኤ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ትንሣኤ

በመልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገ/መድህን

በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረው አዳም
አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ፍጥረታትን ለተከታታይ አምስት ቀናት ከፈጠሩ በኋላ በስድስተኛው ቀን /ዐርብ/ በነግህ እንዲህ አሉ።  ‹‹ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር›› /ዘፍ ፪-፲፰/።  ሥላሴ በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ማለታቸው እንዴት ነው ቢሉ።  ሥላሴ ለባውያን፣  ነባብያን፣  ሕያዋን ናቸው።  አዳምም ለባዊ፣  ነባቢ፣  ሕያው ነው።  ሥላሴ ፍጹም መልክእ እንዳላቸው አዳምም ፍጹም መልክእ  አለው።  ሥላሴ በልብ በቃል፣  በእስትንፋስ ይመሰላሉ ለሰውም ልብ፣  ቃል፣  እስትንፋስ አለው። ሥላሴ በባሕሪያቸው የሚገዙትን አዳም በጸጋ እንዲገዛ ሥልጣን ሰጥተውታል። 

ይህን ታላቅ ጸጋ ፈጣሪው አድሎት በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረው አዳም አስቀድሞ በትዕቢቱ ከክብሩ ለተዋረደው ለሳጥናኤል ማሳፈሪያ የእግዚአብሔር ፍጹም መለኮታዊ ጥበብ መገለጫ ሆኗል።  እንደ ብርጭቆ የሚያንጸባርቅ እንደ ጽጌያት /አበቦች/ የሚያሸበርቅ አድርጎ በመፍጠሩ።  ይልቁንም አዳምን ዐዋቂ አድርጎ በመፍጠሩ የእግዚአብሔር የማይመረመር ጥበብ ተገልጦበታል።  እግዚአብሔር አዳምን በአራቱም ማዕዘን ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ላይ አሠለጠነው።  ‹‹ወፈጠረ ሎቱ እም ሥጋሁ ረድኤተ፤ ከአካሉም ልትረዳው ሔዋንን ፈጠረለት››።  መወደድ ባለው በምሥራቅ በኩል በገነትም አኖራቸው።  /ገነት አራት ማዕዘን አለውና በምሥራቅ በኩል ይላል/።  ‹‹ወወሀቦሙ ይትፌሥሑ በኩሉ ሠናያት አምላካውያት ዘእንበለ ክልዓት፤ ከአምላክ በሚገኘው ነገር ሁሉ ደስ ይላቸው ዘንድ ያለ መከልከል ሰጣቸው››።  ከዚህ ሁሉ በኋላ ስለ አንዲት ዕፅ ብቻ ትዕዛዝ ወሰነባቸው።  ያችም ዕፅ ዕፀ በለስ ትባላለች።  ባይበሏት በጎ ቢበሏት ክፉ የምታሳውቅ ናት።  የገዥና የተገዥ ምልክት ሆና የተሰጠች ናት።  ከእርሷ የበሉ እንደሁ የሞት ሞትን ይሞታሉና እንዳይበሏት ታዘዙ። 

ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፍ
ከሰባት ዓመት ከገነት ቆይታ በኋላ ግን አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን ትዕዛዝ አፈረሱ አትብሉ ከተባሉት ዕፅ በልተው በራሳቸው ሞትን አመጡ።  አባታችን አዳም ሕግ በመጣሱ ሞት ተፈረደበት።  የሰይጣንን ሞክር ሰምቶ ከፈጣሪው በመለየቱ የሰይጣን ተገዥ ሆነ።  በዚህ ዓለም ያዘነ የተከዘ ሆኖ ኖረ። ካገኘውም ፀዋትወ መከራ የተነሣ ቁጡ ዕንባን አፈሰሰ፡ በገነት ከነበረው ክብር ተድላ ደስታ በመለየቱ ሳይሆን የማይገባ ሥራ ሠርቼ ፈጣሪዬን  አሳዘንሁት ብሎ አዘነ። አለቀሰ። አዳም በኃጢአቱ ከማልቀስ በቀር ሌላ ምክንያት አልነበረውም የሚለንም ለዚህ ነው። 

የሞት ሞት ስለተፈረደበት ከምድር አፈር የተፈጠረው፣  እስትንፋስ እግዚአብሔር የተዋሐደው አዳም ሥጋው ወደ መቃብር እንዲወርድ ሆነ።  ነፍሱንም የሲኦል ሕማም አገኛት።  በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም አግኝቶት ለሞት ተሰጠ።  እንስሳት አራዊት አጎንብሰው እንደሔዱ አዳም ግን ቀና ብሎ የተፈጠረበት /ወደ ሰማይ እንዲመለከት የሆነበት/ ምክንያት ነበረው።  እነርሱ ቀድሞም በደመ ነፍስ የሚጓዙ ኋላም ፈርሰው በስብሰው የሚቀሩ መሆናቸውን እርሱ ግን ሕያዊት፣ ዘላለማዊት ነፍስ ያለችው ኋላም እግዚአብሔር ባዘጋጀለት በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር መሆኑን ለመግለጥ ነው።  ነገር ግን በስሕተት ምክንያት ቀንቶ የተፈጠረውና የከበረው ሰው በመቃብር ተረታ።  በሞት ተሸነፈ። ሞት የአዳምን ሥጋ በመቃብር እያፈረሰ እያበሰበሰ ነፍሱን በሲኦል ለስቃይ እያደረገ ለዘመናት ኖረ። 

ውሉደ አዳም ደቂቀ አዳምም በዚህ የሞት ወጥመድ ተያዙ። ነፍሳቸውን ነጥቆ በሲኦል ሥጋቸውን በመቃብር እያኖረ ሞት ተስፋ በሌለው ድቅድቅ ጨለማ ጣላቸው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በዕፀ በለስ ምክንያት ስለመጣብን ሞት አንሥቶ በመንፈስ ቅዱስ አቀራራቢነት አዳም አባቱን እንዲህ እያለ ይጠይቃል።  ‹‹አዳም ሆይ የሞት ፍርድን ያመጣህብን ምን አደረግንህ? አዳም ሆይ ደስታ ባለበት በገነት በጌታ ማደራያ ደስ ይለን ዘንድ ያልተውኸን ሞን አደረግንህ? ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ? እነሆ በኃጢአት ብዛት ሥጋችን ጠቆረ በሰማያውያን አምሳል በኖርነ ነበር›› /ቅዳሴ አትናቴዎስ  ቁ ፳፰ - ፳፱/።  ሊቁ እንዳለው በአንዱ አዳም ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ በልጆቹ ሁሉ ላይ የሞት ፍርድ ወደቀብን። 

የዓለም ቤዛ
ይህንን የሞት ሥልጣን ለመሻር ከፍጥረታት ወገን ሥልጣን ያለው አልተገኘም። ሁሉ በእዳ ተይዞ ስለነበር የድኅንነታችን ምክንያት ከሆነችው ከቤዛዊት ዓለም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በቀር የአዳም ዕዳ በደል ያልወረደበት ስላልተገኘ የሰው ልጆች ካሣ መክፈል አልቻሉም። እንስሳትና መላእክትም ቢሆኑ በሥጋና በነፍስ ለበደለው ለአዳም ካሣ ለመክፈል አቅሙ አልነበራቸውም። በዚህ ምክንያት ነው እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ሊልክ የፈቀደው። በቀዳማዊ አዳም ወደ ዓለም የገባ ሞት በዳግማዊው አዳም በክርስቶስ እንዲሻር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ሆነ። ስለዚህም የሚወደውን አንድያ ልጁን በእንተ ፍቅረ ሰብእ ወደ ዓለም ሰደደ።  ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ ነው ሲጽፍ እንዲህ ብሎናል። ‹‹እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም እስመ ወለዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ ኵሉ። »አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስከመስጠት ደርሶ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና። በእርሱ ያመኑ ሁሉ እንዳይጎዱ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኙ ዘንድ ልጁን ልኮታል። እስመ ኢፈነወ እግዚአብሔር ለወልዱ ውስተ ዓለም ከመ ይኮንኖ ለዓለም። እግዚአብሔር በዓለሙ ሊፈርድበት ልጁን ወደዚህ ዓለም አልሰደደውም።  አንድም አስቀድሞ ያልተፈረደበት ሆኖ ሊፈርድበት አልሰደደውም።  ተፈርዶበታልና ከተፈረደበት ፍርድ ሊያድነው ነው እንጂ ይለናል /የሐዋ ፫- ፲፮/።

የሰውን ልጅ ለመቤዠት ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ወደ ምድር ወረደ፡ ሥጋን ተዋሐደ።  ሰው ሆነ። የቀደመ አዳምን በደል ስሕተት ለመፋቅ እርሱ ዳግመኛ አዳም ሆኖ ተገለጠ። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር እንደ ሰው ሁሉ ሆነ። ከፅንስ በኋላ ከልደት በፊት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀን ሳለ ከመንበሩ ሳይለይ ከልደቱም በኋላ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከመንበሩ ሳይለይ ሰው ሆነ። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰት እንዲህ ይላል። «ፍጥረትን ሁሉ ስብሰቦ የያዘን ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ሕፃን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርዓያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት›› /አንቀጸ ብርሃን ዘኮንኪ/።  በሰማይ በመላእክት እየተመሰገነ በረቀቀ ጥበቡ ሥጋችንን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆነ። ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደ አብ ወልደ ማርያምን በመካከላችን አገኘነው። ሥጋችንን ተዋሕዶ ከተገለጠ በኋላም በቃሉ ትምህርት በእጁ ተአምራት የሰውን ልጅ ወደ እርሱ አቀረበ።

ከቀራንዮ እስከ ጎልጎታ
በመጨረሻም በቀራንዮ ኮረብታ በመልእልተ መስቀል ተሰቅሎ ስለአዳም መተላለፍ እርሱ በተዋሐደው ሥጋ በፈቃዱ ሞተ። እንበለ ሕማም እንበለ ኃጢአት ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም የነሳው ቅዱስ ሥጋ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዋለ። ዮሴፍና ኒቆዲሞስም ሥጋውን ገንዘው በሐዲስ መቃብር አኖሩት። አይሁድ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት እውን እንዳይሆን በመፍራት መቃብሩን በሮማ ወታደሮች አስጠበቁ። በሦስተኛው ዕለት ተነሣ የሚለውን ድምፅ ላለመስማት ሦስቱን ዕለታት በትጋት ጠበቁ። ነገር ግን እነርሱ የሞትን ሥልጣን ተንሰራፍቶ እንዲኖር ከዲያብሎስ ጋር ቢተባበሩም በፈጣሪ የማይቸነፍ በአምላካዊ ሥልጣን የማይረታ የለምና ሥግው ቃል ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ሥጋ የተፈጠረበት ተስፋ ትንሣኤ እንዳለው ዘለዓለማዊ እንደሆነ የተገለጠበት ምስጢር በክርስቶስ ትንሣኤ እውን ሆነ። እርሱ የትንሣኤ በኩር ሆኖ ሁላችን ትንሣኤን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠን / ፩ቆሮ ፲፭-፳/። በእሩቅ ብእሲ ሥልጣን ሊከወን የማይችለው ሥጋን ተዋሕዶ በተገለጠው በእርሱ ተከወነ። የሞት ሥልጣን በአምላካዊ ኃይሉ ለዘለዓለም ተሻረ። ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው እንዲህ ይላል። ‹‹የሞትን ድል መንሣቱን አጠፋ ሕይወት ነውና ፈጣሪም ነውና ሥጋ ገንዘቡ እንደሆነ በሥጋም እንደሞተ፣  ሞቶም እንደ ተነሣ ሞትንም እንዳጠፋ፣ ለእኛም ባህሪይም የባህሪይ ሕይወቱን ሁሉ እንደሰጠ እናውቅ ዘንድ ይገባል። ይህ ሥራም /ማለት/ ሞትን ድል መንሣት፣ ሥልጣኑንም ማጥፋት እንደ እኛ ያለ የደካማ ሰው ሥራ አይደለም። ከሰው ዐቅም ፈጽሞ የራቀ ነው እንጂ›› /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ም ፸፱-ቁ ፲፫/። 

ትንሣኤ ዘክርስቶስ
የአዳም ሥጋ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ ከመቅረት በቀር ኃይል ተነሥቶት ቢቆይም ኋላ ግን ከመለኮታዊ ባህሪይ ጋር በመዋሐዱ ኃይል አግኝቶ ሞትን ድል ነሣ። መለኮት በሥጋ ታሞ ተንገላቶ ወደ መቃብር ከወረደ በኋላ በሥልጣኑ ሞትን ድል ነስቶ የተዋሐደውን ደካማ ሥጋ አቸናፊ አድርጎታል። የተዋሐደውን፣ የተናቀውን፣  የተረገጠውን የሰው ልጆች ሥጋ በተዋሕዶ አክብሮ ወደ ቀደመ የክብር ቦታው መልሶታል። 

አንግዲህ ትንሣኤ የሞት ሥልጣን መኖሩን ያስታውሰናል። ትንሣኤ የፈጣሪን ታላቅ ቸርነት ያስታውሰናል። ትንሣኤ ፈርሰን በስብሰን በመቅረት ፈንታ ክርስቶስን አብነት አድርገን በኋለኛው ዘመን እንደምንነሣ ያስታውሰናል።  ስለዚህ ነው ከዓበይት በዓላት አንዱ አድርገን በዓለ ትንሣኤውን የምናከብረው። በብሉይ ኪዳን ከሞት የተነሡ ብዙዎችን ታሪክ አንብበናል /፪ነገ ፲፫-፳/። እነዚህ ሁሉ ግን ሞታችንን አልሻሩም የሞትን ዘለዓለማዊ ሥልጣን አላስወገዱም። ከሞት ሲነሡም በነቢያት በሐዋርያት ጸሎት በፈጣሪ ቸርነት ለራሳቸው ሊኖሩ ተነሥተዋል።  መልሰውም ካመለጡት ከሞት ጉያ ገብተዋል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በባህሪይ ሥልጣኑ ሞትን ለዘለዓለም ድል አድርጎ ተነሣ። የሰው ልጆችንም ከሞት ወደ ሕይወት አሸጋገረን። 

ፋሲካችን ክርስቶስ
እስራኤል ዘሥጋ ከግብፅ ባርነት ከወጡ ዘመን ጀምሮ ባርነታቸው መራራ እንደነበር ለማስታወስ በየዓመቱ የፋሲካን በዓል ያከብሩ ነበር። በዚህ በዓላቸው መራራውን የግብፅ ሕይወት የአባቶቻቸውን ሥቃይ መከራ ያስታውሱ ነበር። እግዚአብሔርም በተለያዩ ዘመን በነቢያቱ በኩል ሲያነጋግራቸው ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ ይላቸው ነበር /ዘፀ ፳-፩/።  እርሱ እንዴት ነጻ እንዳወጣቸው ያስታውሳቸዋል። ከዚህ ጋር በማያያዝ በሐዲስ ኪዳን ፋሲካን የምናከብረው ዋናውን የነፍስ ነጻነት ያገኘንበት ስለሆነ ነው። ከግብፅ ምሳሌ ሆኖ ከቀረበበት ከሲኦል ባርነት ነጻ ስለወጣን እስራኤል ዘነፍስ ክርስቲያኖች በዓሉን በመንፈሳዊ ሐሴት እናከብራለን።  የአዳምና የልጆቹን የሥቃይ የመከራ ሕይወት በሰሙነ ሕማማት ስናስታውስ ከርመን በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ ፋሲካችንን እናከብራለን። ፋሲካችን ክርስቶስ ነው  /፩ቆሮ ፭-፯/ በሥግው ቃል በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ሕማማት ነጻ መውጣታችንን እናስባለን። 

መልካም ትንሣኤ


አዘጋጅ፡-
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል


Written By: host
Date Posted: 4/18/2014
Number of Views: 8359

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement