View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

《በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ።》ዘፀ 33፡1-3

ኅዳር 11 ቀን 2005 ..
በመምህር ኢዮብ ይመኑ

 

በረሃብ ስደት ምክንያት ከከነዓን ወደ ግብፅ የመጡት ሰዎች ከዮሴፍ ጋር ሰባ ነበሩ፡፡ /ሐዋ.7/ በግብፅም በአባታቸው በያዕቆብ ምርቃት ቁጥራቸውም እጅግ በዛ፡፡ ይህም የቁጥራቸው መብዛት 1280-1445 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተነሣውንና ዮሴፍን የማያውቀውን ንጉሥ አስፈራው፡፡ /ዘፀ.18/ ንጉሡም ጠላት ይሆኑብናል ያም ባይሆን ጠላት ቢነሳብን አብረው ይወጉናል በሚል ፍርሃት አገዛዝ በማጥናት በቀን በሌሊት በከባድ ሥራ እየጠመደ በጭካኔ ጡብ እያስገነባ ፊቶም፣ ራምሴ፣ ዖንን የተባሉ ታላላቅ ከተሞችን እያሠራ ኖራ እያስወቀጠ ጭቃ እያስረገጠ በሥራ ደክመው ልጅ እንዳይወልዱና ጉልበታቸውን እየደከመ በጅራፍ አየገረፈ መከራ አጸናባቸው፡፡ ይህን ቢያደርግም ጉልበታቸው እየበረታ ከእርሱ መከራ የአባቶቻቸው ምርቃትና ቃል ኪዳን እየረታ አሁንም ሲበዙ ወንድ ሲወለድ በመግደል እስራኤልን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ ግን የመከራው ብዛት የሕዝቡም ጩኸት የራሔልም እንባ እግዚአብሔርን፡- “የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ” አስብሎ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት በሙሴ ጸሎት በግብፅ ምድር 9 መቅሰፍቶች 10 ሞተ በኩር  11 ስጥመተ ባሕር የወጡት እስራኤል ከነዓን ገብተዋል፡፡ ይህም የኅዳር 12 መታሰቢያ በዓል መጽሐፍ ቅዱስ “በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ… በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤” ዘፀ.331-3 እንዳለ ከመከራ የወጡትን እስራኤል በጉዞአቸው ካለው መሰናከል እየጠበቀ “በመንገድ ላይ” እንዳይጠፉ እያማለደና በምሕረት እየታደገ ከጠላት ሲዋጉ አብሮ እየቀደመ ከዲያብሎስ ተንኮል እየሰወረ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ያስገባው “መልአክ” የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ነው፡፡

 

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ድካም የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ የሰው ልጅም የእግዚአብሔርን ውለታ የሚዘነጋ የተደረገለትንም የሚረሳ ፊቱ ባለ ነገር ብቻ የሚጨነቅ ነገ በሚመጣው ብቻ የሚጠበብ እንጂ ትላንትን አስቦ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ባለመሆኑ የሰው ልጅ ትላንት የተደረገለትን እንዳይረሳ ይልቁን ትላንትን እያሰበ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን መጪውን ትውልድ ከትላንት እውነት ጋር እንዲዋሐድ ያለፉት ሥራዎቹ እንዲታሰቡ እንጂ ከቶ እንዲዘነጉ ስለማይፈለግ መታሰቢያን ሰጥቶናል፤ ይህም እኛን በእርግጥ ለመርዳት የተደረጉ ድኅነታችንን ለማገዝ የተሠሩ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ መጽሐፍ “መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው፡፡…. ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፣ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል” መዝ.1011218 እንዳለ መታሰቢያነቱ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማድነቅ ለማመስገን ሆኖ ተጠቃሚውም ከድርጊቱ በኋላ የሚመጣ አዲስ እንግዳ ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ማቅረቢያ ለነገ ኑሮ ደግሞ ማዘጋጃና የበረከትም ምክንያቶች ይሆናል መታሰቢያ፡፡ ለዚህ ነው በዳርቷን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ የዮርዳኖስን የሞላ ውኃ በእግዚአብሔር ተአምራት ተቋርጦ በደረቅ መሻገራቸውን ለማሰብ “ኢያሱም አላቸው፡- በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ ከናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቁጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም፡፡ ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል ልጆቻችሁም በሚመጣ ዘመን የእነዚን የድንጋዮች ነገር ምንድር ነው? ብለው ሲጠይቁአችሁ እናንተ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ ይሆናል ትሏቸዋላችሁ፡፡” ኢያሱ 44-7 በማለት የመታሰቢያ ዮርዳኖስን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናገኘው፡ የመታሰቢያ ዕለታት ወይም በዓላት ወይም ምልክቶች ጥቅም ስላላቸው ነው ሥርዓት የተሠራላቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ሰው እግዚአብሔርን አመስግኖ ከቅዱሳኑ በረከት አግኝቶ ራሱን በቅድስና ሥፍራ አውሎ ቅድስናን ተምሮ ለቅድስና የሚያበቃውን በረከት ያገኛል፡፡

 

እግዚአብሔር ሥራ የሠራበት፣ በጽኑ ተአምራት ሕዝቡን የታደገበት መንገድ እንደ ቀላል በዝምታ የሚታለፍ ሳይሆን መታሰቢያ የሚደረግባቸው ዕለታት ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ተዘከረ ገብረ ለስብሐቲሁ፡- ለተአምራቱ መታሰቢያ አደረገ” መዝ1104 ይላልና፡፡ ይህ ኅዳር 12 እግዚአብሔር በታላላቅ ተአምራት ሕዝቡን ነጻ ያወጣበት ዕለት በመሆኑ የመታሰቢያ በዓል ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር በባሕሪው የእርሱ ለሆኑት ቅዱሳን ክብርና ሞገስ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ሰዎች የእርሱ የሆኑትን እንዲያከብሩለት የሚፈልግ አምላክም ነው፡፡ ለዚህ ነው “እነሆም መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ፡፡” ራዕ.39 የሚለው ወዳጆቹን ማክበር እርሱን ማክበር ነው እነርሱን ማሰብ እርሱን ማሰብ ነውና ነው፡፡የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው ያለው” ዕብ.137 እነርሱን መመልከት እርሱን መመልከት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የከበረ ዕለት በመንገድ ላይ እሥራኤል እንዳይጠፉ በይቅርታ መልአክ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና ጥበቃ በእርሱም መሪነት ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ገብተዋልና ለቅዱስ ሚካኤል በቤቱና በቅጽሩ መታሰቢያና ስም ይሰጣቸዋል፤ ምንም እንኳን ቤቱ የእርሱ ቢሆንም መታሰቢያነቱን ለወዳጆቹ ደስ ላሰኙት ይሰጣል፡፡ /ኢሳ.564/ ልዩ ከሆነው ስሙ ጋር ስማቸው አብሮ እንዲነሣ ያደርጋል፡፡ አድሮባቸው ሥራ ሠርቷልና፤ እንዲሁ አይተዋቸውም እንዲታሰቡለት ያደርጋል፡፡ በቤቱም ብቻ ሳይሆን በፊቱም እነርሱ ሲታሰቡ ሲከብሩ ደስ መሰኘት ብቻ ሳይሆን ምንጩ እርሱ፣ ፈቃጅም ራሱ ነው እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ፡፡” ሚል.316 እነርሱ ስሙን በፍጹም አስበዋልና እርሱ እግዚአብሔር ደግሞ ስማቸው በሌሎች /በእኛ/ እንዲታሰብ ፈቅጿል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንጻር ከእስራኤል ዘሥጋ ነጻ መውጣት ጋር “ስሜ በእርሱ ስለሆነ ዘጸ.2320 የተባለለት ቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያው ሆኖ ይከበራል፡፡

 

የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ እንዲፈጽሙ የረዳቸው ያጸናቸው እርሱ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ዲያብሎስ በተንኮል የሙሴን መቃብር አሳይቶ ሕዝቡን በአምልኮ ጣዖት ሊጥል ሲያደባ በጣዖት ወድቀው እግዚአብሔርን በድለው እንዳይጠፉ ከፊታቸው ቀድሞ ከዲያብሎስ ስውር ሤራ የጠበቃቸው ይህ ቅዱስ ሚካኤል ነበረ፡፡ ይሁዳ.19 “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለሙሴ ሥጋ ሲነጋገር” እንዲል፡፡ ዳግመኛም ቀኑን በደመና ዓምድ ከበረሃው ዋዕይ እየጋረደ ሌሊቱን በብርሃን ዓምድ ጨለማውን እያስወገደ ከመሰናክል እያዳነ ከመከራ እየጠበቀ ነጻ አውጥቶአቸዋልና መታሰቢያ ተደርጎለታል፡፡ ዘጸ.2320 መዝ.337

 

በኦሪት የሶምሶንን አባትና እናት ማኑሄንና እንትኩደንን ልጅ እንደሚወልዱ ያበሠረውን መልአክ “ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? መኀ.1317 ማለቱ በምስጋናና በደስታ ቀናቸው ይህን ተአምራት ያሳያቸውን መልአኩን ለማክበርና መታሰቢያ ለማድረግ ትውፊት መኖሩን በሚገባ ያሳያል፡፡ ይህ የደስታና የምስጋና ቃል የሚያሰማበት ቀን ደግሞ በዓል ይባላል፤ በዓልም ይሆናል፡፡ መጽሐፍበዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ የምስጋና ቃል አሰሙ” መዝ.415 ይላልና እኛም በዚህ ዘመን እግዚአብሔር አድሮባቸው ሥራ የሠራባቸውን ተአምራቱን የገለጸባቸው ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታትና መላእክት የመታሰቢያ በዓል አድርገን በደስታና ከምስጋና ቃል ማክበራችን ፍጹም አምላካዊና መንፈሳዊ መንገድ መሆኑን አምነን እንመሰክራለን፡፡ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል” ተብሏልና፡፡ ሮሜ 146

 

From <http://eotcmk.org/site/component/contentbloglist/?task=editcontent&catid=22&id=1143>


Written By: useducation
Date Posted: 11/20/2015
Number of Views: 3095

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement