View in English alphabet 
 | Thursday, March 28, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የደመራ በዓል - በዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና በዋሺንግተን ግዛቶች በድምቀት ተከበረ

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ 13 አብያተ ክርስቲያናት አንድ ላይ በመሆን የመስቀል ደመራ በዓልን ዓርብ መስከረም 16 ቀን 2007 ቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንደርያ ከተማ በሚገኘው በቤን ብረንማን ፓርክ ከቀኑ 4 ጀምሮ የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል።

በዋሽንግተን ግዛት፣ በሲያትልና አካባቢ የሚገኙ አምስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመተባበር ከየአጥቢያው በመጡ አበው ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት እንዲሁም ምእመናንና ምእመናት በተገኑበት መስከረም 18 በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

 

የሲያትሉን በዓል ያስተባበሩት በካሊፎርኒያ ሀ/ስብከት የዋሺንግተን ግዛት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙት የደ/መድኃኒት ቅ/አማኑኤል ወ አቡነ አረጋዊ፤ የደ/ሰላም ቅ/ሚካኤል፣ ደ/ቁስቋም ቅ/ማርያም ወደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ የደ/ምሕረት ቅ/ሚካኤል እና የደብረ አሚን አቡነ ተ/ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ በተመሳሳይ መልኩም የጥምቀትን በዓል በጋራ እያዘጋጁ መሆኑ በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል።


በዕለቱ ለምእመናን መልእክት ያስተላለፉት የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት መ/ኃይል ቆሞስ አባ ዘመልአክ “ሃይማኖታችንን፣ ክርስቲያናዊ ባህላችንን መጠበቃችን በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስ የሚያሰጠን ጸጋችን ነው” ካሉ በኋላ ምእመናን በዚህ አገር የሚወልዷቸውንና የሚያሳድጓቸውን ልጆቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲያሳድጉ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲያመጧቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።


ዝግጅቱ የተዋጣለት መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን ጸሎቱ፣ መዝሙራቱ እንዲሁም የዕለቱ ትምህርት እና አጠቃላይ ዝግጅቱ በሰዓቱ ተጀምሮ በተባለው ሰዓት መፈጸሙን እንደ ትልቅ ጠንካራ ጎን ጠቅሰው ከካህናቱ ጸሎትና መዝሙር ባሻገር የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ተተኪ የሚሆኑ ሕጻናት በጋራ ያቀረቡት ዝግጅት ሊበረታታ እንደሚገባው ተናግረዋል።
   በ2006 ዓ.ም በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በአካባቢው ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ቀይ ምንጣፍ በማንጠፍ በመሐል አደባባይና በዋና ዋና ጎዳናዎች በማቋረጥ የተከበረ ሲሆን በዚህ ዓመትም ይኸው የአንድነት እና የሕብረት ዝግጅት ቀጥሎ በጥር ወር ላይም እንደሚደገም የወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለምእመናን አስታውቋል። በዓሉ የደመራውን ችቦ በመለኮስና በማቃጠል ከተከበረ በኋላ ምእመናን ከትርኳሹ በራሳቸው እና በልጆቻቸው ግንባሮች ላይ የመስቀል ምልክት በመሥራት ከበረከቱ ተካፍለው ተመልሰዋል።


Written By: host
Date Posted: 9/30/2014
Number of Views: 6069

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement