View in English alphabet 
 | Wednesday, April 24, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በዓለ ጥምቀትና ትውፊቱ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከቅድስት ሥላሴ ረቂቅ ልደት ሊወለድ የቻለበትን፣ ወደ ክርስቶስ ቤተሰብነትና የክርስቲያን ማኅበር አንድነት ብሎም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚተላለፍበትን በዓለ ጥምቀትን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የመታሰቢያ  በዓል አድርጋ ታከብረዋለች። ቤተ ክርስቲያናችን በሥዕላዊ መልክ ከምታከብራቸው በርካታ በዓላት መካከል በዓለ ጥምቀት አንዱ ነው። ሥዕላዊ መልክ ማለት በዓሉን በማስመልከት መዝሙር መዘመር፣ ምስጋና ማቅረብ፣ በበዓሉ ዕለት የተፈጸመውን ድርጊት በኅሊና ማሰብ ብቻ አይደለም። የበዓሉን ጥንታዊ ድርጊት በሚታይ ነገርና ሁኔታ መግለጥ ማለት ነው። ይህም የረቀቀውን አጉልቶ፣ የራቀውን አቅርቦ ለማሳየት ነው። የጥንተ ክርስትናውን መሠረት ሳትለቅ ከቀደምት አበው በተላለፈው እምነትና ሥርዓት የምትጓዘው ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ጥምቀት በዓል አከባበር የራሷ ትውፊት አላት። የብሉያትና ሐዲሳት መጻሕፍት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ እንደሚገኙ ሁሉ ሥርዓቱንም በዓሉንም አስተባብራ ይዛ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት።

የበዓለ ጥምቀት አከባበር በኢትዮጵያ የተጀመረው የክርስትና እምነት እንደገባ መሆኑ ይታመናል። እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ግን የጥምቀት በዓል አሁን በምናከብርበት ሁኔታ የሚታሰብበት ሁኔታ አልነበረም። በዓለ ጥምቀትን በሜዳና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት (530-544 ዓ.ም.) እንደሆነ ይነገራል። ይህም ከማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ (505-572 ዓ.ም.) ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር። ጻድቁና ጠቢቡ ንጉሥ ላሊበላ (1140 – 1180 ..) ሁሉም አጥቢያ  አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው በሚቀርባቸው ቦታ በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቷል። በምትኩም በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ጥመቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፏል። ይህም ተግባራዊ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅት እና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውናና በስብከተ ወንጌል ተግተው ያገለግሉ የነበሩ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቅለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል። በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም.) በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት (1203-1304 ዓ.ም.) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዓተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል። የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ።

በመንፈሳዊነታቸውንና በደራሲነታቸው መጻሕፍትን ጽፈው፣ ሥርዓትን ሠርተው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ /1426-1460 ዓ.ም./ ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ። ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ /1486-1500 ዓ.ም./ ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበትና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር። ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታ እና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ካወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ። ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድሩ ጀመር።

ታቦተ ጽዮን በኢሎፍላውያን ተማርካ፣ የሚያመልኩበትን ጣዖተ ዳጎንን ድል አድርጋ ተአምር ሠርታለች። በኋላም በእሥራኤላውያን ተመልሳ በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመታት ተቀምጣለች። የአሚናዳብ ቤትም በበረከት ተሞልቶ ነበር /1 ሳሙ 7፡2/። ዛሬም ኦርቶዶክሳዊው ምእመን በየአካባቢው ታቦታቱ እንዲያድሩለት የሚፈልገው፣ ታቦታቱ የሚያድሩበትን ድንኳን ከቦ የሚያነጋው ያን በረከት ለማግኘት ነው። ይህ ታሪካዊ ሂደት ሳይቋረጥ ቀጥሎ እስካሁን ድረስ ፍጹም መንፈሳዊና ትውፊታዊ ይዘቱን ሳይለቅ እየተከበረ ይገኛል። በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚዘመረውና የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር በጥምቀት የምናገኘውን ጸጋና በረከት የሚያመሠጥር ነው። የሚከናወነው ሥርዓትም ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው። ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ ሲያያዝ እንደመጣው በዓለ ጥምቀት የሚታሰበው ከዋዜማው ጥር 10 ቀን ጀምሮ ነው።

ሀ/ በዋዜማው ጥር 10 ቀን

በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ “ባሕረ ጥምቀት”፣ “የታቦት ማደሪያ” እየተባል ይጠራል። ባሕር፡ የውኃ መሰብሰቢያ /ምእላደ ማይ/፣ የውኃ መከማቻ /ምቋመ ማይ/ ነው። በሌላ አነጋገር “የውኃ አገር” /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው። ጥምቀት፡ ከውኃ መንከር፣ መዝፈቅ፣ ከውኃ ማግባት፣በውኃ ማጠብ፣ ውኃን በራስ ገላ ላይ ማፍሰስ፣ መቸለስ፣ መርጨት፣ ማረብረብ ሲሆን፣ ምጥማቃት ሲል ደግሞ መጥመቂያ፣ ማጥመቂያ፣ መጠመቂያ ቦታ ማለት ነው /ኪ.ወ.ክ፡ 261 እና 502-503/። በመላው ኢትዮጵያ የታነጹት ከ20 000 በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጥር 10 ቀን በየአካባቢያቸው በተመደበላቸው አብሕርተ ምጥማቃት ይወርዳሉ። ካህናቱም ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ። በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዓተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9 ሰዓት ሡርሆተ ሕዝብ ይሆናል።

በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን “ማይ ሹም”፣ በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ”፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን ጃንሜዳን ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ።

እንደ ሊቀ ማእምራን ጽጌ ከበረ ገለጻ፡ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ /ይዞ/ መጓዝና ወደ ወንዝ መውረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልአዛር ጊዜ ነው። ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም ነበር። እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡ ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው ተሻግረዋል /መጽ ኢያሱ 3፡8-9/። የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ተብሎ ይጠራል። መምሬ ተዘራ ወርቁና ሊቀ ትጉሃን ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ማርያም ስለዚህ ሲያስረዱ፡ “ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው /ይዘው/ የወንዙን ዳርቻ በረገጡበት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል። ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃም ታቦተ ጽዮንን ያከበሯት /የያዙት/ ካህናት ከወንዙ መሃል ቆመው ነበር። በዚህ መሠረት “ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት” ተብሎ ተጽፏል። ይህም “የካህናት እግር  የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጡ እንደ ጥምቀት ሆናቸው” ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ  ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሳት ነው። ከተራ ማለት መዝጋት፣ ማቆም፣ ማገድ፣ ማጠር፣ ዙሪያውን መያዝ፣ መክበብ፣ መከለል ማለት ነው።

ታሪኩ ከጌታችን ጥምቀት ጋረ በተያያዘ ምሳሌነት አለው። ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ጊዜ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል። የታቹም ወደታች ሸሽቷል። የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደክምር ተቆልሎ መቅረቱ፣ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ለመቅረቱ፣ ከአበው ወደ ዉሉድ ላለመተላለፉ፣ የታችም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም ከሥሩ እንደተነቀለ ወይራ ሆና ለመውደቋ ምሳሌ ነው። እስራኤል ፈለገ  ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ አቅንተው መሄዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከቁራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት፣ ወደ እረፍት መንግስተ ሰማያት አቅንተው ለመሄዳቸው ምሳሌ ነው። በጠቅላላ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል ዘሥጋ የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው። ለአይሁድ በትእዛዝ ከታወጁት ስምንት በዓላት አንዱ የዳስ በዓል /በዓለ መጸለት/ ነው። ይህም የአዝመራ መክተቻ በዓል ነው። በሰባተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን እህል ከተከማቸ በኋላ የእስራኤል ልጆች ለሰባት ቀናት ዳስ ጥለው ድንኳን ተክለው እየተቀመጡ አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር /ዘሌ 23፡39-42/። የበዓለ መጸለት ምሳሌነቱ ለሐዲስ ኪዳኑ በዓለ ጥምቀት ነው። ይህም ዛሬ እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል።

ቀደም ባለው ጊዜ የአንድ አጥቢያ ታቦት በከተራ ዕለት የሚወርደው ከአንድ የተወሰነ ቦታ ብቻ ሳይሆን በየሰበካው አቅጣጫ ነበር። ታቦቱ የወረደበት ሰፈር ድግስ ይደገሳል። ይህም በየዓመቱ ስለሚለዋወጥ ሕዝቡ ደስ ብሎት ያደርገዋል። በገጠሩ ክፍል ውኃ በማይገኝበት አካባቢ ወንዶቹ ለባሕረ ጥምቀቱ ይሆን ዘንድ እየቆፈሩ ይከትራሉ። ሴቶች ደግሞ ከሩቅ ቦታ እየሄዱ ውኃ በእንስራ እየቀዱ እያመጡ የከተራው ግድብ በውኃ ተሞልቶ የዮርዳኖስን ባሕር እንዲመስል ያደርጉታል። ታቦተ ሕጉ ለአዳር ሲጓዝ እናቶች ለበዓሉ መስተንግዶ ምግቡንና መጠጡን አሰናድተው ካህናቱንና በባሕረ ጥምቀቱ የሚያድሩትን ይጋብዛሉ። ጥር 10 ቀን /ከተራ/ ቅዳሜና እሁድ ገጥሞ በዓለ ሰንበት ካላገደ በቀር በዚህ ቀን ገበሬው ሞፈር ቀንበሩን አቀናብሮ በቅርብ ማሳ ላይ በሮዎቹን ጠምዶ መሬቱን ተልሞ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ፈር ከዚያም በላይ ቢሆን ማረስ የተለመደ የሃገር ባህልና ልማድ ነው። በዚህ ቀን መሬቱ ሲተለም ረድኤት፣ በረከት እንደሚገኝ ያምንበታል /ዶር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፡ የቤተ ክርስቲያን የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡ቅጽ 12፡ ገጽ 196/

ጥር 10 ቀን ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዋዜማ ይቆማል። ከሰዓት በኋላ ታቦታቱ በተለያየ ሕብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቃድስ ወደ ቤተ አብሕርተ ምጥማቃት ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምጽ ያሰማሉ። ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በነቂስ ወጥተው በዐጸደ ቤተ ክርስቲያንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ይሰበሰባሉ። ካህናቱ “ወረደ ወልድ ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም፣ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ በሰላምና በደስታ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከሰማያት ወረደ፤ ከዊኖ  ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ፣ ሰው ሆኖ  በዮርዳኖስ ተጠመቀ” እያሉ ይዘምራሉ። እልልታ፣ ሆታ፣ሃሌታ፣ ግርግርታ ይሰማል። የሰንበት ት/ቤት መዘምራን በዝማሬና በሽብሸባ፣ ጎበዙ በሆታ፣ ሴቶች በእልልታ... ሁሉም በሚረዱት መንገድ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። ታቦታቱን አጅበው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በኅብረት ያመራሉ።

ዩኑፎርም የለበሱ ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ  የለበሱ ዲያቆናትና ቀሳውስት ከታቦታቱ በፊት፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ አረጋውያን አበውና መላው ምእመናን ከታቦታቱ ኋላ ይጓዛሉ። እጣኑ፣ ዝማሬው፣ ታቦታቱ አገሩን እየባረኩት ነው የሚጓዙት። ቀደም ብለው በባሕረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሰፍረው የታቦታቱን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁ ምእመናን  በእልልታ እና በስግደት ይቀበላሉ። የዓመቱ ተረኞች የሆኑት አድባራት /የምራት ባለተረኞች መዘምራን/ “ወረደ ወልድ ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም” የሚለውን ግስ ቃኝተው ያሸበሽባሉ፡ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ ታቦታቱ ለማደሪያ ወደተዘጋጀላቸው ወደ መንበረ ክብራቸው ይገባሉ። ካህናቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ማህሌት እስከ መንፈቀ ሌሊት ያደርሳሉ። ከምእመኑም የበረቱት በማኅሌት ይሳተፋሉ። የተቀሩትም በታቦታቱ ማደሪያ ዙሪያ በተተከሉ ድንኳኖች ለሊቱን ያሳልፋሉ። ታቦታቱ ወደ ማደሪያ ድንኳናቸው እንደገቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተለያዩ  መርሐ ግብሮችን በመዘርጋት ጣዕመ ዝማሬዎችን በማሰማት ምእመናንን እያስተማሩ እስከ ንዋመ ሌሊት ይቆያሉ። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ሥርዓተ ቅዳሴው ይካሄዳል።

“የምራት ባለተረኞች” የሚባሉት በዓመቱ ግሱን ለመቃኘትና ለማሸብሸብ፣ ማኅሌት ለመቆም፣ ቅዳሴ ለመቀደስና ሌላውንም ሥርዓት ለመፈጸም ሐላፊነት ያለባቸው ገዳማትና አድባራት ካህናት ናቸው። ለቀጣዩ ዓመት ተረኞች የሆኑትና በአሁኑ ዓመት የምራት ባለተረኞች የሚረዱት ገዳማትና አድባራት ካህናት ደግሞ “አንሺዎች” ይባላሉ።

የበዓለ ጥምቀት ጸሎተ ቅዳሴ የሚከናወነው በመንፈቀ ለሊት ነው። የጥምቀት ዋዜማ ከጥሉላት በማልዕት ይጾማል፤ የሚቆርብም ሰው አክፍሎ ያድራል። እርሱም ጋድ ይባላል። ለውጥ፣ ምትክ ማለት ነው። ጥምቀት ረቡዕ ቢውል ጋዱ ማክሰኞ፣ ዐርብ ቢውል ጋዱ ኀሙስ ለውጥ ሆኖ የጾማል፤ ጥምቀት የሚውልባቸው ረቡዕና ዐርብ አይጾሙም /ፍት ነገ አን 15/።

በአጠቃላይ በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት የሚከተለው ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው። ታቦቱ የጌታችን፣ ታቦቱን አክብሮ /ይዞ/ የሚሄደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጀበው የሚሄዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው። ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል። “ጥምቀት የሞቱ አርአያ፣ የመቃብሩ አምሳል ነው። ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የሚሻ ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ለመፈጸም በዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ።” /ኪ.ወ.ክ. 517/። ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናም፣ የበረዶ ወራት ነው። እንኳንስ ከወንዝ ዳር ከማናቸውም ቦታ ቢሆን ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም። በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር። በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ በድንኳኖች የተከለሉ ዳሶች ይጣላሉ።

ለ/ በዕለቱ ጥር 11 ቀን የበዓለ ጥምቀቱ አከባበር

ጥር 11 ቀን ንጋት፡ ካህናቱ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው መጽሐፈ ጥምቀት ይነበባል። ተስማሚው ቃል እግዚአብሔር ደርሶ ሲያበቃ ጥምቀቱ የሚገኝበት ቦታ መንበረ ፓትርያርክ ያለበት ከሆነ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የመንበረ ጵጵስና ቦታ ከሆነ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጳጳሱ ወይም ኤጲስ ቆጶሱ፣ ይህም ካልሆነ ቆሞስ አልያም በቦታወ በክብርና በሥልጣን የሚበልጠው ካህን ወይም ገባሬ ሠናይ ቄስ ባሕረ ጥምቀቱን ይባርካል። አራት የሚበሩ ጧፎች የታሰሩበት መስቀለኛ እንጨት ወደ ባሕሩ ይለቀቃል። ይህም ጌታችን ሲጠመቅ ብርሃን የመውረዱ ምሳሌ ነው። ጸሎተ አኮቴት ደርሶ ሥርዓተ ቡራኬው ከተፈጸመ በኋላ ሕዝቡ በረከት ለመቀበል እየተጋፋ ጠበሉን እየተሻማ ይረጫል። ...

ምእመናኑ በመረጨትም ይሁን በዋና ቡራኬ ካገኙ በኋላ ታቦታቱ ካደሩበት ወጠተው በተዘጋጀላቸው ቦታ የቆማሉ። መዘምራንም ከታቦታቱ ፊት “ኀዲጎ  ተስዐ ወተስዐተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባሕር ገብአ ወወፅአ በሰላም፤ ዘጠና ዘጠኙን የመላእክት ነገድ ትቶ በባሕር መሀል ቆመ” የሚለው ግስ በባለተራው /የምራት ባለተረኛ/ ደብር መሪነት ተቃኝቶ ይሸበሸባል። የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም በዓሉን የተመለከተ መንፈሳዊ መዝሙር ይዘምራሉ። የበዓሉን መንፈሳዊ ታሪክ የተመለከተ ትምህርት ይሰጣል። በተገኙት አባት ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ ካህናቱ “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” የሚለውን ግስ እየዘመሩ ታቦታቱን ከድንኳን አንስተው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ እልልታው ይደምቃል። መንገዶች በሕዝባዊ ማዕበል ይጥለቀለቃሉ። ሕዝቡ ግን ግፊያውን አይሰቀቀውም። ይልቁንም ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳኑ ካለው ፍቅር የተነሣ ላቡን እያፈሰሰ፣ ፍጹም ኃይል በተሞላበት ደስታ እያመሰገነ ታቦታቱን አጅቦ ጉዞውን ይቀጥላል። ...

ሁሉም በየወገኑ እንዲህ ባለው ሁኔታ በክብር አጅቦ ያወጣውን ታቦት በክብር አጅቦ ወደ ቤተ መቅደሱ ይመልሳል። ታቦታቱ ከጥምቀተ ባሕር ተነስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው፣ ጌታችን ከተጠመቅ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ መሄዱን ያጠይቃል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በገዳመ ቆሮንቶስ ትመሰላች።

የበዓለ ጥምቀት ትውፊታዊ አከባበር በስብከት ከሚገለጠው ይልቅ የተጨበጠ ክርስቲያናዊ ማስረጃ ሆኖ ክርስትናን ጠብቆ ኖሯል። ብዙዎች ጥንታዊውን ክርስቲያናዊ ትውፊት በተመለከቱ ጊዜ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እያስታወሱ የሚመለሱበት ታላቅ ምክንያት ሆኗል። በማኅበራዊ ኑሮና በባህል በኩል ደግሞ ሕዝብ ከሕዝብ የሚገናኝበት፣ የግል ስሜቱን የሚገልጥበት፣  ባህላዊ ጨዋታን የሚያሳይበት ዕለትና በዓል ስለሆነ ሕዝቡ በናፍቆት ይጠብቀዋል። ... በአጠቃላይ ክርስቲያናዊ እምነቱን የሚያጸናበት፣ ማኅበራዊ ግዳጁን የሚፈጽምበት፣ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ” በነቂስ ወጥቶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ነው - በዓለ ጥምቀት።

ምንጭ፡- ሐመር - ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም.

 

በኢ////ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ

ማኅበረ ቅዱሳን

የአሜሪካ ማዕከል የትምህርትና

ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል


Written By: useducation
Date Posted: 1/17/2016
Number of Views: 9023

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement