1. ርቱዕ በሃይማኖቱ
የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችንን ልዩ የሚያደርጓት የእምነት ባሕርያት አሏት።
ሀ. የተረዳች ናት
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በትምሕርተ ሃይማኖቷ በቀኖናዋ እና በትውፊቷ እንከን አይገኝባትም ምክንያቱም ሐዋርያት በቃልም በጽሑፍም ያስተማሩትን በሙሉ ይዛለችና። 2 ተሰ. 2፥15 ይኸም ዘመኑ የግንጥል ጌጥን ትምህርት ይዞ ለሚያነሳቸው ምሥጢረ ሥጋዌ ፣ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ የምልጃ ትምህርት፣ አጽዋማት፣ በዓላትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ለመመለስ አስችሏታል።
ለ. ርትዕት ናት
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋሪያዊት የሆነች ያልተበረዘች ያልተከለሰች ያልወየበች ያልተጨመረባት ያልተቀነሰላት ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝም ልክ ለኢያሱ እንደተነገረው ( ኢያ. 1፡7) ያላለች ርትዕት ቀጥተኛ ሃይማኖት ነች። አንዳንዶች ጭልጥ ብለው ሲክዱ ሌሎች ደግሞ እውነተኛውን መንገድ ለቀው በመሰላቸው ሰውኛ ፍልስፍና ሲመሩ እርሷ ግን ሐዋርያት እንደተከተሏት ሳትዛነፍ በቅብብል (Apostolic Succession) ከእኛ ደርሳለች። ሁለቱም ወገኖች ዛሬ ቢያስቡበትና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመልሰው ልብ ቢሉ ያለምንም ጥርጥር ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታቸው በተመለሱ ነበር።
ሐ。ምልዕት ናት
ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት አንዱን ጥላ አንዱን አንጠልጥላ አትሄድም ስለ እምነት ስታስተምር ምግባርን አስተባብራ ነው።( ያዕ 2፣26) ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስታስተምር የእናቱን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የወዳጆቹን የሐዋርያትን፣ የጻድቃን እና የሰማዕታትን፣ የቅዱሳን መላእክትን ክብር እና ምልጃ ሳትዘነጋ ነው። ልጆቿ ቅዱሳት መጽሐፍትን እንዲማሩ ስታደርግ በራሳቸው ፈቃድ ሐረግ እየመዘዙ ሳይሰነጥቁ አባቶቻቸው ሐዋሪያት ብሎም ከነርሱ በኋላ መንገዳቸውን የተከተሉ አበው ያስተማሩትን በመያዝ ነው። ምክንያቱም እኛ ክርስትናን ተቀበልነው እንጂ አልጀመርነውምና የቀደሙትን ማየት ያስፈልጋል።
( ኤር 6፣16)ስለዚህ በመንገዱ መጓዝ እንጂ አዲስ ፈር አናወጣም። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥልጣነ ክህነት ስትሰጥ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ተሳትፎ ሳትንቅና የቤተ ክርስቲያን አካል መሆናቸውን እያስተማረች ነው።
ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት እምነታችን ምግባር ከሃይማኖት እንደ ዘይትና ክር አዋሕዳ የምታስተምር ናት።
መ。መጽሐፍ ቅዱሳዊት ናት
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለቀኖናና ለትውፊት ታላቅ ቦታ ትሰጣለች። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ያገኘችው በትውፊት (ከአባቶች በመቀበል ነውና)ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖትም ሆነ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመንፈስ ላነበባቸው ስለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ስለ ምልጃ ትምህርት፣ ታቦት እና ቤተ መቅደስ ትምህርቷ እውነተኛነት ይመሰክራሉ።
2。ርቱዕ በምግባር
የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ልጆች ልዩ የሆነ የምግባር ባሕርይ አለን።
ሀ。 የግል ጸሎት
ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በጸሎት ከአምላካቸው ጋር መገናኘት አለባቸው። አንኳኩ ይከፈትላችኋል ተብሏል እና (ማቴ。7፣7) ስለዚህ በቀን የተወሰነ ሰዓት መድቦ ስለ ራሱ፣ ስለ ሀገሩ፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ዕለት ሥራው፣ ወዘተ 。。 መጸለይ አለበት። ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረን አቡነ ዘበሰማያት ጀምሮ የአበው የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን የጸሎት መጽሐፍት፣ መዝሙረ ዳዊትን እና ሌሎችንም ይጨምራል።(ዕብ 11፣7)
ለ。 የማኅበር ጸሎት
አባቶቻችን ሐዋርያት በኅብረት ሆነው ለጸሎት ይተጉ እንደነበረው (የሐዋ。8፣2)በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የምእመናን አንድነት እንዲኖር ጸሎተ ምሕላ፣ ጸሎተ ኪዳን፣ ሰዓታትና ማኅሌትን በመሳሰሉት የአንድነት ጸሎተ ሥርዓቶች መካፈል አለብን።
ሐ。 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለቅዳሴም ሆነ ለምሥጋና ሰዓት ለዕለት ተዕለት የክርስቲያኖች የወንጌል ምግብነት ያመች ዘንድ መጽሐፍ ግጻዌ (የመጽሐፍ ቅዱስ የዕለት ምግብ) ተዘጋጅቷል። ለምክር፣ ለተግሳጽ፣ ልብንም ለማቅናት፣ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይገባል። የዕለት ምግባችንን ስጠን ዛሬ የሚለው ጸሎት የሚያመለክተው እንጀራችንን ብቻ አይደለምና።
መ。 ድርሳናትን ማንበብ
የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ምሳ 10፣7፤ በተባለው መሠረት ቅዱሳንን በተለያየ መንገድ ታስባቸዋለች፤ ስለ በረከታቸውም ታከብራቸዋለች። ከዚህም አንዱ ገድላቸውን፣ ተአምራታቸውን ጽፋ ለትውልድ ማውረሷ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን አበውን እየጠቀሰ በዕብራዊያን 11 ላይ የእምነት ምሥክር እንዳደረጋቸው ሁሉ ይኼው ትውልድ የቅዱሳን አባቶችን ታሪክ ገድልና ምክር በማንበብ መማር አለበት።
ሠ。 ማስቀደስ እና መቁረብ
ጸሎተ ቅዳሴ በውስጡ 3 ነገሮችን ይዞአል። የነገረ መለኮት ትምህርት፣ ጸሎት እና ቅዱስ ቁርባን ናቸው። ይኸውም በምሥራቃውያን (ኦርየንታል ቸርችስ)የመንፋሳዊ ዜማ ልህይ (Melody) የሚቀርብ ነው።ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ክርስቲያን በዚህ ጸሎተ ቅዳሴ ላይ መገኘት አለበት። ቅዳሴው “ይበል ካህን፤ ይበል ዲያቆን” እንደሚለው ሁሉ “ይበል ሕዝብም” ይላልና በዚህ ሰዓት ተገኝቶ ትምህርቱን መማር የጸሎቱ ሙሉ ተካፋይ መሆን በመጨረሻም ሥጋወደሙን መቀበል ይገባዋል።
ረ。 መጾም
በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት አጽዋማት ይገኛሉ። የአዋጅ አጽዋማት(ኢዮ 1፡14)
- ረቡዕና ዓርብ፣
- የሐዋርያት፣
- የነቢያት፣
- ዐብይ ጾም፣
- ጾመ ፍልሰታ፣
- ጾመ ነነዌ፣
- ጾመ ገሃድ፣
እነዚህ አጽዋማት ከአባቶቻችን የወረስናቸው የኑሮ ፍሬዎች ሲሆኑ የእናታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መከራዋን እያሰብን ፍቅራችንን የምንገልጽበት በሐዋርያት፣ በነቢያት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት ፈለግ ለመሄድ እግዚአብሔርን እየጠየቅን ሕይወታቸውን የምንኖርበት የጌታችን የመድኃኒታችንን ስቃዩን፣ መከራውን ለኛ ሲል የሠራልንን የፍቅሩን መግለጫ ሞቱን የምናስብበት ወቅት ነው።
የግል አጽዋማትም በፈቃድ ለጸጋ የሚደረጉና በምክረ ካህን፣ በትዕዛዘ ካህን ለንስሐ የሚደረጉትን ያጠቃልላል። እነዚህም የኃጢአት መሠረት የሆነውን ዲያቢሎስን ለመዋጋት የሚደረጉ ናቸው(ማቴ。17፣21 ሉቃ 2፣36-38) የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በአባቶቻችን ሥርዓት እንደሚገባ መጾም ያስፈልጋል።
ሰ。 ለቤተ ክርስቲያን በዓል ላይ መሣተፍ
ሰሞነ ሕማማትን በመሰሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት፣ በጾምና በስግደት ቅዱሳን መጽሐፍትን በማንበብና በመዘመር በሚዋልባቸው መንፈሳዊ ሰሞናት የውጭ ተመልካች ሳይሆኑ ከበረከቱ መካፈል።
ሸ。 ምክረ አበውን መቀበል
የቀደሙ አባቶች በመንፈሳዊ ጉዞ ብዙ ጸጋ አግኝተውበታልና፥ከቃላቸውና ከሕይወታቸው ወጣቱ ብዙ ይማራል። ስለዚህ ሊቃውንትና ካህናትን ቀርቦ መንፈሳዊ ምክራቸውን ተጋድሎዋቸውንና ትምህርታቸውን መማር ያስፈልጋል። ጢሞቴዎስ ያደገው በጳውሎስ ምክር ነው። ለጢሞቴዎስ የተላከው መልእክት ጳውሎስ በመንፈስ በተጓዘበት ጎዳና ያገኘውን ትምህርት ለልጁ ያካፈለበት ነው።
በዚህ ዓይነት መንገድ አባቶች ካወጡት ሥርዓት ጋር አንድ ሆነን በእምነትም በምግባርም ኦርቶዶክሳውያን መሆን እንችላለን፣ በዚህም እግዚአብሔርን እያከበርን በፍቅሩ እቅፍ ውስጥ እንገባለን ነገር ግን በጭፍን ሞራል (fanaticism) አይደለንም። ሁሉንም በፍቅር እንቀርባለን ነገር ግን ከእምነታችንና ሥርዓታችን እንዲሁም ትውፊታችን ለሰው ስንል የምንተወው አሊያም የምንለውጠው አይኖረንም ።
ምንጭ፡- ሐመር ጥር 1986 ዓ/ም