View in English alphabet 
 | Tuesday, September 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በ/ኢ/ኦ/ተ/ቤክ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርታዥ

በየዓመቱ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚካሄደው በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል ጠቅላላ ጉባኤ በዘንድሮው ዓመትም ለአሥራ ስድስተኛ ጊዜ “አገልግሎትህን ፈጽም” በሚል መሪ ቃል በቺካጎ ኤሊኖይ ተካሄዷል ::
ከግንቦት ፳፬ - ፳፮ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ለሦስት ቀናት የቆየው ይህ ጉባኤ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 5:00pm በቺካጎ ደብረ ኤዶም ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ካቴድራል በኒውዮርክና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ እና በካህናት አባቶች ጸሎተ ኪዳን በማድረስ የመክፈቻ መርሐግብሩ ተከናውኗል:: በማስከተልም ብፁዕነታቸው ቃለምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል:: በመቀጠልም ሕጽበተ እግር እና የእራት መስተንግዶ ከተከናወነ በኋላ  እንግዶች ወደየተዘጋጀላቸው ማረፊያ ተጉዘዋል።

በማግስቱም ቅዳሜ ጠዋት መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ በብፁዕ አቡነ ዛካርያስ “አገልግሎትህን ፈጽም” (፪ ጢሞ ፬፥፮) በሚለው ኃይለ ቃል መነሻነት ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል:: በዚሁም ትምህርታቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ታይታ፣ ማስመሰል የሌለበትና እውነተኛ መሆን እንዳለበት ይልቁንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዳስተማረው በቃልም በኑሮም በትምህርትም ምሳሌ ሊሆን እንደሚገባው ገልጠዋል:: የማኅበሩ አባላት የጀመሩትን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በትዕግስትና በጽናት፤ ከአባቶች ጋር በመመካከር፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት በሚያጠናክር መንገድ መቀጠል እንዳለባቸው መመሪያ ሰጥተዋል:: 

ጉባኤው በተያዘለት መርሐግብር መሠረት በበጀት ዓመቱ ውስጥ የአሜሪካ ማዕከል እና በሥሩ የሚገኙት ንዑስ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች የእቅድና የአገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል::በቀረበውም ሪፖርት በ፳፻፮ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመን በአሜሪካ ማዕከል ከተከናወኑት ተግባራት መካከል በአቡነ ጎርጎርዮስ ማዕከል ማስተባበሪያ ሥር የተዋቀረው የምክር አገልግሎት በዚህ ዓመት በማዕከሉ ጽ/ቤት በቋሚነት በሳምንት ፪  ቀናት በካህናት አባቶች የምክር አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ፣ የማዕከሉን ጽሕፈት ቤት /ቤተ ማኅበረ ቅዱሳን ዘአሜሪካን/  ለመገንባት/ለመግዛት እንዲቻል የጥናት ኮሚቴ በጽ/ቤቱ ሥር ተዋቅሮ አስፈላጊውን ጥናት ተጠናቆ ዝርዝር የአፈጻጸም ምክረ ሃሳብ ተዘጋጅቶ ለጠቅላላ ጉባኤው መቅረቡ፣  በዲሲና በሲያትል ከተሞች መለስተኛ ስቱድዮ በማቋቋም የሚዲያውን አገልግሎት ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑ፣ ከ፴በላይ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል የተሳተፉበት የመምህራን  የምክክር ጉባኤ ተካሂዶ ፲፫ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በመምህራኑ ጥልቅ ውይይት እንደተደረገባቸው፣በማዕከሉ ሥር በተዋቀሩት ፲፪ ንዑስ ማዕከላትና ፬ ግንኙነት ጣቢያዎች  በአገልግሎት  የሚሳተፉት አባላት በየአጥቢያቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በማዕከሉና በየማዕከላቸው የተለያዩ የአገልግሎት መስኮች የሚቻላቸውን ሁሉ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸው፣ በማኅበሩ የመረጃ ቴክኖሎጂ ክፍልም የቤተክርስቲያንን ሀብቶች በተለያየ መልክ በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች (በስልክ፣ በአይፖድ፣ ...) አዘጋጅቶ ለማሠራጨት እንዲሁም የማዕከሉን አገልግሎት ሊያፋጥኑ የሚችሉ የተለያዩ የአገልግሎት መርጃዎችን እንዲሁም የአኅጉረ ስብከት ድረ ገጽ ለማዘጋጀትና ለማስተካከል ጥረት መደረጉን፣ በሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ክፍልም ለቤተክርስቲያን የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል አባላትን በተለያዩ የሙያ ቡድኖች ማዋቀር መጀመሩን እንዲሁም የማኅበሩን የመጻጻፍና የመረጃ ልውውጥ ለማሳለጥ የሚረዳ አሠራር መዘርጋቱ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለሚደረገው የስብከተ ወንጌል አገልገሎት ማስፋፊያ፣ ለቅዱሳት መካናት እና አብነት ት/ቤቶች ድጋፍ፣ ለሚዲያ አገልግሎት ከአባላትና ከምእመናን የተገኘው እርዳታን ጨምሮ የማዕከሉ አጠቃላይ የገቢና ወጪ ዝርዝር በዘመናዊ የሂሳብ አሠራር ሥርዓት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ጸድቋል።

በማስከተልም የዋናው ማእከል መልዕክትና ሪፖርት የማኅበሩን ዋና ማዕከል (Head office) ወክለው በተገኙት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ቀርቧል::በዚሁ ሪፖርታቸው ውስጥ ማኅበሩ በዘንድሮው ዓመት አሥር ወር ውስጥ በሦስት መቶ አርባ ሦስት (፫፻፵፫ ) ግቢ ጉባኤያት ውስጥ እያስተማራቸው ስላሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች፤ ለእነሱም ስለተዘጋጀው  “ጉባኤ ቃና” መጽሔት፤  እንደዚሁም “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” በሚል  መሪ ቃል ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ስለተካሄደው ሐዋርያዊ ጉዞ እና ሌሎች ከመቶ ሠላሳ ሰባት ( ፻፴፯ ) በላይ የሕዝብ ጉባኤያት መደረጋቸውን  ጠቅሰዋል:: በተጨማሪም ሃያ ሁለት (፳፪ ) የትምህርትና የስብከት ካሴቶች፣ ሰባት መቶ ሰማንያ (፯፻፹) ሺህ ሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣዎች ታትመው መሰራጨታቸውን ገልጸዋል::  እንደዚሁም በ፲ ዓመቱ  የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር አስተባባሪነት ከአኅጉረ ስብከት ጋር በቅንጅት ከተከናወኑት ተግባራት መካካል በገጠርና ጠረፋማ አካባቢዎች አራት ሺህ አምስት መቶ (፵፭፻) ኢአማንያን  መጠመቃቸውንና አብያተ ክርስቲያናት ለሌላቸው ለእነዚሁ ምእመናን አብያተ ክርስቲያናት ለማነጽ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ፤ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐግብሩ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው አኅጉረ ስብከት ለተወጣጡ ለሁለት መቶ አስር ወጣቶች የተተኪ መምህራን ሥልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል::  ማኅበሩ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን የአገልጋዮች እጥረት ለመቅረፍና ተተኪ አገልጋዮችን ለማፍራት በዘረጋው ትልም መሠረትም ማኅበሩ ከበጎ አድራጊ ምዕመናን ጋር በመሆን በመቶ ሃምሳ የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ እያደረገ ያለውም ድጋፍ ተገልጧል:: እንደዚሁም የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር በተጓዳኝ እንዲማሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት አምስት መቶ (፭፻) ተማሪዎች በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስም በተመሠረተው የነጻ ትምህርት ዕድል (Scholarship) ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል::

ከሪፖርቱ በኋላ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት እና የማኅበሩ የሥራ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ተክለ ማርያም ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል::

ጉባኤው በዚሁ ቀጥሎ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተሳታፊዎችን ግንዛቤ የሚያሳድጉና ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገባቸው አራት ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል:: ከጥናታዊ ጽሑፎቹ መካከል “በአሜሪካ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕድሎች እና ተግዳሮቶች” በሚል የቀረበው ዝግጅት የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊ አገልግሎት ግብ ምን መሆን እንዳለበት ያመላከተ፣  ምዕመናንም ሆኑ የማኅበሩ አባላት ለሀገርም ሆነ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ የሚያሳይ ዓይን ገላጭ ዝግጅት ይገኝበታል::  ከዚሁ ዝግጅት ጋር ተያይዞ  በቀረቡ ሁለት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የጉባኤው ተሳታፊዎች በተለያዩ  ምድቦች ተከፍለው የቡድን ውይይት አድርገዋል:: ተተኪዎችን ከማፍራት አንጻር ማእከሉ በሕጻናትና ወጣቶች ማስተማርያ ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ዘርፍ  በስድስት ደረጃ እየሠራቸው ያሉት ሥራዎች የተገለጹ ሲሆን ለዚሁ ተግባር ከተዘጋጁት መጻሕፍት መካከል የደረጃ ሁለት የመምህሩ ማስተማሪያ መጽሐፍ (Teachers guide) በዕለቱ ተዋውቆ ለአገልግሎት ተሰራጭቷል:: አባላት ማኅበሩ እያዘጋጀ ያለውን ሥርዓተ ትምህርት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ በማድረጉ ሥራ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑና ግብረ መልስ (Feedback) በማሰባሰብም የትምህርትና ሐዋርያ አገልግሎት ክፍሉን እንዲያግዙ ጥሪም ቀርቧል::

ቅዳሜ ማታ ከቀረቡት ዝግጅቶች መካከል “አብረን እንሥራ ለውጥም እናመጣለን” በሚል ስለገዳማትና ቅዱሳት መካናት ድጋፍ የተደረገው የልምድ ልውውጥ ይገኝበታል:: በወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት የቀረበው ይህ የልምምድ ልውውጥ እጅግ ልብ የሚነካና “ሀገር ቤት የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን መደገፍ ለምን ያስፈልጋል?” ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ የሰጠ፤ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉት ገዳማትና አድባራት ያለባቸውን ችግር፣ የተደቀነባቸውንም አደጋ በጉልህ ያመላከተ፤ ለበለጠ ሥራ በቁጭትና በመንፈሳዊ ቅናት የሚያነሳሳ ነበር::

ጉባኤው ከቅዳሴ በኋላ በተደረገው በእሑድ ዕለት ውሎው የማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል ጽ/ቤት (የቤተ ማኅበረ ቅዱሳን ዘአሜሪካ) ግንባታን በተመለከተ በማዕከሉ የሕንጻ ግዥ ኮሚቴ በቀረበው ጥናትና ምክረ ሐሳብ ላይ ተወያይቷል::

በውይይቱም ወቅት የማኅበሩን  የማስፈጸም አቅም ከማሳደግ በተጨማሪ : በማዕከሉ በኪራይ ቤት የተጀመሩትን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ አገልግሎቶች፣ የሚዲያ ዝግጅትና ቀረጻ ሥራዎች፣ የሕጻናትና ወጣቶች ትምህርት ዝግጅት፣ የምክር አገልግሎት እና ሌሎችም ተግባራት በስፋት ለመቀጠልና ለማጠናከር የቤተ ማኅበረ ቅዱሳን ዘአሜሪካ አስፈላጊና ተገቢ መሆኑ በጉባኤው ተሳታፊዎች ታምኖበታል:: ይልቁንም የቀረበው ምክረ ሃሳብ የበለጠ ዳብሮና የማኅበሩን የወደፊት እድገት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ሃሳብ የተሰጠ ሲሆን በጉባኤው ላይ የተገኙ አባላትና ተጋባዥ ምዕመናን ለቤተ ማኅበረ ቅዱሳን ግንባታ የሚችሉትን ለማዋጣት ቃል ገብተዋል:: ንዑሳን ማዕከላትና ግንኙነት ጣቢያዎችም በዕለቱ ጉባኤ ላይ ያልተገኙ አባላት እንዲሁም በጎ አድራጊዎችና ተባባሪዎች በሥራው ላይ የሚሳተፉበትን መድረክ እንዲያመቻቹና ለሥራው ከፍተኛ አጽንኦት እንዲሰጠው ጉባኤው ወስኗል::

በመቀጠል ጉባኤው በመርሐግብሩ መሠረት የአሜሪካ ማዕከልን ለቀጣይ ሁለት ዓመት በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ አባላትን ወደመምረጥ ገብቷል:: ቅዳሜ እለት ከጉባኤው የተመረጡት አስመራጮች የማኅበሩን የምርጫ  ደንብ ተከትለው ያመጡትን አሥራ ሰባት እጩዎች ዝርዝር ለጉባኤው አቅርበው አስተያየት ከተሰጠ በኋላ በካህናት አባቶች ውዳሴ ማርያም ተደግሞ እና ጸሎት ደርሶ የዕጣ ማውጣት ሥርዓት በማከናወን አሥራ አንዱ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ተለይተዋል::
የምርጫው ሥነ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ የማዕከሉና በሥሩ ያሉት አገልግሎት ክፍሎች  ቀጣይ  በጀት ዓመት (ከግንቦት ፳፻፮ - ሚያዚያ ፳፻፯ ዓ/ም) የሥራ ዕቅድ ቀርቦ ውይይትና ማዳበሪያ አስተያየት ተሰጥቶበት ጸድቋል::

በመጨረሻም የአሥራ ስድስተኛው ጉባኤ አዘጋጅ የሆነው የቺካጎ ንዑስ ማዕከል በጉባኤ ዝግጅቱ ያጋጠሙ ሂደቶችንና ክስተቶችን በሚያዝናና ትምህርታዊ በሆነ መልኩ በግጥም ሪፖርት አቅርቧል:: በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ : አሥራ ሁለት (፲፪) አበው ቆሞሳትና ካህናት፣ የጉባኤው አዘጋጅ የሆኑ የቺካጎ ማዕከል አባላትን ጨምሮ ሁለት መቶ ሃያ  (፪፻፳ ) አባላት እንዲሁም ስልሳ (፷) ሕጻናትና ታዳጊዎች ተገኝተዋል::  በዚሁም ወቅት ብዙ አባላትን ቀስቅሰው በመምጣትና ወቅታዊ መረጃ በመሥጠት አርአያ ለሆነው ንዑስ ማዕከል፤ ለጠቅላላው ጉባኤ ዝግጅት እንዲረዳ በንዑስ ማዕከሉ በተዘጋጀው ድረ ገጽ መረጃውን ከሁሉ አስቀድሞ ላስገባው አባል፤ እንዲሁም በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተሳተፉትን ሕጻናትና አዳጊ ወጣቶች በትጋትና በአርአያነት ስታስተምር ለነበረችው እህት ያዘጋጁትን ሥጦታ አበርክተዋል:: ከዚያም በጸሎትና በዝማሬ እግዚአብሔር በሚቀጠለው ዓመት የማዕከሉ አሥራ ሰባተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድበት በቴኔሲ ያገናኘን በማለት ተመራርቆ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: host
Date Posted: 6/3/2014
Number of Views: 8044

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement