View in English alphabet 
 | Tuesday, September 28, 2021 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የጥምቀት በዓል በዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና በዋሺንግተን (ሲያትል) ግዛቶች በድምቀት ተከበረ

(ማኅበረ ቅዱሳን፤ ሲያትል)፦ በዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የሚገኙ አስራ አራት (14) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት በመሆን የ2007 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓልን በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል።

 

በዚሁ ደማቅ አከባበር ላይ በተለይም በከተራው ታቦታቱ ከየመንበረ ክብራቸው ተነስተው ወደ ተዘጋጀላቸው መንበረ ክብር ሲገቡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ወረደ ወልድ እምሰማያት የሚለውን ዝማሬ ከቃኙ በኋላ የየአብያተ ክርስቲያናቱ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በዝማሬና በእልልታ አጅበውታል። የዲሲና ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ቡራኬ ሰጥተው የከተራው ስነ ሥርዓት ተጠናቋል። በማግስቱም ከንጋቱ 7 ሰዓት (1:00 AM) ጀምሮ ስርዓተ ማኅሌቱ ከተካሄደና በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የተመራው ቅዳሴ እንደተጠናቀቀ እለቱን የተመለከት ትምህርት ተሰጥቷል። በመጨረሻም የጥምቀተ ባሕሩ ስርዓተ ፀሎትና የመርጨት ስነ ስርዓት ከደረሰ በኋላ ታቦታቱ በዝማሬና በእልልታ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል።  በዕለቱ የተገኙት የአስራ አራቱ  አብያተ ክርስቲያናት ዝርዝርም
1) መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም - ዲሲ

2) ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል - ዲሲ
3) ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት - ቨርጂኒያ
4) ፍኖተ ጽድቅ  ቅዱስ ጊዮርጊስ - ቨርጂኒያ
5) መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ - ቨርጂኒያ
6) ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ - ቦልቲሞር
7) መካነ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል - ዲሲ
8) አቡነ ተክለሃይማኖት - ቨርጂኒያ
9) ኆኅተ ምስራቅ ኪዳነምሕረት - ሜሪላንድ
10) መደብረ መንክራት ቅዱስ አማኑኤል - ቨርጂኒያ
11) አቡነ አረጋዊ - ቨርጂኒያ
12) ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወ ገብርኤል - ሜሪላንድ
13) ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም - ቨርጂኒያ
14) ቅድስት አርሴማ - ቨርጂኒያ እንደነበሩ ተገልጿል::

በተያያዘ ዜናም ታላቁ የጥምቀት በዓል በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ የዋሺንግተን ጠቅላይ ግዛት በሲያትል ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። በኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት የዋሺንግተን ስቴት ቤተ ክህነት ባስተባበረውና ስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተሳተፉበት በዚህ ታላቅ ክብረ በዓል ላይ በሲያትልና በአካባቢው የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ተገኝተው ከበዓሉ በረከት ተሳትፈዋል።

ታቦታቱ መነሻቸውን ካደረጉበት ከደብረ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ማረፊያቸው እስከተዘጋጀበት የከተራው ሥፍራ ድረስ ዋና ዋና መንገዶች ለክብረ በዓሉ ዝግ ሆነዋል። ካፊያ ባጠላበት የሲያትል ደመናማና ዝናባማ ምሽት ከሁሉም አጥቢያዎች የመጡ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ጎዳናውን በመዝሙራቸው እያደመቁት ተምመዋል። ምእመናኑ ታቦታቱን ከኋላና ከፊት በመዝሙር አጅበው ሲከተሉ ፖሊሶች በሞተረኞቻቸው እየታገዙ መንገዱን ከሌሎች መኪናዎች ነጻ ሲያደርጉ ተስተውሏል።
በዓይነቱ ለሁለተኛ ጊዜ በጋራ በተከበረው በዚህ የጥምቀት በዓል ላይ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ይትባህል ታቦታቱ በዋና ዋና መንገዶች ሲጓዙ ማየት ልቡናን እጅግ የሚያስደስት ሆኖ አልፏል። የሲያትል ከተማ ነዋሪ በጎዳናዎቹ በመከናወን ላይ ያለውን የደመቀ በዓል ምንነት ለመረዳት ከምእመናን መካከል ሰዎች ሲጠይቅ፣ ፎቶግራፎችን ሲያነሳ፤ ስለ በዓሉ ምንነት የተጠየቁ ምእመናንም ስለ ጥምቀት ለማስረዳት ሲሞክሩ አምሽተዋል።
ታቦታተ ሕጉ እንዲያርፉበት በተዘጋጀላቸው ሰፊ አዳራሽ ከደረሱ በኋላ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለበዓሉ የሚስማማውን ጸሎት፣ መዝሙርና ምስጋና አቅርበዋል። ስለ በዓሉ ሰፊ ትምህርትም ተሰጥቷል። ከሊቃውንቱ ባሻገር የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሰንበት ት/ቤት አባላት ያዘጋጇቸውን መዝሙራት ያቀረቡ ሲሆን ምእመናንም በአበው እና እመው ልማድ “ማርያም ወረደች አሸዋ ላሸዋ፤ እሰይ ስለቴ ሰመረ” እያሉ በዓሉን በዝማሬያቸው አድምቀውታል።
ታቦታተ ሕጉን ወደ ከተራው በደመቀ ሁኔታ የሸኘው ምእመን ከሌሊቱ ሥርዓተ ጸሎት እና ቅዳሴ ጀምሮ ከሊቃውንቱ ጋር በዓሉን በማክበር እና ታቦታቱን ወደየመንበረ ክብራቸው በመመለስ በዓሉን በደስታ ፈጽሟል። በዓሉን ያዘጋጀው የስቴቱ ቤተ ክህነት እና አዘጋጅ ኮሚቴው ለበዓሉ በደመቀና በሠመረ ሁኔታ መከበር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዋሺንግተን ስቴት ቤተ ክህነት ሥር የታቀፉት አብያተ ክርስቲያናት 1. የደብረ መድኃኒት ቅ/አማኑኤልቤተ ክርስቲያን፤ 2. የደብረ ሰላም ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ 3. የደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ 4. የደብረ ቁስቋም ቅ/ማርያም ወደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን 5. የደብረ አሚን አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፤ 6. የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ናቸው።  
የጥምቀት በዓል በሲያትል በዚህ መልኩ በጋራ ሲከበር ይህ ሁለተኛው ሲሆን የመስቀል ደመራንም በዓል በጋራ በማክበር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።


Written By: host
Date Posted: 1/21/2015
Number of Views: 8824

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement